በትግራይ ክልል መንግሥትና በፌዴራል መንግሥት መካከል እየተካረረ የቆየውን ውጥረት በመመልከትና በመተንተን ሁለቱ አካላት ወደ ወታደራዊ ግጭት ሊያመሩ ይችላሉ በማለት ሥጋታቸውን ሲገልጹና ሲያስጠነቅቁ የነበሩ ተቋማትና ግለሰቦች ቢኖሩም፣ መንግሥት ከትግራይ ክልል ጋር ወደ ጦርነት ለመግባት ፍላጎት እንደሌለውና ከጥይት ይልቅ ለኅብረተሰቡ ጤና መጠበቂያ የሚሆን ቁስ መላክን እንደሚመርጥ በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ጭምር ሲገልጽ ነበር፡፡
ይሁንና በሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) የሚመራው የትግራይ ክልል በተለያዩ ጊዜያት ሲያሠለጥናቸውና ሲያስታጥቃቸው በቆዩ የሚሊሻና የልዩ ኃይል አባላት በአገር መከላከያ ሠራዊት የሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት መፈጸሙን በማስታወቅ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የመከላከያ ሠራዊቱ ዕርምጃ እንዲወስድና ራሱን ተከላክሎ እንዲቆም ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. ከእኩለ ሌሊት በኋላ ትዕዛዝ አስተላልፈውም ነበር፡፡
በሒደት እንደተገለጸው የዚህ ዘመቻ ዓላማዎች ሦስት ሲሆኑ፣ እነዚህም በትግራይ ክልል የሕግ የበላይነትን ማስጠበቅና ሠራዊቱን ማዳን፣ ተጨማሪ ጉዳት ሊያደርሱ የሚችሉና በሕወሓት ኃይሎች እጅ ይገኛሉ የተባሉ የጦር መሣሪያዎችን (በተለይም ሚሳይልና ሮኬቶችን) ማውደም፣ እንዲሁም በመከላከያ ኃይሉ ላይ ጥቃት እንዲፈጸም ያደረጉ የወንጀል ተጠርጣሪዎችን ለሕግ ማቅረብ የሚሉ ናቸው፡፡
የትግራይ ክልል ዋና ከተማ የሆነችውን መቐለን የፌዴራል መንግሥት ኅዳር 19 ቀን 2013 ዓ.ም. ከተቆጣጠረ በኋላ፣ በክልሉ ሲካሄድ የቆየው ወታደራዊ ዘመቻ ማብቃቱንና አሁን የቀረው በሕግ የሚፈለጉ ሰዎችን ማደንና ለሕግ ማቅረብ ነው ሲል አስታውቆ፣ በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች የጊዜያዊ አስተዳደር እንዲቋቋም መደረጉ ሲገለጽ ነበር፡፡
መንግሥት ምንም እንኳን ጦርነቱ ተጠናቅቋል ያለና በተለያዩ አካባቢዎች እየተንቀሳቀሱ የሚገኙትን የክልሉን አመራሮች በመከታተልና በመፈለግ ላይ መሆኑን ያስታወቀ ቢሆንም፣ በተለያዩ የክልሉ ሥፍራዎች በተለይም በመቐለና አካባቢው የተኩስ ልውውጦች እንደሚሰሙ የተለያዩ ሪፖርቶች ሲያመላክቱ ቆይተዋል፡፡
በሌላ ወገን ደግሞ በትግራይ ክልል በተካሄደው ጦርነት የተጎዱ የኅብረተሰብ ክፍሎችን መደገፍና የተፈናቀሉትንም ወደ ቀዬአቸው በመመለስ በዘላቂነት እንዲቋቋሙ የሚያስችሉ የሰብዓዊ ዕርዳታዎችን ማድረስ፣ በበርካታ ዓለም አቀፍ ተቋማት ግፊት ሲደረግበት የቆየ ጥያቄ ነው፡፡ መንግሥት የመከላከያ ሠራዊት በተቆጣጠራቸው ሥፍራዎች በሚገኙ አካባቢዎች የሰብዓዊ ዕርዳታ ለማቅረብ መንገዶችን ክፍት እያደረገ እንደሚሄድ በተደጋጋሚ ያስታወቀ ሲሆን፣ መቐለን ከተቆጣጠረም በኋላ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጋር ባደረገው ስምምነት በመንግሥት የሚመራ የሰብዓዊ ዕርዳታ ማሠራጫ መንገዶችን ከተለያዩ ተቋማት ጋር በማቀናጀት እየሠራ እንደሆነም ተገልጿል፡፡
በክልሉ እየተከናወነ ያለው ሕግ የማስከበር ዘመቻንና የሰብዓዊ ዕርዳታ ሥርጭትን በተመለከተ ማክሰኞ ኅዳር 29 ቀን 2013 ዓ.ም. በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አዳራሽ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ኮማንድ ፖስት ቃል አቀባይ ሬድዋን ሁሴን (አምባሳደር) ብሔራዊ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽነር አቶ ምትኩ ካሳ ጋር በጋራ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
አሁን እየተወሰደ ያለው ዕርምጃ የሕግ ማስከበር ዘመቻው የመጨረሻ ምዕራፍ ነው በማለት የገለጹት ሬድዋን (አምባሳደር)፣ በዚህም በወንጀል የሚጠረጠሩ ግለሰቦችን በቁጥጥር ሥር ማዋል፣ በተለያዩ ሥፍራዎች ጊዜያዊ አስተዳደር ማቋቋም፣ እንዲሁም የሕግ የበላይነት መከበሩን ማረጋገጥ ናቸው ብለዋል፡፡ የዚህ የሦስተኛው ምዕራፍ ዕርምጃ አንዱ አካል የሆነው ደግሞ፣ የአካባቢውን ማኅበረሰብ መልሶ ማቋቋም እንደሆነና እንደ ኤሌክትሪክና ቴሌኮሙዩኒኬሽን ያሉ መሠረተ ልማቶችን መልሶ መገንባት ነው ብለዋል፡፡
ይሁንና አሁን ጦርነቱ ተጠናቅቋል የሚሉት ሬድዋን (አምባሳደር) በተለያዩ ቦታዎች የቀሩና በኅብረተሰቡ ውስጥ ተሸሽገው የሚገኙ የትግራይ ሚሊሻና ልዩ ኃይል አባላት ተኩስ እንደሚከፍቱ ተናግረዋል፡፡ ይሁንናና ይኼ ጦርነት አለ ማለት እንዳልሆነና በትግራይ ክልል አሁን እየታየ ያለው ተኩስ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች እየታየ ካለው እንደማይለይ በማንሳት ሞግተዋል፡፡ ይኼም በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በአሜሪካ ሳይቀር በከተሞችና በትምህርት ቤቶች ሳይቀር ተኩስ እንደሚሰማ ገልጸዋል፡፡
‹‹ተኩስ ተሰማ ማለት በጦርነት ውስጥ እንገኛለን ማለት አይደለም፡፡ ተኩስ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ መተከልና ኦሮሚያ በመሳሰሉ አካባቢዎች ይሰማል፡፡ በትግራይ ያለው የተለየና ለብቻው የሚታይ አይደለም፡፡ አንዳንድ የልዩ ኃይልና የሚሊሻ አባላት ከሕዝቡ ጋር ተቀላቅለው ከአዛዦቻቸው ጋር ባይገናኙና መሣሪያ ባይደርሳቸውም እንኳን አንዳንዴ ተኩስ ይከፍታሉ፤›› ብለዋል፡፡
ሰብዓዊ ዕርዳታዎችን በተመለከተ የኢትዮጵያ መንግሥት ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እ.ኤ.አ. ኖቬምበር 28 ቀን 2020 መፈራረሙን በማስታወቅ፣፣ በመንግሥት በሚመራው በዚህ የሰብዓዊ ዕርዳታዎችን የማሠራጨት ተግባር ምግብና ምግብ ነክ ያሁኑ ዕርዳታዎች እንደሚሠራጩ አቶ ምትኩ ተናግረዋል፡፡
አቶ ምትኩ እስካሁን ለ250 ሺሕ ሰዎች የሚሆን ሰብዓዊ ዕርዳታ መሠራጨቱን በመጠቆም፣ በጠቅላላቅ የዚህ ድጋፍ ተጠቃሚ የሚሆኑ ሰዎች ቁጥር 1.8 ሚሊዮን ነው በማለት ተቋማቸው የሠራውን ዳሰሳ በማጣቀስ አስታውቀዋል፡፡
ይኼ ስምምነትና የመንግሥት የሰብዓዊ ዕርዳታ ድጋፍ የሰብዓዊ ዕርዳታ ማድረሻ መስመርን፣ የትብብር ማዕቀፍን፣ እንዲሁም የሰብዓዊ ድጋፍን ማሠራጨት የሚሉ ክፍፍሎች እንዳሉት ያስታወቁት አቶ ምትኩ፣ ለዚህም የሚሆን በተለያዩ ጊዜያት ተሞክረው ውጤታማነታቸው የተመሰከረላቸው የሰብዓዊ ዕርዳታ ማሠራጫ መንገዶችን በመጠቀም ወደ ሥራ እንደተገባ ገልጸዋል፡፡
አቶ ምትኩ አክለውም ኢትዮጵያ ለእንዲህ ያሉ ቀውሶች እምብዛም አዲስ እንዳልሆነችና በድርቅና በግጭቶች ሳቢያ ሲሠሩ በቆዩ የሰብዓዊ ዕርዳታ ማሠራጫ ሥራዎች በርካታ ልምድ መቀሰሙን፣ ይኼንንም ለሌሎች ሁሉ ለማካፈል የሚያስችል አቅም አለ ብለዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም የተለያዩ ተግባራትን የሚያከናውኑ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማትን ለማቀናጀት እንዲረዳ በክላስተር የሚመራ ሥርዓት እንደተዘጋጀ በመግለጽ፣ እነዚህ ክላስተሮች የግብርናና የቁም እንስሳት፣ የውኃና የፍሳሽ አገልግሎት፣ ጤና፣ የተመጣጠነ አመጋገብ፣ የምግብ አቅርቦት፣ የምግብ አቅርቦት፣ ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሶች አቅርቦት፣ የሕፃናትና ሴቶች ጥበቃ፣ እንዲሁም የትምህርትና ሳይት ማኔጅመንት ናቸው ብለዋል፡፡ ለአብነት በጠቀሱትም መሠረት የውኃና ፍሳሽ ክላስተርን የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከዩኒሴፍ ጋር በጥምረት የሚመሩት እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ይኼ የሆነበትም ምክንያት ዩኒሴፍ በውኃና ፍሳሽ ረገድ በርካታ ሥራዎችን ስለሚሠራ ወሳኝ ድርሻ ይኖረዋል በማለት አክለዋል፡፡
‹‹ለዚህ ሥራ የሚሆን አስተባባሪ ኮሚቴ ተቋቁሟል፡፡ እንደ ጉጂና ጌዴኦ ግጭቶች ካሉና በተለያዩ ጊዜያት ባጋጠሟት ግጭቶች ወቅት በሠራናቸው ሥራዎች በርካታ ልምድ ወስደናልና ከባድ አይሆንብንም፤›› በማለት አቶ ምትኩ ተናግረዋል፡፡
የአደጋ ሥጋትና ሥራ አመራር ኮሚሽን በትግራይ ክልል ዕርዳታ ያስፈልጋቸዋል ብሎ የለያቸው ሰዎች 1.8 ሚሊዮን ቢሆኑም፣ ቁጥሩ ሊጨምር እንደሚችልና በቀጣይ በሚሠሩ ዳሰሳዎች ከ20 እስከ 40 በመቶ የሚሆኑ የከተማ ነዋሪዎች ዕርዳታ ሊያስፈልጋቸው ይችላል የሚል ግምት አለ ብለዋል፡፡
ኮሚሽኑ በመሀል፣ በደቡብና በምዕራብ ትግራይ አካባቢዎች ሰብዓዊ ዕርዳታዎችን እያሠራጨ እንደሚገኝ በማስታወቅ፣ በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች እየተቋቋመ ያለው የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር መሠረታዊ እንደሆነና የመግቢያ በር እንደሚሆንም ጨምረው ገልጸዋል፡፡ እነዚህ ዕርዳታዎች እየተሠራጩ የሚገኙባቸው አካባቢዎች ስንዴ፣ ጥራ ጥሬዎች፣ የምግብ ዘይት፣ እንዲሁም የበለፀገ የበቆሎ ምርት ይገኙበታል ብለዋል፡፡
ይሁንና ሬድዋን (አምባሳደር) በተለያዩ ከተሞች የጊዜያዊ አስተዳደር እየተቋቋመ እንደሚገኝና የሕዝብ ውይይቶች እየተደረጉ እንዳሉ በማስታወቅ በአክሱም፣ በዓድዋ፣ በአዲግራትና በመቀሌ ግን ጊዜያዊ አስተዳደሩ ገና እንዳልተዋቀረ አልሸሸጉም፡፡
በአንዳንድ አካባቢዎች ታጣቂዎች ጥቃት እንደሚሰነዝሩና መጀመርያ በነበረው የሰብዓዊ ዕርዳታ ማሠራጫ ጉዞ ላይ ጥቃት መፈጸሙን በማስታወስ፣ ከዚህ በመነሳት ማንኛውም የሰብዓዊ ዕርዳታ ሥርጭት በወታደር አጀብ እየተደረገ እንደሚከናወን ሁለቱ ኃላፊዎች አስታውቀዋል፡፡
አሁን የሚታዩ እንደ ፀጥታ ያሉ የሰብዓዊ ዕርዳታ ማዳረስ ተግዳሮቶች በ15 ቀናት ውስጥ ተወግደው ሙሉ ለሙሉ ምቹ የሰብዓዊ ዕርዳታ ማሠራጫ መንገድ ይኖራል ብለው እንሚጠብቁና ለዚህም በርትተው እየሠሩ እንደሚገኙ ያስታወቁት አቶ ምትኩ፣ በትግራይ የሚደረገው የሰብዓዊ ዕርዳታ ሥርጭት እ.ኤ.አ. 2021 ድረስ እንደሚዘልቅ አስገንዝበዋል፡፡
ይሁንና የሰብዓዊ ዕርዳታ ማዳረስ ተግባር ከመልሶ ማቋቋም ጋር እጅ ለእጅ መሄድ አለበት በማለት፣ ይኼንን ማድረግ ካልተቻለ ለችግረኞች በቂ የሆነ ድጋፍ ማድረግ አስቸጋሪ ይሆናልም ሲሉ አሳስበዋል፡፡
አምባሳደር ሬድዋን በበኩላቸው ምንም እንኳን መንግሥት ድጋፍ ቢሻም፣ ለትግራይ ክልል ሰብዓዊ መብት ድጋፍ የሚውል ሀብት 60 በመቶ ከመንግሥት ካዝና የወጣ እንደሆነም አስገንዝበዋል፡፡
ከዚህ ባለፈም የመከላከያ ሠራዊቱና የፖሊስ ኃይሎች በጥምረት እየሸሹ ያሉ በወንጀል ተጠርጥረው የሚፈልጉ ሰዎችን እያሰሱ እንደሚገኙ በመጠቆም፣ እስካሁንም የሕወሓት ሥራ አስፈጻሚ አባላት የሆኑት የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ የነበሩት ወ/ሮ ኬሪያ ኢብራሂምና የትግራይ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር የነበሩት አምባሳደር አዲስ ዓለም ባሌማ በቁጥር ሥር ሆነው ለፖሊስ ቃላቸውን እየሰጡ እንደሚገኙ ጠቁመዋል፡፡ የእነዚህ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላትና የክልሉ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ለፖሊስ የሰጡት ቃል ለሕዝብ ይፋ እንደሚሆን አምባሳደር ሬድዋን ተናግረዋል፡፡
በትግራይ ክልል የፕሬዚዳንት ጽሕፈት ቤት በተደረገ ፍተሻ የመሬት ውስጥ ዋሻ መገኘቱን በማስታወስም፣ በመከላከያ ላይ ለደረሰው ጥቃት ቅድመ ዝግጅት ሲደረግ እንደቆየ ማሳያ የሆነ ግኝት ነውም ሲሉ አያይዘውታል፡፡
አሁን በሕግ የሚፈለጉ ተጠርጣሪዎች በሽሽት ላይ ናቸው የሚሉት ሬድዋን (አምባሳደር)፣ አንዳንድ ሰዎች ተመልሰው በመደራጀት ሽምቅ ውጊያ ሊጀምሩ ይችላሉ በማለት ቢሠጉም ይኼ በፍፁም አይሆንም ሲሉ አጣጥለውታል፡፡
በዚህ ጦርነት ውስጥ የፈጸሙ ጥቃቶችንና ተያያዥ ጉዳዮችን በሚመለከትም ገለልተኛ አካል ገብቶ የማጣራት ሥራ እንዲመረምር ለማድረግ መንግሥት እንዳላሰበ፣ መንግሥት ይኼንን ማድረግ አልችልም ብሎ ካመነና ካልተሳካለት ገለልተኛ የሆኑ የውጭ አጣሪዎችን ሊያስብ ይችላል በማለት ተከራክረዋል፡፡ ነገር ግን አሁን በኢትዮጵያ እየሠራ ያለና ጠንካራ መንግሥት በመኖሩ ማንኛውም የውጭ አካል ግብዣ እስከሚቀርብለትና መጠበቅ አለበት በማለት፣ ‹‹እየሞቱም እየገደሉም ያሉት ኢትዮጵያውያን ናቸውና ከእኛ በላይ በዚህ ጉዳይ የበለጠ ተቆርቋሪ አካል ሊኖር አይችልም፤›› ብለዋል፡፡
በትግራይ ክልል የአገር መከላከያ ሠራዊት ሲያካሂድ የቆየው ዘመቻ እነሆ አምስተኛ ሳምንቱን የያዘ ሲሆን፣ እስካሁን ድረስ በወጡ ሪፖርቶች ትግራይ ክልልን በአመራርነት ሲያገለግሉ የቆዩ ባለሥልጣናት እየሻሹ እንደሚገኙና እነርሱ ሲጠቀሙባቸው ነበሩ 40 ተሽከርካሪዎችም በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ተነግሯል፡፡ ይሁንና፣ ምን ያህል ሰዎች እንደሸሹ አልታወቀም፡፡
ዘመቻው በተጀመረ በሦስተኛው ሳምንት የአገር መከላከያ ሠራዊት መቐለ መግባቱን ተከትሎ ጦርነቱ በመገባደዱ ካሁን በኋላ የሚቀረው የፖሊስ ሥራ እንደሆነ፣ የሚፈለጉ ሰዎችንም በማሰስ ወደ ሕግ ማቅረብ ብቻ እንደሚቀር ሲነገር ቆይቷል፡፡ ለዚህም መንግሥት የሦስተኛው ዙር ዘመቻ አካል ነው የሚለውን ‹‹ወንጀለኞችን የማደንና የመልሶ ማቋቋም›› እንቅስቃሴ መጀመሩን ሲያስታውቅ ቆይቷል፡፡