Tuesday, February 27, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በጣፋጭ ምርቶች ላይ የተጣለው የኤክሳይስ ታክስ ህልውናችንን አደጋ ላይ ጥሎታል ሲሉ አምራቾች ገለጹ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በቅርቡ ተግባራዊ የሆነው አዲሱ የኤክሳይስ ታክስ አዋጅ መሠረት የ30 በመቶ የኤክሳይዝ ታክስ የተጣለባቸው የጣፋጭ አምራቾች ከገበያ እያስወጣና ህልውናቸውንም እየተፈታተነ መሆኑን ገለጹ፡፡

ተሻሽሎ እየተተገበረ ያለው የኤክሳይስ አዋጅ ዘርፉን በእጅጉ እየጎዳ ስለመሆኑ በጥናት ላይ የተመሠረተ መረጃ ጭምር ያቀረበው የኢትዮጵያ የስኳርና ጣፋጭ አምራቾች ማኅበር በጣፋጭ አምራቾች ላይ የተጣለው የ30 በመቶ የኤክስሳይስ ታክስ በዘርፉ የተሰማሩትን የአገር ውስጥ አምራቾች ከገበያ ውጪ እያደረጋቸው ነው፡፡

ከ110 በላይ አባላት ያሉት የኢትዮጵያ የስኳርና ጣፋጮች አምራቾች ማኅበር ሰሞኑን ይፋ ባደረገው ጥናት አዋጁ ተግባራዊ ከተደረገ ወዲህ ባለፉት አምስት ወራት አምራቾቹ በከፍተኛ ደረጃ ሽያጫቸው ቀንሶባቸዋል፡፡ የ14 ድርጅቶች የንግድ እንቅስቃሴ ለማሳያነት ተወስዶ በተካሄደው የዳሰሳ ጥናት ውጤትም ዘርፉ እየደረሰበት ያለውን የጉዳት መጠን የሚያሳይ ነው ተብሏል፡፡ የኤክሳይስ ታክስ ከመተግበሩ በፊት እነዚህ 14ቱ ድርጅቶች አጠቃላይ ሽያጫቸው ወደ 225.5 ሚሊዮን ብር እንደነበር ከኤክሳይስ አዋጁ መተግበር በኋላ ግን እነዚህ ድርጅቶች ሽያጫቸው ወደ 84.2 ሚሊዮን ብር እንደወረደ የቀረበው ጥናት ያመለክታል፡፡ 

ይህም የ14ቱ ፋብሪካዎች ሽያጭ 62 በመቶ መውረዱን ይኼው ጥናት አመልክቶ አዲሱ የኤክሳይስ ታክስ በጣፋጭ አምራቾቹ ላይ እያሳረፈ ያለውን ተፅዕኖ አመላክቷል፡፡

ማኅበሩ ባስጠናው ጥናት መሠረት በዚህ ዘርፍ ላይ እየደረሰ ያለውን ተፅዕኖ በተለያዩ ማሳያዎች ያመለከተ ሲሆን፣ አምራቾቹ በሚያመርቷቸው ጣፋጭ ምርቶች ላይ ከተጣለው 30 በመቶ የኤክሳይስ ታክስ በተጨማሪ፣ ለግብዓት በሚጠቀሙት ስኳር ምርት ላይ 20 በመቶ ኤክሳይስ ታክስ በመጣሉ ዘርፉን እንደጎዳው አመልክቷል፡፡ የጣፋጭ አምራቶቹ 80 በመቶ የሚሆነውን የማምረቻ የጥሬ ዕቃቸውን ከአገር ውስጥ በመጠቀማቸው የውጭ ምንዛሪ ማዳን መቻላቸውንና ፋብሪካዎቻቸው ከአዲስ አበባ ወጣ ያሉ አካባቢዎች በመሆናቸው ለአካባቢው ማኅበረሰብ የሚያደርጉት አስተዋጽኦ ትንሽ የሚባል እንዳልሆነ ገልጸዋል፡፡

 የኅብረተሰብ ጤናን የሚጎዱ በመሆናቸው በስኳርና መሰል ግብዓቶች ላይ በኤክሳይስ ታክስ መጣሉ ይታወሳል፡፡ በዚህም ምክንያት የጣፋጭ አምራቾች የማምረቻ ዋጋቸው 50 በመቶ እንዲጨምር በማድረጉ ገበያ ውስጥ ተወዳዳሪ እንዳይሆኑ አድርጓቸዋል፡፡ ከዚህ ቀደም 100 ብር ሲሸጥ የነበረ አንድ ጣፋጭ ምርት ተጨማሪ እሴት ታክስን ተጨምሮ 115 ይሸጥ የነበረ ሲሆን፣ አሁን ላይ ግን ሽያጩ ወደ 150 ብር ከፍ በማለቱ ተወዳዳሪ ዋጋ በማቅረብ በገበያ ውስጥ ለመቀጠል የማያስችል መሆኑንም ይጠቅሳል፡፡

የማምረቻ ወጪው በዚህን ያህል ደረጃ መጨመር ደግሞ የአገር ውስጥ አምራቾችን የሚጎዳና ከውጭ የሚገቡና ምንም ዓይነት የሥራ ዕድልና እሴቶችን ሳይጨምሩ ተመሳሳይ ምርቶችን የሚያስመጡ ድርጅቶችን የሚያበረታታ እንደሆነም ጥናቱ ያመለክታል፡፡

በዚህ ጉዳይ ላይ ያነጋገርናቸው የሚኖራ የጣፋጭ አምራች ኢንዱስትሪ ባለቤት ወ/ሮ አንቺነሽ ተስፋዬ ይህን ሥጋት ከሚያነሱና በዘርፉ የተሰማሩት ውስጥ አንዱ ናቸው፡፡ እንደ ወ/ሮ አንቺነሽ ገለጻ፣ እሳቸው በባለቤትነት የሚያስተዳድሩት ፋብሪካቸው ከ300 በላይ ሠራተኛ ያሉት ሲሆን፣ አዲስ የኤክሳይስ ታክስ ተግባራዊ ከሆነ በኋላ የማምረት አቅማቸውን መቀነሱ ብቻ ሳይሆን የተመረተውንም ለመሸጥ አለመቻሉን ይገልጻሉ፡፡

አሁን ባለው ሁኔታ ሥራቸውን ለመሥራት እየተቸገሩ መሆኑን ጠቅሰው፣ የኤክስሳይስ ታክስ በማስቀረት በውጭ ምንዛሪ ማግኘት እንዲችሉ ቢያደርጉና ዘርፉን በተለያዩ መንገዶች መንግሥት እንዲደግፍው ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ኬንያን ጨምሮ ከኢትዮጵያ ጣፋጭ አምራቾች ጋር የሚደረገው ውድድር ከፍተኛ መሆኑን የሚገልጹት ወ/ሮ አንቺነሽ በኬንያ የስኳር አቅርቦት ተመጣጣኝ፣ የኤክሳይስ ታክስም ሆነ የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት ችግር የሌለባቸው ከኢትዮጵያ አምራቾች ባነሰ ዋጋ እየሸጡ በመሆኑ ከዚህ አካባቢ በሚገባ ምርት የኢትዮጵያ አምራቾች ከገበያ ውጭ የመሆን ሥጋት ተጋርጦባቸዋል ብለዋል፡፡

በተለይም የቸኮሌት ምርት ለሚያመርቱ ፋብሪካዎች ጥሬ ዕቃ ከውጭ የሚገባ በመሆኑ የኤክሳይስ ታክስ ሲጨመር እስከ 40 በመቶ እንዲሁም የጉምሩክ ክፍያ ሲጨመርበት ወደ 70 በመቶ ከፍ የሚል በመሆኑ በዚህን ያህል ዋጋ ጭማሪ ተወዳዳሪ መሆን እንደማይችል ወ/ሮ አንቺነሽ ገልጸዋል፡፡

ኤክሳይስ ታክስ ከተጣለ አምስት ወራት በኋላ የተሠራው ይህ ጥናት የሚያሳየው ከኤክሳይስ ታክስ በፊትና በኋላ ተብሎ በኢንዱስትሪው ላይ የደረሰውን ጉዳት ከፍሎ ያሳየ ነው፡፡ በተለይ በዚህ ጥናት 12 ዋና ጥሬ ዕቃ አቅራቢዎች የስኳር፣ የግሉኮስና ፍሌቨር የሚያቀርቡት ኤሳይስ ታክስ ከመጣሉ በፊት የግዥ መጠንና ከዚያ በኋላ ያለው ተፅዕኖ ከፍተኛ መሆኑንም የሚጠቅስ ነው፡፡

አንድ ግሉኮስ የሚያቀርብ ድርጅት መረጃ እንደሚያመለክተው ከኤክሳይስ ታክስ በፊት 90 በመቶ የሚሆነውን ምርቱን ለጣፋጭ ኢንዱስትሪ ያቀርብ እንደነበር ከኤክሳይስ ጭማሪው በኋላ ሽያጩ ዜሮ መድረሱንም በዕለቱ ከቀረበው ጥናታዊ ጽሑፍ ላይ ተጠቅሷል፡፡

የግሉኮስና የፍሌቨር አምራቾች የሽያጫቸው መጠን እየወረደ ሲመጣ ደግሞ በውስጡ የሚሠሩ ሠራተኞች ቁጥር ሊቀንስ እንደሚችል በመጥቀስ የዚህ ኢንዱስትሪ መጎዳት ሠራተኞችን እስከመበተን ያደርሳልም ተብሏል፡፡

በዘርፉ ላይ የተጣለው የኤክሳይዝ ታክስ መጠን የተገለጹትን ጉዳቶች እያስከተለ በመሆኑ እየታየ መስተካከል አለባቸው ተብሎ የታመነባቸው ሐሳቦች በጥናቱ ተካተዋል፡ ከነዚህ ውስጥም መንግሥት በምርቱ ላይ የተጣለው የኤክሳይስ ታክስ ከተቻለ ሙሉ ለሙሉ እንዲቀር ማኅበሩ የጠየቀ ሲሆን፣ ካልተቻለ ደግሞ ተመጣጣኝ የሆነ መጠን ያለው ምጣኔ እንዲስተካከል የሚለው ይገኝበታል፡፡  

ኤሳይስ ታክስ የተጣለበት ወቅት ላይ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መከሰት በይበልጥ ችግሩን ያጎላ መሆኑን በዚህም ሠራተኞች፣ ፋብሪካዎች ተዘግተው ሊበተኑ ጫፍ ላይ የደረሱ ፋብሪካዎች እንዳሉ ተገልጿል፡፡ 

በጥናቱ ከተካተቱ ተያያዥ ጉዳዮች ውስጥ የኤክሳይስ አዋጁና የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ተደራርቦ መምጣት በወቅቱ የኮሮና ቫይረስ አስቸኳይ አዋጅ ሠራተኞቻቸውን ማባረር በሕግ የተከለከለ በመሆኑ ከ33 በመቶ በላይ ጊዜያዊ ሠራተኞች ለመቀነስ እንደተገደዱ ጥናቱ ጠቁሟል፡፡

መንግሥት የኤክሳይስ ታክስ የጨመረው በዋናነት በቅንጦት ሸቀጣ ሸቀጦችና የኅብረተሰቡን ጤና የሚጎዳ የሚጣል የግብር ዓይነት እንደሆነ ይታወቃል፡፡

በዚህም በስኳር ላይ የጣለው የኤክሳይስ ታክሲ ሊነሳ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፣ ለመተግበርም የሕግ ረቂቅ መዘጋጀቱ ታውቋል፡፡

በረቂቅ አዋጁ አንቀጽ 30 ላይ የስኳር ኢንዱስትሪው የኤክሳይስ ታክስ ነፃ ስለማድረግ በሚል ድንጋጌ ሥር፣ ‹‹በቅንጦት ሸቀጣ ሸቀጦች ላይ የሚጣለው የኤክሳይስ ታክስ በስኳር ኢንዱስትሪው ላይ ተፈጻሚነት አይኖረውም›› ይላል፡፡

በዚህም በስኳር ምርት ላይ 33 በመቶ የኤክሰይስ ታክስ ጭማሪ የተደረገ ሲሆን፣ በጣፋጭ ምርት ደግሞ 30 በመቶ መሆኑ ይታወቃል፡፡ የጣፋጭ አምራቾች ማኅበር ሥር የተሰባሰቡት ፋብሪካዎች ዋና ዋና ምርቶቻቸው የተለያዩ ከረሜላ፣ ቸኮሌት ናቸው፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች