በቀደሞ የመከላከያ ሠራዊት ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም የነበሩት ሌተና ጄኔራል ፃድቃን ገብረ ትንሳኤን ጨምሮ በ40 በማገልገል ላይ የሚገኙና በጡረታ በተገለሉ የመከላከያ ሠራዊትና የፌዴራል ፖሊስ አባላት፣ በአገር ክህደት ወንጀል ተጠርጥረው የመያዣ ትዕዛዝ ወጣባቸው፡፡
የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ዓርብ ታኅሳስ 2 ቀን 2013 ዓ.ም. አመሻሽ ላይ ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው፣ ማዘዣ የወጣባቸው 40 ሰዎች ከመንግሥትና ከሕዝብ የተጣለባቸውን ከባድ ኃላፊነት ወደጎን በመተው፣ መቀመጫቸውን ትግራይ ክልል ካደረጉ የሕወሓት ከፍተኛ አመራሮች ተልዕኮ በመቀበልና በፅንፈኝነት አስተሳሰብ በመነሳት፣ እንዲሁም ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ የሚጥል ተግባር ውስጥ በቀጥታና በተዘዋዋሪ መንገድ በመሳተፍ፣ የአገር ክህደት ወንጀል የተጠረጠሩ መሆናቸውን አስታውቋል፡፡
ተጠርጣሪዎቹ በትግራይ ክልል ተልዕኮ ላይ በነበረው የሰሜን ዕዝ የመከላከያ ሠራዊት አባላት ላይ የተከፈተውን ጥቃትና ዕገታ እንደመሩና እንዳስተባበሩ በምርመራ የተደረሰባቸው መሆኑን አመልክቷል፡፡
እነዚህም ተጠርጣሪዎች የቀድሞ ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም የነበሩት ሌተና ጄኔራል ፃድቃን ገብረ ትንሳኤ፣ ኮሎኔል ይህደጎ ስዩም ወልደማርያም፣ ሌተና ኮሎኔል ደስታ ገብረየሱስ ገብረመድህን፣ ኮሎኔል ሀጎስሰ ግደይ (ጡረተኛ)፣ ሌተና ኮሎኔል ሙሉ አብርሃ፣ ሌተና ኮሎኔል ግዑሽ ባህታ አስገዶም፣ ሌተና ብርጋዴር ጄኔራል ተስፋዬ ዓባይ ኪሮስ፣ ሌተና ኮሎኔል ነጋሽ አህመድ አብዱረህማን፣ ሌተና ኮሎኔል አብርሃ ገብረ ጊዮርጊስ ሀዱሽ፣ ሌተና ኮሎኔል ነጋሲ ከበደ ንጉሤ፣ ሌተና ኮሎኔል ፈጠነ ፍስሃ ሱራፌል፣ ኮሎኔል ካህሳይ መሐሪ ምራጎ ይገኙበታል፡፡
ተጠርጣሪዎቹን ለመያዝ መቀሌ ከተማ የገባው የኮማንዶና የወንጀል ምርመራ ቡድን በሚያደርገው አሰሳና ኦፕሬሽን የሚገኘውን ውጤት ለሕዝብ ይፋ እንደሚያደርግ ያስታወቀው ኮሚሽኑ፣ መላው የአገሪቱ ሕዝብ ተጠርጣሪዎቹን ይዞ ለሕግ ለማቅረብ የበኩሉን እንዲወጣ ጥሪ አቅርቧል፡፡