Monday, March 20, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

የግፍ ፅዋ ሲሞላ!

ሰላም! ሰላም! አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹የሰዎቹ መጨረሻ ምን የሚሆን ይመስልሃል?›› አለኝ፡፡ ስለእነ ማን እንደሆነ ማብራራት አይጠበቅብኝም። ምክንያቱም ወሬው ሁሉ ቆላ ይሁን ደጋ ውስጥ ስለተደበቁት ሰዎች ነውና። ‹‹አቶ አንበርብር! የሰዎቹን መጨረሻ ለመተንበይ የግድ ነብይ ወይም አጉል አዋቂ መሆን አያስፈልግም…›› መልሴን ሳይጠብቅ ሲለኝ ከማዳመጥ በቀር ምንም አማራጭ አልነበረኝም፡፡ ‹‹ግፍ ሠርተህ ከሰው መደበቅ ብትችል ፈጣሪ ካለህበት ውስጥ አንጠልጥሎ ያወጣሃል…›› ብሎ ሲጨምር፣ ‹‹ለመሆኑ በቅንጦት መኪና ሲንፈላሰሱ የነበሩ ቆላና ደጋውን ብቻ ሳይሆን፣ ተረተሩንና ሸንተረሩን እንዴት ይችሉታል?›› ማለት በየዋህነት፡፡ አጅሬው ከት ብሎ ስቆ፣ ‹‹አያድርስ እኮ ነው፡፡ ከቅንጦትና ኑሮና መኪና አውርዶ ዱር ለዱር የሚያሳድዳቸው እኮ የሠሩት ግፍ ነው አልኩህ፡፡ እንዴት ይችሉታል ላልከው ደግሞ ፈጣሪ ሊቀጣህ ሲፈልግ፣ ማሰቢያህን ዘግቶትና ልብህን አደንድኖት ስለሆነ፣ ይችሉታል ወይ ብለህ ከምታስብ ሥቃዩን ሲቀምሱት ግፋቸው ትዝ ይላቸዋል ወይ ብትል ያምርብሃል…›› ብሎኝ በግልምጫ በቆምኩበት ጥሎኝ ሄደ፡፡ አንዳንዱ ሰው እኮ ይናገረዋል!

ሰሞኑን በሰሜኑ የአገራችን ክፍል እየሆነ ያለውን ሁነት ሲያዳምጥ የሰነበተው ምሁሩ የባሻዬ ልጅ፣ ‹‹ወዳጄ የተባለውን አልሰማህም እንዴ?›› እያለ መልስ ከእኔ ሲጠብቅ፣ ‹‹ምን እንደሆነ አንተው ንገረኝ እንጂ…›› አልኩት። ‹‹ለእኔ ራሴ አንድ ወዳጄ ነው የነገረኝ፡፡ ‹ሁሉም ያገኘዋል የሠራውን ሥራ፣ ዝቅ ያለው በገንቦ ከፍ ያለው በእንስራ› ነው የተባለው…›› ሲለኝ እኔ ብቻ ነኝ እንዴ ተቀባይ የሆንኩት ብዬ በራሴ አዘንኩ›። ‹‹በእነዚህ ሰዎች ድርጊት ምክንያት ሕፃናት እንኳ ሳይቀሩ ‘በቶም ኤንድ ጄሪ’ መሳቅ ከተው ሰነበቱ። የሰዎቹ የጭካኔ ድርጊት እንዴት ይረሳል…›› ብዬ የበኩሌን ለማዋጣት ጥረት አደረግኩ። ምሁሩ ወዳጄ ፈገግ ብሎ ሲያየኝ ማሻሻል ያለብኝ ነገር እንዳለ ተረዳሁ፡፡ አንዱ ባለፈው ምን አለኝ? ‹‹አንበርብር ሁሌ ሳይህ ዘና ብለህ ነው የምትኖረው፣ ባለህ ነገር ረክተህ የዝግታ ሕይወት ነው የምትመራው…›› ብሎኝ ሲያበቃ ‘ቀናሁብህ’ ይለኛል ብዬ ስጠበቅ፣ ‹‹ለመሆኑ በሰላም ነው?›› ብሎ አይጠይቀኝ መሰላችሁ? ከዚያን ጊዜ ወዲህ ኮስተር ማለት ጀምሬ አላምርብህ ብሎኛል፡፡ ምን ይሆን የሚያምርብኝ!

 ይህን ሰሞን በጠዋት ነበር ከአልጋ የምወርደው። ከማንጠግቦሽ ጋር አንድ አንድ ስባባል ቆያይቼ ቁርስ ብጤ (እንደ ነገሩ) ቀማምሼ እወጣለሁ። እጇን ይባርከውና ያነሰውን አብዝታ የሚመረውን አጣፍጣ እንዳይከፋኝ የምትችለውን ታደርጋለች፣ ውዷ ባለቤቴ ማንጠግቦሽ። አቤት! ስንቱ ባለትዳር እንደ እኛ ቢሆን ምን ነበረ? በተለይ የዘንድሮን ትዳር ሳስበው ምን እንደሚመጣብኝ ታውቃለችሁ? ምናለበት መንግሥት ጥሩ የግብር ከፋይ ብሎ አንዳንድ ታታሪዎችን እንደሚያበረታታው፣ አርዓያ ሊሆኑ ለሚችሉ ባለትዳሮችም እንዲህ ያለ ነገር ቢያደርግ መልካም ነበር ብዬ አስባለሁ። በተለይ በጊዜው አጠራር ‘ሕይወት ትዳሩ’ እያለ እንደ እኛ ያለውን ቢያበረታታ፣ ኢኮኖሚያችን በሁለት አኃዝ ማደግ ይጀምር ነበር። የእስካሁኑ ውሸት ነበር ስለተባለ ነው ‘ይጀምር ነበር’ ብዬ ያልኩት፡፡ ይኼኔ መቼም አንዳንዶቻችሁ መንግሥት ትዳር ላይ ቢሠራ ኢኮኖሚው ያድጋል ማለቴን እንደ መቀላቀል ሳትቆጥሩት አትቀሩም። አኼኼ! እኔ መቼ አጣሁት? ‹‹እንኳን ይህችን የዝንብ ጠንጋራም እናውቃለን…›› አሉ ባሻዬ። አደራ በደህናው ጊዜ ነው እሳቸው ይኼን የተረቱት። አሁንማ ኑሮ ደህና አድርጎ አጠናግሮን እንኳን የዝንብ የሰውም አንለይ ብለናል፡፡ እውነት አይደል እንዴ!

 ለማንኛውም ቀላቅዬም ቢሆን ጠቆም ላደርጋችሁ የወደድኩት ይኼንኑ ነው። ሲጀመር የዘመኑ ሥራ የማይዛመደውን ማዛመድ ሆኗል። ሲቀጥል ማዛመድ የሚሠራው ‘አዛምድ’ ተብሎ ፈተና ላይ ሲመጣ ብቻ ነው። ይኼን ለማረጋገጥ ጥሩ ምሳሌ የሚሆነን የፈረደበት ‘የአገራችን ቴሌቪዥን’ ነው። እግረ መንገዴን በዚህ ሁሉ ትችት ሳይማረሩ ፣እስካሁን የቀጠሉ ብርቱ ሠራተኞቹን ሳላደንቅ ማለፍ ይከብደኛል። ‹‹ይኼ የሚያሳየው በኢኮኖሚ ዕድገቱና በሕዝቡ ኑሮ መሻሻል ምን ያህል እንደተመሰጡ ነው…›› ብሎ ያሳቀኝ ሰው ነበረ። አሁን በቀጥታ ወደ ምሳሌዎቻችን እንግባ። ‹‹ዘንድሮ ይካሄዳል ተብሎ የሚጠበቀው ምርጫ በሕወሓት መቃብር ላይ መሆኑ ተገለጸ…›› የሚል ዜና ከቴሌቪዥናችን ጣቢያችን ጠብቁ ብል፣ ተናጋሪው ማን ነው አዳማጩስ የሚል ጥያቄ እጠብቃለሁ፡፡ እኔ በቁሜ አፈር ልሁንለትና ምናለበት አንድ ቀን እንኳ ቃላቱን ቢያስተካክል ማለታችሁም አይቀርም፡፡ ‹‹በቤኒሻንጉል ጉምዝ በመተከል ዞን በአማራ ተወላጆች ላይ ግድያ የፈጸሙ ተለቃቅመው ታሰሩ… ባለ ማግሥት ግድያ ሲሰማ፣ ገዳዮችን አሳዶ ለመያዝ እየተሠራ እንደሆነ ተጠቆመ ብሎ በሰበር ዜና ሊያጨናንቀን ይችላል…›› ሲለኝ የሰነበተው የባሻዬ ልጅ ነው። ነገርን ነገር ሲያነሳው በጥቂቱ ይህን ይመስላል እላችኋለሁ። ምን ልበል ታዲያ!

ወዲያው አንድ የሚከራይ ቤት ነበረና ለማከራየት አሰሳ ጀመርኩ። ሆኖም ቤቱ በፍቺ ምክንያት ጣጣው ያላለቀ ነበርና ከሸፈ። እኔም የከሸፈውን ትቼ ለእኔ ያለውን ሥራ ማሳደዴን ቀጠልኩ። አንድ የሚከራይ ‘ሎቤድ’ እንድፈልግለት አስጨንቆ የጠየቀኝ ደንበኛዬን ለማስደሰት ያዝ እንግዲህ አልኩላችሁ። እንዲህ ያለው የኮንስትራክሽን መሣሪያ ኪራይ ሥራ የሚመጣው አልፎ አልፎ ሆኗል። አንድ ሰሞን ለአከራዩም ለተከራዩም ብርቅ ሆኖባቸው ነው መሰለኝ ይኼ ሆኖ ነበር ሥራችን። ከዚሁ ጋር አያይዤ የአገራችንን የግንባታ ነገር ሳስብ ብዙ ነገር ውስጤ ይማሰላል። በተለይ የሕንፃ ግንባታዎችን ባሰብኩ ቁጥር። ይገርማችኋል ከሦስት ቀናት በፊት በአንድ ሠፈር ውስጥ ሳልፍ ለመጠናቀቅ ጥቂት ከቀረው ሕንፃ አንድ የቀን ሠራተኛ ወድቆ፣ አይተርፉ አተራረፍ ተረፈና ሰው ከቦት እያዘነ እንዲህ ሲነጋገር ሰማሁ። ‹‹ውይ! ምስኪን ለአንድ ሀብታም ሲል እንዲህ ይሁን?›› ይላል አንዱ። ‹‹ለማይጠቅም ምንዳ (የጉልበት ዋጋ) ብሎ…›› ይቀጥላል ሌላው። ምን አለፋችሁ አንድም ሰው ‹‹ለአገር ጥቅም፣ ለከተማ ውበትና የሕንፃ ኪነ ጥበብ ዕድገት ብሎ…›› ሲናገር ሳልሰማ ቀረሁ። ሁኔታው ጥያቄ በውስጤ ፈጠረና የባሻዬን ልጅ ሳገኘው ጠየቅኩት። እሱም፣ ‹‹በአሁኑ ጊዜ በዚህ ኢፍትሐዊ በሆነ አኗኗር አንዱ መብላት እያቃተው አንዱ ሕንፃ ሲሠራ ማየት፣ እንዴት ቀና አስተሳሰብ ይፈጥራል ብለህ ትጠብቃለህ? በኪነ ሕንፃ ጥበብስ የትኛው አገራዊ ፍልስፍና፣ ዕሳቤና እሴት ሲንፀባረቅ አየን? የጥንቶቹ ግሪክ፣ ጣሊያንና ባቢሎን የገዛ ራሳቸው አስተሳሰብና ፍልስፍና እንደተንፀባረቀበት ያለ የአገራችንን ባህል፣ የሕዝብ አኗኗርና እምነት ሲገልጽ የምናየው ሕንፃ ሲገነባ ወይም ሊገነባ ሲታሰብ የት አየን? መቼ ሰማን?›› ሲለኝ ዕፀ ፋሪስ እንደ ቀመሰ ሰው ፈዘዝኩ። በስንቱ እንፋዘዝ!

እንዳልኳችሁ አንድ የሚከራይ ሎቤድ ሳገኝ ከደንበኛዬ ጋር አገናኝቼ የወትሮዬን ኮሚሽን ተቀበልኩ። ወዲያው ደግሞ ሌላ ሥራ ፍለጋ። እንጀራና ሕይወት ምን ያመሳስላቸዋል ብትሉ ያው ክብነታቸው ነው መልሱ። ቀኑ ሳይመሽብኝ ወዲያ ወዲህ ስል አንድ የወሬ ሱሰኛ ወዳጄ (መቼም ከጎጂ እስከ ጠቃሚው የሱስ ዘመን ሆኗል) መጣና ‹‹ሰማህ?›› አለኝ። ‹‹ምን?›› አልኩት። ‹‹ጠቅላይ ሚኒስትሩ መቀሌ ሄዱ የተባለው ውሸት እንደሆነ…›› ሲለኝ ውስጤ ነደደ፡፡ በዚህ የመረጃ ዘመን እንዲህ ያለ የነተበ ወሬ ብሎ መናገሩ፣ ከአንተ የተሻለ አዋቂ ነኝ ሊለኝ እንደፈለገ አድርጌ በመረዳቴ፣ ‹‹አንተ ጥራዝ ነጠቅ ጥፋ ከዚህ…›› ስለው ሹልክ  ብሎ ሄደ። ዘንድሮ እኮ ያልተጣራ ወሬ ተሸክሞ መዞር ዕውቀት እየመሰለው ሰው አላስቀምጠን ብሏል። ‹‹ምንጩ ያልታወቀ ሀብትና መነሻው ያልታወቀ ወሬ አገር ሲያምስ ምሁራኖቻችን ምን እየሠሩ ይሆን…›› እያልኩ ስብሰለሰል ምሁሩ ወዳጄ፣ ‹‹እነሱ አይደሉ እንዴ ዩቲዩብ ከፍተው የሚሸቅሉበት…›› ሲለኝ ነደድኩ፡፡ እነዚህን ለማስተማር የተከሰከሰው የደሃ አገር ገንዘብ እሳት ውስጥ እንደ ገባ ቅቤ ሲቀልጥ ታየኝ፡፡ ከመጠን ያለፈ ራስ ወዳድነት እንዲህ ዝቃጭ ያደርጋል ወይ ብዬ ለማሰብ ብሞክር ብዥ አለብኝ፡፡ ወይ ዝቅጠት!

‹‹ጨረስክ?›› አልኩት ትክት እንዳለኝ ከፊቴ እያስታወቀ። ‹‹ሁለተኛው የዚህ አገር ምሁራን ችግር ምን እንደሆነ ታውቃለህ?›› ብሎ ጠየቀኝ። ‹‹የነበሩ መንግሥታት ምሁራንን ስለማይወዱ ተስፋ ቢስ ሆነው ነው ሲባል የሰማሁ መሰለኝ…›› አልኩት ደግሞ ምን ሊል ነው እያልኩ። ‹‹እንዲያ ቢሆን ይሻል ነበር። መጨቆንና መገፋት አልነበረም አልልህም፡፡ ግን… ነገር ግን…›› አለኝ እንድጠይቀው እየገፋፋኝ። ‹‹ምን ይሆን?›› አልኩት። ‹‹የምሁራኑ ችግር አድርባይነትና የጋን ውስጥ መብራት መሆን ነው፡፡ መንግሥት ምሁራንን ይጠላል በሚባለው ሽፋን ስንቱ መሰለህ ብኩርናውን ለሳንቲም የሸጠው… ስንቶቹ መሰለህ የገዛ ጓደኞቻቸውን አሳልፈው የሰጡት… በዚህ ላይ ደግሞ ትውልዱን ለማነፅ ምንም ፍላጎት ስለማያሳዩ ዕውቀታቸው ምን ያህል እንደሆነ አይገባህም…›› ብሎኝ በንዴት ሳቀ። የንዴት ሳቅ ውስጥን እንደ አሲድ ይበላል ሲባል የሰማሁ መሰለኝ፡፡ አሲዳም ዘመን! 

እንዲህ ሳወራ ያለችኝ ቀን እየተሟጠጠች በማለቋ ወደ ቤቴ ማዝገም ግድ አለኝ። ድካም ቀስ እያለ መላ ሰውነቴን ይጫወትበታል። ይኼን ጊዜ የባሻዬ ልጅ፣ ‹‹እህ ወዴት ነው?›› አለኝ። ‹‹ዛሬስ በጣም ደከመኝ በጊዜ ቤት ልግባ ብዬ ነው…›› አልኩት። ‹‹እጅ አትስጥ፣ እርጅና እንደሆነ ሲመጣ አይታወቅበትምና ቶሎ ብለህ ጉልበት የሚተካ ነገር ፈላልግ…›› ብሎኝ ሲያበቃ፣ ‹‹አንበርብር ቀድሞ መዘየድ ኋላ ከመንፈራገጥ ያድናል። የረጅም ጊዜ ራዕይ  ማስፈጸሚያ ቁልፉ ተተኪ ትውልድ ነው። እባክህን እንደው ለእኔ ስትል አንድ ልጅ ዱብ አድርግ…›› ብሎኝ አረፈው። እኔም እሾህን በእሾህ ጥርስ የነቀልኩበት ስለሆነ፣ ‹‹እሱን ሂድና ለአጉል ፖለቲከኞች ንገር…›› አልኩታ። ተሳስቀን እንደተለያየን ከወደ ታች ሠፈር አዛውንቱ ባሻዬ በዝግታ እየተራመዱ ሲጠጉኝ አየኋቸው። እንደተደራረስን፣ ‹‹ከየት ነው እንዲህ በጥድፊያ?›› አልኳቸው። ችኮላቸው የጤና አይመስልም። ‹‹አንድ ወዳጄ ልጁ ከውጭ አገር መጥቶለት እንኳን ደስ አለህ ለማለት ነው የምሮጠው…›› ብለውኝ በቅጡ ሳያናግሩኝ ገሰገሱ። የሰው ደስታ ደስታቸው ሐዘኑ ሐዘናቸው ነው ባሻዬ። አንዳንዴ ስለባሻዬ ሳስብ አንዳንድ የምናፍቃቸው እሴቶች መገኛ ብቸኛ ደሴት ይመስሉኛል። የሚያስፈልገን እንዲህ ዓይነቱ ደሴት ነው አትሉም ታዲያ!

ገርበብ ያለውን የቤቴን ሳንቃ ከፍቼ ስገባ ማንጠግቦሽ ነጠላዋን እየተከናነበች ወጥታ ለመሄድ ትጣደፋለች። ‹‹ወዴት ነው ከመሸ?›› አልኳት ለዘለዓለም ጥላኝ ትሄድ ይመስል። ወይ ፍቅር አትሉም? ‹‹እከሊት እኮ ወንድሟ ከዕገታ ተለቆላት እንኳን ደስ አለሽ አትላትም?›› ብላ መለሰችልኝ። በመቀጠልም፣ ‹‹አይ የአርባ ቀን ዕድል አይ መታደል!›› እያለች ወጥታ ስትሄድ፣ ‹‹ከሞት መትረፍ በአርባ ቀን ዕድል? እሱም በስንት ዕድል!›› ማለት እያሰኘኝ ድካም አሸንፎኝ አልጋዬ ላይ ተዘረርኩ። ማንጠግቦሽ አመሻሽታ ስትመጣ ቀስቅሳኝ እራት ብላ አለችኝ፡፡ ራቴን እያቀራረበች፣ ‹‹እ.ህ.ህ…›› ትላለች፡፡ የእህ.ህ.ታው መደጋገም ቢያሳስበኝ፣ ‹‹ምን ተፈጠረ ደግሞ?›› አልኳት፡፡ ‹‹ምን የማይፈጠር ነገር አለ? ሰው በገዛ አገሩ ስደተኛና መጤ ተደርጎ ሲገደልና ሲፈናቀል መንግሥት እንዴት ዝም ይላል? በገዛ አገሩ እየተገደለ የሚፈናቀል ዜጋስ እንዴት አገር አለችኝ ይላል?›› እያለች እዬዬዋን ስታቀልጠው በቤኒሻንጉል ጉምዝ መተከል ዞን ሥቃይ የሚቀበሉ ወገኖቻችን ጉዳይ ትዝ አለኝ፡፡ መንግሥት ዜጎች በገዛ አገራቸው ሲገደሉ፣ ስደተኛና ተፈናቃይ ሲሆኑ ምን እያደረገ ይሆን? ‹‹በዝቅተኛ ደረጃ ያሉ አመራሮችና ካድሬዎች በፈጸሙት ስህተት…›› እየተባለ እስከ መቼ ሰበብ ይደረደራል? እንደ ዜጋም እንደ አገርም ይህንን ኃጢያት ካላራገፍን አሁንም ችግር አለ፡፡ ችግሩ ሲገፋ ደግሞ መርገም ይሆናል፡፡ መርገምቱን ለማስቀረትና በደለኞች ከኃጢያታቸው እንዲነፁ ንሰሐ ይግቡ፡፡ ካልገቡ ግን የግፈኞቹ ዓይነት ፅዋ ሲሞላ መጨረሻቸው እንደ ሕወሓት ይሆናል፡፡ መልካም ሰንበት!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት