Monday, June 24, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ኦሮሚያ ኢንሹራንስ ኩባንያ የዓረቦን ገቢው ቢጨምርም ትርፉ ቀንሷል

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ኦሮሚያ ኢንሹራንስ አ.ማ. በተጠናቀቀው የ2012 የሒሳብ ዓመት ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ የዓረቦን ገቢ ቢያገኝም፣ ከታክስ በፊት ዓመታዊ ትርፍ ምጣኔው ካለፈው ዓመት በ18 ሚሊዮን ብር ቀንሶ 74.2 ሚሊዮን ብር ማትረፍ ችሏል፡፡

ኩባያው የ2012 የሒሳብ ዓመት አፈጻጸሙን ባለፈው ቅዳሜ ይፋ ባደረገበት ወቅት እንደተገለጸው፣ ኩባንያው በ2012 የሒሳብ ዓመት ከታክስ በፊት 74.2 ሚሊዮን ብር አትርፏል፡፡ ሆኖም በ2011 የሒሳብ ዓመት ከታክስ በፊት አግኝቶት ከነበረው የትርፍ መጠን 92.3 ሚሊዮን ብር ጋር ሲነፃፀር ዝቅተኛና ከ18 ሚሊዮን ብር በላይ ቅናሽ የታየበት ነው፡፡ ከታክስ በኋላ የተገኘው ትርፍ ደግሞ ከቀደመው ዓመት በ13.3 ሚሊዮን ብር ቅናሽ ያሳየ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡ በቀዳሚው 2011 የሒሳብ ዓመት ከታክስ በኋላ አግኝቶት የነበረው የትርፍ መጠን 87.2 ሚሊዮን ብር እንደነበር ይታወሳል፡፡ የትርፍ ምጣኔው መቀነስ ኩባንያው ባለአክሲዮኖች የሚከፋፈለውን የትርፍ ድርሻ መጠን ቀንሶታል፡፡ በ2011 ዓ.ም. አንድ አክሲዮን አስገኝቶት የነበረው የትርፍ ድርሻ 390 ብር የነበረ ሲሆን፣ በ2012 ላይ ወደ 230 ብር ዝቅ እንዲል አድርጎታል፡፡

በሌላ በኩል ግን ኩባንያው በሒሳብ ዓመቱ የትርፍ ምጣኔው ከዓረቦን ካሰባሰበው ረገድ ከቀዳሚው ዓመት ብልጫ ያለው ውጤት ያገኘበት እንደ ነበር ተጠቅሷል፡፡ ከዓረቦን ያገኘው ገቢ ከዕቅዱ አንፃር የተወሰነ ቅናሽ ቢኖረውም፣ በ2011 የሒሳብ ዓመት ካሰባሰበው ብልጫ የታየበት መሆኑን ከኩባንያው ዓመታዊ የሒሳብ ሪፖርት ለመረዳት ተችሏል፡፡

ኩባንያው በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት በጥቅል 505 ሚሊዮን ብር ዓረቦን ያሰባሰበ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ ሕይወት ነክ ካልሆነ የመድን ዘርፍ ማሰባሰብ የቻለው የዓረቦን መጠን 478 ሚሊዮን ብር ሲሆን፣ ከማክሮ መድን ዘርፍ ደግሞ 17.8 ሚሊዮን ብር የዓረቦን ገቢ ማሰባሰብ ችሏል፡፡ ከሕይወት መድን ዘርፍ ደግሞ 9.48 ሚሊዮን ብር ማሰባሰብ መቻሉን የኩባንያው ሪፖርት ያመለክታል፡፡ ኩባንያው በሒሳብ ዓመቱ ከጠቅላላ መድን ዘርፍ 525 ሚሊዮን ብር፣ ከማክሮ ኢንሹራንስ 12.5 ሚሊዮን ብርና ከሕይወት መድን ዘርፍ ደግሞ 10.2 ሚሊዮን ብር ነበር፡፡ ከዕቅዱ አንፃር ከጠቅላላ የመድን ዘርፍ አገኛለሁ ብሎ ካቀደው ዓረቦን 91 በመቶውን ማሳካት ሲቻል የ2012 የሒሳብ ዓመት አፈጻጸሙ ከቀዳሚው ዓመት የ10 በመቶ ብልጫ ያለው ሆኗል፡፡

ከማክሮ መድን ዘርፍ ግን ያገኘው ገቢ ከዕቅዱ በላይ ማከናወን መቻሉን የሚያመለክት ሲሆን፣ ከዚህ ዘርፍ 12.5 ሚሊዮን ብር የዓረቦን ገቢ ለማሰባሰብ አቅዶ 17.8 ሚሊዮን ብር ማሰባሰብ ችሏል፡፡ ይህም የዕቅዱን 143 በመቶ ማሳካቱን ነው፡፡ ከማክሮ መድን ዘርፍ ያገኘው የዓረቦን ገቢ ከቀደሚው ዓመት ማሰባሰብ ከቻለው የ77 በመቶ ዕድገት ያሳየ ነው፡፡ ከሕይወት መድን ዘርፍ ግን ከዕቅዱ ያነሰ አፈጻጸም ቢያሳይም ከቀዳሚው ዓመት የ14 በመቶ ብልጫ ያለው ዓረቦን መሰብሰብ ችሏል፡፡

ከኩባንያው ዓመታዊ ሪፖርት መገንዘብ እንደሚቻለው በ2012 የሒሳብ ዓመት ከጠቅላላ የኢንሹራንስ ዘርፍ ውስጥ ከፍተኛውን ዓረቦን የሰበሰበው ከሞተር ወይም ከተሽከርካሪዎች መድን ሽፋን ሲሆን፣ ከሞተር መድን ያሰባሰበው የዓረቦን መጠን 317.8 ሚሊዮን ብር ነው፡፡

ኩባንያው በሒሳብ ዓመቱ ከቀረቡለት 372.6 ሚሊዮን ብር ዋጋ ያለው የካሳ ጥያቄ ውስጥ የሞተር ወይም የተሽከርካሪ የካሳ ክፍያ 273.5 ሚሊዮን ብር ድርሻ ይዟል፡፡ ይህም ለካሳ ክፍያ ከዋለው ውስጥ ከ65 በመቶ በላይ የሚሆነው የዚሁ የሞተር ኢንሹራንስ ድርሻ ሆኗል፡፡ ከሞተር መድን ዘርፍ ቀጥሎ ኩባንያው ለካሳ ክፍያ ያዋለው ለኮስት አደጋ የመድን ዘርፍ ያዋለው ሲሆን ይህም 30.1 ሚሊዮን ብር ነው፡፡

ኩባንያው ከሌሎች የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ለየት ባለ ሁኔታ በተለያዩ ኢንቨስትመንቶች ላይ በመሳተፍ የሚጠቀስ ሲሆን፣ እስካሁን ከ786 ሚሊዮን ብር በላይ የሚሆን የኢንቨስትመንት ወጪ አድርጓል፡፡ ከእነዚህ ኢንቨስትመንቶች በ2012 የሒሳብ ዓመት ከባንክ ተቀማጭ ወለድን ጨምሮ ከ87 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢና ትርፍ አስገኝተውለታል፡፡ ኩባንያው ከዋና መሥሪያ ቤት ወጪ ካደረገው ኢንቨስትመንት ሌላ መዋዕለ ንዋዩን ፈሰስ ካደረገባቸው ኩባንያዎች ውስጥ ጉቱ ኦሮሚያ ቢዝነስ አ.ማ.፣ ኤሌምቱ ኢንተግሬትድ ወተት ኢንዱስትሪ፣ ኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ፣ የኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ፣ የኢትዮጵያ ጠለፋ መድን አ.ማ.፣ ኦዳ ኢንተግሬትድ ትራንስፖርት፣ ሸገር ማይክሮ ፋይናንስ ኦሮሚያ፣ ኢንተርናሽናል ባንክና ኦዳ ሪልስቴት አ.ማ. ይጠቀሳሉ፡፡ በተለያዩ ተቋማት ኢንቨስት ያደረገው የገንዘብ መጠን ከቀዳሚው ዓመት ብልጫ ያሳየ ሲሆን፣ እስከ 2011 የሒሳብ ዓመት መጨረሻ ድረስ 539 ሚሊዮን ብር የነበረ ሲሆን፣ በ2012 መጨረሻ ላይ ደግሞ 786.2 ሚሊዮን ብር ደርሷል፡፡ የኦሮሚያ ኢንሹራንስ ኩባንያን ያህል በተለያዩ ተቋማት ውስጥ ኢንቨስትመንት ያለው የግል ኢንሹራንስ ኩባንያ ያለመኖሩን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

ኦሮሚያ ኢንሹራንስ ኩባንያ እ.ኤ.አ. በ2009 ጃንዋሪ በ540 ባለአክሲዮኖች፣ በ26 ሚሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታል ወደ ሥራ የገባ ነው፡፡ ሰኔ 2012 መጨረሻ ድረስ የኩባንያው የተከፈለ ካፒታል መጠን 400.4 ሚሊዮን ብር ደርሷል፡፡ የኩባንያው አጠቃላይ የሀብት መጠንም 1.43 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡

በአሁኑ ወቅት አገልግሎቱን በ43 ቅርጫፎችና በሰባት አገናኝ በሮች አገልግሎት እየሰጠ ያለው ኦሮሚያ ኢንሹራንስ ኩባንያ 396 ሠራተኞች አሉት፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች