Tuesday, February 27, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

መንግሥት 63 ማዕድን ማምረትና ምርምር ንግድ ፈቃዶች መሰረዙን አስታወቀ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር በማዕድን ማምረትና ምርምር ላይ ፈቃድ ከተሰጣቸው ተቋማት ውስጥ 63 ተቋማት ፈቃዳቸው መሰረዙ ታወቀ፡፡ ተቋማቱ ባሳዩት የአፈጻጸም ድክመትና የሕዝብና የመንግሥት ሀብትን ማባከናቸው በመታወቁ በሚል የተሰጣቸው ፈቃድ ሙሉ በሙሉ መሰረዙን ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ገልጿል፡፡

ተቋማቱ የተሰጣቸው ፈቃድ የተሰረዘባቸው፣ የተሰጣቸውን ፈቃድ ጊዜውን ጠብቀው ባለማደስና በውል የገቡበትን ግዴታ ባለማክበር፣ ከአቅም በታች በማምረትና የሮያሊቲ ክፍያ ባለመፈጸማቸው መሆኑን የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስትሩ ታከለ ኡማ (ኢንጂነር) ማክሰኞ ኅዳር 6 ቀን 2013 ዓ.ም. ለጋዜጠኞች በሰጡት ማብራሪያ ተናግረዋል፡፡

አዋሽ ባንክ የጨረታ ማስታወቂያ

ፈቃዳቸው ከተሰረዘባቸው 63 ተቋማት ውስጥ 38ቱ በማዕድን ምርት ላይ ተሰማርተው የነበሩ ሲሆን፣ ቀሪዎቹ ተቋማት ደግሞ በማዕድን ምርምር ላይ ሲሠሩ የነበሩ እንደሆነ ተገልጿል፡፡

ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የተቋማቱን ቁመና ለማጥናትና ዕርምጃ ለመውሰድ በሙያው ለበርካታ ዓመታት ልምድ ያካበቱ ባለሙያዎችን የያዙ ሁለት ኮሚቴዎችን በማቋቋም፣ በጥንቃቄና ሚዛናዊ በሆነ አሠራር እንደሠራው ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡

የሥራ ፈቃዳቸው ከተሰረዘባቸው ተቋማት በተጨማሪ የውጭ ምንዛሪና የተለያዩ የመሠረተ ልማት ችግር ያሉባቸው 150 ተቋማትን ሚኒስቴሩ ክትትልና ቁጥጥር እያደረገባቸው መሆኑም ተገልጿል፡፡

እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ የሥራ ፈቃዳቸው የተሰረዘባቸው ተቋማት ‹‹በአገር ሀብት ሲቀልዱ የነበሩና ከዚህ በኋላ ቢታገዙም ወደ ማምረት ሊመለሱ የማይችሉ ናቸው፤›› ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ የማዕድን ሀብት ወደ ግዙፍ ኢንቨስትመንት ደረጃ ማደግ የሚችል ቢሆንም፣ ዘርፉ ለብልሹ አሠራር የተጋለጠ ሆኖ መቆየቱንና በዘመናዊ መንገድ መደገፍ ባለመቻሉ፣ ለአገር ማበርከት ያለበትን ፋይዳ እንዳላበረከተ ተገልጿል፡፡

ፈቃዳቸው የተወሰደባቸው የማዕድን ቦታዎች፣ በአፋጣኝ ወደ ሥራ እንዲገቡና የአገርና የሕዝብ ሀብቶች የሆኑት የማዕድን ቦታዎች በተገቢው መልኩ ጥቅም ላይ እንዲውሉ እንደሚደረግም ሚኒስትሩ ጠቁመዋል፡፡

በአገሪቷ የሚገኙ የማዕድን ሀብቶች በተሻለ መልኩ ለመጠቀምና የማዕድን ዘርፉ በከፍተኛ ኢንቨስትመንት እንዲመራ ዘመናዊ የመረጃ ሒደትን መዘርጋት አስፈላጊ በመሆኑ፣ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በማዕድን ዘርፉ ያሉ የተለያዩ መረጃዎች የተደራጁበት እንዲሁም ፈቃድ የመውሰድና የማመልከት ሒደቱን የሚያቀልና ዘመናዊ የሚያደርግ፣ የካዳስተር ፖርታል ሥርዓት መዘጋጀቱን ኢንጂነር ታከለ አክለዋል፡፡

የተዘረጋው ሥርዓት በየክልሎቹ በማዕድን ዘርፍ ላይ የተሰማሩ ተቋማት ያሉበትን ሁኔታ የሚያሳዩ መረጃዎች በካዳስተር ፖርታሉ ላይ እንዲገኙ ተደርጎ የተዘጋጀ ነው፡፡ በተጨማሪም ለኢንቨስተሮች ስለኢትዮጵያ የማዕድን ዘርፍና በአገሪቱ ስላሉ የማዕድን ሀብቶች የተደራጀ መረጃ  የሚገኝበት ነው ተብሏል፡፡

ባለፉት አምስት ወራትም ከማዕድን ዘርፍ 302.9 ሚሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱ ተገልጿል፡፡ በዚህም በአምስት ወር 4083.2 ኪሎ ግን ወርቅ ለውጭ ገበያ ቀርባ የተገኘው ገቢ 299.1 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪ መሆኑንና ከጌጣጌጥ ማዕድናት ደግሞ 3.8 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ገቢ መገኘቱ ተገልጿል፡፡  

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች