Friday, December 1, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ዘመን ኢንሹራንስ ከሰበሰበው 161 ሺሕ ብር ዓረቦን በላይ ከ18.3 ሚሊዮን ብር አተረፈ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ገበያውን ከተቀላቀለ ዓመት አልሞላውም

በኢትዮጵያ የኢንሹራንስ ገበያን ዘግይቶ የተቀላቀለውና 17ኛው የግል ኢንሹራንስ ኩባንያ በመሆን ሥራ የጀመረው ዘመን ኢንሹራንስ አ.ማ. በ2012 የበጀት ዓመት ከሰበሰበው ዓረቦን በእጅጉ ብልጫ ያለውን 18.3 ሚሊዮን ብር ማትረፍ መቻሉ ተገለጸ፡፡ ኩባንያው በእጅጉ የበለጠ ትርፍ ማግኘት የቻለው ከባንክ የወለድ ክፍያ ነው፡፡

ዘመን ኢንሹራንስ ባለፈው ቅዳሜ ባካሄደው የመጀመርያው ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ባቀረበው ሪፖርት ሥራ በጀመረ የተወሰኑ ወራቶች ውስጥ ያስመዘገበው የትርፍ መጠን ሥራ ላይ በቆየባቸው ስድስት ወራቶች ከሰበሰበው 161,840 ብር የዓረቦን ገቢ ሲሆን፣ በዓመቱ መጨረሻ ላይ ያገኘው ትርፍ 18.3 ሚሊዮን ብር ነው፡፡

ኩባንያው ወደ ሥራ ከገባ በወራት የሚቆጠር ዕድሜ ያለው ሲሆን ከጥር እስከ ሰኔ 2012 ዓ.ም. መጨረሻ ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ የሰበሰበው የዓረቦን መጠን ግን 161,840 ብር ብቻ ነው፡፡ ይህም ከሞተር ኢንሹራንስ 138,518 እንዲሁም ከማሪን (ከባህር ትራንስፖርት) ኢንሹራንስ 23,322 ዓረቦን ሰብስቧል፡፡ ኩባንያው ይህንን ያህል ዓረቦን ሰብስቦ ከ18 ሚሊዮን ብር በላይ ማትረፉ በኢንዱስትሪ ውስጥ ከሰበሰበው ዓረቦን በላይ ትርፍ በማስመዝገብ ብቸኛው የኢንሹራንስ ኩባንያ ሊያደርገውም ችሏል፡፡

እንደ ኩባንያው መረጃ ከሆነ በ2012 በጀት ዓመት መጨረሻ ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ በኢንዱስትሪው ዝቅተኛውን ዓረቦን የሰበሰበ ቢሆንም፣ ያገኘው ትርፍ ግን ከፍተኛ ነው፡፡ ኩባንያው ይህንን ትርፍ ለማስመዝገብ የቻለው ወደ ሥራ ከመግባቱ በፊት ከአክሲዮን ሽያጭ የሰበሰበውን ገንዘብ በባንክ በማስቀመጥ ካገኘው ወለድ ጠቀም ያለ ገቢ በማግኘቱ ነው፡፡

በጊዜ ገደብ በባንክ የተቀመጠው የኩባንያው ገንዘብ ከመደበኛ የተቀማጭ ገንዘብ 1.05 ሚሊዮን ብር፣ በጊዜ ገደብ ከተቀመጠ ተቀማጭ ገንዘብ ደግሞ 18.83 ሚሊዮን ብር፣ እንዲሁም ከመንግሥት ቦንድ ግዥ 275,439 ሺሕ ብር ገቢ ማግኘቱን የኩባንያው ሪፖርት ያመለክታል፡፡ ከአክሲዮን ሽያጭ የአገልግሎት ክፍያም 5.73 ሚሊዮን ብርና ከሌሎች ገቢዎች 4,549 ብር ገቢ ስለማግኘቱ ሪፖርቱ ያመለክታል፡፡ በመሆኑም ኩባንያው ወደ ሥራ በገባበት በመጀመርያው ዓመት (በስድስት ወራት) ከታስ በፊት 18 ሚሊዮን ብር ትርፍ ሊያስገኝለት ችሏል፡፡

በዚሁ ትርፍ መሠረት ለባለአክሲዮኖቹ የትርፍ ድርሻ ለማከፋፈል የቻለ ሲሆን፣ የ2012 የሒሳብ ዓመት አንድ አክሲዮን 20 በመቶ ትርፍ እንዳስገኘ ታሳቢ ተደርጓል፡፡ የኩባንያው አደራጆች ወደ ሥራ የገቡት እ.ኤ.አ. በዲሴምበር 2017 በመሆኑ ከአክሲዮን ሽያጭ የተገኘው ገንዘብ የባንክ ወለድ ሲታሰብበት በመቆየቱ ከባንክ ወለድ ብቻ ከ18 ሚሊዮን ብር በላይ ለማግኘት ችሏል፡፡  

ዘመን ኢንሹራንስ እስከ 2012 መጨረሻ ድረስ ኩባንያውን ለማቋቋም ያወጣውን 5.2 ሚሊዮን ብር ጨምሮ አጠቃላይ ወጪው 8.03 ሚሊዮን ብር እንደነበር አመልክቷል፡፡ ዘመን ኢንሹራንስ ኢንዱስትሪውን የተቀላቀለው በ79.8 ሚሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታልና በ112 ሚሊዮን ብር ቃል በተገባ ካፒታል ነው፡፡ በ2012 መጨረሻ ላይ የተከፈለ ካፒታል መጠኑ 98.7 ሚሊዮን ብር ሲደርስ የተመዘገበ ካፒታል ደግሞ 116.6 ሚሊዮን ብር ደርሷል፡፡

የዘመን ኢንሹራንስ የመጀመርው የቦርድ ሊቀመንበር በመሆን ማገልገል የጀመሩት የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት መላኩ እዘዘው (ኢንጂነር) ናቸው፡፡ የኩባንያው የመጀመርያው ዋና ሥራ አስፈጻሚ በመሆን የተሰየሙት ደግሞ አቶ ሹመቴ ዘሪሁን ናቸው፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች