Thursday, December 1, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  የሳምንቱ ገጠመኝየሳምንቱ ገጠመኝ

  የሳምንቱ ገጠመኝ

  ቀን:

  ጊዜን የመሰለ ደግ ነገር ያለ አይመስለኝም፡፡ ‹‹የጊዜ እንጂ የሰው ጀግና የለውም›› ሲባል ያን ያህል አባባሉ አይገባኝም ነበር፡፡ ሰው በፈጸመው ገድል እንዴት ጊዜ ይወደሳል ያልኩበት ጊዜም ነበር፡፡ ነገር ግን ዕድሜ እየጨመረና አስተሳሰብ እየዳበረ ሲሄድ ሁሉም ነገር ግልጽ ይሆናል፡፡ ዕድሜ የማያስተምራቸውና ለአስተሳሰብ ዕድገት ያልታደሉ ደግሞ ይህንን ፀጋ አያገኙትም፡፡ ለዚህም ይመስለኛል ያለ እኛ ማን አለ እያሉ ሲፎክሩ የነበሩ እንዳይሆኑ ሆነው የቀሩት፡፡ ጊዜ ይህንን ገጠመኝ ለመጻፍ ስላበቃኝ እንዲህ ላቅርብላችሁ፡፡

  የዛሬ 28 ዓመት ገደማ መሥሪያ ቤታችን ውስጥ ድንገተኛ ስብሰባ ይጠራል፡፡ ዛሬ በሕይወት የሌሉ አለቃችን ይመሩታል ብለን የጠበቅነው ስብሰባ ላይ የማናውቃቸው ሰዎች መድረኩን ይዘውታል፡፡ አለቃችን እንደ ተሰብሳቢ ፊት ረድፍ ላይ ከማኔጅመንት ቡድን አባላት መሀል ተቀምጠዋል፡፡ ስብሰባውን ለመምራት የመጡ ሰዎች ንግግር ሲጀምሩ፣ ኢሕአዴግ የሚባለውን ድርጅት የሚዘውሩት የሕወሓት ሰዎች እንደነበሩ ግልጽ ሆነልን፡፡ አለባበሳቸው እንደ ነገሩ የነበሩት ሰዎች ሥርዓት ላለው ንግግር ደንታ ቢስና በድል አድራጊነት ስሜት የተሞሉ በመሆናቸው፣ በዕድሜ የገፉትን አለቆቻችንና ሠራተኞችን አንተ/አንቺ እያሉ ነበር የሚጠሩት፡፡

  ስብሰባው የተጠራው ግምገማ በማድረግ የማይፈለጉትን ለማባረርና አዲስ አመራር ለመሰየም ስለነበረ፣ በድርጅታዊ ዘዴ የተዘጋጁ ዓይን አውጣዎች በሐሰት የተከበሩ ሰዎችን ስም ማጥፋት ነበር የተያያዙት፡፡ የእነዚህ ባለጌዎች ድርጊት ያናደዳቸው ሰዎች እጃቸውን አውጥተው እውነቱን ለመናገር ቢጥሩም፣ በባለጌዎቹና በገምጋሚዎቹ ‹‹ደርግ/ኢሠፓ›› እየተባሉ አርፈው እንዲቀመጡ ተገደዱ፡፡ አንዲት የማልረሳት በወቅቱ ጸሐፊ የነበረች ጀግና ሴት፣ ‹‹እናንተ ተጠቃቅሳችሁ መጥታችሁ ኃጢያት ብትሠሩም እኛ ግን በሞራል ስለምንበልጣችሁ አታሸንፉንም…›› ብላ ስትናገር አዳራሹ በጭብጨባ ተናጋ፡፡

  ይህ ንግግርና ምላሹ ያስደነገጣቸው ካድሬዎችና የእነሱ ተለጣፊዎች ድንጋጤ ውስጥ ወደቁ፡፡ አንደኛው ሰብሳቢ ሌባ ጣቱን እያወዛወዘ፣ ‹‹ደርግ/ኢሠፓ የተቆጣጠረውን መሥሪያ ቤት ሰሞኑን ነፃ አውጥተን እናሳያችኋለን…›› ብሎ ስብሰባው ማብቃቱን ሲናገር፣ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ሠራተኞች በጉምጉምታ ተቃውሞአቸውን አሰሙ፡፡ ከአንድ ሳምንት በኋላ ሰኞ ዕለት ሠራተኞች ወደ ሥራ ሲመጡ የመሥሪያ ቤቱ ዋና በር ተቆልፏል፡፡ በሩ ላይ ከሥራ የተሰናበቱ ሠራተኞች ዝርዝር ተለጥፏል፡፡ በወቅቱ ከ150 ሠራተኞች ውስጥ ከ100 በላይ የሆኑት በሕወገወጥ መንገድ ተባረሩ፡፡ ነፃ አውጪ ነን ባዮቹ አዲሶቹ ጨቋኞች ሆነው ግፍ ሠሩ፡፡

  እኔና መሰሎቼ ወደ ግል ሥራ ስንገባ ብዙዎች ግን በጣም ተቸግረው ይህችን ዓለም እንደተሰናበቷት አስታውሳለሁ፡፡ እኔ የግል ሥራ ውስጥ ብገባም እንዲህ እንዳሁኑ ቀላል ስላልነበር፣ ያየሁትን መከራ እኔና ፈጣሪዬ ነን የምናውቀው፡፡ ብዙዎች ያለ ጥፋታቸው ከሥራቸው ተባረው ለረሃብና ለከፍተኛ እንግልት መዳረጋቸውን ብዙዎች አይዘነጉትም፡፡ በተቃራኒው ግን ነፃ አውጪ ነን ባዮቹ በዘረፉት ሀብት ጥጋብ አናታቸው ላይ ወጥቶ እንዴት ያደርጋቸው እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው፡፡ ጊዜ ተመቸን ብለው የሠሩት ግፍ ተቆጥሮ አያልቅም፡፡

  ጊዜ ደጉ እነሱ የዛሬ ሦስት ዓመት ገደማ ከአራት ኪሎ ሸሽተው መቀሌ ሲገቡ በዓይናችን ዓየን፡፡ የሠሩት ግፍ በጣም ብዙ ነበርና ሊያሳርፋቸው ስላልቻለ፣ ተመልሰው ለመምጣት ሲያደቡ ሰንብተው ጦርነት አነሱ፡፡ የማይነካውንና የማይደፈረውን አደገኛ ነገር ማለትም የሰሜን ዕዝ ሠራዊት ላይ ነውረኛ ድርጊት ሲፈጽሙ፣ የግፋቸው ፅዋ ሞልቶ ነበርና በገዛ እጃቸውን መቃብራቸውን ቆፈሩ፡፡ የግፉአን ዕንባና የንፁኃን ደም በከንቱ አልቀረምና ዕድሜ ለጊዜ ግፈኞቹ የገደሉ ጠርዝ ላይ ቆመዋል፡፡ ይህንን ማየት በራሱ መታደል ነው፡፡

  በቀደም ዕለት ከቤቴ ወጥቼ በእግሬ ስንንቀሳቀስ መሬት አይብቃኝ ብሎ ሲነጥር የነበረ የአካባቢዬ ሰውዬ፣ ሰው አየኝ አላየኝ በሚል ጭንቀት ውስጥ ሆኖ አንገቱን ደፍቶ መኪናውን በዝግታ ሲነዳ አየሁት፡፡ ለወትሮ ሉጫ ፀጉሩን አበጥሮ ይንጠባረር የነበረ ይህ ግብዝ ማንም ዞር ብሎ ባያየውም፣ እሱ ግን ከቢጤዎቹ ጋር የሠራውን ያውቃልና ሰፋ ያለ ባርኔጣ ደፍቶ ሳየው ወይ ጊዜ ነው ያልኩት፡፡ ይህ ሰው ትዕቢቱና ጥጋቡ ከልክ ያለፈ ስለሆነ ውድ ሞዴል መኪናውን በፍጥነት እየነዳ ሰው ላይ ውኃና ጭቃ ይረጭ ነበር፡፡ ለምን መንገዴ ላይ ሰው አየሁ ብሎ መሳደብ አመሉ ነበር፡፡ ዛሬ ግን ከተደበቀበት ቤቱ ለጉዳዩ ሲወጣ አነስተኛ ቪትዝ እየነዳ ሲሄድ አንገቱን ደፍቶ ነው፡፡ ደግነቱ ማንም የአካባቢው ሰው ነገሬ ብሎ እንኳ አያየውም፡፡ ይህንን መሰሉን ጨዋነት ነው ሲያራክሱብን የኖሩት፡፡

  አንዲት የረዥም ዓመት ጎረቤቴ፣ ‹‹እግዚአብሔርን ለምን እንደማመሠግነው ታውቃለህ?›› ብላኝ፣ ‹‹እንደ እነሱ ጭካኔና አረመኔነት ቢሆን ኖሮ የእኛ ሕዝብ ብዙ አሳዛኝ ድርጊቶች ይፈጽም ነበረ፡፡ ነገር ግን ፈሪኃ እግዚአብሔር የታደለ ሕዝብ ስለሆነ ጨዋነቱና አስተዋይነቱ ከላይ ነው…›› ያለችኝ እውነት ነበር፡፡ ፈጣሪ አስተውሎትና ምግባር ሲሰጥ የሕዝባችን የጨዋነትና የመልካምነት እሴቶች በሰፊው ይገለጻሉ፡፡ ጊዜ ደጉ ደግሞ እነዚህን የሚያኮሩ እሴቶች በግፈኞች ፍፃሜ ላይ እያሳየን ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነትን ለማጥፋት የተሸረበው ሴራ መክኖ፣ ኢትዮጵያዊያን ሲተባበሩና ሲደጋገፉ ከማየት በላይ ምንም ደስ የሚያሰኝ ነገር የለም፡፡ ኦ ጊዜ ለኩሉ!

  (አምሳሉ ረታ፣ ከፈረንሣይ ሌጋሲዮን)

  spot_img
  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  [በተቋሙ ሠራተኞች የተወከሉ አንድ ባልደረባ ሚኒስትሩን ለማነጋገር ቀጠሮ ይዘው ወደ ቢሯቸው ገቡ]

  ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም ሰላም ... ተቀመጥ! አመሠግናለሁ ክቡር ሚኒስትር!...

  የጉራጌ ዞን ጥያቄና የክላስተር አደረጃጀት የገጠመው ተቃውሞ

  መንግሥት የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል አካል የነበሩ ዞኖችንና...

  አዋሽ ባንክ ካፒታሉን ወደ 55 ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ያስገደደው ምክንያት ምንድን ነው?

  ባለፈው ቅዳሜ ጠቅላላ ጉባዔውን ያካሄደው አዋሽ ባንክ የ43 ቢሊዮን...

  አቢሲኒያ ባንክ ካለፈው ዓመት የ127 በመቶ ብልጫ ያለው ትርፍ በማግኘት አዲስ ታሪክ አስመዘገበ

  አቢሲኒያ ባንክ ከቀደሚ የሒሳብ ዓመት የ127 በመቶ ብልጫ ያለው...