የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የዲጂታል ሪፎርም ፕሮጀክት ትግበራ እያከናወነ ይገኛል፡፡ ከዚህ ውስጥ የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የሪፎርም ፕሮግራም አካል የሆነው የሥራ ቅልጥፍና ፕሮግራም (Ease of Doing Business) ይገኝበታል፡፡ የኤሌክትሮኒክ ወይም ዲጂታል መንግሥት መፍጠርና ለዚህ የሚመጥን የሰው ኃይል ማብቃትን አልሞ እየሠራ የሚገኘው ሚኒስቴሩ ከአውሮፓ ኅብረት፣ ከማስተር ካርድ ፋንዴሽንና ከሌሎች አጋዦች ጋር በመተባበር ኢትዮጵያን የትራንስፎርሜሽኑ ግብ ከሆነው ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ለማድረስ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡ አቶ አቤል ሰለሞን በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር (ሚኒት) የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ፕሮግራም ፕሮጀክት ዋና ሥራ አስኪያጅ ናቸው፡፡ ምሕረት ሞገስ አነጋግራቸዋለች፡፡
ሪፖርተር፡- ዲጂታል ስትራቴጂ የተነደፈው በተለይ አገር በቀል ኢኮኖሚውን ለማገዝ ነው፡፡ ስትራቴጂው ምን ይመስላል?
አቶ አቤል፡- ስትራቴጂው አራት ትኩረቶች አሉት፡፡ ግብርና፣ ቱሪዝም፣ ከፍተኛ ትምህርትና ጤና ናቸው፡፡ በእነዚህ ዘርፎች ኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ ምን ሊያበረክት ይችላል? ምን ዓይነት መተግበሪያ (አፕሊኬሽን) እና ቴክኖሎጂዎች ቢተገበሩ በቀጣይ አምስት ዓመት ውጤት ልናመጣ እንችላለን? የሚለውን የያዘ ስትራቴጂ ነው፡፡ በመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥ በተለይ ንግድ መጀመር ሲፈለግ ምን ያህል ፈታኝ ነው? በቀላሉ እንዴት ሥራ መጀመር ይችላል? የሚሉትና ሌሎች የመንግሥት አገልግሎቶችን ማሻሻልን ያካተተ ነው፡፡ የሥራ ቅልጥፍና ደረጃ አለው፡፡ አገሮች ምን ያህል ለንግድ ክፍት ናቸው የሚለውን በተመለከተ የዓለም ባንክ በየዓመቱ ደረጃ ያወጣል፡፡ በዚህ ደረጃ ዝቅ ብሎ መታየት በተለይ የውጭ ኢንቨስትመንትን ለማምጣት አዳጋች ያደርገዋል፡፡ ስትራቴጂው ይህንን የሚፈታና የመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥን በበይነ መረብ የበለጠ ተደራሽ ለማድረግ ያለመ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ግብርናው፣ ጤናው፣ ከፍተኛ ትምህርቱና ቱሪዝሙን ወደ ዲጂታል ቴክኖሎጂው በማስገባት የተቀላጠፈ አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረግ የስትራቴጂው አካል ነው፡፡ በየትኛው ዘርፍ ተጀምሯል? ምን ደረጃ ላይ ደርሷል?
አቶ አቤል፡- አንዱ ስህተት የነበረው ኤሌክትሮኒክ ወይም ዲጂታል መንግሥት መፍጠር የእኛ ተቋም ሥራ ብቻ ተደርጎ መወሰዱ ነው፡፡ ሥራው የሚኒስቴራችን ብቻ ሊሆን አይችልም፡፡ ተቋማችን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሆኖ ስለግብርና አውቶሜሽን ለመሥራት ከግብርና ተቋማት ጋር አብሮ መሥራት አለበት፡፡ በሌሎቹ በቱሪዝም፣ በጤናና በከፍተኛ ትምህርትም ኃላፊነቱን ከወሰዱ ተቋማት ጋር በጋራ መሥራት አለብን፡፡ ከዚህ አንፃር ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ጋር የምንሠራው ኦንላይን (የበይነመረብ) ጋለሪና ኤግዚቢሽን ነው፡፡ በዚህ ‹ፕላትፎርም› ከሚኒስቴሩ ጋር የሚገኙ የተለዩና የትም ገበያ ላይ የማይገኙ ፎቶዎችን ከድረ ገጽ ላይ የማይወርዱ፣ ግን የሚታዩ በማድረግ ከስፖንሰርና ከማስታወቂያ ገቢ ማግኘት እንዲቻል፣ የተገኘው ገቢ ደግሞ በኮቪድ-19 ምክንያት ገቢ ላጡ የቱሪስት መዳረሻ ሥፍራዎች ማዋል እንዲቻል ሥራውን እያገባደድን ነው፡፡ በቅርቡ የመግባቢያ ሰነድ እንፈራረማለን፡፡ ከጤና ሚኒስቴር ጋር የኮቪድ-19 መረጃ ቅብብልን ለማዘመን፣ ከግብርና ሚኒስቴር ጋር ደግሞ በዓሳ ሀብት ልማት ዙሪያ እየሠራን ነው፡፡ እነዚህ በዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ስትራቴጂ ላይ የተነደፉ ፕሮጀክቶች ናቸው፡፡ ፕሮጀክቶቹ ፈንድ የሚያስፈልጋቸው ከሆነ ተፈልጎ የሥራው ባለቤት ከሆኑ ሚኒስቴሮች ጋር አብረን በጋራ የምንሠራቸው ናቸው፡፡
ሪፖርተር፡- በከፍተኛ ትምህርት ዘርፍስ?
አቶ አቤል፡- ‹ዲጂታል ሊትረሲ›ን ለማስፋፋት ከዓለም አቀፉ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ማሠልጠኛ ተቋም (ሲስኮ) ጋር በመሆን አንድ አካዳሚ ተከፍቷል፡፡ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚመረቁ ተማሪዎች ከአካዳሚውም ሰርተፊኬት እያገኙ እንዲወጡ እየሠራን ነው፡፡ አካዳሚው የመንግሥት ቅጥሮችንና የተማሪዎችን አቅም ያዳብራል፡፡ የመንግሥት ተቀጣሪዎችን አቅም ለማዳበር ወደ ሥልጠና ገብተናል፡፡ 250 ያህል የዲጂታል ሰርተፊኬሽን ሠልጣኞች ሥልጠና እየወሰዱ ነው፡፡ በቀጣይ ወደ ተማሪዎች እንሄዳለን፡፡
ሪፖርተር፡- አሁን ከኮቪድ-19 ጋር አስተሳስራችሁ እየሠራችሁ ነው፡፡ በቀጣይስ?
አቶ አቤል፡- ኮቪድ-19 ቢጠፋም ፕሮጀክቱ የሚቋረጥ መሆን የለበትም፣ ይቀጥላል፡፡ ለምሳሌ በአዲስ አበባ በአንድ ጤና ጣቢያ የሚመረመር ሰው የጤና መረጃ በማዕከል የሚያዝበት ቴክኖሎጂ ሌላ ጊዜ ለቲቢ፣ ለወባና ለሌሎች በሽታዎች መረጃ የሚይዝና የሚሰበስብ ይሆናል፡፡ ቴክኖሎጂው ዓላማ ያደረገው ኮቪድ-19 ብቻ አይደለም፡፡ እያደገና እየሠፋ የሚሄድ ነው፡፡ አሁን ኮቪድ-19 ላይ ያተኮርነው ወቅቱ ለጠየቀው መልስ ለመስጠት ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ቴክኖሎጂ ወይም ዲጂታላይዜሽን ሲታሰብ ብቁ የሰው ኃይል ማግኘት ቅድሚያ የሚሰጠው ነው፡፡ በመንግሥት ተቋማት ያሉ ሠራተኞች ምን ያህል ለቴክኖሎጂው የቀረቡ ወይም ዕውቀት ያላቸው ናቸው?
አቶ አቤል፡- በአምስት ዓመታት ውስጥ 70 በመቶ ዲጂታል ዕውቀት ያለው ኢትዮጵያዊ ማኅበረሰብ ለማግኘት ግብ ተይዞ እየተሠራ ነው፡፡ ይህንን የሚመራ ዲፓርትመንትም አለን፡፡ ሰዎች የኮምፒዩተር ቴክኖሎጂን ለምን አይጠቀሙም ብለን ካለን ልምድ ስናይ፣ መጀመርያ ያገኘነው ምክንያት ሰውን ማዕከል ያደረገ ሥርዓት ተከትሎ ባለመሠራቱ ነው፡፡ ማንበብና መጻፍ የማይችል ሰው (ጎልማሳ) አንድሮይድን ሕፃናት እንደሚነካኩትና እንደሚጠቀሙት ሁሉ፣ አገልግሎት የምንሰጥባቸውን ድረ ገጾቻችን ለምን አይጠቀምም ብለን በዓለም አቀፍ ድርጅት አስጠንተናል፡፡ ምክንያቱ ሰውን ማዕከል ያደረገ ሥርዓት ባለመከተላችን ነው፡፡ ከጥናቱ በኋላ ሰውን ማዕከል ያደረገ ዲዛይን ‹‹Human Centered Design›› አሠርተናል፡፡ ለሥራ ቅልጥፍና ፕሮጀክት የተጠቀምነው ሰውን ማዕከል ያደረገ ዲዛይን ተከትለን ነው፡፡ ድረ ገጹን ስናበለፅግ የሰዎችን ስሜት፣ ምልከታና ፍላጎት የጠበቀ አሠራር ተከትለናል፡፡ ሰዎች የበለጠ እንዲጠቀሙ ለማድረግ ሠርተናል፡፡ ምን ያህል ሕዝቡን ተጠቃሚ ያደርጋል የሚለው ቀጣይ ጥናት ቢፈልግም፣ አሁን ከዚህ ቀደም ከነበረው በተሻለ አንድ ደረጃ አሳድገናል፡፡ ሰዎች ምን ያህል ዕውቀት አላቸው የሚለው ብቻ ሳይሆን መተማመንስ አላቸው ወይ የሚለውም መታየት አለበት፡፡ በሚያገኙት አገልግሎት ምን ያህል ተማምነው የኢንተርኔት ተጠቃሚ ይሆናሉ የሚለው ላይ ብዙ መሥራት ይጠበቅብናል፡፡ መተማመኑ የሚመጣው ከመጠቀም ነው፡፡ በእኛ በኩል ከፍተኛውን ትኩረት አገልግሎት ሰጪው አቅም ላይ አድርገናል፡፡ አገልግሎት ሰጪው በብቃት ሥራውን መሥራት ከቻለ ማኅበረሰቡ ተገልጋይ ይሆናል፡፡ ማኅበረሰቡ ከእኛ ቀድሟል፡፡ ወደ ኋላ የቀረው አገልግሎት ሰጪው ነው ብለን እናምናለን፡፡ እያገኘን ካለነው የገንዘብ ድጋፍም ብዙውን የያዝነው ለሥልጠናና ለመሠረተ ልማት ግንባታ ነው፡፡ የኢንተርኔት ቴክኖሎጂ ሲታሰብ መሠረተ ልማቱ እንኳን ለክልል ለአዲስ አበባም በቂ አይደለም፡፡ ስለዚህ የሰው ኃይልና መሠረተ ልማት ላይ ብዙ ኢንቨስት ሊደረግ ይገባል፡፡ ሊሻሻልም ስለሚገባ እዚህ ላይ እየሠራን ነው፡፡
ሪፖርተር፡- በአዲስ አበባ ከተማ መቆራረጥ ቢኖርም የተሻለ መሠረተ ልማት አለ፡፡ እናንተ ክልል ከተሞች ላይም አሠራሮችን ዲጂታላይዝ ለማድረግ እየሠራችሁ ነው፡፡ በክልሎች ደግሞ የመሠረተ ልማት ችግር አለ፡፡ ይህ እንዴት ታስቧል?
አቶ አቤል፡- ሁሉም በአንዴ ይቀረፋል ብለን አናስብም፡፡ በሒደት ይሻሻላሉ፣ እየተሻሻሉም ነው፡፡ ወደፊት አዳዲስ ኦፕሬተሮች ሲገቡ መንግሥትም ትኩረት የሰጠው ዘርፍ ስለሆነ በቶሎ ይሻሻላል ብለን እናስባለን፡፡ እኛ ለዚህ ቀድመን ሠርተን መጠበቅ አለብን፡፡ ለምሳሌ ኢንተርኔት የማይገኝ ከሆነ መጠቀሙን ለማምጣት አይቻልም፡፡ ይህን መሥራት ይገባል፡፡ ሰዎች የኢንተርኔት አገልግሎት እያለ መጠቀም የማይችሉ ከሆነ ደግሞ፣ በየተቋማቱ የኢንተርኔት ካፌ አገልግሎት የሚሰጡ ሱቆች ተከፍተው በዚያ በኩል አገልግሎት ፈጽመው እንዲሄዱ ማድረግ ነው፡፡ የኢንተርኔት አገልግሎት ለሚሰጡም የሥራ ዕድል ይፈጥራል፡፡ የትራንስፖርት ዘርፍ በሥራ ቅልጥፍና ፕሮጀክት ላይ ስላልተካተተ እንጂ በእኛ ፕላትፎርም ነው የሚሠሩት፡፡ በኢትዮጵያ ላሉ ኦዲተሮች ፈቃድ የሚሰጠው የኦዲት ቦርድ አገልግሎት የሚሰጠው በኢ-ሰርቪስ (ኢንተርኔት አገልግሎት) ነው፡፡ ቦርዱ እንደ ተቋም በየክልሉ እየሄደ ሥልጠና ይሰጣል፡፡ መረጃዎች በዩቲዩብና በበራሪ ወረቀት እየተዘጋጁ ተጠቃሚዎች እንዴት መጠቀምና አገልግሎት ማግኘት እንደሚችሉ መረጃ እየተሰጠ ነው፡፡ ዲጂታል ሊትረሲው ላይ በተከታታይ ሥልጠና በመስጠት አገልግሎት ሰጪውን ማጎልበትና ይህንን የሚመጥን አሰራር ማምጣት አለብን፡፡ እንዳየነው ከኅብረተሰቡ ይልቅ የአገልግሎት ሰጪው አቅም ሊጎለብት ይገባል፡፡ አገልግሎት ሰጪውን ካሻሻልነው ቀጥሎ ያለው ይሻሻላል፡፡
ሪፖርተር፡- ሚኒስቴራችሁ እስከ ዞን ድረስ የሚዘልቅ መዋቅር አለው፡፡ ይህንን ተጠቅማችሁ ጤናውን፣ ግብርናውንና ሌሎቹን ዲጂታላይዝ ለማድረግ የተጀመረ እንቅስቃሴ አለ?
አቶ አቤል፡- ሚኒስቴሩ ዓመታዊ ዕቅዱን ከየዞን ቴክኖሎጂ ነክ ቢሮዎች ጋር አቀናጅቶ ይሠራል፡፡ ለምሳሌ አረንጓዴ አሻራ ሲተገበር መረጃ አሰባሰቡን በኮምፒዩተር የታገዘ አድርገናል፡፡ ይህ ሲሆን ሚኒስቴራችን አዲስ አበባ ላይ ብቻ የሚሠራው በቂ ባለመሆኑ በሁሉም ክልሎች ላይ መቀናጀት ነበረበት፡፡ የችግኝ ተከላው በቀበሌ ደረጃ የሚሠራ ነው፡፡ ሥልጠና ማድረግ ስለነበረብን እስከ ዞን ድረስ ወርደን በዞኑ በኩል ለግብርና ቢሮ ባለሙያዎች ሥልጠና ተሰጥቶ መረጃ አሰባሰቡን ውጤታማ አድርገናል፡፡ ግንኙነቱ ቢኖርም ብዙ መሥራት አለብን፡፡ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱና የሥራ ቅልጥፍና ፕሮጀክቱን ለመተግበር ጥናት ሲደረግ፣ ሁሉም ክልሎች ተሳትፈውበታል፣ ሐሳብ ሰጥተውበታል፡፡ ሆኖም ያለን ግንኙነት ከዚህ በላይ ሊጠነክር ይገባል፡፡
ሪፖርተር፡- ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 የተባለው ፕሮጀክት ምን ላይ ያተኮረ ነው?
አቶ አቤል፡- ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ስትራቴጂያችን ግብ ነው፡፡ ግቡ በ2025 ዲጂታል ኢትዮጵያን መመሥረት ነው፡፡ ብዙዎቹ የመንግሥት አገልግሎቶች ዲጂታል የሆኑበት፣ መረጃ አሰባሰብና አያያዝ የተቀናጀበት፣ ተቋማት እርስ በርስ የተሳሰሩበት፣ መንግሥት አገልግሎቱን በዲጂታል ቴክኖሎጂ የሚያቀርብበት፣ ኅብረተሰቡም በዲጂታል ቴክኖሎጂ አገልግሎት የሚያገኝበትና አሳታፊ ብልፅግናን የያዘ ማድረግ ነው፡፡ ወጣቶችን ማዕከል ያደረገ የሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ ትኩረት አድርጎ መሥራት ይገኝበታል፡፡ ዲጂታል መንግሥት ወይም ወረቀት አልባ አገልግሎት መዘርጋትም ግቡ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ወደ ዲጂታል መንግሥት ሲመጣ የዲጂታል ደኅንነት ጉዳይ ዋናው ነው፡፡ ቀድሞ ወደ ቴክኖሎጂ የገቡት የሠለጠኑ አገሮች ለሰዓታት ብሎም ለቀን ያህል የተወሰኑ አገልግሎቶቻቸው በሳይበር ጥቃት ምክንያት መስተጓጎል ይገጥማቸዋል፡፡ ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ሲታቀድ ለሳይበር ጥቃት ያለው ዝግጁነት ምን ይመስላል?
አቶ አቤል፡- ዲጂታል ሊትረሲ ወይም የዲጂታል ዕውቀት ያለው ማኅበረሰብ እንፈጥራለን ስንል የዲጂታል ደኅንነትንም ያካተተ ነው፡፡ ኅብረተሰቡ የቴክኖሎጂውን ደኅንነት ጠብቆ እንዴት መብቱን ሳያስነካና ጥቅሙን አስከብሮ መጠቀም ይችላል? የሚለውን ለማሳካት በትምህርትና ሥልጠናው አብሮ የሚሰጥ ነው፡፡ የሳይበር ደኅንነትን በተመለከተ እንደ አገርም እንደ መተግበሪያም ሌሎች ትልልቅ ፕሮጀክቶች አሉት፡፡ ኢ- ሰርቪስና የሥራ ቅልጥፍናን ከኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ (ኢንሳ) ጋር ነው የምንሠራው፡፡ ኢንሳ ይሁንታ ሳይሰጠን ወደ ሥራው አንገባም፡፡ ወደ ሥራ ከገባን በኋላም በተለያዩ ጊዜያት እናስፈትሻለን፡፡ የኤሌክትሮኒክ ክፍያ ሲጀመር ደግሞ ችግሩ የሚሰፋ ስለሚሆን በዚሁ መጠን እኛም መዘጋጀት አለብን፡፡
ሪፖርተር፡- በአዲስ አበባ በዲጂታል ሥርዓት በበይነ መረብ አገልግሎት መፈጸም ቢቻልም፣ ገንዘብ መክፈል ባለመቻሉ ቅሬታዎች ይነሱ ነበር፡፡ ይህ በምን ተፈታ?
አቶ አቤል፡- ተገልጋዮች በበይነ መረብ ሥርዓቱ ገንዘብ መክፈል አይችሉም ነበር፡፡ አምና የኤሌክትሮኒክ ክፍያ አዋጅ አልፀደቀም ነበር፡፡ ወደ ሥራ ያልገባበት አንዱ ምክንያት ይህ ነው፡፡ በአሁኑ የትግበራ ዕቅድ ተገልጋዮች አመልክተው እዚያው ከፍለው አገልግሎት ማግኘት የሚችሉበትን እንሠራለን፡፡
ሪፖርተር፡- አዲስ አበባ ውስጥ በተመረጡ የመንግሥት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት የተሠራው ዲጂታላይዜሽን ምን ያህል ውጤታማ ነው?
አቶ አቤል፡- አዲስ አበባ ሥራን ሊያቀላጥፍ የሚችል ድረገጽ (ፖርታል) ተከፍቷል፡፡ እያንዳንዱ ክፍለ ከተማና በማዕከል ደረጃ የሚሰጡ አገልግሎቶች ተለይተዋል፡፡ ተገልጋዮች ፖርታሉን ተጠቅመው ሲያመለክቱ ተቋማቱ ሒደቱን በበይነ መረብ ይጨርሱታል፡፡
በአዲስ አበባ የዓለም ባንክ የሚጠቀምባቸውን የተቀላጠፈ አሠራር የሚያበቁ አሠራሮችን ለመዘርጋት ኮሚቴ ተቋቁሞ ወደ ሥራ ገብቷል፡፡ ኢንሼቲቩ የተጀመረው በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) ነው፡፡ በሥራ ቅልጥፍና ኢትዮጵያን ከቀዳሚ 100 አገሮች ውስጥ ለማስገባት ያለመ ፕሮጀክት ነው፡፡ በመሆኑም አምና ፖርታል ተሠርቶ ለሥራ ውሏል፡፡ በዚህም በአዲስ አበባ የግንባታ ፈቃድና የሀብት ማስመዝገብ ሥራዎችን በበይነ መረብ ማድረግ የሚያስችል ሥራ ተጀምሯል፡፡ የዓለም ባንክ ከ100 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ላላቸው አገሮች የ‹‹Ease of Doing Business›› ደረጃ ሲሠራ ሁለት ትልልቅ ከተሞችን ይገመግማል፡፡ ባንኩ ሊሆን የሚችለውን ከተማ ባያሳውቀንም ሊሆኑ ይችላሉ ያልናቸውን ከተሞች ለይተን አዲስ አበባ ላይ የተሠራውን የሥራ ቅልጥፍና በድሬዳዋና ባህር ዳር ለመሥራት እየጣርን ነው፡፡ አዲስ አበባ የተሠራውን ዲጂታላይዜሽን ሥራ በከተሞቹ ለማስፋፋት ታስቧል፡፡
ሪፖርተር፡- የኤሌክትሮኒክስ መንግሥትና ዲጂታል ሥነ ምኅዳር ለመገንባት ሚኒስቴሩ ሥራ ጀምሯል፡፡ ከምን ደርሷል?
አቶ አቤል፡- ዲጂታል ሥነ ምኅዳር የተለያዩ አካላት የሚሠሩበት ነው፡፡ ከዚህ ውስጥ የኤሌክትሮኒክ አገልግሎት አንዱ ሲሆን፣ ለዚህም ሚኒስቴራችን መተግበሪያውን ሠርቷል፡፡ የግል ዘርፍ፣ አገልግሎት ሰጪው፣ አገልግሎት ተቀባዩ፣ የመረጃ ማዕከሉና ሌሎች ብዙ ተቋማት በአንድ ላይ ተቀናጅተው የሚሠሩበት ነው፡፡ በኢ-ኮሜርስ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትም ይጀመራል፡፡ እነዚህን ሁሉ ሊያስተናግድ የሚችል የሕግ ማዕቀፍ፣ መሠረተ ልማትና ሁሉም የሚሳተፍበት ሥነ ምኅዳር ሊኖረን ይገባል፡፡ የሕግ ማዕቀፉ ፀድቆ መመርያው እየተዘጋጀ ነው፡፡ በቀጣይ ሁለት ወራት ወደ ሥራ እንገባበታለን፡፡
ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያ ወደ ዲጂታል ቴክኖሎጂ ለመግባት ጊዜ የወሰደባት ለምንድነው?
አቶ አቤል፡- አንዱና ትልቁ ፈተና የሕግ አለመኖር ነው፡፡ የኤሌክትሮኒክ ፊርማን ብናይ እንኳን እስከ አምና የተፈቀደ አልነበረም፡፡ ዲጂታል ደረሰኝ ይዞ ገንዘብ ሚኒስቴር ቢኬድ ተቀባይነት አያገኝም፡፡ እነዚህ በሌሉበት በቴክኖሎጂ አሠራር ሥርዓት መዘርጋት አይቻልም፡፡ አሠራራችንም ወጥ አይደለም፡፡ አንድ የመንግሥት ተቋም የሚሠራበት ከሌላው የመንግሥት ተቋም ይለያል፡፡ ይህ ደግሞ እያንዳንዱ የመንግሥት መሥሪያ ቤት የየራሱን የዲጂታል ሥርዓት እንዲያሠራ ይጠይቃል፡፡ በዚህ መሀል የአሠራር ለውጦች ይመጣሉ፡፡ መመርያዎች ይለዋወጣሉ፡፡ በሌላ በኩል የሰዎች ቴክኖሎጂውን አምኖ የመቀበል ሁኔታ፣ ያለን ልምድና የዕውቀት መጠን ይወስነናል፡፡ ሙስናም ትልቁ ማነቆ ነው፡፡ የትም ቦታ ሄዶ በወረቀት የተሰናዳን መረጃ ማውጣት በተለመደበት ሥርዓት አሰራሩን ዲጂታል መደረጉን የማይፈልጉ አሉ፡፡ እንጀራቸውን በዚህ የመሠረቱ በመኖራቸው ቴክኖሎጂውንና አዲሱን አሠራር የማይፈልጉ አሉ፡፡ የመሠረተ ልማትና ሌሎች ችግሮችም ማነቆ ሆነው ቆይተዋል፡፡