አካል ጉዳተኞች መብታቸው ተጠብቆ ሥራ እንዲሠሩ ቢደረግም፣ ያላቸውን አቅም እንዲጠቀሙ ለማድረግ የሚያነሳሳ ተቋም ግን ብዙም አይታይም፡፡ የአካል ጉዳተኞች የሥራ ላይ መብት አዋጅ 568/2000 ፀድቆ ወደ ሥራ ቢገባም፣ ችግሩ ግን አልተቀረፈም፡፡ ችግሩን ለመፍታት ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማኅበር ፌዴሬሽን በጋራ ተቀናጅተው እየሠሩ ይገኛል፡፡ አቶ ዓባይነህ ጉጆ የኢትዮጵያ የአካል ጉዳተኞች ፌዴሬሽን ዋና ዳይሬክተር ናቸው፡፡ ጉዳዩን በተመለከተ ተመስገን ተጋፋው አነጋግሯቸዋል፡፡
ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማኅበራት ፌዴሬሽን እንዴት ተመሠረተ?
አቶ ዓባይነህ፡- የኢትዮጵያ አካል ጉደተኞች ማኅበራት ፌዴሬሽን በ1986 ዓ.ም. አራት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ማኅበራት አንድ ላይ በመሆን ያቋቋሙት ነው፡፡ ማኅበራቱ የዓይነ ሥውራን ብሔራዊ ማኅበር፣ የሥጋ ደዌ ተጠቂዎች ማኅበር፣ የእንቅስቃሴ እክል ያለባቸው አካል ጉዳተኞች ማኅበርና መስማት የተሳናቸው ብሔራዊ ማኅበር ናቸው፡፡ እስካሁን ድረስ አንድ ላይ በመሆን ያሉትን ችግሮች ለመፍታት እየሠራን እንገኛለን፡፡ በተለይም መንግሥት የትኛውም ቦታ ላይ የምንሳተፍበትን እንዲያመቻችልን እያደረግን ነው፡፡ በሥራ በኩልም ማንኛውም አካል ጉዳተኛ ተሳታፊ እንዲሆን ጥረት እያደረግን እንገኛለን፡፡
ሪፖርተር፡- ማኅበሩ ምን ዓይነት አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል?
አቶ ዓባይነህ፡- ማኅበሩ በዋናነት እየሠራ ያለው የአካል ጉዳተኞችን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮቻቸውን ለመፍታት ነው፡፡ ፖለቲካን ጨምሮ በተለያዩ ዘርፎች ተሳታፊ እንዲሆኑ እየሠራን ነው፡፡ መንግሥትንም በሕግ ጉዳዮች ላይ በማማከር እንዲሁም ደግሞ አስቸኳይ አገራዊ ችግሮች በሚነሱበት ጊዜ ከመንግሥት ጎን በመቆም የአካል ጉዳተኞች ማኅበራትን የሚያስተባብር ነው፡፡ የተለያዩ ፖሊሲዎች በሚወጡበት ጊዜ መንግሥትን በማማከር በኩል ሰፊ ሥራ እየተሠራ ይገኛል፡፡ በማኅበረሰቡ ዘንድ ሥር ሰዶ የቆየውን ስለ አካል ጉዳተኝነት ያለው የተሳሳተ ግንዛቤ እንዲቀየር ለማድረግ ሌት ተቀን እየሠራን ነው፡፡ ኢትዮጵያም ከምትከተለው እኩል የሥራ ዕድል መርህ ጋር በተያያዘ የተለያዩ ሥራዎችን ሠርተናል፡፡ ለአካል ጉዳተኞችም ምቹ የሥራ ሁኔታ ለመፍጠር እየሠራን ነው፡፡ ይሁን እንጂ በአንዳንድ ቦታዎች ላይ ችግሩ ይታያል፡፡ አካል ጉዳተኞች በሥራ ላይ የሚሳተፉበት መንገድ የተመቻቸ፣ ሰብዓዊ መብታቸው የተጠቀ እንዲሆን አዋጅ 568/2000 ተደንግጎና ፀድቆ ወደ ሥራ ገብቷል፡፡ ይህም አካል ጉዳተኞች መብታቸው ተጥብቆ ሥራ እንዲሠሩ ያደርጋል፡፡ አካል ጉዳተኞችም ያላቸውን አቅም መጠቀም እንደሚችሉ ግንዛቤ ይሰጣል፡፡
ሪፖርተር፡- ለአካል ጉዳተኞች የተመቻቸ ሁኔታ ከመፍጠር አኳያ ምን ሠርታችኋል?
አቶ ዓባይነህ፡- ማኅበረሰቡ ስለ አካል ጉዳተኞች ያለውን አመለካከት መቀየር ዋናው ሥራችን ነው፡፡ አመለካከት ላይ ለውጥ ካመጣን ብዙ ነገሮችን መፍታት ይቻላል፡፡ ከማኅበራዊና ከኢኮኖሚያዊ ችግሮችም ተላቀው እንዲኖሩ ከማስቻል አንፃር ሰፊ ሥራዎችን እየሠራን ነው፡፡ ማኅበሩ ከተመሠረተ ጊዜ ጀምሮ ብዙ ሥራዎችን እየሠራ ነው፡፡ በዋናነት ከእነዚህ የዓለም አቀፍ መብቶች ጥበቃ ኮንቬንሽን ይገኝበታል፡፡ ለዚህም ከአሥር ዓመት በፊት መንግሥት በአዋጅ አፅድቆ ወደ ሥራ እንዲገባ ግፊት ማድረጋችን ይጠቀሳል፡፡ የአካል ጉዳተኞች የሥራ ሥምሪት አዋጅ የሕንፃና የቀረጥ ነፃ አዋጆችንም በማፅደቅ በሥራ ላይ እንዲውሉ ማኅበሩ ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ በዚህ መሠረትም አካል ጉዳተኞች በሁሉም ዘርፍ እንዲሆኑ ማድረግ ችለናል፡፡ አካል ጉዳተኝነት ሁሉም ሰው በኪሱ ይዞት የሚዞረው መሆኑን አውቆ፣ አካል ጉዳተኞችን በየዘርፉ ማሳተፍ ያስፈልጋል፡፡
ሪፖርተር፡- በማኅበሩ ላይ በአካል ጉዳተኞች ምን ዓይነት ችግሮች አሉ? ችግሩን ለመፍታት ምን ታደርጋላችሁ?
አቶ ዓባይነህ፡- በማኅበሩ ላይ ይህንንም ያህል ችግር የለም፡፡ ነገር ግን በማኅበራት ላይ የአቅም ውስንነት ይታያል፡፡ በሚፈለገው ልክም እየሠሩ አይደለም፡፡ እንደ አጠቃላይ ግን አካል ጉዳተኞች በበቂ ሁኔታ የትምህርት ዕድል አለማግኘትና ለአካል ጉዳተኞች ተደራሽ የሚሆኑ የሕንፃ ግንባታዎች ያለመኖሩ እንደ ትልቅ ችግር የሚታይ ነው፡፡ ብዙ ጊዜም የሚሠሩ ሕንፃዎች አካል ጉዳተኞችን ያማከሉ አይደሉም፡፡ ችግሮቹን ለመፍታት ከመንግሥትም ጋር ሆነ ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በቅርብ ብንወያይም መፍትሔ ማግኘት አልተቻም፡፡ በሕግ ማዕቀፍ ላይም ተካትቶ እንዲሠራ ብናደርግ በማኅበረሰቡም ሆነ በመንግሥት ዘንድ ትኩረት ማግኘት አልቻልንም፡፡ የአካል ጉዳተኞች ዋነኛ ችግር የሆነው በኅብረተሰቡ ዘንድ ያለው የግንዛቤ ችግር ነው፡፡ ይህ ከተቀረፈና በሥራ ሥምሪት ጊዜ አካል ጉዳተኞች ተሳታፊ ከሆኑ ትልቅ ቦታ መድረስ ይቻላል፡፡
ሪፖርተር፡- ለአካል ጉዳተኞች ምን ዓይነት ድጋፍ ታደርጋላችሁ?
አቶ ዓባይነህ፡- በኢትዮጵያ በአጠቃላይ ከ20 ሚሊዮን በላይ የአካል ጉዳተኞች ይገኛሉ፡፡ ነገር ግን በየማኅበራቱ ሄደው የሚመዘገቡ አካል ጉዳተኞች ቁጥር አነስተኛ ነው፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ያለባቸውን ችግር ለመፍታት በቂ ባይባልም ድጋፍ የምናደርግ ይሆናል፡፡ በየማኅበራቱ ያሉ የአካል ጉዳተኞችም የተለያዩ ድጋፎች ይደረግላቸዋል፡፡ መንግሥትም የአካል ጉዳተኞች ጉዳይ ያገባኛል በማለት በአሁኑ ወቅት ሰፊ ሥራ እየሠራ ይገኛል፡፡
ሪፖርተር፡- የሥራ ዕድል የሚያገኙበት መንገድ እንዴት ነው?
አቶ ዓባይነህ፡- ለአካል ጉዳተኞች የሥራ ዕድል የሚያገኙት መንገድ በጣም ጠባብ ነው፡፡ አሁን ያለው ሁኔታም የሥራ ሥምሪት አዋጁና አካል ጉዳተኞች ያሉበት ሕይወት የተመጣጠነ አይደለም፡፡ አዋጁ የወጣበት ዋነኛ ምክንያት የአካል ጉዳተኞችን ችግር ለመቅረፍ ቢሆንም፣ ብዙም እየተሠራበት አይደለም፡፡ አካል ጉዳተኞች የተመቻቸ ሁኔታ ከተፈጠረላቸው ብዙ መሥራት የሚችሉ ናቸው፡፡ እንደ ምሳሌነት የሚጠቀሱና በዓለም አቀፍ ደረጃ ትልቅ ሥራ የሠሩ አካል ጉዳተኞች አሉ፡፡ እነዚህንም በመመልከት ብዙ የአካል ጉዳተኞች አቅማቸውን በማውጣት እየሠሩ ነው፡፡ እንደዚህ ዓይነት ነገርንም መንግሥት በመደገፍ ዋና ተዋናይ በመሆን የአካል ጉዳተኞችን ስሜት ማዳመጥ ያስፈልጋል፡፡
ሪፖርተር፡- ለአካል ጉዳተኞች የሚውሉ ግብዓቶችን እንዴት ታገኛላችሁ?
አቶ ዓባይነህ፡- ኢትዮጵያ እያደጉ ካሉ አገሮች ተርታ የምትመደብ በመሆኗ፣ ለአካል ጉዳተኞች የሚውል ግብዓት በቀላሉ ለማግኘት የምንቸገር ይሆናል፡፡ ይሁን እንጂ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር የተለያዩ ፕሮጀክቶችን በመቅረፅ፣ በገቢ ማሰባሰብ ገንዘብም ሆነ ቁሳቁሶችን እያገኘን ነው፡፡ መንግሥትም በየዓመቱ በሚያደርግልን ዓመታዊ በጀት ግብዓቶችን እንገዛለን፡፡ ኤጀንሲዎችም የተለያዩ ግብዓቶችን በማቅረብ አካል ጉዳተኞችን በመታደግ ላይ ናቸው፡፡ የአቅርቦቱ ሁኔታ በየማኅበራቱ የሚለያይ ነው፡፡ ብዙ ጊዜም ከግብዓትና ከአቅርቦት አንፃር ብዙም ችግር የለም፡፡ ትልቅ ችግር የሆነው ማኅበሰቡ ስለአካል ጉዳተኞች ያለው አመለካከት አናሳ መሆኑ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ማኅበሩ በቅንጅት ከማን ጋር እየሠራ ነው?
አቶ ዓባይነህ፡- የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማኅበራት ፌዴሬሽን ከሁሉም ሚኒስቴሮች ጋር ተቀናጅቶ እየሠራ ነው፡፡ ምክንያቱም ሁሉም መሥሪያ ቤት የአካል ጉዳተኞች ሁኔታ የሚያገባው በመሆኑ ነው፡፡ በቅርበት ግን በአዋጁ መሠረት ሥልጣን የተሰጠው ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ስለሆነ ከእነሱ ጋር ሰፊ ሥራ እየሠራን ነው፡፡ ክልል ላይ አካል ጉዳተኞች ከሚመለከታቸው ማኅበራት ጋር በጋራ እየሠራን ነው፡፡ በተለያዩ ጉዳዮች ላይም ሰፊ ውይይቶችን አድርገናል፡፡ ከዚህም በኋላ የምናደርግ ይሆናል፡፡
ሪፖርተር፡- መንግሥትስ ምን ዓይነት ድጋፍ ያደርግላችኋል?
አቶ ዓባይነህ፡- መንግሥት የአካል ጉዳተኞች ችግር ያገባኛል ብሎ የተለያዩ ነገሮችን ለመፍታት ድጋፍ እያደረገልን ነው፡፡ ነገር ግን እያደረገ ያለው ድጋፍ በቂ የሚባል አይደለም፡፡ የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በየዓመቱ ከአሥር ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ያደርግልናል፡፡ ከዚያ ባሻገር የተለያዩ ዓውደ ጥናቶች የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎችን በማዘጋጀት ለማኅበራት እየሰጠ ይገኛል፡፡ ድጋፉ ሌሎች ባለድርሻ አካላትን የሚመለከት ጉዳይ ስለሆነ ታሳቢ ተደርጎ ሊሠራበት ይገባል፡፡ ተባብረን ከሠራን የአካል ጉዳተኞች ችግር በቀላሉ የሚቀረፍ ይሆናል፡፡
ሪፖርተር፡- ከኮሮና ቫይረስ ጋር ተያይዞ በማኅበሩ ላይ ምን ዓይነት ችግር ነበር?
አቶ ዓባይነህ፡- የኮሮና ቫይረስ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊም ሆነ ማኅበራዊ ችግሮችን አስከትሏል፡፡ በዚህም የተነሳ ዋነኛ ተጠቂ የሚሆኑት የአካል ጉዳተኞች በመሆኑ እነሱ ላይ ሰፊ ሥራ በመሥራት ግብዓቶችን አቅርበናል፡፡ ከ17 ሚሊዮን ብር በላይ ገንዘብ በመመደብ በጣም ለተቸገሩ አካል ጉዳተኞች የተለያዩ ዕርዳታዎችን ሰጥተናል፡፡ አብዛኛውን ጊዜ አካል ጉዳተኞች ለበሽታው ተጋላጭ እንዳይሆኑ የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራዎችን ሠርተናል፡፡ አካል ጉዳተኞች ኑሮን ለማሸነፍ ደፋ ቀና በሚሉበት ጊዜ በሽታው እንቅስቃሴያቸውን ገድቦታል፡፡ ማኅበሩም ይህንን በመገንዘብ ምግብ ነክ አቅርቦት ስናደርግ ነበር፡፡
ሪፖርተር፡- በቀጣይ ምን ለመሥራት አስባችኋል?
አቶ ዓባይነህ፡- ከመንግሥት፣ ከመገናኛ ብዙኃንና ከሲቪል ማኅበረሰቡ ጋር በቅንጀት አብሮ ለመሥራት ዕቅድ ይዘናል፡፡ በተለይም በፖሊሲ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ሰጥተን ለመሥራት የምንንቀሳቀስ ይሆናል፡፡ የአካል ጉዳተኞች ማኅበራትን አቅም ከመገንባት ጋር ተያይዞ ጠለቅ ባለ መልኩ ለመሥራት እንቅስቃሴዎችን ጀምረናል፡፡ አካል ጉዳተኞች ራሳቸው ስለራሳቸው ችግር የሚናገሩ፣ ስለ ራሳቸው ጉዳይ ራሳቸው መሥራት እንዲችሉና ሌላው ጣልቃ እንዳይገባ ለማድረግ እየሠራን ነው፡፡ በየትኛውም ጉዳይ ላይ ተሳትፎ እንዲኖራቸው የሚደረግበትን ሁኔታ ለማስቀጠል እየሠራን እንገኛለን፡፡