ሰላም! ሰላም! ጀግንነትና አርበኝነት ውርስ በሆነበት አገር ውስጥ በመወለዴ እኔ ደላላው አንበርብር ምንተስኖ ከፍተኛ ኩራት ቢሰማኝም፣ ‘ወደፊት ሂድ’ ብዬ ወደ ሥራዬ ተሰማርቻለሁ። ጀግኖች ታሪክ በሚሠሩበት በዚህ ዘመን ከጀግኖች በላይ የሚፎክሩ የድል አጥቢያ አርበኞችን ቆሞ ከመታዘብ፣ የራስን ኃላፊነት በብቃትና በኃላፊነት መወጣት ባያፀድቅም ያስከብራል፡፡ ዘመኑን አማነውም አላማነውም፣ መንግሥትን አማረርነውም አሞገስነውም፣ መዓልትና ሌቱ መምሸት መንጋቱን መቼ ይተዋል? ውስጤ በደስታ ተጀቡኖ ወደ ሥራ ስሰማራ ደስታዬ እጥፍ ይሆናል፡፡ ታዲያላችሁ አንድ የሚከራየው ቤት ማግኘት የተቸገረ ሰው አላስቆም አላስቀምጥ ብሎኝ እንከራተትለታለሁ። ወገኔ ነዋ፡፡ ይገርማችኋል ይኼ ቤት አጥቶ ዕረፍት አሳጣኝ የምላችሁ ሰው የተከራየውን ቤት ለቆ እንዲወጣ ምሕረት የለሽ ውሳኔ የተላለፈበት በተጠናቀቀው ወር ነው። በዚህ ውርጩ ሸንቋጭ በሆነበት፣ ቅዝቃዜው አጥንት ድረስ ዘልቆ ውኃ በሚያደርግበት ኅዳር ወር መጨረሻ ነው፡፡ የምለው ገባችሁ? እንዴት አይገባችሁ!
‹‹ምንስ ቢሆን አሁን በዚህ ውርጭ ወዳጅ ቀርቶ ጠላት ይሸኛል?›› ብላቸው አዛውንቱ ባሻዬ፣ ‹‹ወይ አንተ! ይህንን ምስኪን ሰውና ጥጋበኞችን ምን አገናኛቸው? የሚያገናኛቸው አለ ብትለኝ እንኳ ሽኝት የሚለው ነው፡፡ ምስኪኑ ሰው የተሻለ ከፋይ መጥቶበት በአከራዩ ሲሸኝ፣ ጥጋበኞቹ ደግሞ የግፋቸው ዋንጫ ሞልቶ ሲፈስ ነው የኢትዮጵያ ሕዝብ ሆ ብሎ ተነስቶ ወደ የማይመለሱበት የሸኛቸው…›› ሲሉኝ ቅኔያቸው አስገርሞኝ ፈዝዤ እያየሁዋቸው ቆየሁ፡፡ እነሆ ይኼን ያህል ዘመን ያስቆጠረ የሰው የክፋት ጥግ መጨረሻው፣ በሰፈሩት መሰፈር አይቀርም ሆኖ እየተቋጨ ይመስላል። ‘ፍቅር ታማኝ ነው ወረትን አያውቅም፣ እንደ ሰው ለክፋት ቦታውን አይለቅም’ እየተባለ እስከ መቼ? አንዱ ነገረኛ፣ ‹‹አንበርብር ምን አግኝተህ ነው በደስታ ፍንጥዝ ያልክ ትመስላለህ?›› ሲለኝ፣ ‹‹አንተ ደግሞ ምን ሆነህ ነው በንዴት ፊትህን የዘፈዘፍከው?›› ብዬ ቆሌውን ገፈፍኩት። መላው የአገሬ ሰው ከጫንቃው ላይ የዓመታት ሸክሙ ተቃሎለት ሲደሰት እያየ፣ እኔን ብቻ ነጥሎ ሲነቁረኝ ችግር አለበት ማለት ነው፡፡ እዚያው ከቢጤዎቹ ጋር አፍንጫውን ይንፋ!
አንድ ቀልደኛ ወዳጄ ደግሞ ፊቱ ፋሲካ መስሎ መጣ፡፡ የእሱ እንዲህ መፍካት አስገርሞኝ፣ ‹‹ጃል ምን ተገኘ እባክህ?›› ስለው፣ ‹‹ዘንድሮ ሰው ቀልዱን ተክኖበት የለ እንዴ…›› ብሎ ይስቅ ጀመር፡፡ እኔም ሳቁን ልጋራው ፈልጌያለሁና መቆስቆስ ጀመርኩ፡፡ ‹‹በላ ከቀልዱ ልቀቅብኝና ቀኔን ላሳምረው…›› እያልኩ ላግባባው ስሞክር ስልኩን ከኪሱ መዝረጥ አድርጎ ሲከፍተው፣ በትልቅ ትሪ ሳህን የተለያዩ ምግቦች ተደርድረው ያስጎመዣሉ፡፡ መሀል ላይ ጥብስ ቀይ ወጥ ሆኖ ዙሪያውን ክትፎ፣ ቀይና ነጭ ጥብስ፣ ጎመን በሥጋ፣ ዱለት፣ አልጫ ፍትፍትና ጥብስ ፍርፍር ከበውታል፡፡ ዓይኔን በልጠጥ አድርጌ ጽሑፉ ላይ ሳፈጥ ‹ጁንታው ተከቦ› ይላል፡፡ ሳቄን መቆጣጠር አቅቶኝ እንደ ገመሬ ዝንጀሮ ሳሽካካ ወጪና ወራጁ ያበድኩ መስሎት በሥጋት ያየኝ ነበር፡፡ ይኼው ጉደኛ ሌላውን ዞር አድርጎት፣ ‹አንዱ ክፍት የሥራ ቦታ ማስታወቂያ ከግድግዳ ላይ እየቀዳደደ ሲጥል ምን ነካህ ሲሉት፣ በእኔ ቦታ ሊቀጥሩ እኮ ነው ያወጡት እያለ ሲበሳጭ ይኼስ ያስጠጣል› የሚለውን ጽሑፍ ሲያስነብበኝ፣ እኔ ደግሞ ከሥልጣናቸው የተባረሩት ጦርነት ያስነሱትንና ሞታቸውን ያፋጠኑትን ሳስብ ሥራዬ ትዝ ብሎኝ ፈትለክ አልኩ፡፡ ሥራ ክቡር ነው አትሉም!
ወደ ሥራዬ ሳመራ አንድ ጊዜ የሰማሁት ሌላ ቀልድ ትዝ አለኝ፡፡ ቀልዱ የቆየ ቢሆንም ለዛሬው ወጋችን ሳይጠቅም አይቀርም፡፡ አንዱ ነው አሉ መጠጥ ቤት ገብቶ ቢራ ከማስቀዳቱ፣ ቤቱ ውስጥ ያሉትን መገርመም ጀመረ፡፡ የሰውየው ሁኔታ ያላማራቸው ደግሞ እንዳላየ ሆነው ወጋቸውን ቀጠሉ፡፡ ሰውየው በጠባብ ቲሸርት የተወጠረውን ጡንቻውን እያሳየ ባንኮኒውን ሲደልቅ አስተናጋጁ ሮጦ መጥቶ፣ ‹‹ምን ልታዘዝ?›› ማለት፡፡ ጥጋበኛው አስተናጋጁን በጥፊ አጩሎ፣ ‹‹ማን ጠራህና ነው ፊቴ የምትገተረው?›› ብሎ ሌሎች ሰዎችን ማማተር ሲጀምር፣ ከአንድ ቀጠን ካለ ወጣት ጋር ዓይን ለዓይን ተጋጩ፡፡ ጥጋበኛው ማን ነውና ነው እንዲህ የሚያየኝ ብሎ ተንደርድሮ ወደ ወጣቱ ይሄዳል፡፡ ‹‹አንተ ምን ስለሆንክ ነው እንዲህ አፍጥጠህ የምታየኝ?›› ሲለው፣ ወጣቱ ሳቅ እያለ አንገቱን በሐዘን አነቃነቀ፡፡ ጥጋበኛው የወጣቱ ሁኔታ አናዶት እንደለመደው በጥፊ ሊያጮለው እጁን ሲሰነዝር፣ ወጣቱ ተፈናጥሮ በመነሳት ከጥፊው ያመልጣል፡፡ አጅሬው በንዴት፣ ‹‹እኔ ነኝና ታይሰን…›› ብሎ እጁን ለቦክስ ምት ሲያዘጋጅ፣ ወጣቱ በማርሻል አርት ትርዒት ሠርቶ ያሳልፈዋል፡፡ ይኼ ሁሉ ሲሆን የወጣቱ ዲሲፕሊንና ትዕግሥት አስገራሚ ነበር፡፡ ‹ታይሰን› ደረቱን እየደለቀ ተንደርድሮ ወደ ወጣቱ ሲያመራ በቀላል የካራቴ ምት ከመሬት ጋር ተገናኘ፡፡ በምቱ ምክንያት የተለያዩ ኅብረ ቀለማት ሳያይም አይቀርም፡፡ ስንቶቹ እንዳዩ አውቃለሁና!
አጅሬ ‹ታይሰን› ለደቂቃዎች ያህል ትንፋሽ አጥሮት ውኃ ተቸልሶበት ሲነቃ ከታች ሱሪው በሽንት ርሷል፡፡ አስተናጋጁና አንድ ሌላ ሰው እንደምንም ደጋግፈው ሲያነሱት ዓይኑን መግለጥ ተቸግሮ ነበር፡፡ አንድ ጥግ ላይ ካሳረፉት በኋላ ትንፋሹን ለመሰብሰብ በርካታ ደቂቃዎች ነጎዱ፡፡ ትንፋሹ ተመልሶ ውኃ እንዲጎነጭ ሲደረግ፣ ‹‹የት ነው ያለሁት? ምን ሆኜ ነበር?›› እያለ ሲቀበጣጥር በጥፊ ያጮለው አስተናጋጅ እየሳቀበት፣ ‹‹ጉራህን ስትቸረችር አንድ ጩጬ በካራቴ ዘርሮህ ነው ሽንት በሽንት የሆንከው…›› ሲለው በኃፍረት አንገቱን ደፍቶ፣ ‹‹እኔ ቦክስ እንጂ ካራቴ አልችልም፣ በቦክስ ለምን አይገጥመኝም ነበር…›› በማለት ሽንፈቱን ሊያድበሰብስ ሲሞክር የመጠጥ ቤቱ ሰዎች በሙሉ ሳቁበት፡፡ ጎበዝ ‹ጦርነት ባህላችን ነው› ያሉት ሰዎች ጀሌዎች እኮ እንዲህ እያሉ ነው እያሳቁን ያሉት፡፡ ‹‹ጠመንጃ ይዘው ድሮን ሲቀጠቅጣቸው ምን ይበሉ ታዲያ…›› እያሉ ማስተዛዘን አይሠራም፡፡ አይደለም እንዴ!
እግሬ ወዲያ ወዲህ እያለ ስዘዋወር ያገኘሁት ሥራ ያው የቤት ድለላ ሆነ። ምን ይደረግ ቤት በሌለበት አገር ቤት ፈላጊው በዝቶ እኮ ነው። ቤቱን ለመሸጥ የቀረበውን ዋጋ ስሰማ ሄጄ ለማየት ጓጓሁ። የተባለውን ቤት ሄጄ ሳየው የተጠሩት ሚሊዮን ብሮች ያንሱታል እስክል ድረስ አስገራሚ ነበር። ወዲያው የማገኘውን ኮሚሽን ሳሰላው ሐሴት ያቁነጠንጠኝ ጀመር። ገዥ ይገኛል ብዬ ካሰላሁት ሰዓት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ሁለት ደንበኞች ሲገጥሙኝ ግን ድንግጥ አልኩላችሁ። ምን አስደነገጠህ አትሉኝም? በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ በሚገኘው የኅብረተሰብ ክፍል ልክ፣ ሚሊዮን ምንም የማይመስለው የኅብረተሰብ ክፍል መበራከቱ ነዋ። ‘ካፒታሊዝም ይሉሃል ይኼ ነው!’ የሚለው ምሁሩ የባሻዬ ልጅ ስላቅ ምፀት አዘል አባባል ጆሮዬ ላይ ደወለ። ይኼኔ አንድ በመሬት ድለላ የከበረ ሰማኝ መሰል፣ ‹‹ታዲያስ! ዕድገት የለም ትላላችሁ ግን ይኼው ሚሊዮን በግለሰብ ደረጃ አስቆጠርናችሁ…›› ብሎ ገላመጠኝ። ምን ትሉታላችሁ? የዚህ መሬት ወራሪ ንግግር ደንበኛዬ ጆሮ ጥልቅ አለ መሰል፣ ‹‹ምንድነው የሚለው?›› ብሎ ጠየቀኝ። እኔም የተናገረውን ስደግምለት፣ ‹‹ተወው እባክህ ‘ሌባና ግፈኛ የሠራው መቼ ይለቀውና?’›› ብሎ ተረተበት። ተረቱ ብዙ ቦታ ይሠራል!
ሥራዬን ጨራርሼ በነጋታው ኮሚሽኔን ለመቀበል ቀጠሮ ይዤ ሳበቃ ወደ ቤቴ ገሰገስኩ። ሠፈር ስደርስ ከባድ ዝምታ ነግሷል። ግራ ገብቶኝ ወደ ቤቴ ሮጥኩ። ልክ በሩን ከፍቼ ስገባ ባሻዬና ማንጠግቦሽ ተቀምተው ወግ ይዘዋል። ‹‹ባሻዬ? ምን እግር ጣለዎት?›› አልኳቸው ካፖርቴን እያወለቅኩ። ‹‹ጭር ሲልብኝ ጊዜ እዚህ ይሻለኛል፤ ብዬ መጣሁ…›› አሉኝ የአባትነት ፈገግታቸው በቅንነት ፊታቸውን እያበራው። ሳቅ አልኩና ከጎናቸው ስቀመጥ፣ ‹‹ሰሞኑን ወሬው ጉድ ነው። ሰበር ዜናው ከመብዛቱ የተነሳ ጠንቀቅ ብላችሁ ስሙ። መቼም ወሬ ባይገድልም መጠንቀቅ አይከፋም…›› ብለው ማንጠግቦሽን እያዩ ሲናገሩ ውሎዬ እየገረመኝ በውስጤ እስቃለሁ። ሰበር ዜና ከመብዛቱ የተነሳ አንዳንዱ ቁርሱን ጭምር ወሬ የሚበላ ይመስለኛል። በቀደም ዕለት አንዱ ሲሮጥ መጥቶ፣ ‹‹መቀሌ እኮ በቁጥጥር ሥር ዋለ…›› እያለ ሲያለከልክ፣ ‹‹ሳምንት ያለፈውን ወሬ ከፍሪጅ ውስጥ አውጥተህ አሙቀህ ነው እንዴ የምታቀርብልን?›› ሲለው ዕንባ በዕንባ እስክሆን ነበር የሳቅኩት፡፡ ሳቅና ዕንባ ጎን ለጎን መሆናቸው በጀ!
በሉ እስኪ እንሰነባበት። ያንን ጉደኛ ቤት ካሻሻጥኩና ደህና ገንዘብ ካገኘሁ በኋላ ልክ አልነበርኩም። የኮሮና ወረርሽኝ ባይኖር ኖሮ ሲሸልስ፣ ባንኮክ፣ ዱባይ፣ ካሪቢያን ደሴት ሄዶ መዝናናት አምሮኝ ነበር። ይህችን የነተበች ካፖርቴን በአዲስ ቀይሬ መዘነጥ ልቤ ቋምጦ ነበር። ከዚያ ‘ቤትሽን ከቤቴ ላይ አንሺልኝ’ ከሚባልበት ሠፈር ወጥቶ አፓርትመንት መከራየትም አሰኝቶኝ ነበር። ሳስበው ዓይን ውስጥ መግባት ስለሆነ፣ ዓይን ውስጥ መግባት ደግሞ እንደምታውቁት ከዓይን ያጠፋልና አርፌ፣ እንደ ወትሮዬ ወደ ተለመድችዋ ግሮሰሪ አመራሁ። ስገባ ግሮሰሪያችን ቀዝቅዛለች። ባለቤቱም በገበያው መቀዛቀዝ ተጨንቆ መንፈሱ ቀዝቅዟል። ከደጅ አየሩ ይቀዘቅዛል። ውስጥ ‹ሙዱ› ቀዝቃዛ ነው። ሁሉም ማለት ይቻላል የግሮሰሪው ደንበኞች ስልካቸው ላይ አቀርቅረው ሰበር ዜና ይጠብቃሉ፡፡ ጥቂት ቆይቶ ምሁሩ የባሻዬ ልጅ ከች አለ። ሁለታችን አንድ አንድ ቢራ ይዘን፣ ‹‹አንበርብር ይኼን ፍራ!›› አለኝ። ‹‹የቱን?›› ስለው፣ ‹‹ይኼን ጭርታውን…›› አለኝ። ‹‹ለምን እፈራለሁ? እንዲያውም የመሠልጠን ምልክት ነው… ይኼ የሚያሳየው የ‹ፕራይቬሲ› ባህላችን እያደገ እንደሆነ ነው…›› አልኩት የግሮሰሪዋ ባለቤት እንዳይሰማኝ ድምፄን ዝቅ አድርጌ። ‹‹እኮ የእኛ ባህሪ በአንድ ቀን ተቀይሮ? እናም ሥልጣኔ አልከው? እውነት ቁጥብ ሆንን እያልከኝ ነው? መልስልኝ…›› ሲለኝ ድንገት በአንድ ጊዜ ‹‹ኤጭ…›› የሚል ብሽቀት ስልካቸው ላይ ካቀረቀሩት ተሰማ። እንዴ ምንድነው ነገሩ ብለን ስንገለማመጥ፣ ወዲያው ወሬው ከግራና ቀኝ መጣ፡፡ ሰበር ዜናው ተስተባብሏል ነው ለካ ብስጭቱ፡፡ ያልተጣራ ወሬ ሲስተባበል ያናድዳል እንዴ? በውሸት መረጃ ነው እንዴ ደስታ የሚገኘው? ድንቄም ሰበር ዜና፡፡ መልካም ሰንበት!