Sunday, April 14, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ብቸኛው የጠለፋ መድን ሰጪ ኩባንያ ትርፉን ወደ 186 ሚሊዮን ብር አሳደገ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በኢትዮጵያ ብቸኛው የጠለፋ መድን ሰጪ ኩባንያ በመሆን የሚታወቀው የኢትዮጵያ ጠለፋ መድን አክሲዮን ማኅበር፣ በተጠናቀቀው በ2012 የሒሳብ ዓመት ዓመታዊ የትርፍ ምጣኔውን 186.4 ሚሊዮን ብር ማድረሱን አስታወቀ፡፡ ታካፉል (ከወለድ ነፃ ኢንሹራንስ) የጠለፋ መድን ሽፋን ለመስጠት ዝግጅት ማጠናቀቁንም ገልጿል፡፡

ኩባንያው ታኅሳስ 6 ቀን 2013 ዓ.ም. ባካሄደው ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባዔ ላይ እንዳስታወቀው፣ በ2012 የሒሳብ ዓመት ያገኘው 186.4 ሚሊዮን ብር ትርፍ ከቀዳሚው ዓመት ከ41 ሚሊዮን ብር በላይ ብልጫ አሳይቷል፡፡  

በሒሳብ ዓመቱ ከተገኘው ጠቅላላ ትርፍ ውስጥ ከጠቅላላ መድን ዘርፍ  166.9 ሚሊዮን ብር ማትረፍ የቻለ ሲሆን፣ ከሕይወት መድን ዘርፍ ደግሞ 19.5 ሚሊዮን ብር እንዳተረፈ አስታውቋል፡፡ እያንዳንዱ አክሲዮን ያስገኘው የትርፍ ድርሻ 21.29 በመቶ መሆኑም ታውቋል፡፡ ኩባንያው በ2012 የሒሳብ ዓመት ያስገኘው የትርፍ ድርሻ ግን በ2011 አስገኝቶት ከነበረው አንፃር ሲታይ መጠነኛ ቅናሽ የታየበት ነበር፡፡ የትርፍ ድርሻ መጠኑ የቀነሰበትን ምክንያት በተመለከተ ከተሰጠው ማብራሪያ መረዳት እንደተቻለው፣ የኩባንያው የተከፈለ ካፒታል በ23.3 በመቶ መጠን ቢጨምርም የትርፍ ድርሻ ክፍፍሉ ላይ ቅናሽ ታይቷል፡፡

ከዓረቦን አሰባሰብ አንፃር የኢትዮጵያ ጠለፋ መድን አክሲዮን ማኅበር ከአጠቃላይና ከሕይወት ነክ የመድን ሽፋን ዘርፎች 874.7 ሚሊዮን ብር አግኝቷል፡፡ ይህ ገቢ ከተመሳሳይ ወቅት አፈጻጸም ጋር ሲነፃፀር የ25 በመቶ ዕድገት ማስመዝገቡን ያሳያል፡፡ የኩባንያው ሪፖርት ከዚህ የዓረቦን ገቢ ውስጥ 327.5 ሚሊዮን ብር ወይም 38 በመቶ በጠለፋ መድን ከተሰጠ ዓመታዊ ሽፋን፣ 518.4 ሚሊዮን ብር ወይም 59 በመቶ ከእያንዳንዱ የመድን ሽፋን ውል አግኝቷል፡፡ በተጨማሪም ከውጭ አገሮች 7.7 ሚሊዮን ብር በማግኘት የሒሳብ ዓመቱን ማጠናቀቁ ተገልጿል፡፡

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ኩባንያው በአጠቃላይ 218.1 ሚሊዮን የካሳ ክፍያ የፈጸመ ስለመሆኑ ኩባንያው አስታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ የጠለፋ መድን አክሲዮን ማኅበር በጠቅላላ መድንና በሕይወት መድን ዘርፎች የጠለፋ መድን ሥራ ላይ የተሰማራ በኢትዮጵያ ብቸኛው ኩባንያ ነው፡፡

የኩባንያው  ባለአክሲዮኖች ከመንግሥትና ከግሉ ዘርፍ የተውጣጡ ሲሆን፣ በአጠቃላይ ሰባት ባንኮች፣ 17 የኢንሹራንስ ኩባንያዎች፣ 80 ግለሰቦችና አንድ የሠራተኛ ማኅበር ይገኙበታል፡፡ የኩባንያው አጠቃላይ የተፈረመ ካፒታሉ 997.3 ሚሊዮን መድረሱም ታውቋል፡፡ ከዚህም ሌላ በ2012 የሒሳብ ዓመት መጨረሻ ላይ የኩባንያው ጠቅላላ ሀብት 1.79 ቢሊዮን ብር የደረሰ ሲሆን፣ ይህም ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር የአሥር በመቶ ዕድገት አሳይቷል፡፡ በበጀት ዓመቱ የኩባንያው የተከፈለ ካፒታል 787.6 ብር ሚሊዮን ደርሷል፡፡ ይህም ካለፈው በጀት ዓመት ጋር ሲነፃፀር የ29 በመቶ ዕድገት እንዳሳየ ተጠቅሷል፡፡

የኩባንያውን ተጨማሪ የሥራ አፈጻጸም የሚያሳዩ መረጃዎች፣ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ኩባንያው በዓለም አቀፍ ደረጃ ብቁና ጠንካራ ከሆኑ የጠለፋ መድን ሰጪ ተቋማት ጋር የድርብ ጠለፋ መድን መፈጸሙን ያመለክታሉ፡፡ በዚህም በመላው አፍሪካ ካሉት አገሮች ጋር ካለምንም ቅድመ ሁኔታ መሥራት የሚያስችል ስምምነት ስለመፈረሙም ኩባንያው አስታውቋል፡፡

የዚህ ኩባንያ መቋቋም ዋነኛ ዓላማው የአገሪቱ ኩባንያዎች ለጠለፋ መድን ለውጭ ኩባንያዎች በውጭ ምንዛሪ ይከፍሉ የነበረውን ወጪ ለመቀነስ ያለመ ነው፡፡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት የኢንሹራንስ ኩባንያዎቹ በዓመቱ ከሚሰበስቡት ጠቅላላ ዓረቦን ውስጥ እስከ 30 በመቶ የሚሆነውን ለውጭ ኩባንያዎች ለጠለፋ መድን ይከፍሉ እንደነበር ነው፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ የኢትዮጵያ ጠለፋ መድን አክሲዮን ማኅበር በኢትዮጵያ የመጀመርያ የሚባለውን የታካፉል ጠለፋ መድን አገልግሎት ለመጀመር በዝግጅት ላይ መሆኑ ታውቋል፡፡

ኩባንያው ከጥቂት ወራት በፊት የታቀደውን የታካፉል መድን አገልግሎት ሕግ መውጣት ተከትሎ ለሚቋቋሙ የታካፉል ወይም ከወለድ ነፃ የኢንሹራንስ አገልግሎት ለመስጠት ይቻለው ዘንድ ከወዲሁ መዘጋጀቱን አመልክቷል፡፡

የወለድ አልባ የባንክ አገልግሎት ሥራ ላይ ለማዋል ከወጣው ሕግ ጎን ለጎን ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ለመጀመር የሚያስችለው ሕግ በብሔራዊ ባንክ ከወጣ በኋላ፣ ታካፉል ኢንሹራንስ ኩባንያን ለማቋቋም ጥያቄዎች እየቀረቡ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ታካፉል ኢንሹራንስ በመስኮት ደረጃ እየሰጠ ያለው ግሎባል ኢንሹራንስ ብቻ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች