Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትየአትሌቲክስ ፈዴሬሽን ተምሳሌታዊ ጅምር

የአትሌቲክስ ፈዴሬሽን ተምሳሌታዊ ጅምር

ቀን:

ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ከተለጠፈባት የአስከፊ ገጽታ መገለጫ  ነፃ ከሚያወጧት ዓበይት ክንዋኔዎች አንዱና ዋነኛው አትሌቲክስ ነው ቢባል አያከራክርም፡፡

በርካቶች ከአገራቸው ውጪ ሆነው ከየት እንደመጡ ተጠይቀው ከኢትዮጵያ በማለት ሲመልሱ ወደ ጠያቂዎቹ አዕምሮ የሚመጣው የመጀመርያው ነገር፣ አገሪቱን ከጀግኖች አትሌቶች ጋር በማስተሳሰር ‹‹ኦ የአበበ፣ የማሞ፣ የምሩፅ፣ የደራርቱ፣ የኃይሌ፣ የመሠረት፣ የቀነኒሳ፣ የጥሩነሽ፣›› እና ሌሎችም የሚለው ቀዳሚው መገለጫ ነው፡፡

እነዚህ ታላላቅ ብርቅዬ አትሌቶች በመላው ዓለም የናኘና የተከበረ ስም የተጎናፀፉ ከመሆን አልፈው፣ ኢትዮጵያን ከረሃብ፣ ከጦርነትና ከመከራ ጋር አስተሳስረው ለሚመለከቱ ባዕዳን አገሪቱ ያልተነገሩ በርካታ በጎ ታሪካዊ ማንነት እንዳላት በማመላከት የተዛባውን አተያይ ሙሉ በሙሉ ባይቀይረውም እንኳን በተሻለ መልኩ እንዲመለከቱ የሚያስገድዳቸው ታላቅ የማንነት ምንጭ ለመሆኑ አስረጅ አያስፈልገውም፡፡ ርዕሰ ብሔሯ ወ/ሮ ሳህለ ወርቅ ዘውዴ በሕይወት ተሞክሯቸው ይህንኑ በአስረጅነት ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡

ኢትዮጵያ በተለያዩ ዘርፎች በዓለም መድረክ ስመ ጥር የሆኑ ግለሰቦች ያሉባት አገር ነች፡፡ ነገር ግን ታላላቅ ግለሰቦች በሚታወቁበትና በሚወደሱበት መልኩ በአገር ውስጥ ይህ ነው የሚባል ሥፍራም ሆነ ክብር መስጠት ለአብዛኞቹ ዳገት ሆኖ ቆይቷል፡፡ ኢትዮጵያ ጀግና መፍጠር እንጂ ማክበር የማታውቅ አገር በማለት በርካቶች የሚሳለቁባትም ለዚህ ይመስላል፡፡

ይህን ጀግናን የማክበር ችግርና ፈተና ለማረቅ እንዲሁም ፈር ቀዳጅ የሆኑ ጀግኖችን በማወደስ አዳዲስና ተተኪ ጀግኖች ለመፍጠር ቀዳሚዎቹን ማክበር አስፈላጊነት ላይ የወሰነው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን፣ የአገሪቱን ስምና ሰንደቅ በዓለም መድረክ ከፍ ያደረጉትን ጀግኖች የሚዘክር ታላቅ መርሐ ግብር ባለፈው እሑድ በሸራተን አዲስ አከናውኗል፡፡

በዕለቱ ‹‹የባዶ እግር ትሩፋቶች›› በሚል ከሜልቦርን እስከ ሪዮ ኦሊምፒክ የኢትዮጵያን ስምና ሰንደቅ ከፍ ያደረጉና ያስጠሩ አትሌቶችን አክብሯል፣ ዘክሯል፣ ዕውቅና ሰጥቷል፣ ሸልሟል፡፡ ይህ የፌዴሬሽኑ መልካም ጅምር በርካቶች አብሮነትንና መነሳሳትን የሚፈጥር መርሐ ግብር እንደነበር እየገለጹት ይገኛል፡፡ ፌዴሬሽኑ ባዘጋጀው መርሐ ግብር ላይ የተገኙት ፕሬዚዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ የፕሮግራሙን ተምሳሌታዊነት ሲናገሩ፣ ለቀደምቶቹ መሪዎች፣ ለጀግኖቹ አትሌቶችና ለፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት ኮማንደር ደራርቱ ቱሉ ያላቸውን ክብርና አድናቆት በመግለጽ ነበር፡፡

በአውስትራሊያ ሜልቦርን ኢትዮጵያ እንደ አገር በዓለም አቀፍ የውድድር መድረክ የመጀመርያ ተሳትፎ ያደረገችበት የኦሊምፒክ ጨዋታ ነው፡፡ የኢትዮጵያ የኦሊምፒክ ልዑክ ሜልቦርን ለመድረስ በአውሮፕላን ስምንት ቀን መጓዙን መዛግብት ያስረዳሉ፡፡

የመጀመርያ በሆነውና እ.ኤ.አ. 1956 በተከናወነው ሜልቦርን ኦሊምፒክ ላይ ኢትዮጵያን ወክለው በአጭርና መካከለኛ ርቀት የተወዳደሩት ንጉሤ ሮባ (የ100 እና 200 ሜትር)፣ በየነ አያኖ (100፣ 400 እና 800 ሜትር) ለገሰ በየነ (100፣200 እና 400 ሜትር)፣ ኃይሉ አበበ (200 እና 400 ሜትር)፣ ማሞ ወልዴ (800 እና 1,500 ሜትር) ባሻዬ ፈለቀና ገብሬ ብርቄ (ማራቶን)፣ እንዲሁም በ4×400 ሜትር እና 4×400 ዱላ ቅብብል ተወዳድረዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከተሳትፎ ወደ ሜዳሊያ ሰንጠረዥ የገባችው ደግሞ ከአራት ዓመት በኋላ በጣሊያን በተዘጋጀው ሮም ኦሊምፒክ ላይ ነው፡፡ የባዶ እግር ትሩፋትም ከዚህ ይጀምራል፣ የሮም ኦሊምፒክ ለኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ከውድድር ባሻገር ከፋሺስት ጣልያን ወረራ ጋር በተገናኘ ለየት የሚል ታሪክ ያለው መሆኑ ይታወቃል፡፡

ኢትዮጵያን በሮም ኦሊምፒክ ከወከሉት አትሌቶች መካከል በማራቶን ለኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን በቆዳ ቀለማቸው የአሸናፊነት ግምት ለማይሰጣቸው ጥቁሮች የድል ፈር የቀደደው ሻምበል አበበ ቢቂላ አንዱ ነበር፡፡ ከዓለም ተወዳዳሪዎች ፊት ያውም በባዶ እግሩ ፅናት የሚጠይቀውንና 42 ኪሎ ሜትር 195 ሜትር የሚሸፍነው ማራቶን በአሸናፊነት በማጠናቀቁ በታሪክ መዝገብ የሰፈረ የመጀመርያው ጥቁር አፍሪካዊ ሆኗል፡፡

በአበበ ቢቂላ ቀዳሚ የድል ብሥራት የወርቅ ሜዳሊያ በተበሰረበት ሮም ኦሊምፒክ ላይ በማራቶን የተሳተፉት ብርቱው ተፎካካሪ አበበ ዋቅጅራ ሰባተኛ መውጣቱ ይታወቃል፡፡ በሜልቦርን ኦሊምፒክ ተሳትፎ ‹‹አንድ›› ብሎ የጀመረው የኢትዮጵያ የኦሊምፒክ ተሳትፎ በታሪክ አጋጣሚ የመሯት መሪዎች በሚከተሉት ርዕዮተ ዓለም ምክንያት ከተሳትፎ ውጪ ከሆነችባቸው (ካናዳ ሞንትሪያል 1976 ከደቡብ አፍሪካው አፓርታይድ ጋር በተገናኘ፣ እንዲሁም 1984 እና 1988 በሎስአንጀለስና በሲኦል ኦሊምፒክ ደግሞ የሶቪየት ኅብረትና የሰሜን ኮሪያ ደጋፊ በመሆን) ካልሆነ ከሮም እስከ ሪዮ ኦሊምፒክ ከሜዳሊያ ሰንጠረዥ ውጪ የሆነችበት አጋጣሚ የለም፡፡

በቅብብሎሽ ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተላለፈ በርካታ ጀግኖችን ያፈራው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ፣ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ያዘጋጀው የዕውቅናና የምሥጋና ፕሮግራም በዚህ መልክ ሲዘጋጅ ለመጀመርያ ጊዜ ቢሆንም፣ ጅምሩ ግን ቀጣይ ጀግኖች ለመፍጠር ብቻ ሳይሆን ለአገሪቱ አንድነትና ዕድገት የሚበጅ ስለመሆኑ ብዙዎች ምስክርነታቸውን የሰጡበት ተምሳሌታዊ መድረክ ሆኗል፡፡

በኮማንደር ደራርቱ ቱሉ የሚመራው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ከሜልቦርን ኦሊምፒክ ተሳታፊዎች ጀምሮ እስከ 1980 ሞስኮ ኦሊምፒክ ድረስ ተሳትፎ ያደረጉ አትሌቶችን ጨምሮ ከዲፕሎማ እስከ ወርቅ ሜዳሊያ ላስመዘገቡ ባለውለተኛ አትሌቶች ማበረታቻ የገንዘብ ሽልማት አበርክቶላቸዋል፡፡ ለሻምበል አበበ ቢቂላ ሁለት ሚሊዮን፣ ለማሞ ወልዴና ምሩፅ ይፍጠር ለእያንዳንዳቸው አንድ ሚሊዮን እንዲሁም ለተሳታፊዎች ከ25 ሺሕ ጀምሮ በየደረጃ የገንዘብ ሽልማት ከመበርከቱ በተጨማሪ የእውቅናና የምሥጋና ዋንጫ ተበርክቶላቸዋል፡፡

ፕሬዚዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴን ጨምሮ በርካታ ከፍተኛ የመንግሥትና የክልል ባለሥልጣናት፣ ታዋቂ ግለሰቦችና የጀግኖቹ አትሌቶች ቤተሰቦች በተገኙበት በተከናወነው የዕውቅና ፕሮግራም፣ ከሞስኮ ኦሊምፒክ በኋላ የተከናወኑትን ጨምሮ እስከ ሪዮ ኦሊምፒክ ድረስ ሜዳሊያ ካስመዘገቡ እስከ ተሳትፎ የዕውቅናና የምሥጋና ዋንጫ በፕሬዚዳንቷ ተበርክቶላቸዋል፡፡ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ለመሰናዶው እስከ ስምንት ሚሊዮን ብር ወጪ ማድረጉም ተነግሯል፡፡

ዝግጅቱን አስመልክቶ ሪፖርተር ያነጋገራቸው ስፖርተኞችና ታዋቂ ሰዎች፣ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የጀመረው የዕውቅናና የምሥጋና ፕሮግራም በሌሎችም የስፖርት ዘርፎች ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...