Wednesday, June 12, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

የምናሸንፈው ስንተባበር ብቻ ነው

ኢትዮጵያውያን ስንተባበር ያምርብናል፡፡ መተባበራችን አሸናፊ ያደርገናል የሚባለውም በምክንያት ነው፡፡ በአንድነት ዘብ ስንቆም አሸናፊ መሆን እንችላለን፡፡ ተባብረን ከሠራን እንለወጣለን፡፡ ስንተጋገዝ አስቸጋሪ የሚባሉ ጊዜዎችን እናልፋለን፡፡ ከተደማመጥን  ደግሞ የተሻለ አገር መፍጠር እንችላለን፡፡ በአንፃሩ እርስ በርስ ከተባላንና ለጋራ ጥቅማችን ከመቆም ይልቅ በየሰፈሩ ተቧድነን የምንቧቀስ ከሆነ ለውድቀት የሚጋብዙ ግጭቶች ላይ እንወድቃለን፡፡ ለልጆቻችንም ክፉ እናወርሳለን፡፡ በሕይወትም ሆነ በንብረት ዋጋ እንከፍላለን፡፡ ከሰው ልጅ ወጣ ባለ ባህሪ እንከበባለን፡፡ ያለመደማመጥና የሰፈር ቡድንተኝነት ለወለዳቸው ክዳቶች ማሳያዎች አንዱ ሰው ተዘቅዝቆ ተሰቀለ የሚለውን ዘግናኝ ጭካኔ ያየንበትና የሰማንበት አጋጣሚ ነው፡፡

ከቆየ ታሪካችን በደንብ እንደምንረዳው ግን በጋራ ሆነን ያሸነፍናቸው ብዙ አጋጣሚዎችን ማሳለፋችንን ነው፡፡ በተለየ የሚወሳልንና በቅኝ ያለመገዛታችን ደምቆ የምናየውና እንደ ዜጋ የምንኮራበት ታሪክ የሚነገርልን ተባብረን ወራሪዎቻችን ድል በማድረጋችን ነው፡፡ ባንተባበርና በአንድ ቆመን አሸናፊ ባንሆን ኖሮ የዛሬ ማንነታችን ባልኖረ ነበር፡፡ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ በጎሳና በዘር እየተቧደኑ መበሻሸቅና አለመደማመጣችን ደግሞ ምን ያህል ዋጋ እያስከፈለን እንደሆነ ለማወቅ እማኝ የማያሻው ጉዳይ መሆኑንም ልብ ማለት ተገቢ ነው፡፡ ብዙ ክፍቶች ታይተዋል፡፡ የማይታሰቡ ጭካኔዎች ተፈጽመዋል፡፡

እንዲህ ያሉ ተግባራት በጋራ የምንቆምበትና የምንገለጽበት የበዛ ታሪክና እውነት እያለን ጥቂቶች በሚቆሰቁሱት ወፍ ዘራሽ ትርክት ትልቁን ቁም ነገራችንን እየበረዘብን በጋራ የምናድግበትንና የምንበለፅግበትን መልካም አጋጣሚዎች ማደነቃቀፉንም መረዳት ያሻል፡፡ ማናችንንም ያልጠቀመ ስለመሆኑም ይኸው በግልጽ እየታየ ነው፡፡ በመከራ የገነባነው ሀብት ሲወድምና ሲፈርስ የምናየውም ለአገር ከማሰብ ይልቅ በቡድንተኝነት ስሜት በሚሰነዘር አደገኛ ትርክት ጭምር ነው፡፡ ከዚህ አዙሪት የግድ መውጣት አለብን፡፡ ወደፊት የምንራመደው ስንተባበር፣ በጋራ ስንቆም ብቻ መሆኑን ማወቅ ግድ ነው፡፡

ደግሞም ኢትዮጵያውያን በጋራ መኖርና ተባብሮ ድል ማድረግ እንደሚችሉ አይተናል፡፡ አገር ስትወረርና ስትደፈር ያለነጋሪ የሚተባበርበት ቁልፍ ምክንያትም የማንነጣጠልና አንድ በመሆናችን የመጣ ጥንካሬዎችን መሆኑን መገንዘብ ያሻል፡፡

ይህንን የማይናወጥ ኢትዮጵያዊነት ለመስበር የሚደረጉ ቡድናዊ አመለካከቶችና ትርክቶች አሸናፊ አይሆኑም የሚባለውም ለዚህ ነው፡፡ ግን ላለመረጋጋታችን ምክንያት ሆነው ቀጥለዋል፡፡ በመደማመጥና በመከባበር በጠረጴዛ ዙሪያ በመምከር ችግር መፍታት እያለ እኔ ያልኩት ብቻ ካልሆነ ብሎ ለያዥ ለገናዥ መጋበዝ ለራስም አይጠቅምም፡፡ ይህንንም በተግባር እያየነው ነው፡፡

ስለዚህ ከሰፈር ቡድንተኝነት ወጥቶ ትልቁን ስዕል ማየት፣ መንደር መንደር ለሚሉትም የሚበጅ ነውና የእስካሁኑ ውል የጠፋበትና ያረጀ አመለካከትን ቀብሮ አገርን በማስቀደም ለአገራችን መለወጥ የምንሠራበት ጊዜ መሆን አለበት፡፡ ችግር ካለ በውይይት እንፍታ፡፡ ለውይይት ወደ ጠረጴዛ ስንመጣ አጀንዳችን ኢትዮጵያን በማስቀደም ማዕከል በማድረግ ይሁን፡፡

ቁንፅል ነገር ይዞ ከመበሻሸቅ የምንላቀቀውና የእኔ ከሚለው ክፉ ነገር ወጥተን የእኛ የሁላችን ወደሚለው መልካም አመለካከት መግባት ያስፈልጋል፡፡ ፅንፍ ተይዞ እኔ እበልጥ የኔ ቡድን ይበልጥ የሚለው አቅም ከማሳጣት ውጪ አያዘልቅም፡፡ ማዶና ማዶ ሆኖ የሚደረጉ የቃላት ጦርነታችን እየከፈቱ መንጫጫትም አሁን ላለንበት ጊዜ አይመጥንም፡፡

መሠረት የሌላቸው ትርክቶችን ይዘን ለመበሻሸቅ የምናጠፋው ጊዜ ይቺን አገር ሊለውጡ በሚችሉ ሐሳቦች መቀየር አለባቸው፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ሊፈጸሙ ቀርቶ የማይታሰቡ ሰቅጣጭ ድርጊቶች የተመለከትንበት አንዱ ምክንያት በብሔር ተቧድኖ በዚያ ቅኝት ለመጓዝ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ለመሆናቸው አንድና ሁለት የለውምና ከዚህ የምንወጣበት መንገድ ማበጀት አለብን፡፡

ክፉ የፖለቲካ ልሂቃን የዘሩት ዘር አንዳችንን ከሌላኛችን በማናከስ የተጠቀሙበትና አደገኛ አካሄድ መሆኑን ተረድተን በሰከነ መንገድ መራመድ ራስን ለጋራ ተጠቃሚነት ማነፅ የግድ ይላል፡፡ ከዚህ አንፃር ብዙ መሠራት ያሉባቸው ጉዳዮች ቢኖሩም ሁሉም በያለበት የበኩሉን ቢያደርግ ብዙ ነገር ይለወጣል፡፡ ከሰሞኑ አገሪቷ የገባችበት ያልተገባ ጦርነት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ብሔር ተኮር የፖለቲካ ቅኝታችን መሆኑን በመገንዘብ ልንማርበት ይገባል፡፡

በአንፃሩ የጋራ ትብብር ድል የሚገኝ መሆኑንም ያየንበት ስለሆነ ይህ አጋጣሚ በትንሹም በትልቁም ነገር ለግጭት መንስዔ የሚሆኑ ነገሮችን የምናቆምበትና በጋራ መሆን አሸናፊ የሚያደርግ መሆኑን የምንረዳበት ይሁን፡፡

እከሌ ተፈናቀለ እከሌ ሞተ እከሌ በማንነቱ ተገደለ የሚለው ሰቅጣጭ ታሪካችን ወጥተን በአገር መደፈር የምናሳየውን ከልብ የሆነ ትብብራችንን አገር ለማሳደግም ማዋል ይገባል፡፡ በተለይ ይህ በኢኮኖሚው ዘርፍ መታየት አለበት፡፡

ከእንቢተኝነትና ዕብሪት ወጥተን በጋራ መተባበር ካልቻልን አሁንም ብዙ ዋጋ እንከፍላለን፡፡ ዕብሪት የትም እንደማያደርስና የኔ ሰፈር ልጆች ያስጥሉኛል ማለት እንደማይችልም መታወቅ አለበት፡፡ ምክንያቱም ሁሌም አሸናፊው እውነት ነው፡፡ ተባብሮ መኖር ሰላምም መሆኑ ግልፅ ነውና መንገዶቻችን ሁሉ ቀና እንዲሆኑ ከተፈለገ አሁንም የሚያምርብን መተሳሰባችንና አንድ መሆናችን ብቻ ነው፡፡

ስለዚህ አሁን ያልፈተለገው ጦርነት ያስከፈለን ዋጋ ሕመሙ እያደር በደንብ እየታወቀን ይመጣል፡፡ ኢኮኖሚው ላይ ትልቅ ጫና ስለመፈጠሩም አይታበይም፡፡ ጉዳቱ እንደ አገር ነውና በጦርነቱ የታጣውን ለመመለስና የጎደሉትን ለመሙላት የሚያስፈልገው መስዋዕትነት ቀላል አይሆንም፡፡

እንደ ሸማች የእያንዳንዱን ኪስ ሊጎዳ የሚችል አጋጣሚዎች ከፊታችን ሊጠብቁን ይችላሉ፡፡ ስለዚህ ይህንን በጋራ ተሳስቦ ማለፍ ያስፈልጋል፡፡ ጦርነቱ ኢኮኖሚው ላይ ሊያሳድር የሚችለውን ተፅዕኖ ለመቀነስ እንደ መንግሥት መሠራት ያለበት ሥራ እንደተጠበቀ ሆኖ ዜጎችም የበኩላቸውን በማድረግ ይህንን ጊዜ በብልሃት መሻገር የሚጠይቅ መሆኑን ማሰብ ያስፈልገዋል፡፡ እዚህ ላይ አንድ ነገር ላነሳ እወዳለሁ፡፡  

ከሰሞኑ በአንድ ዜና ዘገባ ላይ ትውልደ ኢትዮጵያውያን በአገር ጉዳይ እያሳረፉ ያለው አሻራ በብዙ መለወጡን ነው፡፡ በኅብረት ሆነው የአቅማቸውን እያደረጉ ያሉት ድጋፍ ከተባበርን ለውጥ የሚመጣ መሆኑን የሚያሳየን ጥሩ ምሳሌ ነው፡፡

በመረጃው መሠረት ሰሞኑን ብቻ በአጭር ጊዜ ለአገር መከላከያ ሠራዊት ወደ 80 ሚሊዮን ብር ደግፈዋል፡፡ እስካሁን ለህዳሴ ግድብ ያዋጡት እየጨመረ መጥቷል፡፡ ከኮቪድ ጋር በተያያዘም በዓይነትና በጥሬ ከ500 ሚሊዮን ብር በላይ ስለመድረሱ የሚገልጹ መረጃዎችን ሰምተናል፡፡ በዚህም ዓመት ተጠብቆ የማይገኝ ድጋፍ በወራት ውስጥ እንደተገኘ አይተናል፡፡

ይህም ከዚህ ቀደም ከነበረው በተለየ ዳያስፖራዎች ስለ አገር ብለው የሚያደርጉት ያለው ዕገዛ እያደገ መጥቷል፡፡ ለዚህ ሊመሰገኑ ይገባል፡፡ የመተባበርና ለአገር ማሰብ አንዱ ማሳያና መንገድ ይህ ነው፡፡ ይህ እያደገ እንደሚሄድም ተስፋ አደርጋለሁ፡፡  

ከትውልደ ኢትዮጵያውያን ጋር ተያይዞ አንድ መታለፍ የሌለበት ነገር በተለይ በዚህ ወቅት ከእነርሱ የምንጠብቀው አንድ ነገር አለ፡፡ ይህም ወደ አገር የሚልኩትን ገንዘብ በሕጋዊ መንገድ እንዲያደርጉ ነው፡፡ ተደጋግሞ እንደሚሰማው ከባንክ ውጪ የሚላክ ገንዘብ ተጠቃሚዎች ለአገር አደጋ የሚዶልቱትና የሚያሴሩት መሆናቸውን ነው፡፡ ስለዚህ ስለአገር ብለው ሕጋዊ በሆነው መስመር መጠቀም ገንባቸውን ቢልኩ እያደረጉ ያለው ድጋፍ የበለጠ ትርጉም ይኖረዋል፡፡ አገራቸውም ታመሰግናቸዋለች፡፡ በተለይ በውጭ ምንዛሪ እጥረት የምትጉላላውን አገር በዚህ መንገድ በመደገፍ አሌንታነታቸው እንዲያሳዩ ማበረታታትም ተገቢ ነው፡፡

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት