Thursday, February 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊብርቅዬዎቹ እፉኝቶች

ብርቅዬዎቹ እፉኝቶች

ቀን:

ስሙ ሲነሳ የሚዘገንናቸው ብዙዎች ናቸው፡፡ በዓይን ዓይተው የማያውቁት እንኳን በመገናኛ ብዙኃን ሲያዩት ይደነግጣሉ፡፡ አንዳንዶች እንደ እምነታቸው ይገስጹታል፡፡

እባብ (እፉኝት) ከሃይማኖት አንጻርና በማኅበረሰብ ትርክት ክፉ ገጸ ባህሪ በመላበሱ በብዙዎች አይወደድም፡፡ እፉኝቶች ልጆቻቸውን የሚመገቡ በመሆናቸው ብዙውን ጊዜ በሃይማኖትም የተወገዙ ናቸው፡፡

ከዚህም ባለፈ ተንኮለኞችን በእባብ መቀፀል የተለመደ ነው፡፡ ከአባባሎች እንኳን ብንነሳ ‹‹ጥሩ እባብ የሞተ እባብ ብቻ ነው››፣ ‹‹እባብ ለሰለሰ ተብሎ ኪስ ውስጥ አይጨመርም›› የሚሉትና ሌሎችም አባባሎችና ምሳሌዎች ተጠቃሽ ናቸው፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

እባቦች ወይም ድራገኖች ኢትዮጵያ ጨምሮ በጥንታዊ መንግሥታት፣ ሃይማኖቶችና እምነቶች ላይ በብዛት ስሙ ይጠቀሳል፡፡ ኢትዮጵያን ጨምሮ በሜሴፓታሚያ፣ በግብፅ፣ በቻይናና በህንድ የእባብ አማልክት ነገሥታት የእባብ ፈውስ፣ ጥበብ፣ ኃይል ታሪኮች እንደነበራቸው ይጠቀሳሉ፡፡

በእነዚህና በሌሎች ምክንያቶች ከሥነ ምኅዳር የሕይወት ሰንሰለት ከማስጠበቅ አንፃር ያለውን ሚና ወደ ጎን ትቶ በታየበትና ባለበት ሁሉ የሚገደል ሆኗል፡፡ ከዚህም ባለፈ ኢትዮጵያ ካላት ድንቅ የእባብ ሀብት መጠቀም አለመቻል በራሱ የዚህ ሁሉ ተፅዕኖ መሆኑ ለመገመት አያዳግትም፡፡

ለዚህም ‹‹አደገኛና ጠቃሚ እባቦች በኢትዮጵያ›› መምሪያ መጽሐፍ በገበያ ላይ ውሏል፡፡ በአበበ አመሃ (ዶ/ር) አዘጋጅነት የቀረበው ይህ መጽሐፍ በአራት ክፍሎች የተቀናጀ ነው፡፡

ታሪክ፣ ስያሜና እሴቶች፣ እባብ ነክ እውነታዎች፣ የኢትዮጵያ ጎጂ እባቦች፣ የእባብ ደኅንነት አጠባበቅ የሚሉ ክፍሎችን ያጠቃልላል፡፡

በመጽሐፉ በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙ የእባብ ዓይነቶችና የሚሰጡት ጥቅምና አደገኛ የሆኑ ዝርያዎች በምን መልኩ መለየት እንደሚቻል ተቀምጧል፡፡

ዶ/ር አበበ መጽሐፍን የጻፉበትን ምክንያት ሲገልጹ፣ ለትምህርት ውጭ በነበሩበት ጊዜ የክፍል ጓደኛቸው ኢትዮጵያ ውስጥ ስለሚገኙ መርዛማ እባቦች ለማወቅ በመፈለጓ ነው፡፡

ነገር ግን በወቅቱ ኢትዮጵያ ውስጥ ስለሚገኙ መርዛማ እባቦችም ሆነ መርዛማ ያልሆኑት ተሰንደው ባለመኖራቸው መጽሐፍን እንደጻፉ ይናገራሉ፡፡ የመጽሐፍ ደራሲ እንደተናገሩት፣ ማንኛውም ሕይወት ያለው ፍጡር በራሱ እሴት፣ ሀብት በመሆኑ ብቻ እንዲኖር ማድረግ ይጠበቃል፡፡

በኢትዮጵያ በሌሎች ዓለም የማይገኙ የእባብ ዝርያዎች ጭምር አሉ፡፡ ከእነዚህ የኢትዮጵያ ተራሮች እፉኝት ተጠቃሽ ነው፡፡ 92 የሚደርሱ የእባብ ዝርያዎችም በኢትዮጵያ ይገኛሉ፡፡ ዘጠኝ ያህል ደግሞ በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙ ናቸው፡፡

የኢትዮጵያ ተራራዎች እፉኝትና የባሌ ተራራዎች እፉኝት ከብርቅዬዎቹ ተጠቃሽ ናቸው፡፡ እነዚህ ለቱሪስት መስህብነት አስፈላጊ መሆናቸውን ይገልጻሉ፡፡

የሰፊው ማኅበረሰብ ህልውና በሆነው ግብርናው ዘርፍ እባብ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ይነገርለታል፡፡ በማሳዎች በስፋት እህል በመብላት የገበሬውን ሥራ ለሚያመክኑ አይጠ መጎጥና ሌሎች እንስሳት አድኖ በመብላት ትንሽ የሚመስል ነገር ግን ትልቅ ችግር የሚቀርፍ እንደሆነ ተገልጿል፡፡

እባብ ሥጋ በል ወይም ሕይወት ያላቸውን እንስሳት ተመጋቢ በመሆኑ በአርሶ አደሮች ማሳዎች አካባቢ የሚገኙ እህል አውዳሚዎችንና እንቁላሎችን በማደን ይመገባል፡፡

እህል የሚያወድሙ ትናንሽ እንስሳትን የሚቆጣጠር ሥነ ሕይወታዊ የሆነ የመቆጣጠሪያ መንገድ እባብ እንደሆነ ዶ/ር አበበ ይገልጻሉ፡፡ የግብርና ምርትን ከመጠበቅ አንፃር ትንሽ የማይባል አስተዋጽኦ እንዳለውም ያክላሉ፡፡

በተለያዩ ምክንያቶች እንደ መጥፎ ከሚነገርላቸው እባቦች ኢትዮጵያ ማግኘት ያለባትን ጥቅም እያገኘች እንዳልሆነ ያብራራሉ፡፡

ለዚህም ብዙዎቹ ተናዳፊና ተናካሽ ናቸው ተብሎ መታመኑን ሁሉም በፍርሃት እንዲሸሻቸውና እንዲገድላቸው ማድረጉ አሉታዊ ተፅዕኖ አድርጓል፡፡

ኢትዮጵያ በእባቦች በኢኮኖሚ ደረጃ ይኼ ነው የተባለ ጥቅም እንደማታገኝ የሚገልጹት ዶ/ር አበበ፣ ሌሎች አገሮች ቆዳቸውን ለጌጣጌጥ፣ መርዛቸውን ለመድኃኒትነት እንደሚጠቀሙት ያስረዳሉ፡፡ በአንዳንድ አገሮች ከእባብ ጋር ትርዒት በመሥራት ለቱሪስት መስህብነት ይጠቀማሉ፡፡ መርዛማ የሆኑ እባቦችን ከመግደል ይልቅ መርዙን ብቻ ጨምቀው እያወጡ እጅግ ውድ በሚባል ዋጋ እየሸጡ የሚገኙ አገሮችም እንዳሉ ይናገራሉ፡፡

በቻይናና በምዕራብ እስያ አካባቢ እባብ በብዛት አርብተው የሚሸጡ እንዳሉ የጠቆሙት ዶ/ር አበበ፣ እንደ አንድ የግብርና ሥራም እንደሚቆጠር ያስረዳሉ፡፡ በኢትዮጵያ ብቻ ይገኛሉ ከተባሉ ብርቅዬ የእባብ ዝርያዎች አንዱ የኢትዮጵያ የተራራ እፉኝት ከኢትዮጵያ በተለያዩ ጊዜያት በሕገወጥ መንገድ ወጥቷል፡፡

‹‹ዝርያው ከኢትዮጵያ የወጣው እባብ እዚያው በውጭ አገሮች ዝርያዎቻቸውን እያረቡ አንድ የኢትዮጵያ የተራራ እፉኝትን ከ1,500 ዶላር እስከ 2000 ዶላር በኢንተርኔት ላይ ሲዋዋሉ አይቻለሁ፤›› ብለዋል፡፡

ለዚህም አርቢዎቹ የተለያዩ የምግብ ዓይነቶች እየመገቧቸው የሚያመነጩት መርዝ የተለያየ የኬሚካል ውህድ እንዲኖረው እንደሚያደርጉ ይህም ተፈላጊነቱን ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ የዚህ ዓይነት የእባብ ዝርያ ዥጉርጉርና መለኩ የተለየ ነው፡፡

እባብ በመኖሪያ አካባቢ፣ በጉዞና በእያንዳንዱ እንቅስቃሴ ሊያጋጥም ስለሚችል በአካባቢው የሚገኙ የእባብ ዝርያዎችና ዓይነታቸውን ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ የት አካባቢ የትኞቹ የእባብ ዓይነቶች ይገኛሉ፣ ድንገት እባብ ቢያጋጥም ምን ዓይነት ዕርምጃ መውሰድ ይገባል የሚለውን ማንኛውም ሰው ግንዛቤ ቢኖረው ይመከራል፡፡

እባቦች የጭንቅላታቸው ቅርፅ ሦስት ማዕዘን ከሆነ ማርዛማ ሊሆኑ እንደሚችሉ ይገመታል፡፡ ዘንዶ ከሆነ የዳይመንድ ቅርፅ ይኖረዋል፡፡ አንዳንዴ ጎጂ የማይመስሉ ነገር ግን ጎጂ የሆኑ የእባብ ዝርያዎች ሊኖሩ ይችላል፡፡ በዓለም ላይ ስድስት ዓይነት ጎጂ የእባብ የመለያ ዓይነቶች አሉ፡፡

የመጀመርያው የጭንቅላት ቅርፅ ሲሆን፣ የዓይናቸው ብሌን ሞላላ፣ በላይኛው የአፋቸው ክፍል ሁለት ጥርስ ያላቸው ከሆኑ መርዛማ መሆናቸውን ያሳያል፡፡ አንድ ሰው በሚነክሱበት ወይም በሚነድፉበት ወቅት መርዙን በቀጥታ በጥርሳቸው አማካይነት ወደ ሰውነት ያስገባሉ፡፡ ጥርሱ የሚያደርሰው ጉዳትም እንደ እባቡ የመርዝ ዓይነት የሚለያይ ሲሆን፣ አንዳንዱ ነርቭና ጡንቻ የሚጎዳ፣ የደም ሥርዓትን የሚጎዱና እስከመግደል ሊያደርሱ የሚችሉ ናቸው፡፡ አልፎ አልፎ የአካል ጉዳት የሚደርሱም እንዳሉ ጠቁመዋል፡፡

የጅራት ቅርፊቶች ነጠላ፣ ድርድርና ደማቅ የአካል ቀለም ካላቸው መርዛማ የመሆን ዕድላቸው ከፍ ይላል፡፡ በዓለም በየዓመቱ 5,400,000 ሰዎች በእባብ ሲነደፉ ከእነዚህ 2,700,000 ሺሕ ያህሉ ይመረዛሉ፡፡

በአማካይ 100 ሺሕ ሰዎች ደግሞ በእባብ ንድፊያ ሕይወታቸውን እንደሚያጡ ይናገራሉ፡፡

በኢትዮጵያ በርካታ ጎጂ እባቦች በገጠራማ ቦታዎች እንደሚኖሩ፣ በዚህም በተለይ አርሶ አደር፣ አርብቶ አደር፣ አዳኞች፣ አሣ አስጋሪዎች፣ ወታደሮች፣ የጤና ባለሙያዎች፣ መምህራን፣ አገር ጎብኚዎችና የመስክ ሠራተኞች ለእባብ ጥቃት ተጋላጭ እንደሚሆኑ ይጠቁማሉ፡፡

የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የ2004 ዓ.ም. መረጃ እንደሚያሳየው፣ በኢትዮጵያ የሚገኙ 10,530 የጤና ተቋማት መካከል ከአዲስ አበባ ውጭ በሚገኙ 76 ላይ የእባብ ጥቃት ተጋላጭነትን በሚመለከት ለአሥር ወራት ጥናት ተደርጓል፡፡

በየዓመቱ በእባብ ንድፊያ የሚጠቁ ሰዎች 130 ሺሕ እንደሚደርሱ ተመዝግቧል፡፡ ሆኖም መሠረተ ልማት ባልገባባቸው አካባቢዎችና የባህል ሕክምና በሚበዛበት አካባቢ የእባብ ንድፊያ በባህላዊ ሕክምና ስለሚታከም አሃዙን በትክክል ማግኘት አይቻልም፡፡

አንዳንድ ኮብራ እባቦች ሳይነክሱና ሳይናደፉ በሦስት ሜትር ርቀት ላይ ያለውን ሰው ወይም እንስሳት ዓይን ብቻ በማየት አነጣጥረው መርዛቸውን ዓይን ላይ ሊረጩ ይችላሉ፡፡

ዶ/ር አበበ እንደሚሉት፣ ሰዎች በተለያዩ አካባቢዎች ሲጓዙ አካባቢውን ከሚያውቁ ሰዎች ጋር እንዲጓዙ ይመከራሉ፡፡ ይህ ከእባብ ብቻ ሳይሆን ከሁሉም ሥጋት ለመጠበቅ ያስችላል፡፡ ልጆችን ብቻቸውን አለመተው፣ ጠንከር ያለ ጫማ መጫማትም አስፈላጊ ነው፡፡ በተለይም የመስክ ጉብኝት የሚያደርጉ ሰዎች መጠንቀቅ አለባቸው፡፡ በዋናነት ስለሚሄዱበት አካባቢ አደገኛ እንስሳቶች መረጃ ወይም ግንዛቤ መያዙ ከሚመጣው ችግር ራስን ለመጠበቅ ያስችላል፡፡

የአንዳንድ እባቦች መርዝ አንዷ ጠብታ እስከ 20 ሰው ሊገድል ይችላል፡፡ ይህ አንድ ጠብታ በአንድ ሰው ውስጥ ሲገቡ ሞቱን ያፋጥነዋል፡፡ ስለሆነም ለእባብ ንድፊያ መጀመርያ ዕርዳታ የሚሆነው የተነደፈው ሰው እንዲረጋጋ ማድረግና የተነደፈውን የሰውነት ክፍል እንዳይጨናነቅና እንዳይንቀሳቀስ ማድረግ ነው፡፡ በተለይም የተነደፈው ሰው አቅራቢያው ወደሚገኝ የጤና ተቋም መውሰድ በይበልጥ ይመከራል፡፡

ዶ/ር አበበ አምሃ በባህር ሥነ ሕይወትና አሣ ሀብት ልማት ከአስመራ ዩኒቨርሲቲ፣ በሥነ እንስሳት፣ በሥነ ምኅዳር አወቃቀርና ዝምድና ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በዘረመል ሥነ ምድርና ሥነ እንቁራሪት ስዊዘርላንድ በሚገኘው ባዝል ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል፡፡ አደገኛና ጠቃሚ እባቦች በኢትዮጵያ የሚል የግንዛቤ ማስጨበጫ መጽሐፍም ለንባብ አብቅተዋል፡፡

መጽሐፍ በዋናነነት የሚያጠነጥነው በኢትዮጵያ ስለሚገኙ የእባብ ዓይነቶች ነው፡፡ በተለይም ለአገር መከላከያ ሠራዊት፣ ጤና ባለሙያዎች፣ ለመንግሥት ሠራተኞችና ሌሎችም ሰዎች እንደ መማሪያ እንዲያገለግል መሆኑን ዶ/ር አበበ ይገልጻሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ የካቤኔ አባል የሆኑት አንድ ከፍተኛ ባለሥልጣን የሚያቀርቡትን ቅሬታ እያዳመጡ ነው] 

ክቡር ሚኒስትር እየሆነ ያለው ነገር በእጅጉ ስላሳሰበኝ ነው በአካል...

የአፍሪካ ኅብረት ጉባዔና የሶማሊያ ፕሬዚዳንት የፈጠሩት አምቧጓሮ

ባለፈው ቅዳሜና እሑድ በአዲስ አበባ የተካሄደው የአፍሪካ ኅብረት 37ኛው...

የብሔራዊ ባንክ የገንዘብ ፖሊሲ ትግበራ የፈጠራቸው አሉታዊና አዎንታዊ ጎኖች

የአገሪቱ ንግድ ባንኮች በዓመት የሚሰጡት የብድር መጠን ላይ የኢትዮጵያ...

ቱግ ቱግ!

የአፍሪካ ኅብረት ጉባዔ ለመታደም የመጡ እንግዶችን ሸኝተን ከፒያሳ ወደ...