Friday, September 29, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ፈቃዳቸው የተሰረዘ የማዕድን ኩባንያዎች ይዞታ ለአዲስ ኩባንያዎች ሊሰጥ መሆኑ ተጠቆመ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ሰሞኑን ፈቃዳቸው በተሰረዘ 38 የማዕድን አምራች ኩባንያዎችናነዳጅ ፍለጋ ኩባንያዎች ይዞታ ለአዲስ ኩባንያዎችን በግልጽ ማስታወቂያ ለመስጠት የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር መዘጋጀቱ ተጠቆመ። 

ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው ፈቃዳቸው በተሰረዘ ኩባንያዎች የማዕድንና የነዳጅ ድፍድፍ መገኛ ቦታዎች ላይ፣ አዳዲስ ኩባንያዎችን ለመተካት ግልጽ ማስታወቂያው በቀጣዮቹ ጥቂት ሳምንታት ይፋ ይደረጋል፡፡

በሚወጣው ማስታወቂያ ፍላጎታቸውን የሚገልጹ ኩባንያዎች በይዞታዎቹ የሚገኘውን የተፈጥሮ ሀብት ለማልማት የሚያስችል የገንዘብና የቴክኖሎጂ አቅማቸውን በማሳየት፣ የተሻለ አቅም ያላቸው ኩባንያዎች እንደሚመረጡ ለማወቅ ተችሏል።

በቅርቡ ይፋ ይደረጋል በተባለው የማስተዋወቅ ሥራም በወርቅ ማዕድን፣ በታንታለም፣ኮባልትናሊትየም ማዕድናት ክምችትእንዲሁም ድፍድፍ ነዳጅ አለባቸው ተብለው በተለዩ ይዞታዎች ላይ እንደሚሆንም  መረጃያመለክታል። 

በተጨማሪም ፖታሽ፣ ብረትና ጂምስቶን ማዕድናትን ለማምረት ማስታወቂያ እንደሚወጣ ለማወቅ ተችሏል።

በወርቅ ማዕድን ዘርፍ አዲስ ፈቃድ ለመስጠት ማስታወቂያ የሚወጣባቸው በኦሮሚያ፣ በትግራይ፣ በቤኒሻንጉል ጉምዝ፣ በአፋርና በደቡብ ክልል የተለዩ ከካባቢዎች ናቸው።

በፖታሽ ማዕድን ዘርፍም ከፍተኛ የፖታሽ ክምችት እንዳለበት በተረጋገጠው የአፋር ክልል፣ አዲስ ማስታወቂያ እንደሚወጣ መረጃው ያመለክታል።  በአማራ፣ በኦሮሚያና በትግራይ ክልሎች የብረት ማዕድን ክምችት ያለባቸው አካባቢዎች ማስታወቂያ ይወጣባቸዋል፡፡

በጀምስቶን ማዕድን ዘርፍ ደግሞ የተለዩት በአማራ፣ በደቡብ፣ በኦሮሚያ፣ በሲዳማና በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልሎች የሚገኙ ይዞታዎች ናቸው። 

በታንታለም፣ኮባልትናሊትየም ማዕድናት ደግሞ በሲዳማ፣ በኦሮሚያና በቤኒሻንጉል ጉምዝ የሚገኙ የተለዩ ይዞታዎች አዲስ ማስታወቂያ እንደሚወጣባቸው የሚኒስቴሩ መረጃ ያስረዳል።

በድፍድፍ ነዳጅ ረገድ በሶማሌ፣ በኦሮሚያና በአማራ ክልል የተለዩ ይዞታዎች ላይ አዲስ ማስታወቂያ እንደሚወጣ ታውቋል።

የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር ባለፈው ሳምንት በሰጠው መግለጫ፣ የማዕድን ፈቃድ አውጥተው በተገቢው መንገድ ጥቅም ላይ ያላዋሉ ተቋማትን ፈቃድ እንደሰረዘ መግለጹ ይታወሳል።

ዕርምጃው የተወሰደባቸው ተቋማት 63 ሲሆኑ፣ ከእነዚህ ውስጥ ውስጥ 38 ተቋማት በማዕድን ምርት ላይ ተሰማርተው የነበሩ መሆናቸውን መግለጫውን የሰጡት ሚኒስትሩ አቶ ታከለ ኡማ (ንጂነር) ገልጸዋል። ቀሪዎቹ 25 ተቋማት ደግሞ በማዕድን ምርምር ላይ ተሠማርተው የነበሩ ናቸው ብለዋል።

በማዕድን ዘርፍ ተሠማርተው በነበሩት ተቋማት ላይ ዕርምጃው የተወሰደበት ምክንያት በተገቢው ወቅት የተሰጣቸውን ፈቃድ ባለማደሳቸው፣ በውል የገቡትን ግዴታ ባለማክበራቸው፣ ከአቅም በታች በማምረታቸውእንዲሁም የሮያሊቲ ክፍያ ባለመፈጸም እንደሆነ ሚኒስትሩ በወቅቱ አስረድተዋል፡፡

ሚኒስትሩ በማዕድን ዘርፍ ያሉ የተለያዩ መረጃዎች የተደራጁበት፣ እንዲሁም ፈቃድ የመውሰድና የማመልከት ሒደቱን የሚያቀልና ዘመናዊ የሚያደርግ የካዳስተር ፖርታል ሥርዓት በመዘጋጀት ላይ እንደሚገኝ አያይዘው ገልጸዋል፡፡

ካዳስተር ፖርታሉ በኢንተርኔት የማዕድን ማምረትና የምርምር ፈቃድ ማውጣት የሚቻልበት፣ እንዲሁም የማዕድን ሀብት የኢንቨስትመንት መረጃዎች የተካተቱበት ሲሆን፣ ዘርፉን በቴክኖሎጂ የሚደግፍና ግልጽነትን በማስፈን በኩል ሚናው የጎላ እንደሚሆንም ተናግረዋል፡፡

ባለፉት አምስት ወራትም ከማዕድን ዘርፍ 302.9 ሚሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱን የገለጹት ሚኒስትሩከማዕድን ምርት የሚገኘው ገቢ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ እንደሚገኝና ለዚህም የኮንትሮባንድ ንግድን ለመቆጣጠር ከባለድርሻ አካላት ጋር የተሠራው የቅንጅት ሥራ፣ የማዕድን ምርት ማነቆ የሆኑ የመሠረተ ልማትና የአቅርቦት ችግሮችን መፍታት መቻሉ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች