የጀርመን መንግሥት ተራድኦ ድርጅት ከኢትዮጵያ ቡና እና ሻይ ባለሥልጣን ጋር በመሆን ከቡና ጋር የተያያዙ አዳዲስ የፈጠራ ሐሳቦችንና የተሻሻሉ አሠራሮችን የሚያግዝ የ13.5 ሚሊዮን ብር የድጋፍ ፈንድ ተቋቋመ፡፡
በኢትዮጵያ ለሁለተኛ ጊዜ ሊተገበር የታሰበው የድጋፍ ፈንድ የቡና አርሶ አደሮችንና ላኪዎችን ትርፋማነት እንደሚያሳድግና በአቅርቦት ሰንሰለቱ ውስጥ ያሉትን ችግሮች ሊቀርፍ እንደሚችል የኢትዮጵያ ቡና እና ሻይ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አዱኛ ደበላ (ዶ/ር) ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
ከዚህ ባለፈም በቡና ማምረትና ንግድ ላይ የተሰማሩትን ተዋናዮች ፍትሐዊ ድርሻ እንዲኖራቸው የሚያስችል አዳዲስ ሐሳቦች ይመነጩበታል ተብሎ እንደሚጠበቅም ተገልጿል፡፡
የቡና ምርትን ከአመራረቱ እስከ መጨረሻው ተጠቃሚ ለማድረግ ምርትን ጊዜንና ገንዘብን ሊቆጥቡ የሚችሉ የፈጠራና የቴክኖሎጂ ውጤቶች እንደሚገኙበት የሚጠበቀው ሁለተኛው ዓመታዊ ውድድር እስከ ታኅሳስ 20 ቀን 2013 ዓ.ም. ድረስ ለተወዳዳሪዎች ክፍት ሆኖ እንደሚቆይ ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡
በ2012 ዓ.ም. በተደረገው የፈጠራ ውድድር አምስት የቴክኖሎጂ ውጤቶች መገኘታቸውንና ለሽልማት መብቃታቸውን ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡
የዘንድሮው የቡና ፈጠራ ፈንድ ተወዳዳሪዎች ከየትኛውም የዓለም ክፍል በግል ወይም በቡድን በመሆን መወዳደር እንደሚችሉ የገለጹት ዳይሬክተሩ ለአሸናፊዎች ለእያንዳንዳቸው በፕሮጀክት እስከ 50 ሺሕ ዩሮ እንደሚሰጥ ገልጸዋል፡፡
ሊወዳደሩ የሚችሉ የፈጠራ ባለሙያዎች እስከ ታኅሳስ 20 ድረስ በሚያቀርቡት ፕሮፖዛል መሠረት ለስድስት ጠንካራ የቴክኖሎጂ ሐሳቦች ገንዘቡን በመስጠት የፈጠራ ውጤቱን እንዲያቀርቡ ይደረጋል ብለዋል ዋና ዳይሬክተሩ፡፡