‹‹ፍርድ ቤት በአቅራቢያችን ይሰየምልን›› ጥያቄ ውድቅ ተደረገ
ከታሰሩበት ማረሚያ ቤት እስከ ፍርድ ቤት የሚጓዙበት ርቀት በትራፊክ የተጨናነቀ በመሆኑ ለማንኛውም ጥቃት ተጋላጭ እንደሚያደርጋቸው በመግለጽ፣ ‹‹ፍርድ ቤት ለመገኘት አንችልም፤›› በማለት በተደጋጋሚ ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ የቀሩት እነ አቶ ጃዋር መሐመድ፣ በቀጣይ ቀጠሮ በተመሳሳይ ምክንያት ‹‹አንቀርብም›› የሚሉ ከሆነ ተገደው እንዲቀርቡ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ሰጠ፡፡
የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልዳታ ምድብ የሕገ መንግሥትና የሽብርተኝነት አንደኛ ወንጀል ችሎት ትዕዛዙን የሰጠው ታኅሳስ 8 ቀን 2013 ዓ.ም. ሲሆን፣ በፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ መሠረት የማይቀርቡ ከሆነ፣ ተገደው እንዲቀርቡ የተባሉት አቶ ጃዋር መሐመድ፣ አቶ በቀለ ገርባ፣ አቶ ሐምዛ አዳነና አቶ ሸምሰዲን ጠሃ ናቸው፡፡
ፍርድ ቤቱ ተከሳሾቹ በተሰጠው የቀጠሮ ቀን ለመቅረብ ፈቃደኛ የማይሆኑ ከሆነ ተገደው እንዲቀርቡ ትዕዛዝ የሰጠው በአቶ ጃዋርና በአቶ በቀለ ፊርማ ኅዳር 17 ቀን 2013 ዓ.ም. ለፍርድ ቤቱ የቀረበው አቤቱታ ውድቅ በመደረጉ ነው፡፡
ተከሳሾቹ በተጠቀሰው ቀን በማረሚያ ቤቱ በኩል በጻፉት የአቤቱታ ደብዳቤ እንደገለጹት፣ በአገሪቱ ፖለቲካ ውስጥ ካላቸው ሚናና ሲነዛባቸው ከነበረው የሚዲያ ፕሮፓጋንዳ አንፃር፣ ለማንኛውም ጥቃት ተጋላጭ ይሆናሉ፡፡፡ ከሚገኙበት እስር ቤት እስከ ልደታ ፍርድ ቤት ድረስ ያለው ርቀትና የተጨናነቀ መንገድ ተጋላጭነታቸውን የበለጠ ከፍ ያደርገዋል፡፡ በመሆኑም አሁን ካለው የፖለቲካ ትኩሳት ጋር ተደማምሮ አገሪቱን ወደ ቀውስ ሊወስዳት ስለሚችል በቀጣይ ለሚኖራቸው ቀጠሮዎች ታስረው በሚገኙበት አካባቢ ጊዜያዊ ችሎት እንዲቋቋምላቸው ጠይቀው እንደነበር ይታወሳል፡፡
ፍርድ ቤቱ ተከሳሾቹ ያቀረቡትን ጥያቄ ለፍርድ ቤቱ በማስተላለፍ ውሳኔውን እንዲያሳውቅ በሰጠው ትዕዛዝ መሠረት ምላሽ ሰጥቷል፡፡ ፍርድ ቤቱ ምላሹን በችሎት በንባብ እንዳሰማው፣ ፍርድ ቤቱ ችሎቶችን የሚያቋቁመው ሕገ መንግሥቱን መሠረት አድርጎ በወጣው ‹‹የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ማደራጃ አዋጅ ቁጥር 322/95 ድንጋጌ መሠረት በዕቅድና በጥናት መሆኑን ገልጾ፣ ፍርድ ቤቱ ካመነበትና ትዕዛዝ ከሰጠ ግን ማቋቋም ይችላል፡፡
ፍርድ ቤቱ የአስተዳደሩን ምላሽ መሠረት አድርጎ በሰጠው ብይን፣ ተከሳሾቹ ያቀረቡት ምክንያት በቂ ምክንያት አለመሆኑን በመጠቆም፣ ጥያቄያቸው ውድቅ መደረጉን በመግለጽ፣ ክሳቸውን በልደታ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ የሕገ መንግሥትና ሽብርተኝነት ወንጀል ችሎት እየቀረቡ እንዲከታተሉ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡
ፍርድ ቤቱ በተከሳሾቹ ላይ ትዕዛዝ ሲሰጥ፣ ‹‹በትዕዛዙ መሠረት የማይቀርቡ ከሆነ የኃይል ዕርምጃ ተወስዶ እንዲቀርቡ፤›› በማለቱ፣ የተከሳሾቹ ጠበቆች በቃላት አጠቃቀሙ ላይ ቅሬታቸውን አቅርበዋል፡፡ መቶ በመቶ እንደሚቀርቡ እርግጠኛ መሆናቸውን ገልጸው፣ አንቀርብም ቢሉ ‹‹የኃይል ዕርምጃ ተወስዶ፤›› የሚለው ግን ‹‹ተገደው እንዲቀርቡ›› ተብሎ እንዲሻሻል ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል፡፡
ከሳሽ ዓቃቤ ሕግ ጠበቆቹ ያቀረቡትን አቤቱታ (ቅሬታ) በመቃወም ለፍርድ ቤቱ በሰጠው አስተያየት፣ ቅሬታውን ያቀረቡት ተከሳሾቹ ቢሆኑ ያላቸውን የሕግ ግንዛቤ ከግምት ውስጥ በማስገባት ትክልል ሊሆን ይችል እንደነበር ጠቁሞ፣ በሕግ ባለሙያዎች (ጠበቆች) መቅረቡ ሆን ተብሎ ታዳሚ የተለየና ያልሆነ አመለካከት ይዞ እንዲወጣ ለማድረግ አስበው እንጂ፣ ‹‹ተመጣጣኝ ዕርምጃ ወስዶ ያቅርብ›› የሚለው የሕግ ቋንቋ መሆኑንና ምን ማለት እንደሆነም ጠፍቷቸው እንዳልሆነ ገልጿል፡፡ ትክክልም እንዳሆነም አክሏል፡፡
ፍርድ ቤቱም የተጠቀመው ቃላት በሕግ ቋንቋ የተለመደና ችግር የሌለው መሆኑን በመግለጽ፣ በ‹‹ኃይል›› የሚለው፣ ‹‹አስገድዶ›› በሚል እንዲለወጥ የሚል ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡
በመጨረሻም ፍርድ ቤቱ አቶ ጃዋር፣ አቶ በቀለ፣ አቶ ሐምዛና አቶ ሸምሰዲን በቀጣይ ቀጠሮ እንዲቀርቡ፣ በቀረበባቸው ክስ ላይ ለቀረቡት የመጀመርያ የክስ መቃወሚያ ዓቃቤ ሕግ የሰጠው ምላሽ በማረሚያ ቤት ደርሷቸው ምላሻቸውን በቀጣይ ቀጠሮ እንዲሰጡ ትዕዛዝ ሰጥቶ፣ ብይን ለመስጠት ለጥር 25 ቀን 2013 ዓ.ም. ቀጠሮ ሲሰጥ፣ በጠበቆቹና ችሎት በተገኙት ተከሳሾች ቅሬታና ተቃውሞ ተነስቷል፡፡
ተከሳሽ አቶ ደጀኔ ጣፋ ባቀረቡት የቅሬታ አቤቱታ ለፍርድ ቤቱ እንዳስረዱት፣ የተሰጣቸው ቀጠሮ አንድ ወር ከ18 ቀናት ነው ካሉ በኋላ፣ ‹‹ለፍርድ ቤቱ አይከብድም?›› የሚል ጥያቄ አንስተዋል፡፡ አክለውም የተከሰሱት አብዛኛዎቹ የአንድ ፖለቲካ ፓርቲ አባል መሆናቸውን ጠቁመው፣ መንግሥት ዴሞክራሲ ለማምጣት እየሠራ መሆኑን በሚገልጽበት ወቅት ረዥም ቀጠሮ መስጠቱ ተገቢ እንዳልሆነና የቀጠሮው ጊዜ ሊያጥር እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ አገሪቱን ከዱላ ትግል ወደ ዴሞክራሲ ትግል ለመቀየር ሰላማዊ ትግል በማካሄዳቸው መታሰራቸውን ጠቁመው፣ ቀደም ባለው አመራር (ኢሕአዴግ) በታሰሩበት ጊዜ እንኳን ይህንን ያህል ረዥም ቀጠሮ ተሰጥቶባቸው እንደማያውቅ በመግለጽ፣ ‹‹የዛሬው የችሎት መንፈስ ጥሩ ስላልሆነ የምንለምነው የቀጠሮውን ጊዜ እንዲያሳጥርልን ነው፤› ብለዋል፡፡
በችሎት ያልተገኙትንና የተገኙትን ተከሳሾች (22 ተከሳሾች) በመወከል ጥብቅና የቆሙት ጠበቆች (ስምንት ናቸው) ባቀረቡት አቤቱታ ለፍርድ ቤቱ እንዳስረዱት፣ ጉዳዩ ስሜትን የሚያነሳሳ (ሴንሴቲቭ) እና የዓለም አቀፍ ትኩረትን የሳበ ነው፡፡ ደንበኞችን ለለውጡ የአንበሳውን ድርሻ የተወጡ ናቸው፡፡ የቀረበባቸው ክስ ፖለቲካና የድራማ ክስ ነው፡፡ የቀጠሮ ቀን መራዘም የለበትም፡፡ ምክንያቱም በግንቦትና ሰኔ ወር ለሚደረገው ምርጫ የሚያደርጉትን የዝግጅት ጊዜ ያጣብባል፡፡
በመሆኑም ትዕዛዝ የተሰጠበት ጊዜ ስለረዘመ ሊያጥር እንደሚገባ በመግለጽ በተሰጠው ቀጠሮ ቀን ላይ ቅሬታቸውን አቅርበዋል፡፡
ዓቃቤ ሕግ ተከሳቹና ጠበቆቹ ባነሱት ቅሬታና ተቃውሞ ላይ ባቀረበው ምላሽ ለፍርድ ቤቱ እንዳስረዱት፣ ጠበቆቹም ሆኑ ተከሳሾቹ እያቀረቡ ያሉት የፖለቲካ ክርክር በመሆኑ ዓቃቤ ሕግ የሚሰጠው ምላሽ እንደሌለ አስረድቷል፡፡ ለማፈን፣ ከምርጫ ውጪ ለማድረግና ሌሎችም የሚለው መከራከሪያ ሐሳብ ከተከሳሾች ቢነሳ ከብሶት አንፃር ሊሆን ስለሚችል መረዳት ቢቻልም፣ በተለይ በሕግ ባለሙያዎች (ጠበቆች) መቅረቡ ተገቢና የማይጠበቅ ከመሆኑ አንፃር ከክሱ ጋር የማይገናኝ በመሆኑ ምላሽ ሊሰጥ እንደማይችል አስረድቷል፡፡ የፖለቲካ መልስ መስጠት የሚችል አካል ካለ ቀርቦ መስጠት እንደሚችልም አክሏል፡፡
ፍርድ ቤቱ በመጨረሻም ጠበቆቹና ተከሳሾቹ ባቀረቡት ቅሬታና አቤቱታ ላይ እንዳስረዳው፣ ‹‹ችሎቱ ስሜቱ ጥሩ አይደለም፤›› መባሉ ትክክል አይደለም፡፡ ችሎቱ የተለየ ምክንያት የለውም፡፡ ምርጫን በሚመለከትም ‹‹ለምርጫ ተብሎ የሚረዝም ወይም የሚያጥር ቀጠሮ አይኖርም፤›› ካለ በኋላ፣ ቀደም ብሎ በሰጠው ትዕዛዝ ለጥር 25 የሰጠውን ቀጠሮ በመቀየርና በማሳጠር ለጥር 4 ቀን 2013 ዓ.ም. ብይን ለመስጠት ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
የተከሳሾች ጠበቆች አቶ መስተዋርድ ተማም፣ አቶ ሸምሰዲን ጠሃና ሃምሳ አለቃ የዓለም ወርቅ አሰፋ ቤተሰቦች በውጭ አገር ስለሚኖሩ ለሌሎች ተከሳሾች እንደተፈቀደው ቤተሰቦቻቸውን በስልክ እንዲያገኟቸው ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው ለፍርድ ቤቱ አመልክተዋል፡፡ ሌሎቹም ተከሳሾች ቤተሰቦቻቸው በአገር ውስጥ ቢሆኑም ሊያገኟቸው እንዳልቻሉ ገልጸው፣ እነሱም በስልክ እንዲያገኟቸው አመልክተው፣ ለሌሎች ተከሳሾች እንደሚደረገው ማረሚያ ቤቱ በስልክ እንዲያገኙ እንዲያደርግና አገር ውስጥ ሆነውም ቤተሰቦቸውን ማግኘት ላልቻሉ ተከሳሾች እንዲያገናኟቸው እንዲደረግ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡