Saturday, May 25, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ወደ ኃይሌ ጋርመንት የተዘዋወረው የአትክልት ተራ አገልግሎት መስጠት ጀመረ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከጃንሜዳ ወደ ኃይሌ ጋርመንት የተዘዋወረው የአትክልት ተራ ገበያ፣ ሐሙስ ታኅሳስ 8 ቀን 2013 ዓ.ም. አገልግሎት መስጠት ጀመረ፡፡ በዕለቱ ከጠዋቱ 2፡00 ሰዓት አካባቢ በሥፍራው ተገኝተው ለአካባቢው ነዋሪ አገልግሎት መስጠት መጀመሩን ያበስራሉ ተብለው ሲጠበቁ የነበሩት ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ በመጋዘን ውስጥ አትክልትና ፍራፍሬ ባለመግባቱ ምክንያት በቦታው አለመገኘታቸው ታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክት ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፣ የተለያዩ አኅጉረ ስብከት ሊቃነ ጳጳሳት፣ የቅዱስ ሲኖዶስ አባላትና ምክትል ከንቲባዋ ወ/ሮ አዳነች በጃንሜዳ ርክክብ አድርገው አዲስ ወደ ተዘጋጀው አትክልት ተራ ያቀኑ ቢሆንም፣ በወቅቱ በአዲሱ የአትክልት ገበያ፣ ለገበያ የሚውል አትክልትና ፍራፍሬ ሳይገባ በመቅረቱ የከንቲባዋ የርክክብ መርሐ ግብር ሳይከናወን መቅረቱን መረዳት ተችሏል፡፡

ምንም እንኳን በዕለቱ ምክትል ከንቲባዋ በሥፍራው ተገኝተው ርክክብ ባይፈጽሙም የአዲስ አበባ ከተማ ንግድ ቢሮ ኃላፊ አቶ አብዱልፈታ የሱፍ በመርሐ ግብሩ ላይ በመገኘት፣ ወደ ኃይሌ ጋርመንት አካባቢ የተዘዋዋረውን የአትክልት ተራ አገልግሎት መስጠት መጀመሩን ለአካባቢው ነዋሪዎች አስታውቀዋል፡፡

የኮሮና ወረርሽኝ መከሰቱን ተከትሎ ፒያሳ አካባቢ የሚገኘው የአትክልት ተራ የገበያ ሥፍራ በጊዜያዊነት ጃንሜዳ መዘዋወሩ የሚታወስ ነው፡፡ በሥፍራው በአትክልትና ፍራፍሬ ንግድ ተሰማርተው ለነበሩ ዕጣ ለወጣላቸው ሕጋዊ ነጋዴዎች፣ የኃይሌ ጋርመንት የአትክልት ተራ መስጠቱን አቶ አብዱልፈታ በርክክቡ ወቅት አስረድተዋል፡፡

በአጭር ጊዜ ተገንብቶ ለአገልግሎት የበቃው የኃይሌ ጋርመንት የአትክልት ተራ የገበያ ማዕከል ለጅምላ ንግድ የሚውሉ 48፣ ለችርቻሮ የሚውሉ 504 በድምሩ 552 መሸጫ ሱቆች አካቶ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ኃላፊው አብራርተዋል፡፡

በመጀመርያ ቀን የግብይት ሒደት በሕገወጥ መንገድ የአየር በአየር ሽያጭ እንደነበር፣ ይህንንም ችግር በቀጣይ የግብይት ሒደት ላይ የሚፈታ መሆኑን አብዱልፈታ ጠቁመዋል፡፡

የገበያ ማዕከሉ ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል የፈጠረ መሆኑን የገለጹት አቶ አብዱልፈታ በቀጣይም በጀሞ፣ በሲኤምሲ፣ በገርጂ፣ በጉለሌና በኮልፌ አካባቢዎች የገበያ ማዕከላት ተገንብተው በአጭር ጊዜ ውስጥ ለሥራ ዝግጁ እንደሚሆኑ አክለዋል፡፡

የገበያ ማዕከሉ አብዛኛውን ሼዶች ለግብይት አመቺ ሆነው የተዘጋጁ መሆናቸውን የገለጹት አቶ አብዱልፈታ፣ አንዳንድ ያላለቁ ሥራዎችም በአጭር ጊዜ ውስጥ ተጠናቀው አገልግሎቱ በተሟላ ሁኔታ እንደሚካሄድ አስረድተዋል፡፡

የገበያ ማዕከሉ የመንገድ፣ የኤሌክትሪክ፣ የመፀዳጃ ቤትና ሌሎች አስፈላጊ የመሠረተ ልማት ዝርጋታዎች ከማሟላት ባለፈ ከ120 በላይ ተሽከርካሪዎችን የሚይዝ 3,600 ካሬ ሜትር የመኪና ማቆሚያና 300 ሜትር ቁመትና 40 ሜትር ስፋት ያለው ከዋናው መንገድ ጋር የሚያገናኝ መንገድ እንዳለውም አክለው ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን አማካይነት በአንድ ቢሊዮን ብር ወጪ መገንባቱንና 80 ሺሕ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ማረፉም ተገልጿል፡፡ በመጀመርያ ምዕራፍ የተገነቡት 14 ሼዶች ሲሆኑ፣ እያንዳንዱ ሼድ 70 ሜትር ቁመትና 6.6 ሜትር ስፋት አላቸው፡፡

በርክክቡ ወቅት የተወሰኑ ነጋዴዎች ቦታው ለመገበያያ አመቺ አለመሆኑን፣ በተለይም ደግሞ ለትራንስፖርት አስቸጋሪ መሆኑ በሥራቸው ላይ ችግር ሊፈጥርባቸው እንደሚችል ሥጋታቸውን ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

በአዲሱ ገበያ እንደ አዲስ ሥራ መጀመራቸው ጫና እንደሚኖረው፣ የገበያ ሥፍራውንም ለማላመድ ጊዜ እንደሚፈጅባቸውና መንግሥትም እንዲህ ዓይነት ቦታዎችን ሲያዘጋጅ ነጋዴዎችን በቅድሚያ ቢያናግር ኖሮ ሥጋት አይፈጠርም ሲሉ ቅሬታቸውን አሰምተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች