Wednesday, December 6, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

አማራ ባንክ ጠቅላላ ጉባዔውን ለማካሄድ ምልዓተ ጉባዔው ሊሞላለት ስላልቻ ውክልና መስጫ ጊዜውን አራዘመ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የአክሲዮን ሽያጩን ያጠናቀቀው አማራ ባንክ አክሲዮን ማኅበር፣ አጠቃላይ የተከፈለ ካፒታሉ ስድስት ቢሊዮን ብር በመድረሱ፣ ከአገሪቱ የግል ባንኮች ትልቁን የተከፈለ ካፒታል መጠን የያዘ ባንክ ሆኗል፡፡ የውክልና መስጫ ጊዜውን ለ15 ቀናት አራዝሟል፡፡

ባንኩ የአክሲዮን ሽያጩን ማጠናቀቁና ቀጣይ ሥራዎቹን በተመለከተ በሰጠው መግለጫ እንዳስታወቀው፣ ቃል የተገባው የባንኩ ካፒታል መጠን 8.1 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡ ከባንኩ አደራጆች አንዱ የሆኑት ቦርድ ሰብሳቢው አቶ መላኩ ፋንታ እንደገለጹት፣ ከአክሲዮን ሽያጭ ያሰባሰቡት የአገልግሎት ክፍያ 402 ሚሊዮን ብር ደርሷል፡፡ የባንኩ የተጣራ ባለአክሲዮኖች ቁጥር ደግሞ 185 ሺሕ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የባንኩ የአክሲዮን ሽያጭ አንድ ወር ላልሞላ ጊዜ እንዲራዘም በተደረገበት ወቅት ከፍተኛ የሚባል የአክሲዮን ሽያጭ ማድረግ መቻሉንም አመልክተዋል፡፡

ከጥቅምት 26 እስከ ኅዳር 21 ቀን 2013 ዓ.ም. ድረስ የአክሲዮን ሽያጩ እንዲራዘም በተደረገበት ወቅት፣ አንድ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ 1.7 ቢሊዮን ብር ቃል የተገባ አክሲዮን ሽያጭ ተከናውኗል፡፡ በዚህ ጊዜ ውስጥ የተከፈለበት የአክሲዮን ሽያጭ ደግሞ 1.1 ቢሊዮን ብር እንደነበር ገልጸው፣ ይህ የሚያሳየው አሁንም አክሲዮን ለመግዛት ፍላጎት ያለ መሆኑን እንደሆነ አክለዋል፡፡

የአክሲዮን ሽያጩ ይራዘምልን የሚል ጥያቄ ቀርቦ የነበረ መሆኑን ያስታወሱት አቶ መላኩ፣ ይህንን ያላስተናገዱ መሆኑንም አክለዋል፡፡

ሌላው ጠቅላላ ጉባዔውን ለማካሄድ የሚያስችለውን የውክልና ጉዳይ በተመለከተ ከሰጡት ማብራሪያ መረዳት እንደተቻለው እስከ ኅዳር 30 ቀን 2013 ዓ.ም. ባለአክሲዮኖች ውክልና እንዲሰጡ ጊዜ የተሰጠ ቢሆንም በዚህ ጊዜ ውስጥ ጉባዔውን ለማካሄድ የሚያስችል በቂ ቁጥር ያለው ውክልና አለመሰጠቱን ተናግረዋል፡፡

ከኅዳር 1 እስከ 30 ቀን 2013 ዓ.ም. ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ ውክልና የሰጡት ባለአክሲዮኖች 75 ሺሕ ብቻ መሆናቸውን ጠቁመው፣ የሚያስፈልገውን ጠቅላላ ጉባዔ ለማካሄድ የሚያስፈልገውን ምልዓተ ጉባዔ ያላሟላ ነው፡፡

እስካሁን ውክልና የሰጡት ባለአክሲዮኖች ቁጥርም ከ185 ሺሕ ባለአክሲዮን አንፃር ሲታይ 41 በመቶ ብቻ በመሆናቸው ውክልና የመስጫውን ጊዜ ለ15 ቀናት እስከ ታኅሳስ 15 ቀን 2013 ዓ.ም. እንዲራዘም መደረጉን ገልጸዋል፡፡ ይህ ወደ አክሲዮን ክፍያ ሲመነዘርም ሆነ ከባለአክሲዮኖቹ ቁጥር አንፃር እስካሁን ውክልና የሰጠው ጠቅላላ ጉባዔውን ለማካሄድ የሚያስችልና ምልዓተ ጉባዔ የሚያሟላ ባለመሆኑ ባለአክሲዮኖች የባንኩን ምሥረታ ጉባዔ ለማካሄድ በተሰጠው 15 ቀናት ውስጥ እንዲያከናውኑ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

እንዲህ ያለው ነገር የተፈጠረው ብዙ ጊዜ ባለቀ ሰዓት አገልግሎት እናገኛለን ከሚል መዘናጋት ሊሆን እንደሚችል ገልጸው፣ ‹‹ውክልና ባልሰጥስ ምን ችግር አለው›› ከሚል የመጨነ ሊሆን እንደሚችልም አቶ መላኩ ገልጸዋል፡፡ የምሥረታ ጉባዔው ታሪካዊ በመሆኑ በአካል እንገኛለን ከማለትም ይሆናል የሚል እምነታቸውን የገለጹ ሲሆን፣ ይኼ መሆኑ ደግሞ ከሚገባው በላይ ባለአክሲዮኖች ጉባዔው ላይ ይገኛሉ የሚል ሥጋት እንዳላቸውም አመልክተዋል፡፡

ስለዚህ በተሰጠው ጊዜ ውስጥ ባለአክሲዮኖች ውክልናቸውን እንዲሰጡና የመጨረሻዎቹን ቀናት ሳይጠብቁ ከዛሬ (ከታኅሳስ 1 ቀን 2013 ዓ.ም.) ጀምሮ ውክልናውን በመስጠት መሥራች ጉባዔውን ለማካሄድ ባለአክሲዮኖች የበኩላቸውን ሊያደርጉ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡  

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች