Sunday, May 26, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ኪንና ባህል‹‹ከእኔ እስከ ቤቴ›› ሥዕል በድሪቶ

‹‹ከእኔ እስከ ቤቴ›› ሥዕል በድሪቶ

ቀን:

ኢትዮጵያን በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ፣ በማኅበራዊና በሃይማኖታዊ ዘውግ ቀድሞ የነበረውን ከአሁኑ ዘመን ጋር ያዋጀ የሥዕል ዓውደ ርዕይ ነው፣ ‹‹ከእኔ እስከ ቤቴ››፡፡  አገር፣ ቤተሰብና ግለሰብ የሚገልጸው፣ ‹‹ከእኔ እስከ ቤቴ›› በሚል ስያሜ የቀረበው የሥዕል ዓውደ ርዕይ ከኅዳር 28 እስከ ታኅሣሥ 23 ቀን 2013 ዓ.ም. ለተመልካች ክፍት ሆኗል፡፡

በሠዓሊ ኪሩቤል መልኬ ከቀረቡትና ቁርጥራጭ ጨርቅ (ድሪቶ) ከተሠሩ ሥራዎች ውስጥ በዓለም ከእውነት ይልቅ ሐሰት መንገሡን የሚያስረዳ ሥዕል ይገኝበታል፡፡ በዚህ ሥዕል ላይ ነጠላው ተዘቅዝቋል፣ እንደ አገሬው ነጠላ የሚዘቀዘቀው ሐዘን ለማሳየት ነው፡፡ ማን ነው ያዘነው? እውነት ያለው ሰው፣ ማኅበረሰብ ወይም ደግሞ አገር ሊሆን ይችላል፡፡ ሐሰት በዝቶ እውነቱ ሲዋጥ፣ ሰው የሆነ ሰው ያዝናል፡፡ ሐዘኑን የሚገልጸው ደግሞ ልክ እናቶች ሐዘን ቤት ሲሆኑ ነጠላ እንደሚዘቀዝቁት በሥዕሉም ሐሰት በመንገሡ ነጠላው ተዘቅዝቋል፡፡  

በሌላ በኩል ከእውነት ይልቅ ሐሰት ነግሦ እውነት ሲከስም፣ ሐሰት ሲወደስ የሚያሳይ ሥዕል ነው፡፡ ነጠላውም ቢሆን አብዛኛውን ማኅበረሰብ ኑሮ የሚያሳይ ነው፡፡ እናቶች ነጠላቸው ሲቀደድባቸው እንደሚያስጥፉት (እንደሚያበጁት) ዓይነት ብዙዎቹ ሥዕሎች በዚያ ውስጥ ያለፉ ናቸው፡፡

- Advertisement -

በአሊያንስ ኢትዮ ፍራንሴስ ሥራውን ያቀረበው ሠዓሊ ኪሩቤል፣ ሥራዎቹ ከእርሱ ጋር ከጎረቤት፣ ከቀዬ፣ አጠቃላይ ከማኅበረሰቡ፣ ከፍ ሲልም እንደ አገር ያለውን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ የሚያሳዩ ናቸው፡፡

በመግቢያው ላይ ለጎብኚ ዓይን ጎላ ካሉ ሥራዎች አንዱ ስያሜ ያልተሰጠው ሥዕል ይገኝበታል፡፡ በጂንስ ቁርጥራጭ የተሠራው በርና የቤቱ ጣሪያ ደግሞ በአገሬው ጥለት ተወክሏል፡፡ ልክ እንደ ሌሎቹ ጣሪያው የተዘቀዘቀ ጥለት ነው፡፡ ግድግዳውም ቢሆን በተጣፉ (በተሰፉ) ነጠላዎች ተመስሏል፡፡

የተቆለፈው ደጃፍ ‹‹እንኳን ደህና መጡ›› (welcome) ተብሎበታል፡፡ በዋነኛነት ቃል የሚገቡ ነገር ግን ተፈጻሚ የማይሆኑ ተስፋዎችን የሚያሳዩ ናቸው፡፡

በተለያዩ የአገር ልብስና ጂንስ የተሠሩት እነዚህ ሥዕሎች የተለዩ ጉዳዮችን በተለያዩ ቦታዎች የሚያሳዩ ናቸው፡፡ ሥዕሎቹ ከጨርቅ መሠራታቸው በፊት ያለፈውና አሁን ያለውን የአለባበስ ሒደት በተወሰነ መልኩ አንፀባርቋል፡፡

የሙያ ዘርፎችን በአንድ ላይ የሚገልጸው ‹‹ጋወን›› ሌላው ዕይታ የሚስበው ሥራው ነው፡፡ የጋወን ቁልፎች ውስጥ አንዱ የተለየ ሲሆን፣ ሁሉም ተቆልፎ የተለየው ጋር ክፍተት አለው፡፡  

መምህር፣ የጤና ባለሙያዎች በአጠቃላይ ለተለያዩ ሙያዎች ምሳሌነት የሚውለው ጋወን በሠዓሊው ከቀረቡት ውስጥ ተካቷል፡፡ ብዙ የሚያውቁ ባለሙያዎች ክፍተቶቻቸውንና ድክመቶቻቸውን ለአፍታ ከማየት ይልቅ እነሱ የሚሉት ልክ፣ እውነት፣ ሀቅ መሆኑን የሚቀበሉ መኖራቸውን የሚያሳይ ነው፡፡ ይህ አሁን ያለው በሚዲያ ተሰሚ የሆኑትና አንዳንድ ሰዎች የሚሉትን ማጤን እንዳለብን የሚመክር ነው፡፡

አንዳንዶቹ ሥዕሎች ስያሜ አላቸው፡፡ ሌሎቹ ደግሞ ስያሜ ያልተሰጣቸው ናቸው፡፡ ‹‹እናትና ልጅ›› በሚል ስያሜ የተሠራው ሥዕል ሃይማኖትን ይገልጻል፡፡ ለማን ማልበስ (መስጠት) እንዳለብን እንደማናውቅ የሚያስረዳ ነው፡፡

ከሃይማኖት ስንነሳ በአሁኑ ጊዜ የሃይማኖት ተቋም ትኩረታቸው ሕንፃ መገንባት እንጂ የሰው ሰብዕና፣ ሥነ ምግባር ጥሩ ማንነት ላይ ትኩት እንደሚያደርጉ የሚያስረዱ ናቸው፡፡

በሌላ በኩል ሰዎች ሁሉ ከሕይወታቸው ማጥፋት የሚፈልጉት ገጽ (ታሪክ) መገንጠል (መቅደድ) ይኖራቸዋል፡፡ በ‹‹ጠረጴዛው ላይ›› የሚል ስያሜ የተሰጠው ሥዕል በሕገ መንግሥቱ ያለውን አንቀጽ 39 ገፅ ተቀዶ ይታያል፡፡ የዚህ ሥዕል ዕሳቤ ምንም እንኳን የአብዛኛው ሰው ሐሳብ የሚቀበለው ቢሆንም በግለሰብ ደረጃ ትርጉም እንዲሰጥ የተሠራ ነው፡፡ ሁሉም ሰው ከሕይወት ውስጥ ቀዶ (ገንጥሎ) ማንሳት የሚፈልገው መጥፎ አሻራ እንዳለው የሚገልጽ ነው፡፡

‹‹ከሞኝ ደጃፍ ሞፈር ይቆረጣል›› በዓውደ ርዕዩ ከቀረቡ ሥዕሎች አንዱ ነው፡፡ ሐሳቡ የተገለጸው ልክ እንደሌሎቹ ሥዕሎች በድሪቶዎች ነው፡፡ ሰዎች ሰውነታቸውን በልብስ ይሸፍናሉ፡፡ ሲቀደድባቸው ያስጥፋሉ (ያሰፋሉ) አቅም ያለው ይጥላል፡፡ አቅም የሌለው ደግሞ ጠግኖ ይለብሳል፡፡ በጠቅላላው ምናልባትም በልብስ የተደበቁ ብዙ ማንነትን የሚያስቃኙ መሆኑን የሚያስረዳ ነው፡፡

የብዙዎች ኢትዮጵያውያን አኗኗርና ሒደት፣ ፖለቲካ፣ ሃይማኖት ዞር ተብሎ እንዲቃኝ የሚያግዝ ዓውደ ርዕይ ያዘጋጀው ሠዓሊ ኪሩቤል ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አለ የሥነ ጥበብና ዲዛይን ትምህርት ቤት በ2005 ዓ.ም. በቀለም ቅብ ትምህርት ክፍል የመጀመረያ ዲግሪውን አግኝቷል፡፡

ሁለተኛው ሥራ የሆነው ‹‹ከእኔ እስከ ቤቴ›› የተሰኘው የሥዕል ዓውደ ርዕይ የቀረበው በኪልት አርት ነው፡፡ ሠዓሊ ኪሩቤል እንደተናገረው፣ በተለያየ ወቅት የቡድን የሥዕል ዓውደ ርዕይ ያቀረበ ሲሆን፣ በአገር ውስጥና ከአገር ውጪም ሥራዎቹን አቅርቧል፡፡

‹‹ከእኔ እስከ ቤቴ›› ሁለተኛው ሥራው ነው፡፡ እያንዳንዱ ግለሰብ አሁን ያለውን አገራዊ ሁኔታ በድጋሚ ቆም ብሎ እንዲያስብ የሚያስችል ሥራ መሆኑን ያስረዳል፡፡ ምንም እንኳን በስያሜው የተሠራ ሥዕል ባይኖርም ሐሳቦቹ ሠዓሊው ሌሎችን ከሚያይበት ይልቅ ከሌሎች ጋር ያለውን ቀረቤታ የሚያሳይ ሥዕሎችን ይዞ መቅረቡን ያብራራል፡፡

ይኼ ሐሳብ ለሠዓሊው ብቻ ሳይሆን ሁሉም ሰው ሥራዎቹን ሲመለከት ያለበትን ቦታ እንዲያስተውል የሚጋብዝ ነው፡፡ ከቤት፣ ከቀዬው የሚታዩ፣ የሚሰሙ፣ የሚነገሩ ሐሳቦች፣ እውነቶችና ትርክቶችን በአንድ ላይ የሚያሳይ ነው፡፡

የሥዕል ሥራዎቹን ለሁለተኛ ጊዜ ያቀረበው ሠዓሊ ኪሩቤል፣ በውስጡ የነበረው በጨርቃ ጨርቅ (Quilt Art)  ሐሳብን የመግለጽ ሥዕል ላይ ትኩረት አድርጓል፡፡

ሠዓሊ ኪሩቤል እንደሚናገረው፣ የዚህ ሥዕል ዓይነት በተለያዩ የኑሮ ሒደት ውስጥ ያለ ቢሆንም፣ ወደ መድረክ አልወጡም፡፡ ከእናቱ የልብስ ስፌት ሙያ በመቅሰምና በዕለት ተዕለት ሒደት ውስጥ አዳብሮት ለዚህ እንደበቃ ይናገራል፡፡

በኢትዮጵያ ትልቁ ተግዳሮት ለሥዕል የሚሰጠው ትኩረት አናሳ በመሆኑ ዘርፉ መድረስ ያለበት ደረጃ እንዳይደርስ ማድረጉን ብዙዎች ይናገራሉ፡፡ ከትምህርት ቤት ውጪ ሥዕል የማይታይበት ሁኔታ እየተለወጠ መጥቶ በእንጦጦ ላይ የሥዕል ዓውደ ርዕይ ማሳያ መከፈቱ የሚበረታታ መሆኑን ይገልጻል፡፡

በአዲስ አበባ ሁለት ቦታዎች ላይ የሥዕል ማሳያ ጋለሪዎች ሊከፈቱ መሆኑን መስማት ሠዓሊዎችን የሚያበረታታ መሆኑን ሠዓሊ ኪሩቤል ለሪፖርተር ተናግሯል፡፡

መንግሥት ጋለሪዎችን ከመክፈት በተጨማሪ በትምህርት ፖሊሲ ላይ ልጆችን ማስተማርና የሚሠሩ ፕሮጀክቶች ላይ የሥዕል ማሳያ ቦታን እንዲያስብበት ይመክራል፡፡

የሌሎች አገሮች ተሞክሮ እንደሚያሳየው፣ የተለያዩ ግንባታዎች ሲከናወኑ ለሥዕል ማሳያ ቦታ ማካተት ግዴታ ነው፡፡ ይህም ማኅበረሰቡ ለሥዕል ያለው ቦታ ከፍተኛ በመሆኑ ከዘርፉ ሠዓሊዎች ብቻ ሳይሆኑ ተጠቃሚ የሆኑ አገሮች መኖራቸውን ይገልጻል፡፡

ለሥዕል የተሰጠው ትኩረት አናሳ በመሆኑ በዘርፉ የተሠማሩትም ሆነ ኢትዮጵያ ተጠቃሚ አልሆኑም፡፡ አገር ውበት እንዲኖረው፣ የሥራ ተነሳሽነት እንዲጨምር በሚሠሩት ሕንፃዎች፣ የመንገድ ላይ ቅቦችና ሌሎች መሠረተ ልማቶች ላይ የሠዓሊዎች ዕይታና ሥራዎች   ቢታከልበት ለዕይታ የሚማርክ ሀገር መገንባት ያስችላል፡፡

የተለያዩ መለያዎችን (ብራንዶችን) መሥራት፣ ከባህል፣ ከአየር ሁኔታና ከአኗኗር ጋር የሚስማሙ ግንባታዎችን የሚወክሉ ቀለሞችን መምረጥ ላይ ለሚታዩ ክፍተቶች የሥዕል ዕውቀቱ አለመኖር ሚና ተጫውቷል፡፡

እንደ ሠዓሊ ኪሩቤል፣ በመንግሥት ደረጃ ትኩረት ተሰጥቶት መሠራት ካለባቸው ዘርፎች የሥዕል ዕውቀት ይዞ የሚያድግ ማኅበረሰብ መፍጠር አንዱ ሊሆን ይገባል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የፋይናንስ ኢንዱስትሪው ለውጭ ባንኮች መከፈት አገር በቀል ባንኮችን ለምን አስፈራቸው?

የማይረጥቡ ዓሳዎች የፋይናንስ ተቋማት መሪዎች ሙግት ሲሞገት! - በአመሐ...

የምርጫ 97 ትውስታ!

በበቀለ ሹሜ      መሰናዶ ኢሕአዴግ ተሰነጣጥቆ ከመወገድ ከተረፈ በኋላ፣ አገዛዙን ከማሻሻልና...

ሸማቾች የሚሰቃዩት በዋጋ ንረት ብቻ አይደለም!

የሸማች ችግር ብዙ ነው፡፡ ሸማቾች የሚፈተኑት ባልተገባ የዋጋ ጭማሪ...

መንግሥት ከለጋሽ አካላት ሀብት ለማግኘት የጀመረውን ድርድር አጠናክሮ እንዲቀጥል ፓርላማው አሳሰበ

የሦስት ዩኒቨርሲቲዎች ፕሬዚዳንቶች በኦዲት ግኝት ከኃላፊነታቸው መነሳታቸው ተገልጿል አዲስ አበባ...