- ሄሎ!
- የጥንቱ ወዳጄ ክቡር ሚኒስትር እንዴት አለህ?
- የጠፋ ሰው…ዛሬ ከዬት ተገኘህ?
- ከተንቤን፡፡
- ቀልድህ እኮ አይጠገብም።
- ቀልድ አይደለም፡፡
- እና ምንድነው?
- ግራ መጋባት፡፡
- ለምን?
- ቆላ ተንቤን ላይ ከበናቸዋል ስትሉን እሰይ አለቀ ብለን ደስታችንን ገልጸን ሳንጨርስ…
- ከበናቸው ነበር እኮ፡፡
- ታዲያ ምን ተፈጠረ?
- ከበባውን እያጠበብን ስንቀርባቸው እግሬ አውጪኝ አሉ።
- ወዴት?
- ደጋ ተንቤን፡፡
- ቆላ ተንቤን ስትሉ… ደጋ ተንቤን?
- ባህሪያቸውን ታውቀው የለ?
- ክቡር ሚኒስትር አሁን ደግሞ ዘልቀዋል እንዳትለኝ?
- ወዴት?
- ዋሻ ተንቤን፡፡
- የተቃዋሚ ነገር በቃ ማፌዝ ነው አሁንም?
- ለስደት የዳረገኝ ግፍ እረፍት ቢነሳኝ እኮ ነው ምን ላድርግ?
- እዚም ያው ነው… ሁሉም ከመቸኮሉ የተነሳ ስሜቱን መቆጣጠር ተስኖታል፡፡
- ሁሉም ማለት?
- የመንግሥት ኃላፊውም… ሚዲያውም… ሁሉም ጉጉቱን በልኩ ማድረግ ተቸግሮ እኛንም እየጎተተን ነው፡፡
- ወዴት?
- ወደ ስሜቱ ጎትቶን መታወቂያቸውን ይዘናል… ጫማቸው ተገኘ እያስባሉን ነው፡፡
- ልክ ብለሃል ክቡር ሚኒስትር፣ ሁሉም ሰከን ማለት አለበት።
[ለ15 ዓመታት ቤት ይደርሰኛል ብለው ከጥሪታቸው የቆጠቡ ነዋሪዎች እያሉ በአቋራጭ የመጡት የሚንበሸበሹባት አገር እያሉ የክቡር የሚኒስትሩ ባለቤት እያማረሩ ሳለ፣ ክቡር ሚኒስትሩ ቤታቸው ገብተው አረፍ አሉ]
- እንዲያው ምን ይሻላችኋል ግን?
- ምነው ምን ገጠመሽ?
- አንተ ሥልጣን ላይ እስካለህ እኔ ምን እሆናለሁ፡፡
- ታዲያ ምን ተፈጥሮ ነው የምታማርሪው?
- የሌሎችን ለቅሶ የሚያብስ ሲጠፋ እንዴት አላማርር?
- የምን ለቅሶ ነው?
- መች ተሳሳትኩ? እንኳን የምትመሩትን ሕዝብ ዕንባ ልታብሱ ይቅርና በውስጣችሁ ያለውንም ለቅሶ አትሰሙም።
- ለቅሶውን መድረስ እንቸገር ይሆናል እንጂ መስማትስ አንሰማለን፡፡
- ይህንን ለቅሶ ግን መቅረት የለባችሁም፡፡
- የማን ለቅሶ ነው?
- የዕንባ ጠባቂው።
- ዕንባ ጠባቂ ተቋምን ነው የምትይው?
- እህሳ! እንኳን ሊጠብቅ አብሮ እያነባ አይደል?
- ምን ሰምተሽ ነው?
- መኖሪያ ቤት አገኛለሁ ብለው ለ15 ዓመታት የቆጠቡ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ዕንባችንን ያብስልን እንደሆን ብለው ወደ ተቋሙ ሄዱ…
- እሺ፣ የሚሰማቸው አጡ?
- ኧረ አላጡም። ሰማቸው እንጂ… ችግራችሁም እንዲፈታ እናደርጋለን ብለው ሸኛቸው።
- እና ፈታላቸው አይደል?
- ማን ዕንባ ጠባቂው?
- እህሳ?
- የሚሰማው አጥቶ እሱም ለፓርላማ እዬዬ አለ እንጂ… ይኼንን አልሰማህም? እንዲያው ግን ነዋሪው አያሳዝናችሁም?
- እውነት አለሽ… ግዴለም የጀመርናትን ዘመቻ እናጠናቃት እንጂ ይኼ ጉዳይ መቋጫ ያገኛል።
- እሱ ሲጠናቀቅ ሌላ አይመጣም ብለህ ነው?
- ምን?
- ሌላ ዘመቻ!
[ክቡር ሚኒስትሩ ከአንድ የአውሮፓ ከፍተኛ ዲፕሎማት ጋር በቪዲዮ ኮንፈረንስ እየተወያዩ ነው]
- ክቡር ሚኒስትር በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ በእጅጉ ያሳስበናል፣ ያሠጋናልም። ለዚህም ነው በአንክሮ የምንከታተለው።
- ሥጋት እንዳላችሁ እንገነዘባለን። ነገር ግን ያሳሰባችሁ ነገር የኢትዮጵያ ሁኔታ ይሁን አይሁን ለመረዳት ትንሽ ተቸግረናል።
- የሚያሳስበን ነገር እየሆነ ያለው ኢትዮጵያ ውስጥ ሆኖ ሳለ ሌላ ምን ሊያሳስበን ይችላል? የኢትዮጵያውያን መፈናቀል ያሳስበናል፣ የኢትዮጵያ አለመረጋጋት ያሳስበናል።
- የተረጋጋች ኢትዮጵያን ለመፍጠር ስንል የምናካሂደው ዘመቻ ስለሆነ ከጎናችን ብትቆሙ ይጠቅማል። የዜጎች መፈናቀልም ጊዜያዊና በፍጥነት መልክ የሚይዝ በመሆኑ ብዙ መሥጋት የለባችሁም።
- እኛ ሥጋት አለን… ነገሩ ከቁጥጥር ውጪ ወጥቶ ወደ አፍሪካ ቀንድ እንዳይዛመት ሥጋት አለን።
- ገብቶኛል… ሥጋታችሁ ለኢትዮጵያ እንዳልሆነ ቀድሞውንም ተረድቼው ነበር።
- ምን እያሉ ነው ክቡር ሚኒስትር?
- ሜዲትራንያንን የሚያቋርጡ ስደተኞች ቁጥር ይጨምራል በሚል ለራሳችሁ ጥቅምና ፍላጎት ያደላ ሥጋት እንጂ፣ ለኢትዮጵያ ተጨንቃችሁ አይደለም።
- በፍፁም ተሳስተዋል… የኢትዮጵያ ሰላም እንዲደፈርስ አንፈልግም። ይህ ደግሞ ከኢትዮጵያ ጋር ካለን ትብብር ብቻ የሚመነጭ ሳይሆን ለአካባቢውም መረጋጋት ስንል ነው።
- አሜሪካ ከሶማሊያ ጦሯን ለማስወጣት መወሰኗን እንደ ሰሙ እርግጠኛ ነኝ… ይህ የሚያሳያው እኛ አካባቢ ያለመረጋጋት ሥጋት አሳሳቢ አለመሆኑ ይመስለኛል… ለማንኛውም ስለኛ በማሰባችሁ እናመሠግናለን።