Thursday, February 29, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

አረም ነቀላ!

እነሆ ጉዞ ከመገናኛ ኮተቤ። ትናንት ካቆምንበት ልንቀጥል በአዲስ ሞራልና ወኔ ዕፎይ ብለን ልንጓዝ ተነስተናል። በዚህ ምድር የሚለዋወጠው ቀን ብቻ ይመስላል። መሽቶ ይነጋል ነግቶ ይመሻል። እንዲህ እንዲህ እያለ ሁሉም በትናንት አቁማዳ እየታጨቀ ያልፋል። ወያላው ጣፍጦት ስለበላው ሽሮ አጠገቡ ለቆመው ሾፌር ያጫውተዋል። ‹‹እዚህ አገር ለወሬ አቅመ አዳም ከተደረሰ የሚወራው ስለ ሆድ ብቻ ነው። አይ እናት ኢትዮጵያ አላየሽ አውሮፓውያን ምግብ ተርፏቸው ሲደፉ…›› ይላል አንድ የብርድ ካፖርት የደረበ ጎልማሳ ተሳፋሪ። ከሁኔታው አንድ ሁለት አገር ያየ ይመስላል። በቃ ዳያስፖራ ለመምሰልም ይሞክራል፡፡ ወያላውና ሾፌሩ ‘የምግብ ጊዜ ይራዘም’ የሚያሰኝ ጭውውታቸውን ቀጥለዋል። አካባቢው ከወዲያ ወዲህ በሚተራመሰው መንገደኛ ተወሯል፡፡ ከዳያስፖራ ልምሰል ባዩ አጠገብ የተቀመጠች ቀዘባ፣ ‹‹ምን መሰለህ እንዲህ ያለ ፀረ አገር የሆነ ድርጅት አይቼ አላውቅም…›› እያለች በስልክ ታወራለች። ድንገት ስልኳ ይቋረጣል። ‹‹ወይ ኔትወርክ!›› አለች፡፡ ጉዟችን አልተጀመረም። ታክሲውም አልሞላም። እያሟሟቅን ነው!

አፍታም ሳይቆይ ዳያስፖራ ልምሰል ባዩና ውቢት ጨዋታ ጀመሩ። ‹‹ፀረ አገር ስትይ?›› አላት በተደነጋገረ ቀልብ። ‹‹እያየኸው! በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ በሆነው ኑሮአችን የምንጠበሰው አንሶ፣ ጭራሽ ጦርነት አስነስቶ አገርን ችግር ውስጥ ሊከት የነበረው ጀብደኛ ቡድን አላውቀውም ለማለት ነው? እንግዲህ አንድ አገር ውስጥ እየኖርን የሁለት አገር ሰው መምሰል እኮ ነው ያልቻልንበት…›› ትለዋለች። ዳያስፖራ ልምሰል መሳዩ አሁንም ግራ እየተጋባ፣ ‹‹እኔ እዚህ አገር ባልነበርኩበት ጊዜ የተፈጠረ አዲስ ነገር አለ እንዴ?›› ከማለቱ መሀል ወንበር ላይ የተቀመጡ እናት፣ ‹‹ወይ ጉድ! ስልኩን እንደ ጡጦ ታቅፎ እየዋለና ፌስቡክ ላይ ውሎ እያደረ ምን አዲስ ነገር አለ እያለ ያሹፍብን እንጂ…›› ማለታቸው ሲሰማ ዳያስፖራ መሳዩ መነጋገሪያ ሆነ፡፡ ‹‹ማዘር እንዲህ ዓይነቶቹ እኮ ናቸው ሚናቸው አለይ ብሎ ውቃው ደብልቀው ውስጥ የሚያስገባን…›› የሚለው አንድ ጎረምሳ ነው፡፡ ነገር ሊጀመር ነው!

 ወያላው መጥራቱን ቀጥሏል። ሾፌራችን ገብቶ ሞተር እያሞቀ ነው። ታክሲዋ በብዙ ጥገናና እንክብካቤ ያለች ለመሆኗ ማንም የሚረዳው ነው። አንዲት ሴት ግማሽ ማዳበሪያ በርበሬ አሸክመው ወያላውን ሳያስፈቅዱ፣ ‹‹ና እዚህ ጋ አድርገው…›› እያሉ ራሳቸው ለዕቃቸው ቦታ ሰጥተው ተሳፈሩ። ልጅ እግሩ ወያላ እንደ መሳቅ እያለ (ሳይተዋወቁ አይቀሩም)፣ ‹‹ምንድነው ዛሬ ደግሞ?›› አላቸው። ‹‹በርበሬ!›› አሉት ኮስተር ብለው። ‹‹ታዲያ ስንት ይከፍላሉ?›› አላቸው አሁንም ቅንነት ያፈለቀው ፈገግታው ሳይከስም። ‹‹አንተ እስኪ ተወኝ ትንሽ ልተንፍስ። ምን ሊለኝ ነው? ምነው እንዲህ የዘንድሮ ሰው ከበርበሬ ባሰ እናንተ…›› ሲሉ ሁላችንም ፈገግ አልን። ‹‹ኧረ! ቀልዴን መስሏችሁ ነው? በየሄድንበት እኮ የሚያቃጥለን በዛ። ምናለበት መንግሥት ጀብደኞችን ከጫንቃችን ላይ ሊያወርድልን ሲታገል፣ እኛ ደግሞ እርስ በእርሳችን ብንተዛዘን?›› እያሉ ፊታቸውን በነጠላቸው ሸፈን አድርገው ችፍ ያለ ላባቸውን ይጠርጋሉ። እውነት አላቸው!

ታክሲዋ ልትሞላ የሁለት ሰዎች ቦታ ይቀራታል። ‹‹እማማ ሰላሳ ብር ይከፍላሉ…›› አላቸው ወያላው ሲፈራ ሲቸር። ‹‹በቫት ነው ያለ ቫት?›› ሲሉ ተሳፋሪዎች ይስቃሉ። ‹‹ሰማችሁልኝ ይኼንን? ለነገሩ አልከፍልም ብል ምን አመጣለሁ?›› እያሉ አጉረመረሙ። ‹‹አይ በርበሬ ነው ስላሉኝ ነው። በርበሬ ደግሞ ከሕዝብ ጋር አይጫንም ለእርስዎ ብዬ ነው እንጂ…›› ሲላቸው ወያላለው ‹‹እንዲህ ነው ነገሩ! እሰይ ዛሬስ ሕዝብን ማክበርም አወቃችሁበት። ስማ ቢገባህ ከአንተ አመልና ከኑሮ ውድነቱ የባሰ በርበሬ አልጫንኩም…›› ሲሉት ወያላው አሁንም ስቆ፣ ‹‹እሺ ደስ ያለዎትን ይሰጡኛል…›› አላቸው። ‹‹እኔ ነገሬሃለሁ ከታሪፉ ውጭ ምንም የምሰጥህ ነገር የለም፣ ባይሆን የዱቤ ደብተር አዘጋጅና ግድባችን ተገንብቶ ሲያልቅ ከማገኘው የትርፍ ድርሻ እከፍልሃለሁ…›› አሉት። ‹‹ግድቡ ያልቅ ተቆራጭ ይጀመራል ተባለ እንዴ?›› ሲል አንዱ ዘሎ ሴትዮዋ፣ ‹‹በተሰቀለው! እንዴት ነው እዚህ አገር በቻይንኛ መነጋገር ተጀምሮ ነው እንዴ የማንግባባው?›› ሲሉ መላ ተሳፋሪዎችን አሳቁ። ልብ እየደማ ጥርስ መሳቁን ቀጥሏል። ወይ ዘመን!

ታክሲያችን ሞልታ ከተንቀሳቀሰች ቆየት ብላለች። ወያላው ለሾፌሩ፣ ‹‹እኔ ምልህ የኮንትራት ሥራ ተገኝቷል። ክፍለ ሀገር ነው፣ ትወጣለህ?›› አለው፡፡ ሾፌራችን ድምፁን ከፍ አድርጎ፡፡ ‹‹በመጀመርያ ጊዜው የፌደራሊዝም ነው። በብሔር ብሔረሰቦች ዘመን ክልል እንጂ ክፍለ ሀገር ቀርቷል። ግን እንዴት እስካሁን ሳትነግረኝ?›› ሲል ‹‹መቀሌ!›› ብሎ ነገረው፡፡ ‹‹ስንት ይላሉ?›› ሾፌራችን ወያላውን ይጠይቀዋል። ‹‹አሥራ አራት ሺሕ አምስት መቶ ብር ነው የሚሉት…›› ይለዋል ወያላው። ‹‹አሁኑኑ ደውልላቸው…›› ሲለው ሾፌሩ ወያላው እየሳቀ፣ ‹‹አንተ ገንዘብ ካየህ ፈንጂ መሀል ሰተት ብለህ እንደምትገባ አያጠራጥርም›› አለው፡፡ ‹‹እዚህ አገር እኮ ኑሮ ፈንጂ ውስጥ አይደለም ገሀነምም ቢሆን ይከተሃል…›› ሲለው ፍርጥም ብሎ ተስፋ የቆረጠ ይመስል ነበር፡፡ አንዳንዱ ደግሞ ያበዛዋል!

‹‹ትሰማለህ የሚባባሉትን?›› ይላል ከኋላችን የጥንዶች ወንበር ላይ የተቀመጠ ተሳፋሪ። ‹‹እየሰማሁ እኮ ነው፣ ‘እዚህ አገር ከመኖር ጀምሮ የሚያዋጣ ነገር የለም’ አይደል የሚለው። ምን በዚህ አገር በዚህ ዓለም ነው እንጂ ማለት…›› ይለዋል አብሮት የተቀመጠው። ‹‹ግን የእኛ ይብሳል። ትናንትም መጠለያ ዛሬም መጠለያ ጥያቄያችን ነው። ትናንትም ምግብ ዛሬም ምግብ። ቢያንስ ችግራችን እንኳ አልተሻሻለም እንኳን እኛ ልናድግ…›› ሲለው፣ ‹‹መጀመርያ እኛ ስናድግ ነው ችግሮቻችንም የተሻሉ የሚሆኑት…›› ይለዋል ያኛው መልሶ። ሾፌሩና ወያላው ቀጥለዋል። ‹‹ለመሆኑ አንተ መቀሌን ታውቀዋለህና ነው አያዋጣም የምትለው?›› በማለት ሾፌሩ ሲጠይቅ ወያላው፣ ‹‹ተወልጄ ባልድግበትም ከአንዴም ሦስቴ አውቀዋለሁ›› አለው። ‹‹ታዲያ ዙረት ከለመድክ አዲስ አበባ ወያላነት ምን ያደርግልሃል?›› ሲለው፣ ‹‹አዲስ አበባ ወርቅ ይታፈሳል ብለውኝ…›› አለው፡፡ ‹‹እናስ? እንደ ጠበቅከው ሆነ?›› ሲለው ወያላው እየሳቀ፣ ‹‹ኧረ ወፍ የለም!›› ብሎ መለሰለት። እዚያም ሰዎቹ እንደ ወፍ ጠፍተዋል!

ታክሲያችን በግስጋሴ ላይ እኛም በጉዞ ላይ ነን። ሳቅና ጨዋታው ደርቷል። የዕለት ገጠመኝና ቀልዱ ሰውን አላስቀምጠው ያለ ይመስላል። አንዱ እንዲህ ይቀልዳል። ‹‹እኛ ሠፈር የሆነውን ልንገራችሁማ። እንግዲህ እኛ ሠፈር በግ መግዛት ወንጀል ነው። በሕግ ያልተደነገገ ግን በዓይን አስወግቶ የሚጥል ማለቴ ነው። እና አንዱ ዓምና ለፋሲካ በግ ገዝቶ ተሸክሞ ሲሄድ፣ በግ ዲቪ ደርሶት የተሰደደባቸው የሚመስሉ ጭቁኖች ያዩታል…›› እያለ የተሳፋሪዎችን ቀልብ ተቆጣጠረ። ‹‹ምን አሉት ታዲያ?›› አንዱ ተሳፋሪ ለማስጨረስ ይወተውተዋል። ‹‹አምስቱም በተወሰነ ርቀት ላይ ቆሙና ልክ ወደ እያንዳንዳቸው በቀረበ ቁጥር ‘አንተ ብለህ ብለህ ውሻ ተሸክመህ መሄድ ጀመርክ?’ ይሉታል። ከአንደኛው እስከ አራተኛው ሰው ድረስ ምንም አላለም ነበር። አምስተኛው እንደ ገመሬ እያሽካካ ሲስቅበት ደንግጦ፣ በጉን ውሻ ነው ብሎ ጥሎት አይሄድ መሰላችሁ? ለነገሩ የቆየ ተረት ነው…›› ሲል ተሳለቀ፡፡ በድሮ ቀልድ ስንቱ እንደከበረ ለማወቅ ዩቲዩብ ይመስክር!

‹‹እውነት ነው በበግ ያልተቀና በምን ሊቀና ኖሯል?›› ስትል ቀዘባዋ፣ ‹‹ውሸት ሲደጋገም እውነት ይሆናል ማለት እንዲህ ነው…›› ይላል ዳያስፖራ መሳዩ። ‹‹እህ ውሸት ሲደጋገም እውነት ይሆናል አልክ፣ ምን ይሆናል ሆኗል እንጂ። ኢትዮጵያ ፈጣን ዕድገት በማስመዝገብ ላይ ነች ሲሉን የነበሩ አይደሉ እንዴ አጋድመው ሲግጧት የነበሩ መዥገሮች። በሥራ ይሁን በስብከት እውነት መሆኑን ለማወቅ ፈጣሪ ዘንድ መሄድ የለብንም ነበር። ነገር ግን በዓይናችን ዓይተን በእጃቸውን ዳሰን ያረጋገጥነው እውነት አይደል?›› ሲሉ አዛውንቷ ሰው አፉን ከፍቶ እያዳመጠ በምፀቱ ይጎሻሸማል። ‹‹አይ! የእኛ ነገር ሁሌም ወደ ኋላ…›› አለ አንድ ወጣት ከኋላ ተቀምጦ። ‹‹እንዴት?›› ትለዋለች አራተኛው ወንበር ላይ የተቀመጠች ቀጭን ጠይም ወጣት። ‹‹ቆንጆ የእና የዘወትር ችግራችን ምግብ ስለሆነ በግና ዶሮ ደግሞ ብርቅ ናቸው፡፡ እኛ በምግብ እጥረት ምክንያት ካልበላን ማጨብጨብ አናውቅም፤›› ሲላት፣ ‹‹አይምሰልህ መንግሥት እንኳን ለዚህ ለሌላም መልስ አያጣም፤›› ስትለው፣ ‹‹አይ አንቺ አንድ ዚዜ የፓርላማ ስብሰባ ላይ ነው አሉ፡፡ የበግና የዶሮ ጉዳይ ቢጠየቅ ምን እንደተባለ ታውቂያለሽ? ‘ዶሮም በግም የተወደዱት ከበፊቱ በበለጠ ፈላጊያቸውና ተመጋቢያቸው በመጨመሩ ነው። ይኼ የሚያሳየው የሕዝቡ የመግዛት አቅም ማደጉን ነው። ስለዚህ የሚኖረው አማራጭ ቀላቅሎ መብላት ነው…’ ተብሎ ነበር…›› አላት፡፣ ‹‹በምን ሊቀላቀል?›› ብላ ስታፈጥ፣ ‹‹በተገኘው!›› ብሎ ሲስቅ አብረን ሳቅን፡፡ በዚህ ዓይነትማ ስንቱን ቀላቅለን ልንችለው ይሆን!   

 ኮተቤ ደርሰን ጉዟችን ሊጠናቀቅ ተቃርቧል። ሳናስበው እንደ ተገናኘነው ሳናስበው ልንለያይ ጥቂት ጊዜ ቀርቶናል። የዛሬው ጉዟችን መሪ ተዋናይት የነበሩት አዛውንቷ፣ ‹‹ለማንኛውም ለክፉም ለደጉም እንኳን ደስ አላችሁ መባባሉ መልካም ነው። አገር ከላይዋ ላይ መዥገሮች ሲነቀሉላት ደስ ሊለን ይገባል፡፡ ደስታችንም ሌላ መዥገር እንዳይፈጠር ጭምር መሆን አለበት…›› ሲሉ ጎልማሳው ተቀበላቸው፡፡ ‹‹ቢሆንም፣ ቢሆንም፣ ለምንድነው አንዱን አረም ስንነቅል ሌላው የሚያመልጠን? በዚህ በኩል ጥንታዊትና ታሪካዊት አገራችን እያልን መደስኮር፣ በሌላ በኩል አዲሱ ትውልድ የመጣበትን ሳያውቅ ማንነቱ ተበርዞ ሲንገዳገድ ቆሞ መታዘብ፣ በአንድ ወገን ዳዴ የሚለውን ዴሞክራሲያችንን መኮርኮም፣ በሌላ ወገን በሌብነትና በዝርፊያ አንደኛ ለመሆን መፎካከር፣ በዚህ ልማት በዚያ ጥፋት። ምንድነው እንዲህ ዓይነት ግራ የገባው አካሄድ?›› ሲል ተናገረ። ‹‹የተኮስንም  እኛ የቆሰልንም እኛ። ሁሉም በአገር ያምራል። ቢያጡም ቢያገኙ ከወገን ጋር ይሻላል ልጄ። ታዲያማ ይህች አገር ማን አላት ሊባል ነው? አይዞን እንባባል እንጂ…›› ብለው አዛውንቷ ተከዙ በነጠላቸው ፊታቸውን እየሸፈኑ። ከጎልማሳው አጠገብ ያለችው ወጣት፣ ‹‹ግን ነውጠኞችን  እስከ መቼ እንኮኮ እንበላቸው?›› አለቻቸው ሳታስበው በተቆጣ ድምፅ። ለዚህ መልስ የነበረው ከጊዜ ውጭ ማንም አልነበረም። ታክሲያችን እየቆመች ነው። ወያላው በሩን ከፈተውና ‹‹መጨረሻ!›› ብሎ ሲል ወርደን በየአቅጣጫው ስንበታተን ታክሲያችን ውስጥ የነበረው የአመለካከት ልዩነት በሰላማዊ መንገድ ተስተናግዶ መሰነባበታችን ደስ አሰኘኝ፡፡ የተደበላለቁ ስሜቶች ይንፀባረቁ ዘንድ ሁላችንም ብንተጋና እነዚህ ስሜቶች ዋስትናቸው ቢረጋገጥ መንገዳችን ሁሉ ሰላማዊ ይሆን ነበር፡፡ አረም ሲነቀል ሰላም ይሆናል ለማለት ነው፡፡ መልካም ጉዞ!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት