Friday, December 8, 2023

ከሕግ ማስከበር ዘመቻው ጎን የተነሳው የማንነትና የአስተዳደር ወሰን ጥያቄ ቀጣዩ የፖለቲካ ስበት ማዕከል ይሆን?

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

በትግራይ ክልል በሚገኘው የአገር መከላከያ ሠራዊት ላይ የሕወሓት ቡድን ጥቃት መሰንዘሩን ተከትሎ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ‹‹ቀዩ መስመር›› በመታለፉ የኃይል ዕርምጃ እንዲወሰድ መታዘዙን ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. ማስታወቃቸው ይታወሳል። 

በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኘው የአገር መከላከያ ሠራዊት ተንቀሳቅሶ ትዕዛዙን በትግራይ ክልል በስፋት መፈጸም ከመጀመሩ አስቀድሞ፣ የአማራ ክልል ልዩ ኃይል ክልሉን ከትግራይ ክልል በሚያዋስኑ አካባቢዎች የተቃጣውን ጥቃት የመከላከልና መልሶ የማጥቃት ሥራ በመጀመርያዎቹ ቀናት ማከናወኑ ይታወሳል። 

በሌሎች አካባቢዎች የሚገኘው የመከላከያ ሠራዊት ወደ ትግራይ ክልል ወሰኖች ከደረሰ በኋላም፣ የአማራ ክልል ልዩ ኃይል ከመከላከያ ሠራዊቱ ጋር በመሆን ሰፊ የማጥቃትና የትግራይ ክልል ኃይልን ከተቆጣጠራቸው ቦታዎች የማስለቀቅ ዘመቻ ማድረጉ ይታወቃል፡፡

የመከላከያ ሠራዊቱ ትኩረቱን ወደ መቀሌ አድርጎ በተንቀሳቀሰበት ወቅት የአማራ ክልል ልዩ ኃይል ትግራይን ከአማራ ክልል ጋር በሚዋሰኑ አካባቢዎች ላይ ሕግ የማስከበር ኃላፊነት የመወጣት የተሰጠው ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅትም በስፋት በዚሁ አካባቢ የሕግ ማስከበር ሥራ በማከናወን ላይ እንደሚገኝ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

በአሁኑ ወቅት የአማራ ክልል ልዩ ኃይል የተቆጣጠራቸው አካባቢዎች ያልፈተቱ የማንነትና የአስተዳደር ጥያቄዎች ጎልተው የማደመጡበት መሆኑ በገሃድ የሚታወቅ እውነታ ነው

እነዚህ አካባቢዎች ማለትም ማይካድራ፣ ዳንሻ፣ አላማጣ፣ ጥሙጋና ዋጃ፣ በተጨማሪም በራያ ዋጃ፣ አላማጣና ኮረም እንዲሁም በወልቃይት ጠገዴና ሴቲት ሁመራ ሲሆኑ፣ አካባቢዎቹ ላለፉት ሁለት አሥርት ዓመታት በላይ የማንነትና የአስተዳደር ወሰን ጥያቄዎች ሲቀጣጠሉባቸው፣ ሲረግቡ መልሰው ሲቀጣጠሉ የቆዩባቸው ናቸው። 

በአካባቢዎቹ ላይ የሚኖሩ ሰዎች ማንነታቸው አማራ እንደሆነ ጥያቄዎች የሚያነሱባቸውና መተዳደር የሚገባቸውም ማንነታቸውን በሚወክል ክልል እንደሆነ ሲጠይቁ፣ ከሁለት አሠርታት በላይ ቆይተዋል። በተመሳሳይም በእነዚሁ አካባቢዎች ከላይ የተጠቀሰውን የማንነትና የአስተዳደር አከላለል ጥያቄ የማይቀበሉና የአማራ ማንነት እንደሌላቸው የሚገልጹ፣ ያሉበትን አስተዳደራዊ ክልልም የሚቀበሉ የተቃርኖ ድምፆች ሲሰሙባቸው እንደነበር ይታወቃል፡፡

ሁለቱ ተቃራኒ ጥያቄዎች በጊዜ ሒደት ያልጠፉ የመሆናቸውን ያህልያለቀለት ፖለቲካዊም ሆነ ሕጋዊ መፍትሔ ሳያገኙ በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ሥርዓት ጅማሮ አንስቶ የዘለቁ ናቸው።

የትግራይ ክልል የአስተዳደር ወሰን ውስጥ ሆነው ላለፉት ሁለት አሥርት ዓመታት በቆዩት በእነዚህ አወዛጋቢ አካባቢዎች የጊዜ ሒደት ያልሻረው የማንነት ጥያቄ፣ ዛሬ ትኩስ ሆኖ ወደ አገሪቱ የፖለቲካ መድረክ መነጋገሪያ ሆኖ እንደ አዲስ ወጥቷል፡፡

ከትግራይ ክልል የቀድሞ አስተዳደር ነፃ በወጡት የአማራ ክልል አዋሳኝ ከሆኑት አካባቢዎች መካከል በወልቃይት ጠገዴ ቃፍታ፣ በሁመራ ወረዳ አድህርድ ከተማ ላይ ታኅሳስ 1 ቀን 2013 ዓ.ም. በተካሄዱ ሕዝባዊ ሠልፎች የተሳተፉ እጅግ በርካታ የአካባቢዎቹ ነዋሪዎች ለረዥም ዓመታት የተንከባለሉ ጥያቄዎቻቸውን አንስተዋል።

በተካሄዱት ሠልፎች ከተላለፉ መልዕክቶች መካከልም፣ ‹‹ማንነታችን አማራ ድንበራችን ተከዜ ነው፤›› የሚሉና፣ ‹‹ይዘን እንጠይቃለን እንጂ፣ ለቀን አንደራደርም›› የሚሉ መልዕክቶች ይገኙበታል። ይህንኑ የሕዝብ አቋምም የተለያዩ የአማራ የፖለቲካ ልሂቃን እያስተጋቡት ይገኛሉ።

የትግራይ ክልልን በጊዜያዊነት እንዲያስተዳድር በሕግ መሠረት የተቋቋመው ጊዜያዊ አስተዳደር፣ ይኸው ፖለቲካዊ ጥያቄ ሊነሳ አንደሚችል ቀድሞ ገምቶ ነበር። 

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሙሉ ነጋ (/) ለረዥም ጊዜ ሲነሱ የቆዩ የወሰንና ተመሳሳይ ጥያቄዎች የተሰጣቸውን ኃላፊነት በመወጣት ረገድ፣ ቀዳሚ እክል ሊሆኑ እንደሚችሉ ከጥቂት ሳምንት በፊት ለሪፖርተር ገልጸው ነበር። 

‹‹ችግሩ ከአማራ ክልል አስተዳደር ወገን ይመጣል ብለን ባናስብምመሬት ላይ ያለውን ዘመቻ በደንብ ካለመገንዘብ ሊነሱ የሚችሉ ጥያቄዎች ሊኖሩ ይችላሉ። ነገር ግን ይኼንንም በንግግር እንፈታለን ብለን እናስባለን፤›› ብለው ነበር። 

የብልፅግና ፓርቲ ሥሪ አስፈጻሚ ኮሚቴ ሰሞኑን በወቅታዊ የአገሪቱ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ለሁለት ቀናት ባደረገው ስብሰባ ከተመለከታቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ፣ ይኸው በአማራና በትግራይ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች ላይ ዳግም የተቀሰቀሰው የማንነትና የአስተዳደር ወሰን ጥያቄን የተመለከተ ነበር፡፡

የብልፅግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴም በዚህ ጉዳይ ላይ በዝርዝር ተወያይቶ የእነዚህ ሕዝቦች ጥያቄ ሕጋዊና ሰላማዊ ጥያቄ እስከሆነ ድረስ፣ በሕጉ አግባብና አሠራር መሠረት መልስ ሊሰጠው ይገባል የሚል ውሳኔ ማሳለፉን የፓርቲው ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ብናልፍ አንዱዓለም አስታውቀዋል። 

ፓርቲው ያደረገውን ውይይት አስመልክቶ ሰሞኑን መግለጫ የሰጡት የፓርቲው ሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ብናልፍ፣ የእነዚህ ሕዝቦች ጥያቄ መሬት የማስመለስ ሳይሆን የፍትሕ ጥያቄ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

‹‹ለሦስት አሥርት ዓመታት የተነፈገ የፍትሕ ጥያቄ በማንሳታቸው ፍትሕ ሊያገኙ እንጂ ሊወቀሱ አይገባምበእነዚህ አካባቢ የሚኖሩ ሕዝቦች የሚያነሱት ጥያቄ መሬት የማስመለስ ጥያቄ ነው የሚል ስያሜም ሊሰጠው አይገባም፤›› ብለዋል። 

ይህንን የብልፅግና ፓርቲ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ውሳኔ ተከትሎ የአማራ ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ የአቋም መግለጫ አውጥቷል፡፡ በመግለጫውም፣ ‹‹በግፍ ተወረርን እንጂ ማንንም አልወረርንም። ክልላዊ ወሰናችንንና ፌዴራላዊ መብታችንን በመጋፋት በግፍ ተጠቃን እንጂ ማንንም አላጠቃንም፤›› ብሏል። 

በማከልም፣ ‹‹የሕግ የበላይነት ለማስከበር፣ የአገር ሉዓላዊነት ለማፅናት በተደረገ ሁሉን አቀፍ የትግል ጀብዱ በታሪክ አጋጣሚ ወደ ባለዕርስቱ በገቡ በእነዚህ አካባቢዎች (Repossessed Lands) ላይ የሚነሳውን ማንኛውንም ጥያቄ፣ በሥርዓቱና በአግባቡ በቀጣይ ማየት ይቻላል፤›› ሲል አቋሙን አስታውቋል።

ይሁን እንጂ የተነሳው ማንነትን መሠረት ያደረገ ጥያቄ በአገሪቱ ሕግ መሠረት እስኪፈታ ድረስ የአማራ ክልል የፀጥታ ኃይል ከአካባቢዎቹ ይወጣል? ወይስ በአካባቢዎቹ ተቀምጦ ሕጋዊ መፍትሔ እስኪሰጥበት ይጠብቃል? የሚለውን ጥያቄ በተመለከተ ግን በይፋ የተገለጸ ነገር የለም፡፡

ይህ ጥያቄ ገኖ በወጣበት በአሁኑ ወቅት የብልፅግና ፓርቲ መካከለኛ አመራሮች ጎራ ከፍለው፣ በተነሳው ጥያቄ ዙሪያ በተለያዩ ማኅበራዊ የትስስር ገጾች ቃላት እየተወራወሩ ይገኛሉ፡፡

በዚህ የቃላት እሰጥ አገባ ውስጥ ከተሳተፉት የብልፅግና ፓርቲ አመራሮች መካከል የብልፅግና ፓርቲ የኦሮሚያ ቅርንጫፍ አመራር አካል የሆኑት አቶ ታዬ ደንደአ አንደኛው ናቸው፡፡

አቶ ታዬ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ የአስተዳደር ወሰንን በተመለከተ ጥያቄ ያላቸው ወገኖች እንዳሉ የሚታወቅ በመሆኑና መንግሥትም ይህ ጥያቄ ምላሽ ያስፈልገዋል ብሎ በማመኑ፣ የማንነትና የወሰን ኮሚሽን ማቋቋሙን አስታውሰዋል፡፡

ከዚህ ቀደም የተፈጸሙ የአከላለል ስህተቶች በታላቋ ኢትዮጵያ ውስጥ ይታረሙ ዘንድ ፍላጎት ያላቸው ወገኖች ሕጉን ተከትለው ጥያቄ በማቅረብ መፍትሔ መሻት ይኖርባቸዋል ሲሉ ምክር አዘል አስተያየታቸውን አቅርበዋል፡፡

ሕግን በመተላለፍ በጉልበት ፍላጎትን ለማስፈጸም መንቀሳቀስ ግን በቅርቡ የሕግ ማስከበር ዕርምጃ የተወሰደበት የሕወሓት ስብስብ የባህሪ ወራሽ ያደርጋል ሲሉ ተችተዋል፡፡

በሌላ በኩል የተለያዩ የአማራ ብልፅግና ፓርቲ ልሂቃን ከሌሎቹ የብልፅግና ፓርቲ ባልደረቦቻቸው የተሰነዘሩትን ትችቶች በማጣጣል፣ የአስተዳደር ውሳኔ ጥያቄ የተነሳባቸው አካባቢዎች ወደ አማራ ክልል ቢጠቃለሉ፣ ‹‹የአማራ የፖለቲካ አቅም ይፈረጥማል›› የሚል ሚዛኑን ከሳተ የፖለቲካ የመነጨ ትችት ነው ሲሉ ምላሻቸውን አስፍረዋል፡፡

ሪፖርተር ያነጋገራቸው አንድ የፌዴራሊዝምና የሕግ ባለሙያ በትግራይ ክልል የተካሄደው የሕግ ማስከበር ዘመቻ መጠናቀቁ በተገለጸ ማግሥት የተነሳው የማንነትና የአስተዳደር ውስን ጥያቄ፣ በቀጣዩ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ወሳኝ የስበት ማዕከል ይሆናል ብለው እንደሚያምኑ ጠቁመዋል፡፡

ጥያቄው በአገሪቱ ሕግ መሠረት መፍትሔ ከማግኘቱ በፊት ጥያቄው የማንነት ነው? ወይስ የአስተዳደር ጥያቄ ነው? የሚለውን የመመለስ ጉዳይ የመጀመርያው የፍልሚያ ማዕከል ሊሆን እንደሚችል ይገልጻሉ፡፡

ጥያቄው የማንነት ጥያቄ ከሆነ የማንነት ጥያቄውን የሚያነሱ ሕዝቦች የማንነት ጥያቄ መሆናቸውን፣ ተመልሶ ያሉበትን የአስተዳደር ክልል መለወጥ ሳያስፈልጋቸው ባሉበት ክልል ራሳቸውን ማስተዳደር እንደሚችሉ ይገልጻሉ፡፡

ጥያቄው በዚህ መንገድ እንዲፈታ የሚፈልጉ የብልፅግና ፓርቲ አባላት የጥያቄው ይዘትም መፍትሔውም ይህ አይደለም ከሚሉት ጋር ሙግት የሚገጥሙበት እንደሚሆን ያስረዳሉ፡፡

ጥያቄው የማንነት ሳይሆን የአስተዳደር ወሰን ጥያቄ እንደሆነ የሚገልጹ መኖራቸውን የገለጹት እኚሁ ባለሙያ፣ ጥያቄው በዚህ መንገድ መፍትሔ እንዲያገኝ ውሳኔ ካገኘ ደግሞ ጉዳዩ የሕዝብ ጥያቄ ከመሆን ወጥቶ በክልሎች መካከል የአስተዳደር ውስን አከላለል ለውጥ እንደሚሆን አስረድተዋል፡፡

ይህ ከሆነ የአስተዳደር ወሰን ለውጥ ጥያቄ የቀረበበት የትግራይ ክልል በብልፅግና ፓርቲ መዋቅር ውስጥ ቦታ የሌለው በመሆኑ፣ የሚተላለፈው ውሳኔ የፍትሐዊነት ጥያቄ የሚነሳበት ሊሆን እንደሚችልና የአስተዳደር ወሰን ለውጥ ጥያቄው የሚነካቸው አካባቢዎች የሚገኙ ነዋሪዎች የብሔር ስብጥር ሌሎችንም የሚነካ በመሆኑ፣ በቀላሉ መፍትሔ የሚያገኝ ጉዳይ ይሆናል ብለው እንደማይገምቱ ገልጸዋል፡፡

ይህ ሁኔታም በብልፅግና ፓርቲ ውስጥ መሞዳሞድን ወደ መፍጠርና የፓርቲውን የሐሳብ አንድነት ወደ ማሳት ሊሸጋገር እንደሚችል ይገመታሉ፡፡

በመሆኑም የተነሳው ጥያቄ በቀጣዮቹ ዓመታት የኢትዮጵያ ፖለቲካ የስበት ማዕከል ሆኖ የሚቀጥል አወዛጋቢ ጉዳይ ሊሆን እንደሚችል ያስባሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -