ከዛሬ 17 ዓመት በፊት የነበረ የመላው ዓለምን ቀልብ የሳበ ታሪካዊ ክስተት ነው። የአሜሪካ ጦር በኢራቅ ላይ ያካሄደውን ወታደራዊ ዘመቻ ኢራቅን ሙሉ በሙሉ በመቆጣጠር ቢያጠናቅቅም፣ የዘመቻው የመጨረሻ ግብ የነበረው የኢራቅ ፕሬዚዳንት ሳዳም ሁሴንን በቁጥጥር ሥር የማዋል ተልዕኮ ግን አልተጠናቀቀም።
የአሜሪካ ጦር በኢራቅ የነበረውን ጦርነት ካጠናቀቀ በኋላ ፕሬዚዳንት ሳዳም ሁሴንን በቀላሉ በቁጥጥር ሥር ማዋል አልቻለም። ስድስት ወራት ከፈጀ እልህ አስጨራሽ የስለላ ምርመራና አደን በኋላ ግን ሰውዬው ዱካቸው በትንሿ የኢራቅ ከተማ ኤዲ ዳወር ተገኘ። በዚህች ከተማም የመጨረሻው ኦፕሬሽን እ.ኤ.አ. ዲሴምበር 13 ቀን 2003 ተካሂዶ፣ ፕሬዚዳንት ሳዳም ሁሴን ከመሬት በታች መደበቂያ ጉድጓዳቸው ውስጥ ምንም ዓይነት ጉዳት ሳይደርስባቸው በሕይወት ሲያዙ በዓለም የቴሌቪዥን መስኮቶች ታዩ። ፕሬዚዳንቱን የማደን ዘመቻውም እ.ኤ.አ. ዲሴምበር 13 ቀን 2003 ተፈጸመ።
ይህ ታሪክ ከተፈጸመ ከ17 ዓመት በኋላ በተመሳሳይ ቀን በኢትዮጵያ (ዲሴምበር 13 ቀን 2020 ወይም ታኅሳስ 4 ቀን 2013 ዓ.ም.) ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ወታደራዊ ዩኒፎርምና ቀይ ቦኔት ለብሰው በድንገት በመቀሌ ከተማ ተገኝተው፣ በትግራይ ክልል የተካሄደውን የሕግ ማስከበር ዘመቻ ከመሩ ከአገር መከላከያ ሠራዊት የጦር አዛዦች ጋር ተገናኝተው፣ በሦስት ሳምንታት ስለፈጸሙት ወታደራዊ ገድል አሞካሽተው ስለቀሪ ተልዕኳቸውም መመርያ ሰጡ።
መመርያውንም ሲያስተላልፉ ከ17 ዓመት በፊት በዚያው ዕለት በኢራቅ ስለተፈጸመው ታሪክ አስታወሱ። ‹‹አሜሪካ ከአራቅ ጋር ባደረገችው ጦርነት ኢራቅን አሸንፋ ከተቆጣጠረች በኋላ፣ ሳዳምን ለመያዝ ግን በርካታ ወራቶችን ፈጅቶባታል። እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ሲገጥም ድልን ግማሽ ያደርጋል፡፡ ተጨማሪ ወጪ፣ ተጨማሪ ኪሳራ ያስከትላል። ይህ በኢትዮጵያ መደገም የለበትም። ወንጀለኞቹን በፍጥነት በመያዝ ጀግንነታችሁን መድገም ይኖርባችኋል፤›› ሲሉ ምክር አዘል መመርያቸውን ለከፍተኛ ጦር አመራሮች አስተላለፉ።
የአሜሪካ ጦር በኢራቅ የተሰጠውን ወታደራዊ ተልዕኮ በድል ቢያጠናቅቅም፣ የአገሪቱን ፕሬዚዳንት ለመያዝ ያሳለፈው ጊዜና ያወጣው ወጪ ከፍተኛ ነበር።
አሜሪካ በኢራቅ ላይ የፈጸመችው ወታደራዊ ዘመቻ ከተጠናቀቀ በኋላ ‹‹HVT1›› የተሰኘ ምሕፃረ ቃል (High Value Target Number One) መለያ የተሰጣቸውን ፕሬዚዳንት ሳዳም፣ ሬድዳውን (Red Dawn) የተሰኘ እሳቸውን ለመያዝ ያለመ አደን ውስጥ ለመግባት ተገዳለች።
በዚህ ዘመቻም ተልዕኮውን የወሰደው ‹‹Task Force 121›› የተባለ ልዩ ኮማንዶ ከ12 በላይ ወታደራዊ ዘመቻዎችን ቢፈጽምም፣ አንዳቸውም ዒላማቸውን የጠበቁ አልነበሩም። ዋና ተልዕኮ ከወሰደው ኮማንዶ ጦር በተጨማሪ ሌሎች በኢራቅ የነበሩ የአሜሪካ ጦር ኃይሎችም በጥቅሉ 600 ዘመቻዎችን አድርገው፣ ሰውዬውን ለመያዝ አልቻሉም፣ አልያም ዘመቻዎቹ ዒላማቸውን የሳቱ ነበሩ።
በዚህ ብቻ አላበቃም፡፡ የአሜሪካ የስለላ ቡድንም ሰውዬውን ለመያዝ ከ300 በላይ ጥብቅ ምርመራዎችን አድርጓል። ቢሆንም ተፈላጊውን ሳዳም ሁሴን ለመያዝ ውጤት ያስገኘው ከስለላ ቡድኑ የተገኘ መረጃ መሆኑን ሪፖርቶች ያመለክታሉ።
በዚህ የስለላ ተግባር ውስጥም ኤሪክ ማዶክስ የተባሉት ወታደራዊ ሰላይ የመጨረሻውን ጠቃሚ መረጃ በማግኘት፣ በዚህ ታሪክ ውስጥ ስማቸው ከፍ ብሎ የተጠራ ሲሆን፣ የሦስት የክብር ኒሻኖች ተሸላሚም አድርጓቸዋል።
የአሜሪካ ጦር ወታደራዊ ሰላይ የሆኑት ኤሪክ ማዶክስ ሳዳም ሁሴንን በማደን ዘመቻ ውስጥ በነበራቸው መረጃ የመሰብሰብና መረጃውን አንጥሮ የሰውዬውን ዱካ የመከተል ኃላፊነት ውስጥ ትኩረታቸውን ያደረጉት፣ ከተፈላጊው ሰው ጋር ግንኙነት ነበራቸው ተብለው በቁጥጥር ሥር የዋሉ በበርካታ መቶዎች የሚቆጠሩ ግለሰቦች ላይ ምርመራ ማድረግ ነበር።
በዚህ ተልዕኮ ውስጥም የፕሬዚዳንት ሳዳም ሁሴን የቅርብ ቤተሰቦች፣ ዘመዶች፣ ጠባቂዎችና ሌሎች የቅርብ ግንኙነት ከነበራቸው ከ200 በላይ ሰዎች ላይ ምርመራ አካሂደዋል። የተፈላጊው ሰው የቅርብ ሰዎች ተብለው በቁጥጥር ሥር የዋሉት ግለሰቦች ግን ለተፈጸሙባቸው የምርመራ ሥልቶች (ቶርቸርንም እንደሚያካትት ይነገራል) አልተበገሩም። የሚሰጡት መረጃም ወደ ውጤት እንኳን የሚያቀርብ አልነበረም።
በዚህ ሁኔታ የተዳከሙት ኤሪክ ማዶክስ ሥልታቸውን ቀይረው ሌላ የምርመራ ሥልት መከተልን መረጡ። ይህ ሥልትም ምርመራ የሚደረግባቸውን ሰዎች ከማስፈራራት ወይም ከማሰቃየት ይልቅ ጓደኛ ሆኖ መቅረብን የመረጠ ነበር። ምርመራ የሚደረግባቸው እስረኞች ፕሬዚዳንት ሳዳም ተግባራዊ አድርገውታል የተባለውን የፖለቲካ ርዕዮት ከልባቸው አምነው ለመቀበልና ተልዕኮ ለመፈጸም የገፏቸውን ምክንያቶችና ታሪኮች እንደ ቅርብ ጓደኛ ሆነውና ታሪካቸውንም እንዳዘኑ በሚመስል የመመሰጥ ሽፋን ውስጥ መከታተልን፣ እንዲሁም ተመርማሪዎቹን ካሉበት ሕይወት ለማውጣትና የተረጋጋ ሕይወት እንዲመሩ ለመደገፍ ቃል በመግባት የተከተሉት ሥልትና ጥረት አንድ ቀን መሐመድ ኢብራሂም ዑመር አል ሙስሊት የተባለ ስም እንዲተዋወቁ ረዳቸው።
ይህ ግለሰብ የሳዳም ሁሴን ዘመድና የግል ጠባቂ እንደሆነ ያረጋገጡት ኤሪክ ማዶክስ፣ ይህንን ሰው ለማግኘት ያደረጉት ክትትልም የፕሬዚዳንቱ የግል ጠባቂ ሾፌር ዘንድ ያደርሳቸዋል።
ሹፌሩን ከተዋወቁ በኋላ ወደ ውጤት እየመራቸው ያለውን የስለላ ሥልት አጠናክረው በመቀጠል፣ የተፈላጊው ሰው የግል ጠባቂ መገኛን ካመላከተ የተሻለ ሕይወት ለመኖር የሚያስችለው ጠቀም ያለ ገንዘብ ለመስጠትና ማንነቱን ቀይሮ ቀሪ ሕይወቱን ተረጋግቶ መኖር የሚችልበት ከለላ እንደሚያገኝ በገቡለት ቃል መሠረትም፣ ሰውዬው የሚኖርበትን ቦታ አመላከተ።
ይህ መረጃም ተፈላጊው ሳዳም ሁሴን የተደበቁበትን ጉድጓድ ያስገኘ ጠቃሚ ሆኖ ወታደራዊ የስለላ ቡድን አባሉን ኤሪክ ማዶክስን ብሔራዊ የክብር ኒሻኖች አሸለመ። ሳዳም ሁሴን የማደኑን ዘመቻም ዲሴምበር 13 ቀን 2003 ተፈጸመ።
በትግራይ ክልል የሕግ ማስከበር ዘመቻ እንዲፈጽም ተልዕኮ የተሰጠው የመከላከያ ሠራዊት፣ በሦስት ሳምንት ጊዜ ውስጥ በርካታ የትግራይ ክልል አካባቢዎችንና ዋና ከተማዋን መቀሌን ከተቆጣጠረ በኋላ መጠናቀቁ ይፋ ተደርጓል።
ይሁን እንጂ የሕግ ማስከበር ውጊያ እንዲካሄድ ምክንያት ሆነዋል የተባሉና በሕግ እንዲጠየቁ የመያዣ ማዘዣ የወጣባቸው በበርካታ መቶዎች የሚቆጠሩ የሕወሓት አመራሮች እስካሁን መያዛቸው ወይም ያሉበት ቦታ በውል መለየቱ አልታወቀም።
የኢራቅ ፕሬዚዳንት ሳዳም ሁሴን በአሜሪካ ጦር በተያዙበት ዕለት 17ኛ ዓመት ላይ በመቀሌ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር)፣ የአሜሪካ ጦር ጦርነቱን አሸንፎ ኢራቅን ቢቆጣጠርም ተፈላጊውን ሰው ለማግኘት ግን ወራት እንደ ፈጁና ይህም የአሜሪካን ድል በወቅቱ ግማሽ አድርጎት እንደነበር አስታውሰዋል።
‹‹ጦርነትን ካሸነፉ በኋላ ወኝጀለኞችን የመያዝ ሥራው ሲዘገይ ተጨማሪ ወጪ፣ ተጨማሪ ኪሳራ ያስከትላል። የተገኘውንም ድል ግማሽ ያደርገዋል፤›› ሲሉ ለጦር ጄኔራሎቹ ታሪካዊ ምሳሌን አጣቅሰው አስገንዝበዋል።
በትግራይ ክልል ማዘዣ የወጣባቸው ግለሰቦች የት እንደሚገኙ ሙሉ መረጃ ስለመኖሩ እስካሁን ባይታወቅም ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ግን፣ ‹‹ተፈላጊዎቹ በገሃድ ሆነው እየተንቀሳቀሱ አይደለም። በተናጠል ከመኪና ወርደው በየአቅጣጫው ተበትነዋል፤›› ብለዋል።
እዚህ ላይ በሕግ የሚፈለጉትን ለመያዝ ኢትዮጵያዊ ኤሪክ ማዶክስ የሚያስፈልግ መሆኑ አጠራጣሪ እንዳልሆነው ሁሉ፣ በአገሪቱ የደኅንነት መሥሪያ ቤት አቅም ላይ ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎችና የፓርላማ አባላት ሳይቀሩ ከአንድ ወር በፊት ጥያቄ ማንሳታቸውም የሚታወስ ነው።
መንግሥት ተፈላጊዎቹን ለመያዝ የሚከተለው አዋጭ ሥልትና መንገድ ምን ሊሆን ይችላል? በምን ያህል ያጠረ ጊዜ ውስጥስ ውጤት ያስገኛል? የሚለው ጥያቄ በርካቶችን እያነጋገረ ነው።
የዚህ ጥያቄ ትክክለኛ መልስ ለጊዜው ባይታወቅም ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ከፍተኛ የጦር አዛዦች ባገኙበት ወቅት ግን የሚከተለውን ተናግረዋል።
‹‹ወንጀለኞቹ መያዝ አለባቸው። ከዚህ አንፃር የትግራይ ሕዝብ ከፍተኛ ኃላፊነት እንዳለበት ይሰማኛል። ካሉበት ቦታ እንዲያዙ ከሁሉም ዜጋ ትብብር ይጠበቃል፡፡ ይህ ካልሆነ እነሱን ለመያዝ በሚደረገው ሥራ ነዋሪዎች ይጎዳሉ። ስለዚህ በአጠረ ጊዜ ይህ ሥራ መጠናቀቅ አለበት።››
ከማክሰኞ ታኅሳስ 6 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ በመቀሌ ከተማ የቤት ለቤት ፍተሻ የተጀመረ ሲሆን፣ የዚህ ፍተሻ አንዱ ዓላማም ሕገወጥ የጦር መሣሪዎችን መሰብሰብ እንደሆነ ታውቋል። እግረ መንገዱንም የተወሰኑ የሕወሓት አመራሮችንም ሊያካትት ይችላል እየተባለ ነው፡፡