Friday, April 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናኤርትራዊያን ስደተኞች ከሕገወጥ እንቅስቃሴ እንዲቆጠቡ ማሳሰቢያ ተሰጠ

ኤርትራዊያን ስደተኞች ከሕገወጥ እንቅስቃሴ እንዲቆጠቡ ማሳሰቢያ ተሰጠ

ቀን:

‹‹አሁን ከመኪና የወረደ እግረኛ እያሳደድን ነው›› ጄኔራል ብርሃኑ ጁላ፣ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታ ማዦር ሹም

የኤርትራ ስደተኞች የሚያደርጉት ሕገወጥ እንቅስቃሴ በደኅንነታቸው ላይ ችግር ሊፈጥር ስለሚችል፣ ከእንቅስቃሴያቸው እንዲቆጠቡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የመረጃ ማጣሪያ አስታወቀ።

ዓርብ ታኅሳስ 2 ቀን 2013 ዓ.ም. የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የመረጃ ማጣሪያ ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው፣ በትግራይ ክልል በቅርቡ የተደረገው ወታደራዊ ዘመቻ በኤርትራዊያኑ ስደተኞች ላይ በቀጥታ ሥጋት የማይፈጥር መሆኑን ገልጿል፡፡ ነገር ግን በተሳሳተ መረጃ ምክንያት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ስደተኞች ሕገወጥ በሆነ መንገድ ከተለያዩ ጣቢያዎች እየተንቀሳቀሱ መሆኑን ገልጿል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

የመረጃ ማጣሪያው በትግራይ ክልል እየተካሄደ በነበረው የሕግ ማስከበር ዘመቻ ወቅት በተሳሳተ መረጃ ሳቢያ፣ በማይ አይኒና  በአዲ ሐሪሽ የስደተኛ ጣቢያዎች የተጠለሉ ስደተኞች ወደ አዲስ አበባ መንቀሳቀሳቸውን ጠቁሟል፡፡

እንዲህ ዓይነቱ ያልተገባ እንቅስቃሴ ስደተኞችን ለመጠበቅ፣ አስፈላጊውን ድጋፍ ለመስጠት ደኅንነታቸውን ማረጋገጥ እንደማያስችልና በተቀናጀ መንገድ ዕርዳታ ለማቅረብ መሰናክል ስለሚሆን ከሕገወጥ እንቅስቃሴዎቻቸው እንዲታቀቡ ጠይቋል፡፡ መንግሥት አስፈላጊ የሚባሉ ድጋፎችን ለማቅረብ እየሠራ መሆኑም ተመልክቷል፡፡

ኤርትራውያኑ ስደተኞች ያሉባቸው ሥፍራዎች በፌዴራል መንግሥት ቁጥጥር ሥር በመዋላቸው መረጋጋት መፈጠሩን፣ መንግሥትም ስደተኞቹ ወደነበሩባቸው ጣቢያዎች እንደሚመልሳቸው የመረጃ ማጣሪያው አስታውቋል፡፡

በትግራይ ክልል በሦስት የስደተኛ ጣቢያዎችና በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ከ200 ሺሕ በላይ ኤርትራውያን ስደተኞች እንዳሉ የመረጃ ማጣሪያው አመላክቷል፡፡

ይህ በዚህ እንዳለ ሐሙስ ታኅሳስ 1 ቀን 2013 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ ስካይላይት ሆቴል ለአገር መከላከያ ሠራዊት ለተደረገ ድጋፍ ዕውቅና ለመስጠት በተደረገ ሥነ ሥርዓት ላይ የተገኙት የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታ ማዦር ሹም ጄኔራል ብርሃኑ ጁላ፣ የሕወሓት አመራሮች ለሁለት ዓመታት የተዘጋጁበት ጦርነት በሕዝብ ድጋፍ በሁለት ሳምንት መሸነፋቸውን አስታወቁ፡፡

‹‹አሁን ሁሉም ነገር አልቆለታል›› ያሉት ጄኔራል ብርሃኑ፣ የሕወሓት አመራሮች ከመኪና ወርደው እግረኛ ሆነዋል ብለዋል፡፡ ‹‹አሁን ከመኪና የወረደ እግረኛ እያሳደድን ነው፤›› በማለት፣ በሕዝብ ድጋፍ ሠራዊቱ አሸናፊ መሆን መቻሉን አስረድተዋል፡፡

‹‹ሕዝብ ያለ ሠራዊት፣ ሠራዊት ያለ ሕዝብ መኖር አይችልም፤›› ብለው፣ የሕወሓት አመራሮች ለሁለት ዓመት የተዘጋጁበትን ጦርነት በሁለት ሳምንት ማሸነፍ መቻሉም ሠራዊቱ የሕዝብ ድጋፍ ስለነበረው መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

‹‹ጦርነት ፍትሐዊ ሲሆን ማሸነፍ ትችላለህ፣ ካልሆነ ደግሞ ትሸነፋለህ፣ በመሆኑም ፍትሐዊ ስለሆንን ማሸነፍ ችለናል፤›› ብለዋል፡፡

በዕውቅና አሰጣጥ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ፣ የአገር መከላከያ ሚኒስትሩ ቀነዓ ያደታ (ዶ/ር)፣ ጠቅላይ ኤታ ማዦር ሹሙ ጄነራል ብርሃኑ ጁላ፣ የአማራ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ አገኘሁ ተሻገር፣ የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች መገኘታቸው ታውቋል።

በሌላ ዜና ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. በትግራይ ክልል ልዩ ኃይል ታግተው የነበሩት፣ የሰሜን ዕዝ ምክትል አዛዥ ብርጋዴር ጄኔራል አዳምነህ መንግሥቴና አንድ ሺሕ ያህል ከፍተኛና መስመራዊ መኮንኖች መለቀቃቸው ይታወሳል፡፡

የአገር መከላከያ ሠራዊትና የፌዴራል ፖሊስ አባላት በጋራ ባደረጉት ልዩ ዘመቻ ማስለቀቅ መቻላቸውን፣ የመከላከያ ሚኒስቴር ኢንዶክትሪኔሽን ዋና ዳይሬክተር ሜጄር ጄኔራል መሐመድ ተሰማ አስታውቀዋል፡፡

የሕወሓት አመራሮች በሸሹበት ቦታ ሁሉ ይዘዋቸው ሲጓዙ ቆይተው በቀድሞው የትጥቅ ትግል ወቅት ማዘዣ በነበረው አዴት በሚባል ሥፍራ አግተዋቸው እንደነበርና ታጣቂ ኃይላቸውም በሥፍራው መደበቁ በአሰሳና በጥናት እንደተደረሰበት ገልጸው፣ የመከላከያ ሠራዊትና የፌዴራል ፖሊስ ባደረጉት የጋራ አሰሳና በወሰዱት ዕርምጃ መኮንኖቹ ምንም ዓይነት ጉዳት ሳይደርስባቸው መለቃቸውን አስረድተዋል፡፡

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...