አንድ ቢሊዮን ብር የሚገመት ኮንትሮባንድ ዕቃዎች ይዣለሁ አለ
ገቢዎች ሚኒስቴር ከሐምሌ 2012 ዓ.ም. እስከ ኅዳር 30 ቀን 2013 ዓ.ም. ባሉት አምስት ወራት 126.85 ቢሊዮን ብር መሰብሰቡን አስታወቀ፡፡
ባለፉት አምስት ወራት ከአገር ውስጥ ገቢ 80.96 ቢሊዮን ብር፣ ከውጭ ንግድ ቀረጥና ታክስ 45.77 ቢሊዮን ብርና ከሎተሪ ሽያጭ 109.45 ሚሊዮን ብር ገቢ መገኘቱን ሚኒስቴሩ ገልጿል፡፡
በበጀት ዓመቱ 290 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ማቀዱንና በመጀመሪያዎቹ አምስት ወራት ከ126 ቢሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡን ያስታወቀው ሚኒስቴሩ፣ ለዚህም የክትትልና ድጋፍ ሥራዎች መጠናከር፣ የተሻለ የታክስ ሕግ ተገዥነት ላሳዩ ግብር ከፋዮችና በትጋት ሥራ ላከናወኑ አመራሮችና ሠራተኞች ዕውቅናና ሽልማት መሰጠቱ፣ የግብር ከፋዮች መነሳሳት መፈጠሩ ገቢ አሰባሳቡ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ መፍጠሩን አክሏል፡፡
ገቢው ከአምናው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር ከ17.4 ቢሊዮን ብር በላይ ጭማሪ አሳይቷል ተብሏል፡፡ በታኅሳስ ወር 21.33 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ እየተሠራ መሆኑንም ሚኒስቴሩ አስታውቋል፡፡
በተመሳሳይ ወራት ውስጥ የገቢዎች ሚኒስቴርና የጉምሩክ ኮሚሽን በጋራ ባደረጉት እንቅስቃሴ፣ 1,356,000,119 ብር ግምታዊ ዋጋ ያላቸው ገቢና ወጪ ኮንትሮባንድ ዕቃዎች መያዛቸውም ተገልጿል፡፡
ግምታዊ ዋጋቸው 981,590,000 ብር ለመያዝ ታቅዶ 1,100,631,000 ብር የሚገመት ገቢ ኮንትሮባንድን ለመያዝ መቻሉን፣ የገቢ ኮንትሮባንድ ካለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በ24 በመቶ ጭማሪ ሲያሳይ ወጪ ኮንትሮባንድ ደግሞ 72 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱ ተነግሯል፡፡