Monday, July 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

 የዕደ ጥበብ ውጤቶችን ለማጎልበት የተቋቋመው እንሥራ

ኢትዮጵያ ከጥንት ጀምሮ የባህላዊ ቁሳቁሶች መገኛ ነች፡፡ ለበርካታ አገልግሎቶች የሚውሉ የዕደ ጥበብ ውጤቶች አሏት፡፡ ከእነዚህም ውስጥ የሸክላ ሥራ አንዱ ነው፡፡ በተለያዩ አካባቢዎች ተሰማርተው ጀበና፣ ምጣድ፣ የአበባ ማስቀመጫ፣ ድስት እንዲሁም ሌሎች ቁሳቁሶችን እየሠሩ የሚተዳደሩ እናቶች አሉ፡፡  በገጠርና በከተማ በሸክላ ሥራ የተሰማሩ እናቶች ሥራዎቻቸውን ለገበያ ለማቅረብ ከባድ ውጣ ውረዶችን የሚያሳልፉ ቢሆንም፣ የሥራቸውን ያህል ገቢ አያገኙም፡፡ በመሆኑም የዕደ ጥበብ ውጤታቸውን ወደ  ተሻለ ደረጃ ለማሳደግና ገቢ እንዲያገኙ ለማስቻል የእንሥራ የሸክላ ማዕከል በአዲስ አበባ ተቋቁሟል፡፡ ማዕከሉ ከተለያዩ የአዲስ አበባ አካባቢዎች በሸክላ ሥራ የተሰማሩ እናቶችን በማቀፍ እየሠራ ይገኛል፡፡ አቶ ሰለሞን አባተ የእንሥራ የሸክላ ማዕከል አስተባባሪ ናቸው፡፡ ተመስገን ተጋፋው ስለ ማዕከሉ ሥራዎች አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- የእንሥራ የሸክላ ማዕከል እንዴት ተመሠረተ?

አቶ ሰለሞን፡- በኢትዮጵያ የሚገኙ የዕደ ጥበብ ውጤቶቻችን ጠፍተው እንዳይቀሩ ለማድረግ የተቋቋመ ማዕከል ነው፡፡ በተለያዩ ቦታዎች ላይ ተሰማርተው እየሠሩ ያሉ የሸክላ ባለሙያዎችን ሰብስቦ የያዘ ነው፡፡ የቀድሞው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ (ኢንጂነር) ሥልጣን ላይ በነበሩበት ወቅት ሰኔ 2012 ዓ.ም.  ላይ የተቋቋመው፡፡  ተገንብቶ ምንም ዓይነት አገልግሎት ያልሰጠን ሕንፃ በማደስ የእንሥራ ማዕከል አድርገነዋል፡፡  ይህም ሥራው ላይ ባልተመቻቸ ሁኔታ የተሰማሩ  እናቶችን አንድ ላይ በማድረግ በዘመናዊ መልኩ ሥራዎቻቸው እንዲሠሩ እያደረግን ነው፡፡ በቀጨኔ አካባቢ በሸክላ ሥራ የተሰማሩ እናቶችም በማዕከሉ ገብተዋል፡፡ ችግራቸው ተቀርፎላቸው እየሠሩ ይገኛል፡፡  

ሪፖርተር፡- በማዕከሉ ምን ያህል እናቶች እየተገለገሉ ነው?

አቶ ሰለሞን፡- ማዕከሉ ለ1,000 እናቶች የሥራ ዕድል ይፈጥራል ተብለናል፡፡ ይሁን እንጂ በኮሮና ቫይረስ ምክንያት  በሥራው ላይ እንዲሰማሩ የተደረጉት እናቶች 500 ናቸው፡፡ እነሱም የተለያዩ የዕደ ጥበብ ውጤቶችን እየሠሩ ይገኛል፡፡ የሸክላ ድስት፣ መጥበሻ፣ ጀበና፣ የአበባ ማስቀመጫና ሌሎችንም ሥራዎች በመሥራት ላይ ናቸው፡፡ ከዚህ ቀደም ሥራዎችን ሲያከናውኑ ሕፃናት ለጆቻቸውን የሚያስቀምጡበት ይቸገሩ ነበር፡፡ በማዕከሉ ግን ለልጆቻቸው ምቹ የሆኑ ቤቶችን አዘጋጅተናል፡፡ ከዚያም አልፎ እነሱ ሥራቸውን ከጨረሱ በኋላ የሚያርፉበት ቦታ በማዕከሉ ተዘጋጅቷል፡፡ በሚሠሩበት ጊዜም ትልቁ ችግር የሆነባቸው ልጆቻቸውን ይዞ መሥራት የነበረ ቢሆንም ይህንን ችግር መፍታት ተችሏል፡፡ ለልጆቻቸውም ምግብ እየመገብን እንገኛለን፡፡ እነዚህ እናቶች የሠሯቸውን ሥራዎች ወደ ገበያ አውጥተው እንዲሸጡ ለማድረግ የቦታ ማመቻቸት ሥራ እየሠራን ነው፡፡ እስካሁን ባለው ሁኔታ ግን የሠሯቸውን ሥራዎች የሚሸጡት ለነጋዴዎች ነው፡፡ ይህንንም ችግር ለመፍታት የተለያዩ ዕቅዶችን ይዘናል፡፡ ተቋሙ በሸክላ ሥራ ለተሰማሩ እናቶች ብቻ ሳይሆን ሌሎች ማኅበራትን እያደራጁ በቆዳ ውጤት፣ በውበት ሳሎን፣ በኤሌክትሮኒክስና በካፌ የተደራጁ ሰዎችን ወደ ሥራ እንዲገቡ አድርገናል፡፡

ሪፖርተር፡- የሚሠሩበትን ግብዓት ከየት ያገኛሉ?

አቶ ሰለሞን፡- አብዛኛው እናቶች ከበፊት ጀምሮ በሸክላ የተሰማሩ በመሆናቸው ግብዓት ለማግኘት ብዙም አይቸገሩም፡፡ እስካሁን ድረስ በሚያውቋቸው ሰዎች አማካይነት ማዕከሉ ድረስ ይዘው በመምጣት ላይ ናቸው፡፡ ግብዓቶቹ ከተለያዩ ቦታዎች የሚመጡ ናቸው፡፡ እርጥብ ጭቃ ከቀጨኔ አካባቢ የሚመጣ ሲሆን፣ ደምባቂ የሚባል ነጭ አፈር የሚመጣው ከፍቼ አካባቢ ነው፡፡ የሸክላ ዕደ ጥበቡ ከተሠራ በኋላ ለማቃጠያ የሚጠቀሙበትን ኩበትና ሰጋቱራም ከተለያዩ ቦታዎች ገዝተው ይጠቀማሉ፡፡ ለሸክላ ሥራ የሚያገለግሉ ግብዓቶችን አንድ ተቋም የሚያገኙበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ዕቅድ ይዘናል፡፡ እነዚህንም ለሚያቀርቡ ሰዎች የሥራ ዕድል ለመፍጠርም ያስችለናል፡፡  ወደፊት ሥራውን በማስፋት የኢትዮጵያን የዕደ ጥበብ ውጤቶች ለማሳየት የምንንቀሳቀስበት ይሆናል፡፡

ሪፖርተር፡- በተቋሙ ውስጥ ምን ዓይነት ችግር አለ?

አቶ ሰለሞን፡- ተቋሙ ከተቋቋመ ትንሽ ጊዜ ያስቆጠረ በመሆኑ ችግሮች የሉትም ማለት አይቻልም፡፡ በተለይም ደግሞ ዘመናዊ ቴክኖሎጂን ተጠቅመው ሥራ የሚሠሩበት ሁኔታ የለም፡፡ ይሁን እንጂ ይህንን ችግር ለመፍታት እንቅስቃሴዎችን ጀምረናል፡፡ እናቶችም የሸክላ ሥራቸውን አጠናቀው ወደ ማቃጠያ ክፍል በሚወስዱበትና በሚያቃጥሉበት ጊዜ ጭሱ አዙሯቸው ሲወድቁ ዓይተናል፡፡ ይህ የሆነው በማቃጠያ ክፍሉ ጥበትና ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ባለመጠቀም ነው፡፡ በቅርቡ ያለውን ችግር የምንፈታበት መንገድ ይኖራል፡፡ የሸክላ ማዕከሉም ጠባብ በመሆኑ የሚሠሩባቸውን ግብዓቶች ማስቀመጫ የሚያጡበት ጊዜም አለ፡፡ ይኼም እንደ ትልቅ ችግር ይታያል፡፡ የገበያ ትስስሩን በተመለከተም አብዛኛውን ጊዜ የሚሸጡት ለነጋዴ በመሆኑ የሚያገኙት ትርፍ አነስተኛ ነው፡፡ ከዚህ በኋላ ግን የሠሩትን ሥራ በራሳቸው መንገድ እንዲሸጡ ለማድረግ በአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ በአዳነች አቤቤ በኩል ቃል የተገባልን የመሸጫ ማዕከል ስላለ ችግሩ የሚፈታ ይሆናል፡፡ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝም በሥራቸው ላይ ትልቅ ችግር ፈጥሮባቸዋል፡፡ አብዛኛው እናቶችም ስለ በሽታው ግንዛቤ እንዲያገኙና ራሳቸውን ከወረርሽኙ እንዲጠብቁ የተለያዩ ሥራዎችን በአካባቢው ከሚገኘው ወረዳ ጋር አብረን ሠርተናል፡፡ ወረርሽኙን የሚከላከሉበትን ግብዓቶች ሰጥተናል፡፡ እናቶች ጤንነታቸውን ጠብቀው የበለጠ ሥራ እንዲሠሩና አምራች እንዲሆኑ ዘመናዊ ማቃጠያ እየተሠራላቸው ይገኛል፡፡ የውኃ አቅርቦትን በተመለከተ እስካሁን ምንም ዓይነት ችግር አልፈጠረብንም፡፡ ለሸክላ ሥራው የሚያገለግለውን ጭቃ እስካሁን በሰው ነበር የሚቦካው ከዚህ በኋላ ግን ዘመናዊ ማሽን በማዘጋጀት ራሱ አቡክቶ እንዲሰጣቸው የሚደረግ ይሆናል፡፡ ይኼም ችግራቸውን በተወሰነ መልኩ ይቀንስላቸዋል፡፡ 

ሪፖርተር፡- መንግሥትስ ምን ዓይነት ድጋፍ ያደርግላችኋል?

አቶ ሰለሞን፡- ከገንዘብ አኳያ እስካሁን ድረስ መንግሥት ምንም ዓይነት ድጋፍ አላደረገልንም፡፡ እናቶቹም የገንዘብ ዕርዳታ የሚሹ አይደሉም፡፡ ከዚህ ይልቅ የበለጠ ተጠቃሚ የሚሆኑበትን መንገድ ለማመቻቸት ከከተማ አስተዳደሩ ጋር ውይይት እያደረግን ነው፡፡ መንግሥት ለሥራው የሚሆኑ ግብዓቶችሳይቋረጡ ማቅረቡ እንደ ትልቅ ሥራ የሚታይ ነው፡፡ እነዚህን እናቶች ጤንነታቸው ተጠብቆ እንዲሠሩ ዘመናዊ የሆኑ ማሽኖችን ለመትከል እያደረገ ያለው እንቅስቃሴም የሚበረታታ ነው፡፡ ይሁን እንጂ እነዚህ እናቶች ሥራቸውን ለመሥራት ከተለያየ ቦታ የሚመጡ በመሆኑ የትራንስፖርት አገልግሎት ሲቸገሩ ይታያል፡፡ ይህንንም ለመፍታት መንግሥት ኃላፊነቱን ለመወጣት እንቅስቃሴ ጀምሯል፡፡ የሠሯቸውንም የዕደ ጥበብ ውጤቶች በተመቻቸ ሁኔታ ሽያጭ እንዲያከናውኑ የቦታ ይዞታ የሚሰጣቸው ይሆናል፡፡ ችግሮቹ ሲቀረፉ በርካታ እናቶች በኑሯቸው የሚለወጡበት መንገድ ይኖራል፡፡

ሪፖርተር፡- በቀጣይስ ምን ለመሥራት አስባችኋል?

አቶ ሰለሞን፡- በቀጣይነት ተቋማችን ሰፋ ያሉ ሥራዎችን ለመሥራት ዕቅድ ይዟል፡፡ በተለይም ደግሞ የኢትዮጵያን ባህልና እሴት የጠበቁ ዕቃዎችን ለማምረት የምንሠራ ይሆናል፡፡ ለስጦታ ዕቃም ውብ የሆኑ የሸክላ ሥራ ውጤቶችን ለመሥራት ዕቅድ ይዘናል፡፡ ነገር ግን ትልቁና ዋናው ዕቅዳችን እዚህ ያሉት ማኅበራት በራሳቸው ወጥተው የራሳቸውን የሥራ ዕድል ፈጥረው በዓለም አቀፍ ደረጃ ሥራዎቻቸውን የሚያሳዩበት ሁኔታ እንዲኖር ማድረግ ነው፡፡ እንደዚህ ከሆኑ የኢትዮጵያን የባህልና የእሴት ትሩፋቶች ወደ ውጭ የሚወጣበት መንገድ ይፈጠራል፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

ብዝኃ ትምህርቱን ‹ስቴም› ለማስረፅ

ስሜነው ቀስቅስ (ዶ/ር) የስቴም (Stem) ፓውር ግብረ ሰናይ ድርጅት የኢትዮጵያ ዳይሬክተርና የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የቴክኖሎጂ አማካሪ ናቸው፡፡ በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የማስተርስና የፒኤችዲ...

‹‹እውነታውን ያማከለ የሥነ ተዋልዶ ጤና ግንዛቤን ማጠናከር ያስፈልጋል›› ደመቀ ደስታ (ዶ/ር)፣ በአይፓስ የኢትዮጵያ ተወካይ

በሥነ ተዋልዶ ጤና ጉዳዮች ላይ በመሥራት በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚንቀሳቀሰው አይፓስ፣ የኢትዮጵያን ሕግ መሠረት አድርጎ በሴቶች የሥነ ተዋልዶ ጤና ከጤና ሚኒስቴርና ከክልል ጤና ቢሮዎች...

የልጅነት ሕልም ዕውን ሲሆን

‹‹ሰውን ለመርዳት ሰው መሆን በቂ ነው›› የሚል በብዙዎች ዘንድ የሚዘወተር አባባል አለ፡፡ አባባሉ የተጎዳን ሰው ለመርዳት፣ የወደቁትን ለማንሳት፣ ያዘኑትን ለማፅናናት፣ ከገንዘብ ባሻገር ቅንነት፣ ፈቃደኝነት፣...