Tuesday, March 28, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ፀሐይ ሪል ስቴት ያስገነባቸው አፓርትመንቶች ለሐራጅ ሽያጭ ቀረቡ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

አፓርትመንቶቹ 13 ሲሆኑ ከ646 በላይ ወለሎች አሏቸው

በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 13 ውስጥ ወደ አያት በሚያስሄደው መንገድ ከሲኤምሲ አደባባይ በስተግራ የሚገኙት ፀሐይ ሪል ስቴት ያስገነባቸው አፓርትመንቶች፣ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ እንዲሸጡ ሐራጅ ወጣባቸው፡፡

ሪል ስቴቱ ያስገነባቸው አፓርትመንት መኖሪያ ቤቶች በጨረታ እንዲሸጡ ሐራጅ ያወጣባቸው፣ ቡና ኢንተርናሽናል ባንክ አክሲየን ማኅበር ነው፡፡

ባንኩ በአዋጅ ቁጥር 97/1990 የተሰጠውን ሥልጣን በመጠቀም፣ ታኅሳስ 4 ቀን 2013 ዓ.ም. ባወጣው የሐራጅ ማስታወቂያ እንደገለጸው፣ ፀሐይ ሪል ስቴት ለመኖሪያና ንግድ (ቅይጥ) አገልግሎት የሚሆኑ፣ በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 13 ሲኤምሲ አደባባይ በስተግራ በኩል በ30,000 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ የተገነቡ አፓርትመንቶችን በመነሻ ዋጋ 524,386,973 ብር ጥር 4 ቀን 2013 ዓ.ም.  በሚከፈት ጨረታ በሐራጅ እንደሚሸጥ አስታውቋል፡፡

ለአፓርትመንቶቹ ግንባታ ከቡና ኢንተርናሽናል ባንክ ብድር የወሰደው ፀሐይ ሪል ስቴት፣ ከባንኩ ጋር በገባው ኮንትራት ውል መሠረት ክፍያውን ባለመፈጸሙ ተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ እንደተሰጠው፣ የባንኩ የሕግ አማካሪ አቶ ውበቱ አሰፋ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ በተደጋጋሚ ሲጠየቅና ማስጠንቀቂያ ሲሰጠው ግዴታውን ሊወጣ ባለመቻሉ፣ ለመጨረሻ ጊዜ የአንድ ወር ማስጠንቀቂያ ቢሰጠውም ሊከፍል ባለመቻሉ፣ ባንኩ ሐራጅ ለማውጣት መገደዱን የሕግ አማካሪው ተናግረዋል፡፡

ሪል ስቴቱ መቼና ስንት እንደተበደረ የተጠየቁት የሕግ ባለሙያ፣ ጊዜውንና የገንዘቡን መጠን ለመግለጽ አልቻሉም፡፡ የመኖሪያ አፓርትመንቶቹ ሙሉ ለሙሉ ሊባል በሚችል ደረጃ መሸጣቸውን በሚመለከትና የቤት ገዥዎቹ ዕጣ ፈንታ ምን ሊሆን እንደሚችል ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ፣ አንዳቸውም የይዞታ ማረጋገጫ እንደሌላቸውና ስለሽያጩም ሆነ ቤት ገዥዎቹ ባንኩ የሚያውቀው ነገር እንደሌለ ተናግረዋል፡፡

ፀሐይ ሪል ስቴት እ.ኤ.አ. በ2012 በቻይናዎቹ ጂኦሎጂ ኮርፖሬሽን ኦቨርሲስ ኮንስትራክሽን ግሩፕ (CGCOC) እና ሬድፎክስ ኢንተርናሽናል ቢዝነስ ኩባንያ የተመሠረተ ሲሆን፣ በወቅቱ በ30,000 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ 13 የመኖሪያና የንግድ አፓርትመንቶችን ለመገንባት 2.5 ቢሊዮን ብር መድቦ ወደ ሥራ መግባቱ ይታወሳል፡፡

ግንባታውን የቻይናው ኩዊን ታንግ (Qian Tang) ኮንስትራክሽን እ.ኤ.አ. በመስከረም ወር 2013 ዓ.ም. ጀምሮ በማጠናቀቅ ላይ ነው፡፡ ከ140 እስከ 275 ካሬ ሜትር ስፋት ያላቸው ባለ ሁለት፣ ባለ ሦስትና ባለ አራት መኝታ ቤቶች፣ በቂ የመኪና ማቆሚያ፣ ለልጆች መጫወቻና ለአዋቂዎች መናፈሻ የሚሆን ሰፊ ግቢ ያላቸው አፓርትመንቶች ናቸው፡፡

የሐራጅ ሽያጭ መውጣቱን በሚመለከት ቤቱን የገዙ ነዋሪዎች ያላቸውን አስተያየት ለማካተት ሪፖርተር ያነጋገራቸውና ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ ነዋሪዎች፣ የጋራ መኖሪያ ቤቶች የሚተዳደሩበትን ሕግ መሠረት አድርገው ውል በመፈጸም ገዝተው እየኖሩ መሆኑንና ካርታ ለመውሰድ በቀጠሮ ላይ መሆናቸውን ከማወቅ ውጪ፣ ሌላ ነገር እንደማያውቁና ስለሐራጁም የሰሙትም ሆነ የሚያውቁት ነገር እንደሌለ ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች