የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የብድር ወለድ ምጣኔውን ሊከልስ መሆኑንና በሚሰጣቸው የተለያዩ አገልግሎቶች ላይ የታሪፍ ማስተካከያ ሊያደርግ መሆኑ ተገለጸ።
በአሁኑ ወቅት የባንኩ የወለድ ምጣኔ በአማካይ 8.6 በመቶ እንደሆነ የባንኩ የስትራቴጂክ ዕቅድና ክትትል ዳይሬክተር አቶ መሸሻ ደሜ ለሪፖርተር ገልጸው፣ የአገሪቱ አማካይ የብድር ወለድ ምጣኔ ግን 14 በመቶ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ከዚህ አንፃር የንግድ ባንክ የወለድ ምጣኔ አነስተኛ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡
ባንኩ ከገበያ በታች እያበደረ አትራፊ አይደለም የሚሉ አካላት እንዳሉ የገለጹት ዳይሬክተሩ፣ ባንኩ እየሠራና እየደገፈ ያለውን አገራዊ ሚና መዘንጋት የለበትም ብለዋል፡፡
የንግድ ባንክ የብድር ክምችት 784 ቢሊዮን ብር መድረሱን የገለጹት ዳይሬክተሩ፣ ልማትን ሊያፋጥኑ ለሚችሉ ፕሮጀክቶች በዝቅተኛ የወለድ ምጣኔ ብድር እያቀረበ መሆኑንም አስረድተዋል።
ከዚህም በተጨማሪ አብዛኛውን ብድር የልማት ድርጅቶችን ለማገዝ በዝቅተኛ ወለድ እንደሚሰጥ፣ መንግሥት ከውጭ ለሚያስመጣቸው እንደ ስንዴ፣ ዘይትና ስኳር የመሳሰሉ ምርቶችንና ሌሎች ፕሮጀክቶችን ለመደገፍ ያለ ምንም የወለድ ምጣኔ (በዜሮ ወለድ) ሲሰጥ መቆየቱን አስታውሰዋል፡፡ አሁን ግን ባንኩ በገበያ ዋጋ የተመሠረተ የዋጋ ማስተካከያ ማድረግ እንዳለበት አምኖ እየተንቀሳቀሰ ነው ብለዋል፡፡
የባንኩን ተወዳዳሪነትና ትርፋማነት ለማሳደግ የብድር ወለድ ምጣኔ ላይ ከአንድ እስከ ሁለት በመቶ ጭማሪ ለማድረግ የሚያስችል ጥናት ተጠንቶ፣ ለባንኩ ቦርድ መቅረቡን ከዋና ዳይሬክተሩ ገለጻ መረዳት ተችሏል።
ከዚህ በተጨማሪም ባንኩ ከሚሰጣቸው የተለያዩ አገልግሎቶች አንዳንዶችን በነፃ፣ አንዳንዶቹን ደግሞ በዝቅተኛ ዋጋ እየሰጠ መሆኑን፣ በእነዚህ አገልግሎቶችም የዋጋ ማስተካከያ ለማድረግ መታሰቡንም ተነግሯል።
የቁጠባን ባህል ለማሳደግና ለማዳበር በሚል በነፃ ሲሰጡ የነበሩ አገልግሎቶችን አሁን ባንኩ ያለበትን ቁመናና ተወዳዳሪነት ለማሳደግ ተመጣጣኝ ክፍያ መከፈል ይኖርበታል ሲሉ አቶ መሸሻ አስረድተዋል።
በዚህም በየትኛውም የባንክ ኢንዱስትሪ በነፃ የማይሰጡ ለምሳሌ የባንክ ደብተር ባለቤትነትና የሞባይል ገንዘብ ማንቀሳቀስ ዓይነት አገልግሎቶች፣ እስካሁን ምንም ዓይነት ክፍያ አይፈጸምባቸውም ነበር ብለዋል
በተጨማሪም የገንዘብ ማስተላለፍና መቀበል ዓይነት አገልግሎቶች ደግሞ ባንኩ በጣም ዝቅተኛ በሆነ ዋጋ የሚሰጣቸው አገልግሎቶች በመሆናቸው፣ ዋጋ ለማስተካከል እየሠራ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል።
አሁን ሊደረግ የታሰበው የወለድ ምጣኔ ማስተካከያ የተበዳሪዎችን የአደጋ ተጋላጭነት ባገናዘበ መንገድ እንደሚሆን አቶ መሸሻ አክለው ገለጸዋል።
በተያዘው ዓመት ባንኩ ጠቅላላ ሀብቱን ወደ አንድ ትሪሊዮን ብር ለማሳደግ እየሠራ እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን፣ በአሁኑ ጊዜ 877 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ጠቅላላ ሀብት እንዳለው ተነግሯል፡፡
በተያያዘ ዜና የባንኩን አፈጻጸምና አሁናዊ ቁመናውን ለመገምገም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የበጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፣ ልደታ በሚገኘው የባንኩ ቅርንጫፍ ለመስክ ምልከታ ባለፈው ሳምንት ተገኝቶ ነበር።
በወቅቱ የንግድ ባንክ አሠራሩን ከተለመደው ውጣ ውረድ የበዛበት የመንግሥት ቢሮክራሲ በማላቀቅ፣ በሚሰጣቸው አግልግሎቶች ዙሪያ ከደንበኞች የሚነሱ ቅሬታዎችን እንዲፈታ በቋሚ ኮሚቴው አባላት ተጠይቋል፡፡
በመላ አገሪቱ ባሉ 1,600 በላይ ቅርንጫፎቹ ከ63,000 በላይ ሠራተኞችን ይዞ እንደሚንቀሳቀስ የሚነገርለት ባንኩ፣ በአግልግሎቱ ዙሪያ የሚነሱ ቅሬታዎች እየተበራከቱ መምጣታቸው ተነግሯል።
በወቅቱ በቦታው የተገኙት የቋሚ ኮሚቴው አባላት ንግድ ባንክ ምንም እንኳ በርከት ያሉ የአገልግሎት ቅርንጫፎች ቢኖሩትም፣ በአግልግሎቱ ላይ በተደጋጋሚ የሚነሱ ቅሬታዎች እየተለመዱ መምጣታቸውን አስረድተዋል፡፡
በገንዘብ ማውጫ ማሸኖች በቂ ገንዘብ አለመኖርና የማሽኖች አለመሥራት፣ የተንዛዛ አገልግሎት፣ የሲሰተም ብልሽት፣ በተደጋጋሚ ሠልፍ የበዛባቸው ቅርንጫፎችና ደንበኞችን የማያስተናግዱ ብዙ መስኮቶች መበራከትና መሰል ችግሮች በቋሚ ኮሚቴ አባላቱ ተነስተዋል፡፡
ኅብረተሰቡ በመንግሥት ተቋማት ላይ ያለው እምነት ከፍተኛ በመሆኑ ምክንያት የባንኩን የደንበኞች ቁጥር አበዛው እንጂ፣ ባንኩ ያለበት ቁመና ወቀሳ የበዛበት ስለሆነ ደንበኞች በተደጋጋሚ የሚያነሱዋቸውን ችግሮች በፍጥነት እንዲፈታ ጠይቀዋል፡፡