ከሦስት ወራት በፊት በአማራ ክልል ጎርጎራ፣ በኦሮሚያ ክልል ወንጪ፣ እንዲሁም በደቡብ ክልል ኮይሻ አካባቢ እንዲሠሩ ታቅደው ይፋ የተደረጉ የገበታ ለሀገር ፕሮጀክቶችን ዓላማ ባለመረዳት ምክንያት፣ በጣም እየተለጠጡ መሆናቸውን በማስረዳት፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ቅሬታቸውን ገለጹ፡፡
ረቡዕ ታኅሳስ 7 ቀን 2013 ዓ.ም. በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የመሰብሰቢያ አዳራሽ አማራ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ አገኘሁ ተሻገር፣ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ፣ እንዲሁም የደቡብ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ርስቱ ይርዳው በተገኙበትና የአገር አቀፍ ዓብይ ኮሚቴ አባላት የነበሩበትን ስብሰባ የመሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የፕሮጀክቶቹን ዓላማ አለመረዳት መኖሩንና የማስፋት ፍላጎቶች መታየታቸውን ገልጸዋል፡፡ ለዕቅዱ መነሻ የሚሆኑና የግል ዘርፉ ሊቀጥልባቸው የሚችላቸውን ጅምር ሥራዎች ማከናወን እንደሆነ በማውሳት፣ ዋነኛ ትኩረቱ ሳቢ የሆነ መዳረሻ መገንባት ላይ ነው ብለዋል፡፡
በዚህም አግባብ በኦሮሚያ ክልል ያለው ፕሮጀክት ከወንጪ እስከ ደንዲ ሐይቅ እንዲለጠጥ፣ በአማራ ክልል ከጎርጎራ ባለፈ ጎንደርንም እንዲያካትት፣ እንዲሁም በደቡብ ክልል ያለው የኮይሻ ዕቅድ እስከ ዳውሮ እንዲደርስ ፍላጎቶች እንዳሉና የተሠሩት ንድፎችም በዚህ አግባብ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡
ይሁንና ፍላጎቶቹ ከሁኔታው ጋር መጣጣም አለባቸው ብለዋል፡፡ ነገር ግን ፕሮጀክቶቹ ተጀምረው እስከሚያልቁ ድረስ የፌዴራል መንግሥት ፕሮጀክቶች እንጂ የክልል ፕሮጀክቶች ባለመሆናቸው፣ የክልል መንግሥታት ይኼንን አድርጉ፣ ያንን አታድርጉ ማለት እንደማይችሉና ሲፈለግ ብቻ ድጋፍ መስጠት እንደሆነ በማሳሰብ፣ ‹‹ፕሮጀክቶቹ ሲጠናቀቁ ቁልፉን እናስረክባቸኋለን፤›› ብለዋል፡፡ የክልሎቹ ፕሬዚዳንቶችም በውይይቱ እንዲገኙ የተደረገውም በዚሁ ዕሳቤ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
ከዚህ በተቃራኒ ፕሮጀክቶቹን የማስፋት ፍላጎት ቢኖርም፣ ከፍላጎት ጋር የሚጣጣም የገንዘብ ማሰባሰብ ሥራ እንዳልተከናወነ በመጥቀስ ትልልቅ ሐሳቦች ቀርበው ገንዘብ ግን እየመጣ አይደለም ብለዋል፡፡
በሌላ ወገን ደግሞ ፕሮጀክቶቹ በትብብር የሚሠሩ ሳይሆኑ ከመንግሥት ካዝና ገንዘብ የመጠበቅ አዝማሚያዎች እንዳሉም በመጠቆም፣ ብቻ ያለ ገንዘብ የሰበሰቡ ደግሞ የክልሉ ገንዘብ በክልሉ ብቻ ጥቅም ላይ እንዲውል ፍላጎት ያላቸው እንዳሉም አልሸሸጉም፡፡