Friday, March 1, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኅብረት ሥራ ማኅበራት ካፒታላቸውን 28.8 ቢሊዮን ብር አደረሱ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በፌዴራል ሥራ ኤጀንሲ ሥር የሚተዳደሩ የኅብረት ሥራ ማኅበራት ካፒታል 28.8 ቢሊዮን ብር ደረሰ፡፡ ኤጀንሲው የ2012 የሒሳብ ዓመት ሪፖርት ባቀረበበት ወቅት እንዳስታወቀው፣ ማኅበራቱ ካፒታላቸውን ከማሳደግ በሻገር የቁጠባ ካፒታላቸው 19.5 ቢሊዮን ብር መድረሱን የፌዴራል ሥራ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ዑስማን ሱሩር አስታውቀዋል፡፡

ኤጀንሲው ከሐሙስ ታኅሳስ 1 እስከ 3 ቀን 2013 ዓ.ም. የፌዴራል ኅብረት ሥራ ኤጀንሲ የኅብረት ሥራ ዘርፍ የቀጣይ ዓመት ጉዞ ትልም የሚጣልበትን ምክክር አድርጓል፡፡ በመድረኩ እንደተገለጸው፣ 22 ሚሊዮን አባላትን፣ 391 የኅብረት ሥራ ዩኒየኖችና አራት የኅብረት ሥራ ፌዴሬሽኖችን ማፍራት ተችሏል፡፡

የኅብረት ሥራ ማኅበራቱ በደረሱበት የዕድገት ደረጃ ከፍተኛ የፋይናንስ ፍላጎት እየተፈጠረ እንደሚገኝ የሚገልጹት ዳይሬክተሩ፣ የፋይናንስ ፍላጎቱ በተለይ በግብርና፣ በግብርና ምርት ማቀነባበሪያና ኢንዱስትሪዎች ዘርፍ ላይ ከፍተኛ መሻሻል ማምጣቱን አስረድተዋል፡፡

ማኅበራቱ በተለይ የአርሶ አደሩ የአመራረት ሥርዓት ገበያ መር እንዲሆን በማድረግ አምራቹና ሸማቹ እንዲገናኝ ዕድል መፍጠራቸውን አክለዋል፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞም በ2012 ዓ.ም. ለአገር ውስጥ ግብይት ለማቅረብ አቅደው ከነበረው 1.9 ሚሊዮን ቶን ምርት ውስጥ 1.5 ሚሊዮን ቶን ምርት ማቅረብ መቻላቸው ታውቋል፡፡

ለውጭ ገበያ ሊያቀርቡ ዕቅድ ይዘው ከነበረው 35,326 ቶን ምርት፣ 20,685 ቶን ምርትን አቅርበዋል፡፡  በገቢ ዕቅዱ መሠረት ሊገኝ ታቅዶ ከነበረው የውጭ ምንዛሪ 137,000 ዶላር፣ 92,052 ዶላር ብቻ መሳካቱ ተነግሯል፡፡

የኅብረት ሥራ ማኅበራቱን የግብይት ሰንሰለት ለማሳለጥ ብድር እንዲያገኙ ኤጀንሲው ሲያመቻች በቆየው መሠረት፣ በ2012 ዓ.ም. ለቡና ግብይት፣ ለቅባት እህል፣ ለጥራጥሬ፣ ለማርና ቅመማ ቅመም ምርቶች ግብይት፣ እንዲሁም ለምርት ማጠቢያና ማበጠሪያ ቴክኖሎጂዎች ግዥ ከ2.7 ቢሊዮን ብር በላይ የብድር ጥያቄ ቀርቦ ለ22 ኅብረት ሥራ ማኅበራት 2.39 ቢሊዮን ብር ማቅረብ መቻሉ ተጠቅሷል፡፡

እንደ ዳይሬክተሩ አስተያየት ከሆነ፣ የማኅበራቱና ወደ ኢንቨስትመንቱ የገቡ ዜጎች ቁጥር እየጨመረ በመምጣቱ ከፍተኛ የፋይናንስ ፍላጎት ታይቷል፡፡ በመሆኑም ማኅበሩ የራሱን ባንክና ኢንሹራንስ ለማቋቋም ማቀዱን አስታወቀዋል፡፡

ማኅበራቱ በ2008 ዓ.ም. በሚኒስቴሮች ምክር ቤት በፀደቀው አዋጅ 9/85 መሠረት ባንክ ለመመሥረት ጥያቄ ቢያቀርቡም፣ የቁጠባ መጠናቸው በቂ ስላልሆነ ውድቅ መደረጉን ያስታወሱት ዳይሬክተሩ፣ በቂ መጠን እስኪያካብቱ መጠበቃቸውንም አክለዋል፡፡

አሁን ላይ በኅብረት ሥራ ማኅበሩ ሥር ባሉ ዘርፎች በአጠቃላይ 48.8 ቢሊዮን ብር እንደሚንቀሳቀስ የገለጹት ዳይሬክተሩ፣ የማኅበሩን የመሠረተ ልማት ፍላጎት፣ ኢንዱስትሪ ሥራዎችንና በቂ የብድር ፍላጎትን ለማሟላት ባንክ ማቋቋም ግድ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡

ባንክ የማቋቋም ውጥኑ ለመንግሥት የቀረበ ሲሆን፣ ግብርና ሚኒስቴርም ፖሊሲ የማሻሻል ሥራዎችን ሠርቶ ለሚኒስቴሮች ምክር ቤት ማቅረቡን አቶ ዑስማን አክለዋል፡፡

ከዚህ ቀደም ብድር ተበድሮ ሥራ ለመጀመር ለልጅ ዕዳ እንደ ማውረስ የሚቆጠረው ባህል ቀርቶ፣ አሁን ላይ ከወር ወር ከ80 ሚሊዮን እስከ 100 ሚሊዮን ብር ድረስ የብድር ጥያቄ እያቀረበ እንዳለም ተገልጿል፡፡

ከባንክ ምሥረታው በተጓዳኝ ኢንሹራንስ መቋቋሙ ቀድሞ በኅብረት ሥራ ማኅበሩ ሲሰጥ የነበረውን የአነስተኛ መድን ኢንሹራንስ ማሳደግ ያስችላል ተብሏል፡፡

የኅብረት ሥራ ማኅበሩ አሁን ካለበት ሁኔታ ከፍ ለማድረግ አዲስ መዋቅር ነድፎ የትኩረት መስኮችን ማስቀመጡን ገለጸዋል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞም አሠራሮችን በማዘመን የገበያ ድርሻቸውን ማስፋት፣ ከግብርና የሚገኙ ምርቶችን በአገር ውስጥ፣ እንዲሁም የውጭ ገበያን ማሳደግ፣ የግብርና ምርት ላይ እሴት ጨምሮ ለገበያ ማቅረብ፣ ውጤትን ማሳደግና ከውጭ ገበያ የሚመጡትን ምርቶች መተካት፣ ቁጠባና ኢንቨስትመንት ማሳደግ፣ እንዲሁም የኅብረት ሥራ ማኅበሩ ሕጋዊነት መጠበቅ በቀጣይ ለማሻሻል የሚሠራባቸው ዓብይ ጉዳዮች መሆናቸውን ዋና ዳይሬክተሩ አብራርተዋል፡፡

የኅብረት ሥራ ማኅበሩ የአደረጃጀትና የአሠራር ማሻሻያ ማስቀመጡን የገለጸ ሲሆን፣ የአደረጃጀት፣ አሠራርና የሰው ኃይል ላይ ሪፎርም ለማድረግ ማቀዱን አስታውቋል፡፡ በከፍተኛ፣ መካከለኛና ዝቅተኛ በሚል ተከፍሎ የተደራጀ አሠራር ለመከተል ማቀዱን ጠቁመዋል፡፡ ይህ በቂና ዘመናዊ የሰው ኃይል አሠራር ይጨምራል ተብሏል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች