Tuesday, May 28, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊየመጀመርያው የኢሕዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ፍቅረ ሥላሴ ወግደረስ (1938 እስከ 2013)

የመጀመርያው የኢሕዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ፍቅረ ሥላሴ ወግደረስ (1938 እስከ 2013)

ቀን:

‹‹ተነሳ ተራመድ ክንድህን አበርታ

 ላገር ብልፅግና ለወገን መከታ….

 ኢትዮጵያችን ትቅደም ብለን እንገስግስ

- Advertisement -

 ለትውልድ እንዲተርፍ የያዝነው ጥንስስ

 ሀሁ ኢትዮጵያ ትቅደም

 ኢትዮጵያ ትቅደም….››

አምስት አሠርታትን ሊያስቆጥር የሦስት ዓመት ዕድሜ ብቻ የቀረው የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮት በየካቲት በፈነዳ በአምስተኛው ወር የተቋቋመውና ዘውዳዊ ሥርዓቱን አስወግዶ ሥልጣን የጨበጠው የደርግ ጉዞ መባቻ ላይ የወጣው፣ የአየር ኃይል ሙዚቀኞች ‹‹ተነሳ ተራመድ›› ዜማ የለውጡ ማቀጣጠያ እንደነበረ ይወሳል፡፡

ሕዝባዊ ንቅናቄውን ተከትሎ በሰኔ 21 ቀን 1966 ዓ.ም. የተቋቋመው የጦር ኃይሎች፣ የፖሊስ ሠራዊትና የብሔራዊ ጦር አስተባባሪ ደርግ፣ በ4ኛ ክፍለ ጦር ሲሰበሰብ አየር ኃይልን ወክለው ከተገኙት መኮንኖች አንዱ በወቅቱ ማዕረጋቸው የመቶ አለቃ ፍቅረ ሥላሴ ወግደረስ ናቸው፡፡  የመጨረሻውን የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ (1923 እስከ 1967) ከዙፋናቸው ለማውረድ 75 ቀናት የወሰደበት ደርግ፣ እሳቸውን ለማውረድ መስከረም 2 ቀን 1967 ዓ.ም. በፖሊስ ሠራዊት ተወካዩ ሻለቃ ደበላ ዲንሳ መሪነት ወደ ኢዮቤልዩ ቤተ መንግሥት በላከው ቡድን ውስጥ የአየር ኃይሉ መኮንን ፍቅረ ሥላሴ ነበሩበት፡፡

አዋሽ ባንክ የጨረታ ማስታወቂያ

በቀዳሚ መጠሪያው የኅብረተሰብዓዊት ኢትዮጵያ ጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ ከፍተኛ የሥልጣን ዕርከን ላይ ያልነበሩትና በሒደት ሻምበል የሆኑት ፍቅረ ሥላሴ፣ የመጀመርያው ኃላፊነታቸው የዕድገት በኅብረት የዕውቀትና የሥራ ዘመቻ መምርያ ኃላፊነት ነው፡፡  ከኅብረተሰብዓዊነት ርዕዮት ወደ ብሔራዊ ዴሞክራሲያዊ አብዮት ፕሮግራም (1968) ሽግግር ከተደረገ በኋላ፣ የማርክሲዝም ሌኒኒዝም (ማሌ) ትምህርት እንዲቀስሙ ወደ ሶቪየት ኅብረት ከተላኩ የደርግ አባላት መካከልም ሻምበል ፍቅረ ሥላሴ ይገኙበታል፡፡

የደርጉ ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበር ሌተና ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማርያም በርዕሰ ብሔሩ ብርጋዴር ጄኔራል ተፈሪ በንቲ ላይ ጥር 26 ቀን 1969 ዓ.ም. ያካሄዱት ደም አፋሳሽ መፈንቅለ መንግሥት፣ ሻምበል ፍቅረ ሥላሴን ወደ ከፍተኛ ሥልጣን ያወጣቸውን ዋና ጸሐፊነት አስጨበጣቸው፡፡

በብሔራዊ ዴሞክራሲያዊ አብዮት ፕሮግራም መሠረት ‹‹የወዝ አደር ፓርቲ›› የመመሥረት ህልም ዕውን ለማድረግ በነበረው ውጣ ውረድ፣ ሽኩቻና ጥልፍልፍ ተነጥሎ የወጣውና በኮሎኔል መንግሥቱ ይመራ የነበረው ‹‹አብዮታዊ ሰደድ ፓርቲ›› ድርጅታዊ ሥራን ለማጠናከር፣ የፖለቲካውን ጉዳይ የሚከታተል ኮሚቴ መሪ ሆነው መሥራታቸውን ገጸ ታሪካቸው ያስረዳል፡፡

የኢትዮጵያ ማርክሲስት ሌኒኒስት ድርጅቶች ኅብረት (ኢማሌድኅ) ከከሰመ በኋላ በአዋጅ የተቋቋመውን የኢትዮጵያ ሠርቶ አደሮች ፓርቲ አደራጅ ኮሚሽን (ኢሠፓአኮ) በሥራ አስፈጻሚነት ከተመረጡት ሰባት ጓዶች በሁለተኛነት የተመረጡት ሻምበል ፍቅረ ሥላሴ፣ ኮሚሽኑ ተልዕኮውን ፈጽሞ የኢትዮጵያ ሠራተኞች ፓርቲ (ኢሠፓ) ዕውን ሲሆንም የፖሊት ቢሮ አባል ሆነዋል፡፡ የጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ ለ13 ዓመታት (1967 እስከ 1979) የጨበጠውን ሥልጣን የኢትዮጵያ ሕዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክን (ኢሕዲሪ) መሥርቶ ሲያስረክብም፣ ከመስከረም 1 ቀን 1980 ዓ.ም. ጀምሮ ከሁለት ዓመት በላይ የመጀመርያው ጠቅላይ ሚኒስትር በመሆን በ‹‹ጤና›› ምክንያት እስከለቀቁበት ጥቅምት 1982 ዓ.ም. ድረስ ሠርተዋል፡፡

በ1983 ዓ.ም. ወርኃ ግንቦት በኢሕአዴግ አማካይነት የተደረገውን የመንግሥት ለውጥ ተከትሎ፣ ‹‹ያለ ምንም ደም ኢትዮጵያ ትቅደም›› ብለው የተነሱት ደርጎች በዘመናቸው በኢትዮጵያ ከነፃ ዕርምጃ እስከ ቀይና ነጭ ሽብር ድረስ በደረሰ ግድያ፣ ዘርማጥፋትና የሰብዓዊ መብት ጥሰት ወንጀል በ1989 ዓ.ም. በተመሠረተባቸው ክስ፣ ሻምበል ፍቅረ ሥላሴን ጨምሮ ሌሎች ሹማምንት በ2000 ዓ.ም. የሞት ፍርድ ተፈርዶበቸው ነበር፡፡ ከሦስት ዓመታት ቆይታ በኋላ የሞት ቅጣታቸው በይቅርታ ተነስቶ ወደ ዕድሜ ልክ በመቀየሩ፣ በ2004 ዓ.ም. ሲፈቱ አንዱ ተጠቃሚ ሻምበል ፍቅረ ሥላሴ ነበሩ፡፡   

በአዲስ አበባ ከተማ ቀጨኔ ሠፈር ሐምሌ 7 ቀን 1937 .ም. የተወለዱት ሻምበል ፍቅረ ሥላሴ ወግደረስ፣ በኢትዮጵያ አየር ኃይል ማሠልጠኛ 1955 .ም. በመኮንንነት የተመረቁ ሲሆን፣ በአሜሪካም ኮርስ መውሰዳቸውን ገጸ ታሪካቸው ያስረዳል፡፡

ከሁለት አሠርታት እስር በኋላ ያዘጋጇቸውን ‹‹እኛና አብዮቱ›› (2006)፣ እንዲሁም ‹‹እኔና አብዮቱ›› (2013)  የተሰኙ መጻሕፍትን አሳትመዋል፡፡ በቀዳሚው መጽሐፋቸው ላይ እንደገለጹትም፣ የኅትመት ብርሃን ያላገኙ በእስር ቤቶች ያሳለፉትን ሕይወትና ገጠመኞቻቸውን የሚመለከት ‹‹እኔና ስምንቱ እስር ቤቶች››፣ እንዲሁም በእሳቸውና በባልደረቦቻቸው ላይ የተመሠረተውን ክስና የፍርድ ሒደቱን የሚዳስሰው ‹‹እኛ እና ፍርድ ቤቱ›› መጻሕፍትም አሏቸው፡፡

ልከኛና ቄንጠኛ በሆነው አለባበሳቸው የተነሳ ከኅብረተሰቡ ‹‹አለባበስ እንደ ወግደረስ›› የሚል ብሂል ያተረፉት ሻምበል ፍቅረ ሥላሴ፣ ባደረባቸው ሕመም ምክንያት በአገር ውስጥና በውጭ አገር ሲከታተሉ ከቆዩ በኋላ፣ ታኅሳስ 3 ቀን 2013 ዓ.ም. አርፈዋል፡፡ ሥርዓተ ቀብራቸውም ዛሬ ረቡዕ ታኅሳስ 7 ቀን ከቀኑ 900 ሰዓት በመንበረ ፀባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል እንደሚፈጸም ታውቋል፡፡

ነፍስ ኄር ሻምበል ፍቅረ ሥላሴ ባለትዳርና የሦስት (የሁለት ሴቶችና የአንድ ወንድ) ልጆች አባት ነበሩ፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የፋይናንስ ኢንዱስትሪው ለውጭ ባንኮች መከፈት አገር በቀል ባንኮችን ለምን አስፈራቸው?

የማይረጥቡ ዓሳዎች የፋይናንስ ተቋማት መሪዎች ሙግት ሲሞገት! - በአመሐ...

የምርጫ 97 ትውስታ!

በበቀለ ሹሜ      መሰናዶ ኢሕአዴግ ተሰነጣጥቆ ከመወገድ ከተረፈ በኋላ፣ አገዛዙን ከማሻሻልና...

ሸማቾች የሚሰቃዩት በዋጋ ንረት ብቻ አይደለም!

የሸማች ችግር ብዙ ነው፡፡ ሸማቾች የሚፈተኑት ባልተገባ የዋጋ ጭማሪ...

መንግሥት ከለጋሽ አካላት ሀብት ለማግኘት የጀመረውን ድርድር አጠናክሮ እንዲቀጥል ፓርላማው አሳሰበ

የሦስት ዩኒቨርሲቲዎች ፕሬዚዳንቶች በኦዲት ግኝት ከኃላፊነታቸው መነሳታቸው ተገልጿል አዲስ አበባ...