Sunday, March 26, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ዘመን ባንክ የአሥር ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅዱን ለማሠራት ከውጭ ኩባንያ ጋር ተፈራረመ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

ዘመን ባንክ አክሲዮን ማኅበር በባንክ ኢንዱስትሪ የበለጠ ተወዳዳሪ ሊያደርገኝ ይችላል ያለውን የአሥር ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ እንዲያዘጋጅለት ፒደብልዩሲ (Price Waterhouse Cooper) የተባለውን ዓለም አቀፍ ኩባንያ መረጠ፡፡

ባንኩ ይህንን ስትራቴጂክ ዕቅድ እንዲያዘጋጅለት ከመረጠው ኩባንያ ጋር ትናንት ታኅሳስ 6 ቀን 2013 ዓ.ም. በተፈራረመበት ወቅት እንደተገለጸው፣ ዘመን ባንክ በቀጣይ አሥር ዓመታት  የተሻለ ውጤታማ ሊያደርገው የሚችለውን ሰነድ ፒደብልዩሲ በሦስት ወራት ውስጥ አዘጋጅቶ ያቀርባል፡፡ በትግበራው ላይም አብሮ እየሠራ የሚቆይ መሆኑም ታውቋል፡፡

የስትራቴጂክ ዕቅድ ሥራ እንዲሠራለት ባንኩ ዓለም አቀፍ ጨረታ በማውጣት በርካታ ኩባንያዎች ስለመሳተፋቸው የተገለጸ ሲሆን፣ ከነዚህ ኩባንያዎች መካከል በባንኩ ምዘና የተሻለ ውጤት ያመጣውን ፒደብልዩሲን ሊመርጥ ችሏል፡፡

ከተጫራቾች መካከል ለመጨረሻው ውድድር አራት ኩባንያዎች ተለይተው የነበሩ ሲሆን፣ ከአራቱ በቴክኒክ ምዘናና ባቀረበው ዋጋ ፒደብልዩሲ ሊመረጥ ችሏል፡፡ እንዲሁም በሌሎች አገሮች በተመሳሳይ ሥራ ያለውን ልምድና ውጤት በማየት አሸናፊ ሊሆን ስለመቻሉም ተገልጿል፡፡

ዘመን ባንክ ፒደብልዩሲ ተመሳሳይ ሥራዎች የሠራላቸውን ኩባንያዎች በቀጥታ በመገናኘት ያስገኙትን ውጤት ለማየት መሞከሩን የገለጹት የዘመን ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ ደረጀ ዘነበ፣ ኩባንያው ዋነኛ ሥራ በሚቀጥሉት አሥር ዓመታት የዘመን ባንክ ከየት ተነስቶ የት ይደርሳል የሚለውን ስትራቴጂክ ዕቅድ መቅረፅና ተግባራዊ እንዲሆን ማድረግ ነው፡፡

የኢትዮጵያንና የምሥራቅ አፍሪካን ቀጣይ የፋይናንስ ኢንዱስትሪና የኢኮኖሚ ዕድገትን ይህ ስትራቴጂክ ዕቅድ በተለይ በቴክኖሎጂና ደንበኛ አገልግሎት ላይ ትኩረት ያደረገ ይሆናል፡፡ ከባንኩ የሥራ ኃላፊዎች ገለጻ መረዳት እንደሚቻለውም ዘመን ባንክ በደንበኞች ተኮር አገልግሎቱና ዘመናዊ ባንክን ቀድሞ በመጀመር የሚጠቀስ በመሆኑ፣ ይህንን የበለጠ ለማድረግ ስትራቴጂክ ዕቅዱ ዕገዛ ያደርጋል፡፡ ከግምት በማስገባት ዘመን ባንክን ተወዳዳሪ ያደርጋል ተብሎ የሚጠበቀው ፒደብልዩሲም ከዚሁ የባንኩ ነባራዊ ሁኔታ አንፃር ስትራቴጂውን እንደሚቀርፅም ይጠበቃል፡፡

ኩባንያው ለዘመን ባንክ ከሚሠራው የአሥር ዓመታት ስትራቴጂክ ዕቅድ በተጨማሪ፣ የአምስት ዓመታት ስትራቴጂክ ዕቅድ ለብቻው ይሠራል፡፡ ዋናው መታሰብ ያለበት ባንኩ ደንበኛ ተኮር ባንክ ነውና ይህንን ዋነኛ መለያ የሆነውን አሠራሩን ይዞ የበለጠ ማዘመንና የበለጠ ለኅብረተሰቡ እንዴት ተደራሽ ማድረግ ይችላል የሚለውን ዕቅዱ እንዲመልስ ይፈልጋል፡፡

የባንኩ ዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር አበበ ድንቁ (ፕሮፌሰር) እንዳመለከቱትም ይህ ስትራቴጂክ ዕቅድ ባንኩን የወደፊት ተወዳዳሪነት ለማሳደግ ሁነኛ ሚና እንደሚኖረው ነው፡፡ የፒደብልዩሲ ተወካይ ሚስተር ሙኒው ቶቲ እንደገለጹትም ዘመን ባንክ አገልግሎቱን ከፍ ለማድረግና የበለጠ ውጤታማ ሊያደርገው የሚያስችለውን ሥራ ይሠራል፡፡ ዘመን ባንክ ከዚህ ቀደም የነበሩትን ሁለት የስትራቴጂክ ዕቅዶች በማጠናቀቅ አዲስ የስትራቴጂክ ዕቅድ በማስፈለጉ በዚህ መሠረት በዕለቱ በተደረሰው ስምምነት መሠረት የአሥር ዓመታት ስትራቴጂክ ዕቅዱ ከተያዘው የሒሳብ ዓመት ጀምሮ ይተገበራል፡፡

እንዲህ ያለውን ስትራቴጂክ ዕቅድ በታዋቂ ኩባንያዎች ማሠራት አስፈላጊ የሚሆንባቸው በርካታ ምክንያቶች ስለመኖራቸው የባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢና የባንኩ ፕሬዚዳንት በተለያየ መልኩ ገልጸዋል፡፡ በተለይ የቦርዱ ሰብሳቢ አበበ (ፕሮፌሰር) ከዚህ በኋላ በኢንዱስትሪ ውስጥ የበለጠ ተወዳዳሪ ሆኖ ለመቀጠል ግድ ከሚልባቸው ምክንያቶች አንዱ አዳዲስ ባንኮች ገበያውን ይቀላቀላሉ ተብሎ መጠበቁ ነው፡፡

በአሁኑ ወቅት ካሉት 16 የግል ባንኮች በተጨማሪ አዲስ 16 ባንኮች በቀጣዩ ዓመት ገበያውን የሚቀላቀሉ መሆኑን የገለጹት ፕሮፌሰሩ ለዚህ ደግሞ በበቂ መዘጋጀት ተገቢ ስለመሆኑም ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡

ይህንኑ ሐሳብ ያጠናከሩት አቶ ደረጀም ‹‹በርካታ ባንኮች እየመጡ በመሆኑ ‹‹ውድድሩ ምን መምሰል ይችላል›› የሚለውን በማየትና ይህንንም ግምት ውስጥ በማስገባት፣ ፒደብልዩሲ ስትራቴጂክ ዕቅዱን እንዲሠራ ይጠበቃል›› ብለዋል፡፡

ስምምነቱ በተደረገበት ወቅት እንደተገለጸው የአሥር ዓመቱ የስትራቴጂክ ዕቅድ  ባንኩን ወደ ተሻለ ደረጃ ሊመጣ ለሚያስችለው ውድድርም ዝግጁ እንዲሆን ያስችለዋል፡፡

ዘመን ባንክ በአሁኑ ጊዜ ከ16ቱ የግል ባንኮች ዓመታዊ የትርፍ መጠኑን ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ካደረሱት ስምንት ባንኮች አንዱ ሲሆን በተለይ በ2012 የሒሳብ ዓመት ከፍተኛ የትርፍ ዕድገት ካስመዘገቡ ባንኮች አንዱ መሆን የቻለ ባንክ ነው፡፡ ከሦስት ዓመት በፊት የባንኩ ዓመታዊትርፍ ከ300 ሚሊዮን ብር ያነሰ እንደነበር የሚታወስ ሲሆን፣ ባለፉት ሁለት ዓመታት ግን የትርፍ መጠኑን በማሳደግ ይጠቀሳል፡፡ በ2012 የሒሳብ ዓመትም ከታክስ በፊት 1.04 ቢሊዮን ብር አትርፏል፡፡ ባንኩ ዓመታዊ ትርፉ ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ሲያደርስ የመጀመርያ ጊዜው ነው፡፡  

ፒደብልዩሲ በዓለም አቀፍ ደረጃ ፋይናንስ ነክ በሆኑ አገልግሎቶች ከሚታወቁ ኩባንያዎች መካከል አንዱ ሲሆን በተለይ የዓለም ክፍሎችም በዚሁ አገልግሎት ከመታወቁም በላይ በምሥራቅ አፍሪካ አገሮች ባሉ የፋይናንስ ተቋማት ተመሳሳይ ሥራ በመሥራት ላይ ይገኛል፡፡ በቅርቡም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን እንደ አዲስ ለማደራጀትና ቀጣይ የሚሠራበትን ስትራቴጂ ለመቅረፅ ከቀረቡ 40 ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪዎች ውስጥ ለመጨረሻው ውድድር ከቀረቡ አራት ኩባንያዎች ውስጥ አንዱ ፒደብልዩሲ ነበር፡፡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት ፒደብልዩሲ በ2019 ከ284 ሺሕ በላይ ሠራተኞችን ይዞ ሲንቀሳቀስ የነበረ ሲሆን ዓመታዊ ገቢውም 43 ቢሊዮን ዶላር እንደነበር ያመለክታል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች