- እና በመቀሌ ከተማ ተገኝተዋል ነው የምትለኝ?
- እርስዎ መረጃው አልነበረዎትም ነበር?
- በጭራሽ አልሰማሁም። እርግጠኛ ነህ ግን?
- መረጃዎቹ የሚያመለክቱት መቀሌ ተገኝተው ከጦር ጄኔራሎቹ ጋር መምከራቸውን ነው። አብረውም ፎቶ ተነስተዋል?
- እስኪ ፎቶ ግራፉን አሳየኝ?
- ይኽው. . .
- በፎቶ ሾፕ የተሠራ አለመሆኑን እርግጠኛ ነህ?
- መቀሌ መሄድ እየተቻለ ለምን በፎቶ ሾፕ ማስመሰል ያስፈልጋል?
- እንዴ ይኸው . . . ፎቶ ሾፕ ነው።
- እንዴት አወቁ?
- ተመልከት. . . አሁን የሚፈለጉት ሰዎች የተሰበሰቡበትን አዳራሽና ይኼኛውን አዳራሽ ተመልከት።
- እየተመለከትኩት ነው ግን ሊያሳዩኝ የፈለጉት አልገባኝም?
- አዳራሾቹ አንድ ዓይነት አለመሆናቸው አይታይህም?
- አዎ አንድ አይደሉም፡፡
- አየህ ፎቶ ሾፕ ነው አላልኩህም? ስለዚህ አልሄዱም ማለት ነው።
- ተሳስተዋል ክቡር ሚንስትር፡፡
- ምን ላይ ነው የተሳሳትኩት?
- አንድ አዳራሽ ይሰበሰባሉ ብለው ሲያስቡ ሐሳብዎን ሲያምኑ ነው የተሳሳቱት።
- እና የት ሊሰበሰቡ ይችላሉ?
- ብዙ መሰብሰቢያዎች እያሉ እንዴት እርስዎ ያሉት ቦታ ሊሰበሰቡ ይችላሉ?
- እኮ ሌላ የት አለ?
- ለምሳሌ ሰሜን ዕዝ አዳራሽ አለ፡፡
- በጠላት ቡድን ተይዞ የለም እንዴ እሱ?
- አሃ. . . እርስዎ ገና አልገቡም ማለት ነው?
- የት?
- መቀሌ፡፡
- ምን ማለትህ ነው?
- መከላከያ ሠራዊት መቀሌን ከተቆጣጠረ ቆዬ ብዬ ነው።
- እኔን ያሳሰበኝ ዋና ነገር እሱ አይደለም።
- ምንድ ነው?
- እንዴት እኔ ወደ መቀሌ መሄዳቸውን አላወቅኩም፡፡ እንዴት አልተነገረኝም?
- እርስዎ ወጣ ሲሉ ይሆናል እነሱ የገቡት፡፡
- ወዴት ወጣ አልኩ?
- ቆላ ተምቤን
- ሂድ ውጣልኝ!
[ሚኒስትሩ በመኖሪያ ቤታቸው ከባለቤታቸው ጋር የምሽቱን የቴሌቪዥን ዜና እየተከታተሉ ሳለ አለቃቸው ከጦር ጄኔራሎች ጋር እየመከሩ የሚያሳየው የምስል ዜና መቅረብ ጀመረ]
- እስኪ ወደ ሌላ ቻናል ቀይሪው?
- እንዴ. . . ቆይ እንጂ. . . ዩኒፎርሙ ደግሞ እንዴት ያምርባቸዋል ባክህ. . . የት ሄደው ነው?
- መቀሌ ነበሩ፡፡
- ጠዋት እዚሁ ከውጭ የመጣ እንግዳ ሲቀበሉ አልነበረም እንዴ?
- ከተቀበሉ በኋላ ሄዱ፡፡
- ምሣ ላይ እንዴት አላወራኸኝም?
- አንዳንድ መረጃዎች ለማንም እንደማይነገሩ አታውቂም?
- አንተ የካቢኔ አባል አይደለህ እንዴት አይነግሩህም?
- እኔማ አውቃለሁ።
- እና የሚደበቀው ከማን ነው?
- ለአንቺ ያልነገርኩሽ በሚስጥር መያዝ ስለነበረበት ነው ማለቴ ነው።
- አንተ ሰምተህ ለኔ ሳትነግረኝ?
- ምንም ማድረግ አልችልም ነበር።
- ከዚህ የበለጡ ስንት ሚስጥሮች ያልደበቅከኝ ይኼንን ሚስጥር አደረግከው?
- አንዳንድ መረጃዎች ጥብቅ ናቸው ወጥተው ቢገኙ ያስጠይቀናል።
- ቢሆንም ስንቱን ሚስጥር ስታወጋኝ ከርመህ? እኔ ደብቀኸኝ ነው ብዬ አላምንም። ሌላ ነገር እንዳይሆን?
- ምን ሊሆን ይችላል?
- ካንተም የተደበቀ ሚስጥር እንዳይሆን?
- ምን ማለትሽ ነው የካቤኔ አባል አይደለሁ እንዴ?
- እሱማ ነህ ግን. . .
- ግን ምን?
- ይኼ የካቢኔ ስብሰባ አይደለማ?
- እና ቢሆንስ እኔ ማወቅ የለብኝም?
- አሃ. . . እነሱን ጠይቅ እንጂ እኔ ምን አውቃለሁ?
- አጥፊልኝ አሁን ይኼንን ቴሌቪዥን!
[ክቡር ሚኒስትሩ በኢኮኖሚ ጉዳዮች ላይ ለመምከር የተጠራው ከፍተኛ የባለሙያዎች ስብሰባ ከመጀመሩ በፊት ከአንድ የባንክ ፕሬዝዳንት ጋር እየተወያዩ ነው]
- ለውጡ ከተጀመረ ወዲህ ከሠራናቸው ስኬታማ ሥራዎች አንዱ የኢኮኖሚ ዘርፉ ነው። ለሌላውም ተምሳሌት የሚሆን ሥራ ይመስለኛል።
- ስኬት ለማለት አያስቸግርም ክቡር ሚኒስትር?
- ለምን? ሌላውን ተወውና የብር ቅያሬው ስኬት ብቻ ተምሳሌት አይሆንም?
- የብር ኖቶቹ መቀየራቸው ጥሩ ቢሆንም ስኬታማ ነው ማለት አይቻልም።
- እንዴት?
- ገና አሮጌው ብር ተቀይሮ ሳያልቅ እየሆነ ያለውን እያዩት አይደል እንዴ?
- ምን ሆነ?
- የአዲሶቹ ብሮች ፎርጂድ በየቀኑ እየተያዙ ነው። ብሔራዊ ባንክም ከፎርጅድ ብሮች ተጠንቀቁ እያለ ነው።
- ያሳዝናል ግን በለውጥ ላይ የሚገኝ አገር ከሚገጥሙት ፈተናዎች አንዱ እንዲህ ዓይነቱ ነው።
- እንዴት?
- የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማዕከሉን አሳሳቾችና አጭበርባሪዎች ለመቆጣጠር በሚያደርጉት ፈተና መወዛወዝ ይበዛበታል።
- ታዲያ ዘፈኑን በመቀየር መያዝ አይሻልም?
- ማንን?
- ተወዛዋዦቹን!