ኢትዮጵያ ውስጥ በፖለቲከኞች መለመድ ካለባቸው መልካም ተግባራት ውስጥ የሕዝብ ፈቃድና ፍላጎት ማክበር አንዱ ነው፡፡ አገር በመምራት ላይ ያለው ገዥ ፓርቲም ሆነ ሌሎች ተፎካካሪ ፓርቲዎች፣ ከምንም ነገር በላይ ቅድሚያ መስጠት ያለባቸው የሥልጣን ሉዓላዊ ባለቤት የሆነውን ሕዝብ ማክበር ነው፡፡ በዚህ ቁመና ላይ ሳይገኙ ወደ ፖለቲካው ምኅዳር የሚደረግ ጉዞ ከትርፉ ይልቅ ኪሳራው የበዛ ነው፡፡ ሕዝብ ሰላም ሰፍኖ ደኅንነቱ እንዲጠበቅ ይፈልጋል፡፡ ሰላም ሲኖር ከአስመራሪው ድህነት ውስጥ ለመውጣትና የተሻለ ኑሮ ለማግኘት፣ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶቹ እንዲከበሩ፣ በአገሩ ጉዳይ ባለቤትነቱ እንዲረጋገጥና ሌሎች ጠቃሚ ጉዳዮች እንዲከናወኑ ዕድሎች ይመቻቻሉ፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ፉክክር በሕጋዊነትና በሰላማዊነት ቅጽር ውስጥ ይከናወናል፡፡ ሕገወጥነትና ሥርዓተ አልበኝነት ቦታ አይኖራቸውም፡፡ ዝርፊያና ሌብነት አይታሰቡም፡፡ የመንግሥት ሥልጣን በእኩልነት ፉክክር በሚደረግበት አሳማኝ ምርጫ ይያዛል እንጂ፣ ማንም ጉልበተኛ እየመጣ የሚፈነጭበት አይሆንም፡፡ ኢትዮጵያዊያን ከአሁን በኋላ ለጋራ ብሔራዊ ጉዳዮች በአንድነት በመቆም ለዚህ ዓላማ ስኬት ጠንክረው መሥራት ይጠበቅባቸዋል፡፡ በኢትዮጵያና በኢትዮጵያዊያን ዕጣ ፈንታ ላይ መቆመር እንደማይቻል በተግባር ማረጋገጥ ተገቢ ነው፡፡ ሕዝብን ማታለል ስለማይቻል፡፡
ሕዝብ ፊት መቅረብ የሚቻለው በተሻለ አማራጭ እንጂ በነውጥ እንዳልሆነ ለማንም ግልጽ ሊሆን ይገባል፡፡ በኢትዮጵያ ምድር ክርክሩም ሆነ ፉክክሩ እንዲያምር የፖለቲካው ምኅዳር ሁሉንም አሳታፊ፣ ግልጽ፣ ሰላማዊና ሕጋዊ መሆን ይኖርበታል፡፡ ይህ ዓይነቱ መደላድል እንዲፈጠር ደግሞ የራስን አስተዋፅኦ ማበርከት የሁሉም ፖለቲካ ኃይሎች ኃላፊነት ነው፡፡ ባረጀና ባፈጀ አስተሳሰብ ተጀቡኖ ማምታታት ማብቃት ይኖርበታል፡፡ የፖለቲካ ኃይሎች ፍላጎታቸው ከሕዝብና ከአገር ክብርና ህልውና በታች መሆኑን ያረጋግጡ፡፡ ለኅብረ ብሔራዊ ፌዴራሊዝምም ሆነ ለሌላ ዓይነት ፌዴራሊዝም ዓላማ ይቁሙ፣ ከሰላማዊና ከሕጋዊ መንገድ ማፈንገጥ የለባቸውም፡፡ ከሥልጣን በላይ ለሕዝብና ለአገር ቅድሚያ ይስጡ፡፡ የተሻለች ዴሞክራቲክ ኢትዮጵያ በምን ዓይነት የተሻለ አማራጭ ልትገነባ እንደምትችል ፖሊሲ ማሳየት እንጂ፣ የግልና የቡድን ዓላማ ሳይሳካ ሲቀር አገርን በማገት ለማፍረስ ያዙኝ ልቀቁኝ ማለት የትም እንደማያደርስ በሚገባ ታይቷል፡፡ አገርን እንደ ወለድ አግድ ማስያዣ የፍላጎት ማስፈጸሚያ ማድረግም አይቻልም፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከዳር እስከ ዳር በአገሩ መቀለድ እንደማይቻል በግልጽ አስታውቋል፡፡ የመንግሥት ሥልጣን የያዙም ሆኑ ለሥልጣን የሚፎካከሩ ከሕዝብ ፈቃድ ሲያፈነግጡ፣ የአታላይነት ባህሪ ስለሆነ ከሕዝብ ጋር ይጣላሉ፡፡
አገርን ከማንኛውም ዓይነት ጥቃት የመታደግና የሕዝብን ደኅንነት የመጠበቅ ኃላፊነት ያለባቸው የአገር መከላከያ ሠራዊት፣ የፖሊስና የተለያዩ የፀጥታ አካላትን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የፖለቲካ ተቀጥላ ማድረግ ሕገወጥ መሆኑን የጋራ ግንዛቤ ሊኖር ይገባል፡፡ አገርን የመጠበቅ ኃላፊነት ያለባቸው ተቋማትን መታከክ ተገቢ ካለመሆኑም በላይ፣ ገለልተኝነታቸውን ጠብቀው ተልዕኮአቸውን እንዲወጡ አለማገዝ ማስጠየቅ ይኖርበታል፡፡ ይህንን የምናነሳው ያለ ምክንያት አይደለም፡፡ ከዚህ ቀደም ተቋማቱን ላልተፈለገ ዓላማ ለመጠቀም የተሄደበት ርቀት ምን ያህል ችግር ፈጣሪ እንደነበር ስለማይረሳ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በመቀሌ ከተማ ከከፍተኛ የጦር ጄኔራሎች ጋር በነበራቸው ውይይት፣ ሠራዊቱ የብልፅግና ፓርቲ ወይም የእሳቸው ሳይሆን የኢትዮጵያ ሕዝብ ሠራዊት መሆኑን በአፅንኦት መናገራቸው ይታወሳል፡፡ ሠራዊቱ ከፓርቲ በላይ የሆነች ታላቅ አገር የመታደግ ኃላፊነት እንዳለበት ሲያስገነዝቡ፣ ገዥውም ሆነ ሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎች ራሳቸውን ማቀብ እንዳለባቸው ነው፡፡ የአገርን ሉዓላዊነት የሚያስከብር ሠራዊትንም ሆነ ሌሎች የፀጥታ ተቋማትን ማክበርና ኃላፊነታቸውን በነፃነት እንዲወጡ ማድረግ የግድ ነው፡፡ ይህንን ማድረግ ሲቻል ሕዝብና አገር ይከበራሉ፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች አፋቸውም እጃቸውም ሲፆም ከሕዝብ ጋር ፀብ አይፈጥሩም፡፡
የፖለቲካ ፓርቲዎች ሌላው ኃላፊነት የዴሞክራቲክ ተቋማት ማለትም የምርጫ ቦርድ፣ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን፣ የዕንባ ጠባቂ ተቋም፣ የፌዴራል ዋና ኦዲተርና የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን በነፃነትና በገለልተኝነት ሥራቸውን እንዲያከናውኑ መታገል አለባቸው፡፡ ፓርቲዎችም ሆኑ ሌሎች አካላት ጣልቃ ሳይገቡባቸው ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ማድረግ ተገቢ ነው፡፡ እነዚህ ተቋማት ሥራቸውን በነፃነት ሲያከናውኑ ከሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች መከበር ጎን ለጎን ሥርዓተ አልበኝነት እንዲወገድ ትልቅ አስተዋፅኦ ይኖራቸዋል፡፡ የፍትሕና የዳኝነት አካሉ የማንም መሣሪያ ሳይሆን ሥራውን በነፃነት በሚገባ እንዲያከናውን ማድረግ፣ ሕገወጥነትና ገደብ አልባ ሥልጣን እንዲያከትም ያደርጋል፡፡ ዜጎች ፍትሕ እንደ ሰማይ ርቆባቸው መሰቃየታቸው ያቆማል፡፡ ምርጫ ማጭበርበርና የዘፈቀደ ድርጊቶች ያከትማሉ፡፡ በሥልጣን መባለግም ሆነ ማባለግ ነውር ይሆናል፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች እነዚህንና መሰል ተግባራትን ወደ ጎን እያሉ ሥልጣን ላይ ብቻ ሲያንጋጥጡ፣ በጣም አስፈላጊ ነገሮች መባከናቸው ብቻ ሳይሆን የንፁኃን ሕይወትና የአገር ሀብት ለውድመት ይጋለጣል፡፡ ከዚህ ቀደም ለሰላማዊና ለሕጋዊ የፖለቲካ ፉክክር ሥፍራ ባለመሰጠቱ በርካታ ደም ፈሷል፡፡ የደሃ አገር ሀብት ጋይቷል፡፡ ሕዝብ ደግሞ በእነዚህ ድርጊቶች ሳቢያ ቂም ይዟል፡፡
በቅርቡ በትግራይ ክልል በተደረገው ዘመቻ የኢትዮጵያ ሕዝብ አንድነት የተፈተነበት፣ በጣም በሚያስደንቅ ሁኔታም ሕዝቡ አንድ መሆኑን ያሳየበት ነበር፡፡ በብዙዎች አዕምሮ ውስጥ ሲጉላላ የነበረው ፍርኃት ለዘመናት ሲወርድ ሲዋረድ የመጣው አንድነት እንከን እንደ ገጠመው ነበር፡፡ ነገር ግን ሕዝቡ ከዳር እስከ ዳር ቀፎው እንደተነካበት ንብ አንድ ላይ ሲነሳ፣ ኢትዮጵያ ልትበተን ነው ልትፈርስ ነው የሚለውን የሥጋት ግምት አትንኖታል፡፡ ለዚህም ነው ኢትዮጵያ የሚያምርባትና ተስፋዋ የሚፈካው እዚህ ግባ በማይባሉ ልዩነቶች ስትጎሳቆል ሳይሆን፣ ኢትዮጵያዊያን ልዩነቶቻቸውን ጌጥ አድርገው አንድ መሆን ሲችሉ ብቻ ነው፡፡ ፖለቲከኞችም ሆኑ የእነሱ ምስለኔዎች ትክክለኛውን የዕድገት ጎዳና ስተው ሕዝብ ሲከፋፍሉ፣ ዋነኛ ዓላማቸው ግላዊና ቡድናዊ ጥቅም በማስቀደም አገርና ሕዝብን ከቁምነገር አለመቁጠር ነው፡፡ በአገር ጉዳይ ሕዝብና መንግሥት ብቻ ሳይሆኑ አንድ መሆን ያለባቸው፣ የተለያዩ ዓላማዎችን ያነገቡ ፖለቲከኞች ጭምር ናቸው፡፡ ፖለቲከኞች ልዩነታቸውን በሠለጠነ መንገድ እያስተናገዱ ለሕዝብ ውሳኔ ራሳቸውን ሲያዘጋጁ፣ አገር ከፍታዋ እየጨመረ ይሄዳል እንጂ አትጎዳም፡፡ ሥልጣንን ብቻ ግብ አድርገው ‹‹የትም ፍጪው ዱቄቱን አምጪው›› በሚለው ደካማ አስተሳሰብ አይመሩ፡፡ ሕዝብ እንዲህ ዓይነቱ አይረቤ ነገር ሰልችቶታል፡፡
ኢትዮጵያዊያን ከተባበሩ ምንም ነገር እንደማያዳግታቸው በተለያዩ ጊዜያት ማሳያት ችለዋል፡፡ ትልቁ ችግር ግን ይህንን ትብብርና አንድነት የሚንዱ ድርጊቶችን የሚፈጽሙ ፖለቲከኞች ናቸው፡፡ ሰላማዊውን የፖለቲካ ምኅዳር በደም እያጨቀዩ አገር ለማፍረስ ከሚፍጨረጨሩ ሥርዓተ አልበኞች ጀምሮ፣ ለሰላማዊ ፉክክር ምንም ዓይነት አስተዋፅኦ የሌላቸው አደፍራሾች ድረስ ሕግ ሁሉንም ሊገዛ ይገባዋል፡፡ በቅድመ ሁኔታዎች የታጠሩ መደራደሪያ እያቀረቡ ሕገወጥነትን የሚያደፋፍሩ ስመ ፖለቲከኞች በሕግ ሊዳኙ ይገባል፡፡ በእነሱ ምክንያት ንፁኃን ማለቅ፣ ከመኖሪያቸው መፈናልና ያለቻቸው ጥሪት መውደም የለባትም፡፡ በዚህም ምክንያት የአገር ሰላም እየተናጋ ለልማትና ለዕድገት መሠለፍ የነበረበት ወጣት ትውልድ ለግጭት መማገድ አይኖርበትም፡፡ በስንትና ልፋትና ጥረት የሚገኝ ውስን የአገር ሀብትም መውደም የለበትም፡፡ አገር የመጪው ምርጫ ዋዜማ ላይ ቆማ ፋይዳ የሌላቸው ከንቱ ነገሮች ላይ ከማተኮር፣ የመፎካከሪያ ሜዳው ሁሉንም ያለ አድልዎ እንዲያሳትፍ ጠንክሮ መሥራት ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ ቀደም የተሄደባቸው የስህተት መንገዶች በትክክለኛና በአዋጭ መንገድ ይተኩ፡፡ ምርጫ ለማጭበርበር ሲባል ብቻ የሚደረጉ አሳፋሪ ድርጊቶች ከዚህች አገር ይወገዱ፡፡ ለምርጫ በሚገባ ሳይዘጋጁ የበደል አቤቱታ ለማሰማት ብቻ የሚንቀሳቀሱ ካሉም ራሳቸውን በጊዜ ያግልሉ፡፡ የሥልጣን ሉዓላዊ ባለቤት ለሆነው ሕዝብ ዳኝነት መቅረብ የሚቻለው፣ በአስተማማኝ ቁመና ላይ በመገኘት ብቻ እንደሆነ መተማመን ይገባል፡፡ ሕዝብን እየደጋገሙ ማታለል አይቻልምና!