በአገሪቱ እየተባባሰ ከመጣው የውጭ ምንዛሪ እጥረት ጋር ተያይዞ የተፈጠረው ጫና፣ የቆዳ ኢንዱስትሪውን እየፈተነው በመምጣቱንና አምራቾችን ከገበያው እያስወጣቸው መሆኑን የኢትዮጵያ ቆዳ ኢንዱስትሪ ልማት ማኅበር አስታወቀ፡፡
የማኅበሩ አመራሮች በተለይ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ፋብሪካዎች ለምርት የሚያስፈልጋቸውን ግብዓትና የመለዋወጫ ዕቃዎች ከውጭ ማስገባት ባለመቻላቸው፣ ፋብሪካዎቻቸውን መዝጋት የጀመሩ ሲሆን፣ በርካቶች ደግሞ ከማምረት አቅማቸው በመውረድ እስከ አሥር በመቶ ብቻ እያመረቱ ናቸው፡፡
የማኅበሩ ፕሬዚዳንት አቶ ታጠቅ ይርጋ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ባለፉት ጥቂት ወራት ብቻ ከአራት የሚበልጡ አምራቾች ፋብሪካቸውን ሙሉ ለሙሉ የዘጉና ምርት ያቆሙ ሲሆን፣ በርካታ ፋብሪካዎች የማምረት አቅማቸው እስከ አሥር በመቶ በመውረዱ ጥሬ ቆዳ መግዛትም እያቆሙ ነው፡፡
እንደ አቶ ታጠቅ ማብራርያ አምራቾች ለምርቶቻቸው የሚያስፈልጓቸውን ግብዓቶች በተለይም ኬሚካል በማስገባት የሚያስፈልጋቸው የውጭ ምንዛሪ በሚፈልገው ጊዜም ሆነ መጠን ለማግኘት የተቸገሩ ሲሆን፣ በንግድ ባንክ በኩል ያለው አሠራር ዘርፉን ባይተዋር ማድረጉንም ተናግረዋል፡፡
ለዚህም ማሳያ ማኅበሩ በአባልነት ካቀፋቸው አምራቾች ተጨማሪ አቶ ታጠቅ ራሳቸው በሚያስተዳድሯቸው ታዋቂ ፋብሪካዎች በአሁን ሰዓት ምርት መቀነሳቸውንና የጥሬ ቆዳ ግዢ ሙሉ ለሙሉ ማቆማቸውን ጠቅሰዋል፡፡
ለቆዳ ፋብሪካዎች የሚያስፈልጉት ኬሚካልና የመለዋወጫ ዕቃ በምንዛሪ እጥረት ካለማግኘታቸው በተጨማሪም፣ በአገር ውስጥ የሚመረተውን የጨው ግብዓትም በበቂ ሁኔታ ለማግኘት መቸገራቸውን ጠቅሰዋል፡፡
እንደ ማኅበሩ ፕሬዚዳንት ሁሉ ሌሎች አምራቾችም በዘርፉ የገጠማቸውን ፈተናና ውጣ ውረድ በግል ያላቸውን ምሬት ገልጸዋል፡፡ ለአብነትም የኢትዮጵያ ቆዳ ልማት አክሲዮን ማኅበር ኃላፊው አቶ መስፍን ለማ ለሪፖርተር እንዳስረዱት፣ ፋብሪካቸው ጥሬ ቆዳን ለማቆየት የሚያስፈልገው የጨው ምርትም ሆነ ፓውደር የተባለውን ኬሚካል በበቂ መጠን ለማግኘት በመቸገሩ፣ የተገዙ ጥሬ ቆዳዎችን እስከ መጣል ድረስ ተገደዋል፡፡
ምንም እንኳን የጨው ምርት ከአገር ውስጥ ገበያ የሚቀርብ ቢሆንም፣ ከጥቂት ጊዜ ወዲህ በኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ግብዓት ልማት ድርጅት (ኢግልድ) በሞኖፖል እንዲቀርብ መደረጉ ለአምራቾች ችግር መፍጠሩን አንስተዋል፡፡
ምንም እንኳ አምራቾች የጨው አቅርቦትን በተመለከተ ከንግድ ሚኒስቴርና ከኢግልድ ኃላፊዎች ጨምሮ በመወያየት ችግሮችን ለምፍታት ቢሞክሩም፣ በአቅርቦት በኩል ባለው ክፍተት ዘርፉን እየፈተነው መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
ኬሚካልን በተመለከተ ያለው ችግር የከፋ መሆኑን የሚጠቅሱት አቶ መስፍን፣ የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት ከሰባት ወር እስከ አንድ ዓመት ለመቆየት መገደዳቸውን አምርረው ጠቅሰዋል፡፡ በአማራጭነትም የኬሚካል ግብዓት ከአገር ውስጥ ለማሟላት ቢፈልጉም በበቂ መጠን ካለመገኘቱ ባሻገር ብቸኛ አምራቹ የሆነው ደርባ ሲሚንቶ ፋብሪካ ከኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት እጥረት ጋር በተያያዘ የአቅሙን ያህል ማምረት አለመቻሉን አስረድተዋል፡፡
እንደ እሳቸው ማብራርያ ደርባ ሲሚንቶ ፋብሪካ የቆዳ አምራቾችን ለመርዳት ብዙ እርቀት መጓዝ ያለበትን የኃይል እጥረት ለመቅረፍ በራሱ ወጪ ኬብል እስከ መዘርጋት ቢደርስም፣ ከብሔራዊ የኤልክትሪክ ቋት (National Grid) ስላልተለቀቀለት ጥረቱ አለመሳካቱን ታውቋል፡፡
በተመሳሳይ የባህር ዳር ቆዳና የእጅ ጓንት ፋብሪካ፣ የሞጆ ቆዳ ፋብሪካ ኃላፊዎችም ያለባቸውን ተመሳሳይ ችግር በመግለጽ፣ የውጭ ምንዛሪ እጥረቱ አገራዊ ችግር ቢሆንም በመንግሥት በኩል ለአምራች ኢንዱስትሪ የተሰጠው ትኩረት ፍትሐዊ አለመሆኑን ገልጸዋል፡፡
የባህር ዳር የቆዳ ውጤቶችና የእጅ ጓንት አምራች ፋብሪከ ኃላፊ አቶ ግዛው አሰፋ ሲገልጹ፣ የቆዳ አምራች ኢንዱስትሪው ሀብት ፈጣሪ በመሆንና ከፍተኛ የሥራ ዕድል እያበረከተ ያለ ዘርፍ ቢሆንም በመንግሥት ቅድሚያ ከሚሰጣቸው ዘርፍ ውስጥ እንደመሆኑና እንደሚወራለት ያህል የሚገባውን ትኩረት እየተሰጠው አለመሆኑን ይገልጻሉ፡፡
‹‹ይህ ዘርፍ እስከ 90 በመቶ የሚሆነውን ምርት ለውጨ ገበያ እያቀረበ ይገኛል፡፡ በተጨማሪም መንግሥት ብዙ ለሚያወራለት የሥራ ፈጠራ ትርክት የቆዳ ኢንዱስትሪው በአሥርሺዎች የሚቆጠር ሥራ እየፈጠረ ነው፡፡ ነገር ግን በውጭ ምንዛሪ በኩል ያለብንን ችግር ከቁብ ቆጥሮ መፍትሔ ለመስጠት በንግድ ባንክ በኩል ምንም ፍላጎት የለም፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡
ከውጭ ምንዛሪ እጥረቱ ባሻገር ከዓመት በፊት ለኢንዱስትሪው ወይም ለፋብሪካዎቹ የሚያስፈልጉ የመለዋወጫ ዕቃዎች ከቀረጥ ነፃ ይገቡ የነበረ ቢሆንም፣ በቅርቡ ከቀረጥ ነፃ ማበረታቻ መነሳቱ ለአምራቾች ሌላ ፈተና መሆኑን ጨምረው ገልጸዋል፡፡
ለዚያውም የቀረጥ ነፃ ማበረታቸውን ሲያነሳ ለአምራቹ እንኳን ሳያውቅና ቅድመ ምክክር ሳይደረግ መወሰኑን ጨምረው ገልጸዋል፡፡ የውጭ ምንዛሪ እጥረቱን በተመለከተ ሲያብራሩ እንኳን ምንዛሪ ለማግኘት ኤልሲ ለመክፈት በራሱ እስከ አራት ወራት እንደሚፈጅባቸው የጠቀሱት አቶ ግዛው፣ የንግድ ባንክ የአገልግሎትና ለግንባታ ዘርፍ ቅድሚያ በመስጠት የቆዳ ዘርፉ የአበርክቶውን ያህል ፍትሐዊ የምንዛሪ አቅርቦት እየተነፈገው ነው ሲሉ ወቅሰዋል፡፡
አምራቾቹ በማኅበራቸው በኩል ችግሩን ለመፍታት በመንግሥት ትኩረት እንዲሰጠው ያደረጉትን ጥረት ሪፖርተር ለማኅበሩ ፕሬዚዳንት አቅርቦላቸው ነበር፡፡ በሰጡት ምላሽም አቶ ታጠቅ ሲያስረዱ ‹‹በተደጋጋሚ ጥረት አድርገናል፡፡ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የውጭ ምንዛሪን ከሚመለከተው ክፍል ኃላፊዎች የተሰጠን ምላሽ በጣም ተስፋ አስቆራጭ ነው፡፡ አይደለም እናንተ፣ ሚኒስትሩ [የንግድ ሚኒስትሩ] እንኳን ቢመጡ የተለየ ነገር የምናደርገላችሁ ነገር የለም ብለውናል፤›› ሲሉ አቶ ታጠቅ ገልጸዋል፡፡
አሁን ያለውን ችግር መንግሥት ወደ ኋላ መለስ ብሎ ካልፈተሸና ካላሻሻለ፣ በርካታ የማኅበሩ አባሎቻቸውም ሆኑ እሳቸው የሚያስተዳድሯቸው ፋብሪካዎች ከገበያ ውጪ ሊሆኑ እንደሚችሉ፣ እንዲሁም በርካታ ሠራተኞቻቸውን ማቆየት የማይችሉበት ደረጃ ስለሚደርሱ ከአምራችነት ወደ ሌላ የንግድ ዘርፍ ሊገቡ እንደሚችሉ ሥጋታቸውን ገልጸዋል፡፡