በግል ትምህርት ቤቶች የቅድመ መደበኛና በመንግሥት ትምህርት ቤቶች ከአንደኛ እስከ አራተኛ ያሉ ተማሪዎች ከታኅሣሥ 12 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ ወደ ትምህርት ገበታ እንደሚመለሱ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ አስታውቋል፡፡
የትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ዘላለም ሙላቱ፣ ሕፃናት ተማሪዎች ወደ ገጽ ለገጽ የመማር ማስተማር ሒደት ውስጥ ሲገቡ የተዘጋጀው የኮቪድ-19 ፕሮቶኮል በአግባቡ እንዲተገበር የትምህርት ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ የተከለከለው የገጽ ለገጽ የመማር ማስተማር ሒደት ለማስጀመር በተቀመጠው ውሳኔ መሠረት፣ ኅዳር 16 ቀን 2013 ዓ.ም. የስምንተኛና የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች በክለሳ ትምህርት መጀመራቸው ይታወሳል፡፡ በግል ትምህርት ቤቶች ከኅዳር 28 ቀን አንስቶ ከአንደኛ ክፍል፣ በመንግሥት ትምህርት ቤቶች ደግሞ ከአምስተኛ ክፍል ጀምሮ በሦስት ዙሮች መጀመሩን አቶ ዘለላም ገልጸዋል፡፡
በአራተኛ ዙር ሰኞ ታኅሳስ 12 ቀን የግል ትምህርት ቤቶች ተማሪዎች እንዲሁም የመንግሥት ትምህርት ቤቶች ደግሞ ከአንደኛ ክፍል ጀምሮ ሙሉ ለሙሉ ወደ ትምህርት ገበታ ይመለሳሉ ተብሏል፡፡