ቀደም ሲል በመንግሥትና በውጭ ባለሀብቶች ሲተዳደር የቆየውና ከአሥር ዓመታት ወዲህ የሚድሮክ እህት ኩባንያዎች አካል የሆነው ሆራይዘን አዲስ ጎማ ፋብሪካ፣ ለጥሬ ዕቃ ግዥ የሚሆን የውጭ ምንዛሪ ባለማግኘቱ ሙሉ በሙሉ ማምረት እንዳቆመ አስታወቀ፡፡
በዓመት 800 ሺሕ ያህል ጎማዎች የማምረት አቅም ያለው ድርጅቱ ለሥራው ግብይት የሚሆነውንና 90 በመቶ የሚሸፍነውን ጥሬ ዕቃ ከተለያዩ አገሮች እንደሚያስገባ ገልጾ፣ ሆኖም ለግዥ የሚሆነውን የውጭ ምንዛሪ በማጣቱ ምርት እስካቆመበት ያለፉት ሁለት ሳምንታት ድረስ ከአቅሙ 40 በመቶ ብቻ ይሠራ እንደነበር አስታውቋል፡፡
የሆራይዘን አዲስ ጎማ የኮሜርሻል ኃላፊ አቶ ዳዊት ደምሌ ለሪፖርተር እንዳስታወቁት፣ ጎማ ለማምረት ፋብሪካው 102 የሚጠጉ ግብዓቶችና የኬሚካል ውህዶች ይጠቀማል፡፡ ከአገር ውስጥ የሚገኙ ግብዓቶች ከስድስት እንደማይበልጡና በውጭ ምንዛሪ ላይ የተንጠለጠለ ምርት አምራች እንደሆኑ አስረድተዋል፡፡
እንደ ካርበን ብላክ፣ ናይለን ኮርድ፣ ዚንክ ኦክሳይድ፣ ቢድዋኖር የመሳሰሉና ሌሎች በማምረት ምርትን ላለማቆም ሲባል በአውሮፕላን ጭምር ሲጓጓዙ እንደቆየ የገለጹት አቶ ዳዊት፣ የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ከኮንቴይነር አቅርቦት ጋር በተያያዘ ቅድሚያ እንዲያገኙ ባለማድረጉ፣ ውድ በሆነው የትራንስፖርት ዓይነት ለማጓጓዝ ኩባንያው እንደተገደደ አስታውቀዋል፡፡
ፋብሪካው በየዓመቱ ለጥሬ ዕቃ ግዥ 15 ሚሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልገው የገለጹት ኃላፊው፣ ሆኖም ለመጨረሻ ጊዜ የተፈቀደለት አንድ ሚሊዮን ዶላር ያህል እንደሆነና ይህም ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከዓመት በፊት የተገኘ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ ከሌሎች የግል የንግድ ባንኮችም አመርቂ የውጭ ምንዛሪ ባለመገኘቱ፣ ፋብሪካው ከዳያስፖራው ማኅበረሰብ እየገዛ ሲጠቀም መቆየቱን አቶ ዳዊት አስረድተዋል፡፡
በአገር ውስጥ ከፍተኛ የሆነ የጎማ ፍላጎት እንዳለና ይኼንንም ለመቅረፍ ሆራይዘን ስም ካላቸው ተቋማት ማለትም ከኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ ስኳር ኮርፖሬሽንና ከአገር ውስጥ ተሽከርካሪ መገጣጠሚያ ተቋማት ጋር እየሠራ እንደሚገኝ የሚገልጹት የኮሜርሻል ኃላፊው፣ የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት የሚደረገውን ድካም ለመቀነስ ለሚሠራው ድርጅት ከሌሎች የጎማ አስመጪዎች የተሻለ ቅድሚያ የውጭ ምንዛሪ ግኝት የሚያገኝበት ዕድል ሊመቻች ይገባል ይላሉ፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤትን ጨምሮ ሌሎች ተቋማት ድርጅቱ ጎማ እንዲያቀርብላቸው እየጠየቁ ቢሆንም፣ ማምረት በማቆሙ ምክንያት ለሠራተኞቹ የዓመት ፈቃድ እየሰጡ ዕረፍት እንዲወጡ መደረጋቸውን ኃላፊው ጨምረው አስረድተዋል፡፡ መንግሥት አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጣቸው ለንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር፣ ለኬሚካል ኮርፖሬሽንና ለብሔራዊ ባንክ ጥያቄ ማቅረባቸውን፣ በተለይ ብሔራዊ ባንክ የተቋሙን ጥያቄ ይመለከተው ዘንድ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ኬሚካል ኮርፖሬሽን ጥረት እያደረጉ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡
በኤልያስ ተገኝ