በቀደም ዕለት ከቢጤዎቼ ጋር ቢራችንን እየጠጣን ወጋችንን እንሰልቃለን፡፡ ዋናው አጀንዳችን ግን መቼም ቢሆን የማይዘነጋው የአገራችን ጉዳይ ነው፡፡ አንደኛው ጓደኛችን እንደ ወትሮው ከእኛም ከስልኩም ጋር እየተጫወተ በድንገት እገሊት የምትባለው የሕወሓት አንደኛ ቁንጮ ‹‹በሕይወትና በሞት መሀል ሆና ተያዘች›› የሚል ጽሑፍ ከፌስቡክ ገጹ ላይ አሳየን፡፡ ‹‹ይህንን መረጃ ፖስት ያደረገው ‹ሰበር ቁርሱ› የሚባለው ሰውዬ ስለሆነ ምንጩ አስተማማኝ ሳይሆን አይቀርም…›› እያለ መረጃውን እንድናምን በሚመስል ስሜት ተናገረ፡፡ መቼም ከድሮ ጀምሮ ‹‹የአራዳ ልጅ ይግደለኝ›› የምትለውን አባባል በጣም ስለምወዳት፣ ፒያሳ ተወልጄ አድጌ ማንም እየተነሳ ከኋላ ኪሱ አውጥቶ የሚለቀውን ወሬ ለመቀበል ያዳግተኛል፡፡ ለምን ቢባል ምንጭ የሌለው ወሬ ‹‹ከአስተማማኝ ምንጭ›› ተብሎ ለገበያ ሲቀርብ ሳላንገራግር የምሸምት ‹‹ፋራ›› አይደለሁምና፡፡
ለማንኛውም እኔ ብቻ ሳልሆን ሌሎች ጓደኞቼም የእነ ‹‹ሰበር ቁርሱን›› ወሬ እንደ ወረደ መቀበል እንደሌለብን ስለምናምን፣ ጓደኛችንም በተባራሪ ወሬ ‹‹እንዳይሸወድ›› መክረነው ወደ ሌላ ወጋችን ዘለቅን፡፡ የወጋችን ማጠንጠኛ የነበረው ይህች ተያዘች የተባለችው የሕወሓት ቁንጮና አጋሮቿ፣ ምን ያህል በራሳቸው ቢተማመኑ ነው ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በጣም አደገኛ ጦርነት ለኩሰው ድምጥማጣቸው የጠፋው የሚል ነው፡፡ በዕድሜ ከእኛ ከፍ የሚል ጓደኛችን፣ ‹‹እኔ በበኩሌ ሁለት ነገሮችን አስባለሁ፡፡ አንደኛው ሰዎቹ እዚህ አገር ውስጥ ከእነሱ የሚሻል አስተሳሰብና ድፍረት ያለው ሰው እንደሌለ በልበ ሙሉነት ተማምነዋል፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ለዓመታት በፈጸሙዋቸው ግፎች ምክንያት ልባቸው ተደፍኖ ፈጣሪ ከእነ መኖሩ ዘንግተዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ራሳቸውን ከመጠን በላይ አግዝፈው ውድቀታቸውን አጣድፈዋል…›› አለን፡፡
ይህንን ከላይ የተሰጠውን ማብራሪያ ብዙዎች በተለያዩ መንገዶች እየገለጹት በመሆኑ አዲስ ላይሆን ይችላል፡፡ ሌላ አስገራሚ ዕይታ የፈጠረልን ግን በዕድሜ ትንሹ የሚባል ጓደኛችን ነው፡፡ ‹‹እኔ በፌስቡክ ውስጥ ያለፉትን ሦስት ዓመታት በጣም ብዙ ነገሮችን ታዝቤያለሁ፡፡ በተለይ ደግሞ የሕወሓት ሰዎች ከአራት ኪሎ ተባረው መቀሌ ከተሰደዱ በኋላ፣ የእነሱ ተከፋይ ዲጂታል ወያኔዎች ዓብይን አስወግደው መንበረ ሥልጣኑን እንደሚቆጣጠሩ በአለፍ ገደም ማውራት ከጀመሩ ቆይተዋል፡፡ እጅግ በጣም ከመብዛታቸው የተነሳ የተለያዩ ብሔሮችን ስም ይዘው ሲጽፉም ሆነ በተለያዩ ገጾች ላይ እየዞሩ አስተያየት መስጫ ላይ ተመሳሳይ ሐሳቦች ሲያንሸራሸሩ አውቃቸው ነበር፡፡ በተለይ አማራና ኦሮሞን ለማጋጨት በከፍተኛ ደረጃ ዘመቻ ከፍተው አጉል ተቆርቋሪ በመምሰል፣ በፌዴራል መንግሥቱ ላይ ጫና ፈጥረዋል፡፡ የዋሆችም እነሱን እየተከተሉ በተለያዩ አካባቢዎች ለሚከሰቱ ግጭቶች መንግሥትን ተጠያቂ ሲያስደርጉ ነበር፡፡ አገሪቱን ለመበታተን የሚረዱ ድርጊቶችን በማባባስም አገራችንን የመጨረሻው ጠርዝ ላይ ማድረሳቸው አይዘነጋም…›› ብሎን አየት አደረገን፡፡
እኛም ቀጥል በሚል ምልክት ስናሳየው፣ ‹‹ትዝ ይላችሁ እንደሆነ ወለጋ ጉሊሶ ውስጥ የአማራ ተወላጆች በጅምላ ዕልቂት ሲፈጠርባቸው፣ የአማራ አክቲቪስቶችንና ፖለቲከኞችን በሐሰተኛ ስሞቻቸው በማታለል ተገቢ ያልሆነ ድርጊት ሊያስፈጽሟቸው ነበር፡፡ አብን የሰላማዊ ሠልፍ ጥሪ አድርጎ እንደማይካሄድ በክልሉ መንግሥት ሲነገር የተፈጠረው ቅራኔ አደገኛ እንደነበር አትዘነጉትም፡፡ ቆይቶ ግን የአብን አመራሮች ምክንያት ፈጥረው ሠልፉን ሲሰርዙና ተቃውሞው ሲረግብ የዲጂታል ወያኔ ሠራዊት አባላት ዓላማቸው በመክሸፉ፣ በአብንና በአመራሮቹ ላይ በግልጽ ነበር ዘመቻ የከፈቱት፡፡ ያ የተቃውሞ ሠልፍ ቢካሄድ ኖሮ በቦምብ ወይም በሌላ መሣሪያ ጥቃት አስከፍተው ሕዝብ ሲፈጁ፣ በአማራ ክልል ውስጥ አደገኛ ግጭት ተቀስቅሶ መተላለቅ ሲከተል እነሱ ዘው ብለው ሊገቡ ነበር ያሰቡት…›› ካለ በኋላ ልቀጥል ወይ በሚል አስተያየት ሲያየን በመስማማት ፈቀድንለት፡፡
‹‹እናማ ይህ ሴራቸው ሲከሽፍ አዝመራ ከመሰብሰቡ በፊት ድንገተኛ ጥቃት በሰሜን ዕዝ ላይ ከፍተው ከጥቅም ውጪ ካደረጉት በኋላ፣ የአማራ ክልልንና ፌዴራል መንግሥቱን በመቆጣጠር የበቀል ዕርምጃ ውስጥ ሊገቡ ማቀዳቸው የታወቀ ነው፡፡ የኦነግ ሸኔ ጓዶቻቸውን ይዘው አሻንጉሊት መንግሥት በመመሥረት የተለመደውን የበላይነታቸውን ሊጭኑብን ቢያቅዱም፣ ፈጣሪ ክፋታቸውና ግፋቸው አንገፍግፎት መጨረሻቸውን አሳየን፡፡ ፈጣሪ በእነሱ ተንገፍግፎ እንደነበረ ማሳያው አንደኛ የማይነካ ነገር መንካታቸው ነው፡፡ የአገር መከላከያ ሠራዊቱን ነክተውት አውሬ አደረጉት፡፡ በመከላከያ ሠራዊቱ መነካት የተቆጣው ሕዝብ ደግሞ ቀፎው እንደተነካ ንብ ተነሳባቸው፡፡ ሕዝብ ከተነሳብህ አለቀልህ ማለት ነው፡፡ ሌላው ወሳኝ ነጥብ ግን ይህንን ሁሉ ያደረገው ፈጣሪ ኢትዮጵያ ውስጥ በአካል ጭምር ተንቀሳቅሶ ያጠፋቸው ይመስለኛል…›› ሲለን በጣም አስደመመን፡፡ እኛ ታላላቆቹ ለዚህ ታናሽ ወንድማችን አድናቆታችንን የገለጽነው በአክብሮት ጭምር ነው፡፡
ይህንን ጽሑፍ ከመቋጨቴ በፊት ከሦስት ወራት በፊት የገጠመኝን ልንገራችሁ፡፡ አንድ የማውቀው የትግራይ ሰው አንድ ቀን በጠዋት ይደውልልኛል፡፡ የተለመደውን ሰላምታ ከተለዋወጥን በኋላ ምሳ አብረን እንድንበላ እንቃጠርና እንገናኛለን፡፡ ምሳ ካዘዝን ጀምሮ እየበላን ጭምር የፌዴራል መንግሥት ትግራይን ለማንበርከክ ለመውረር መዘጋጀቱን በምሬት እያወራኝ ነበር፡፡ እኔ ግን የሕወሓት አመራሮች ወታደር መልምለው ለጦርነት እየተዘጋጁ መሆናቸውን፣ ሕግ ጥሰው ምርጫ ከማካሄድ አልፈው የፌዴራሉን መንግሥት ዕውቅና መከልከላቸውንና በአጠቃላይ ለአገር የማይጠቅም አደገኛ ድርጊት ውስጥ መግባታቸውን ላስረዳው ብሞክር ሊሰማኝ ፈቃደኛ አልነበረም፡፡
እንዲያውም ወጣቱና አርሶ አደሩ ትግራይን ለመከላከል መዘጋጀታቸውን ነገረኝ፡፡ ማንም ምድራዊ ኃይል እንደማያቆማቸውና አስፈላጊ ከሆነም የፌዴራሉን መንግሥት ከሥልጣን ማስወገድ እንደሚችሉ ደረቱን ነፍቶ ሲነግረኝ፣ ‹‹በህልምህ ነው ወይስ…›› አልኩት፡፡ እሱ ግን ውስጡ በደስታ የተሞላ በሚመል ስሜት፣ ‹‹አብረን በተግባር እናየዋለን…›› እያለ ሲደሰኩር፣ ‹‹ወዳጄ አሪፍ አይቸኩልም፣ ይህ ቅዠት ሲያልፍህ ግን እንነጋገራለን…›› ብዬው ተለየሁት፡፡ የሕወሓትና የቢጤዎቹ ቅዠት መክኖ ያንን ሰው ብፈልገው ግን ላገኘው አልቻልኩም፡፡ ምናለበት አግኝቼው ‹‹ለዚህ ነበር ወይ…›› እያልኩ በሳቅኩበት፡፡ አንጀቴን አጭሶት ነበር እኮ፡፡ ወይኔ የአራዳው ልጅ!
(ተስፋዬ ስጦታው፣ ከፒያሳ)