በኢትዮጵያ ኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ የሚንቀሳቀሱት 18ቱ ኢንሹራንስ ኩባንያዎች፣ የ2012 የሒሳብ ዓመት አፈጻጸማቸውን ይፋ እያደረጉ ነው፡፡
በ2012 የሒሳብ ዓመት ሪፖርታቸውንም ለባለአክሲዮኖቻቸው እያሳወቁ ይገኛሉ፡፡ ሰሞኑን በተከታታይ ሪፖርታቸውን ካቀረቡት የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ውስጥ ፀሐይ ኢንሹራንስ፣ አፍሪካ ኢንሹራንስ፣ ብርሃን ኢንሹራንስ ይገኙበታል፡፡ ሦስቱም ኩባንያዎች የ2012 የሒሳብ ዓመቱን በአትራፊነት ያጠናቀቁ ሲሆን፣ እንደ ብዙዎቹ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ሁሉ ብልጫ ያለውን የጉዳት ካሳ ክፍያ ያዋሉት ለሞተር ወይም ለተሽከርካሪ ኢንሹራንስ ነው፡፡
ከኩባንያዎቹ ዓመታዊ ሪፖርት መረዳት እንደሚቻለው፣ አፍሪካ ኢንሹራንስ ከ45 ሚሊዮን ብር በላይ፣ ፀሐይ ኢንሹራንስ ከ30.2 ሚሊዮን ብር በላይ፣ ብርሃን ኢንሹራንስ ደግሞ ከ35.9 ሚሊዮን ብር በላይ አትርፈዋል፡፡ የኩባንያዎቹ 2012 ዋና ዋና የሥራ አፈጻጸም እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡
ፀሐይ ኢንሹራንስ
ሰሞኑን ዓመታዊ ሪፖርቱን ያቀረበው ፀሐይ ኢንሹራንስ አክሲዮን ማኅበር በ2012 የሒሳብ ዓመቱ አጠቃላይ የዓረቦን ገቢውን 323 ሚሊዮን ብር ማድረስ መቻሉን አስታውቋል፡፡ ይህ የዓረቦን ገቢው ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር በ23 ሚሊዮን ብር ወይም የስምንት በመቶ ዕድገት ያሳየ ነው፡፡ ይህ አፈጻጸም ከዓረቦን ገቢ በዓመቱ ከተያዘው የ357 ሚሊዮን ብር ዕቅድ አንፃር ሲታይ 90 በመቶ ስለመሆኑ በሪፖርቱ አመልክቷል፡፡
በሒሳብ ዓመቱ የካሳ ክፍያ አፈጻጸሙን በተመለከተ ኩባንያው፣ 232.9 ሚሊዮን ብር የካሳ ክፍያ ለደንበኞቹ የከፈለ ሲሆን፣ ከዚህ በተጨማሪም 192.9 ሚሊዮን ብር በመጠባበቂያ መያዙን በሪፖርቱ ጠቅሷል፡፡ ለካሳ ክፍያ ከዋለው 239.9 ሚሊዮን ብር ውስጥ 79 በመቶ የሚሆነው ለሞተር ወይም ለተሽከርካሪ ጉዳት ኢንሹራንስ የተከፈለ ነው፡፡
የዓመታዊ የትርፍ ግኝቱን በተመለከተም በ2012 የሒሳብ ዓመት 30.2 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ አግኝቷል፡፡ ይህ ትርፍ የተገኘው ከኦፕሬሽን፣ ከኢንቨስትመንትና በባንክ ከተቀመጠ የጊዜ ገደብ ቁጠባ ወለድ ገቢ ነው፡፡
ኩባንያው በሒሳብ ዓመቱ ያገኘው ትርፍ ግን ከ2011 የሒሳብ ዓመት አንፃር ሲታይ ከሦስት ሚሊዮን ብር በላይ የቀነሰ መሆኑን ከዓመታዊ ሪፖርቱ ለመረዳት ተችሏል፡፡ ፀሐይ ኢንሹራንስ በ2011 የሒሳብ ዓመት የተገኘው የተጣራ 33.3 ሚሊዮን ብር ነበር፡፡ የኩባንያው ቋሚም ሆነ ተንቀሳቃሽ ሀብት በ2012 የበጀት ዓመት መጨረሻ ላይ 688 ሚሊዮን ብር የደረሰ ሲሆን፣ ይህም ከ2011 ጋር ሲነፃፀር የ89 ሚሊዮን ብር ዕድገት አሳይቷል፡፡
የኩባንያው የተከፈለ ካፒታል 172.5 ሚሊዮን ብር የደረሰ ሲሆን፣ በ2011 የበጀት ዓመት መጨረሻ ላይ ከነበረው 110.8 ሚሊዮን ብር ጋር ሲነፃፀር የ61.7 ሚሊዮን ብር ማለትም በ56 በመቶ ዕድገት ማሳየቱ ታውቋል፡፡
አፍሪካ ኢንሹራንስ
በኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ ቀደም ብለው ገበያውን ከተቀላቀሉት የግል የኢንሹራንስ ኩባንዎች ውስጥ አንዱ የሆነው አፍሪካ ኢንሹራንስ፣ በ2011 የሒሳብ ዓመት አስመዝግቦ ከነበረው ኪሳራ ወጥቶ በ2012 የሒሳብ ዓመት ከ45 ሚሊዮን ብር በላይ ማትረፉን አስታውቋል፡፡
ከኩባንያው ዓመታዊ የሒሳብ ሪፖርት መረዳት እንደተቻለው፣ በ2011 የሒሳብ ዓመት ከ2.8 ሚሊዮን ብር በላይ ኪሳራ ያስመዘገበ ሲሆን፣ በ2012 የሒሳብ ዓመት ግን 45.6 ሚሊዮን ብር ሊያተርፍ መቻሉን ነው፡፡ ኩባንያው በ2012 የሒሳብ ዓመት ከዓረቦን ያገኘው አጠቃላይ ገቢ 573.7 ሚሊዮን ብር ሲሆን፣ ይህም ከ20.9 ሚሊዮን ብር በላይ ብልጫ ያለው ሆኗል፡፡ የጉዳት ካሳ ክፍያን በተመለከተም በ2012 የሒሳብ ዓመት ከ2011 የሒሳብ ዓመት ያነሰ የጉዳት ካሳ የከፈለ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡ ከአብዛኛዎቹ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በተለየ የጉዳት ካሳ ክፍያው ቅናሽ የታየበትም ሆኗል፡፡
ኩባንያው በሒሳብ ዓመቱ የ423 ሚሊዮን ብር የካሳ ክፍያ የፈጸመ ሲሆን፣ በቀዳሚው ዓመት ግን 509 ሚሊዮን ብር ከከፈለው አንፃር የ2012 ዓ.ም. የካሳ ክፍያው በ86 ሚሊዮን ብር መቀነሱን ያመለክታል፡፡ ኩባንያው በ2012 የሒሳብ ዓመት ከተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች 111 ሚሊዮን ብር ማግኘቱንም ለማወቅ ተችሏል፡፡ አፍሪካ ኢንሹራንስ ኩባንያ አጠቃላይ የሀብት መጠናቸው ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ካደረሱ ኩባንያዎች አንዱ ሲሆን፣ በ2012 መጨረሻ ላይ አጠቃላይ የሀብት መጠኑ ከ1.4 ቢሊዮን ብር በላይ ደርሷል፡፡
ብርሃን ኢንሹራንስ
ብርሃን ኢንሹራንስ አክሲዮን ማኅበር በ2012 የሒሳብ ዓመት አጠቃላይ የዓረቦን ገቢ 139.8 ሚሊዮን ብር ማግኘቱንና ይህ የዓረቦን ገቢው ከ2011 የሒሳብ ዓመት ጋር ሲነፃፀር ወደ 15 በመቶ ብልጫ እንዳለው አስታውቋል፡፡
በ2012 የሒሳብ ዓመት አጠቃላይ የጉዳት ካሳ ክፍያው 70.9 ቢሊዮን ብር እንደደረሰ የሚያመለክተው የኩባንያው መረጃ፣ በ2011 የሒሳብ ዓመት ኩባንያው ለካሳ ክፍያ አውሎት ከነበረው 44.2 ሚሊዮን ብር አንፃር ሲታይ፣ ከ27 ሚሊዮን ብር በላይ ጭማሪ ያሳየ ሆኗል፡፡
እንደ ብዙዎቹ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ሁሉ ብርሃን ኢንሹራንስም ለጉዳት ካሳ ካዋለው ወጪ ውጪ ከ70 በመቶ በላይ ለሞተር ወይም ለተሽከርሪ ኢንሹራንስ የከፈለው ነው፡፡ የ2012 የሒሳብ ዓመት አፈጻጸም ከታክስ በፊት 33.7 ሚሊዮን ብር ማትረፉን ገልጿል፡፡ ይህ የትርፍ መጠን ከ2011 የሒሳብ ዓመት ጋር ሲነፃፀር የ9.4 ሚሊዮን ብር ብልጫ ያለው መሆኑንም አመልክቷል፡፡
የብርሃን ኢንሹራንስ ኩባንያ በ2012 የሒሳብ ዓመት የተከፈለ ካፒታሉ ወደ 117.6 ሚሊዮን ብር መድረሱን ያሳወቀ ሲሆን፣ ይህም 23 በመቶ ዕድገት ማሳየቱን ያመለክታል፡፡ አጠቃላይ የሀበት መጠኑ ደግሞ 440.4 ሚሊዮን ብር ደርሷል፡፡