Saturday, June 10, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ዘርፈ ብዙ ጥቅም የሚያስገኘው የማር ሀብት

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

ብዙ መሬትና በርካታ ጉልበትን የማይጠይቅ ነገር ግን ትኩረት ተሰጥቶበት  ቢሠራ ከአንድ፣ ሁለትና ሦስት በላይ ጥቅሞችን እንደሚያስገኝ በዘርፉ ላይ ጥናት ያደረጉም ሆነ ጥናቱን መሠረት አድርገው ሠርተው የተለወጡ ሁሉ ይመሰክሩለታል፣ የማር ሀብት ልማት፡፡

መረጃዎች እንደሚያመላክቱት ከሆነ ኢትዮጵያ በዓመት እስከ 550,000 ቶን የማር ምርት የማቅረብ አቅም አላት፡፡ ነገር ግን አሁን ላይ በዓመት እየተመረተ ያለው  ዘጠኝ በመቶ ማለትም 50,000 ቶን ወይም ዘጠኝ በመቶ ብቻ እንደሆነ የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ የቅርብ መረጃ ያመለክታል፡፡

ዓለም አቀፍ የሥነ ነፍሳት ሥነ ምኅዳር ማዕከል (International Center of Insect Physiology and Ecology – icipe) ከአካባቢ ጥበቃና ነፍሳት ምርምር ጋር የተገናኙ ምርምሮች ለማከናወን የተቋቋመ ተቋም ነው፡፡ ተቋሙ የንብ ልማት በዋናነት በገጠር የሚኖሩና የምጣኔ ሀብት እጥረት ያለባቸው ማኅበረሰቦችን ኑሮ ለማሻሻል ፕሮጀክት ቀርጾ በኢትዮጵያ በተለይም በአማራ ክልል መሥራት ከጀመረ አምስት ዓመታትን አገባዷል፡፡

በሰብል ላይ የሚረጩ መድኃኒቶች ንቦች በሚቀስሙት ምግብ ላይ ተፅዕኖ እያሳደረ ቢሆንም የኢትዮጵያ ማር በጀርመን፣ እንግሊዝና ኖርዌይ ገበያ ላይ ዛሬም ድረስ እየተወደደ ጥቅም ላይ ይገኛል፡፡

በኢትዮጵያ የተለያዩ የማር ዓይነቶች የሚገኙ ሲሆን፣ ዓይነቶቹ እንደሚገኙበት አካባቢና የብዝኃ ሕይወት ስብጥር በማሮቹ ላይ የይዘትና የቀለም ልዩነት አላቸው፡፡ ሰቆጣና ዋግኽምራ በተባሉት የአማራ ክልል አካባቢዎች የሚመረተው ማር እንደ ወተት ነጭ ቀለም ያለው ነው፡፡ በመካከለኛው የኢትዮጵያ ክፍል የሚመረተው ማር የቢጫና ወርቃማነት ቀለም ያለው ነው፡፡ ዝቅተኛ በሆኑ የአገሪቱ ክፍሎች ደግሞ ነጣ ያለ ማር እንዲሁ ይመረታል፡፡

ንብ የማነብ ምርት እንደ ግብርናና ኢንዱስትሪ ዘርፎች ሰፊ የሆነ መሬትና የሰው ኃይል አይጠይቅም፡፡ ለዚህኛው ጾታ ይከብዳል ለዚያኛው ይቀላል የሚባል አይደለም፡፡ መሠረታዊና ዋነኛው ዘርፉ የሚጠይቀው ነገር ቢኖር ተነሳሽነትና ትዕግሥት ብቻ እንደሆነ ዘርፉን ሥራዬ ብለው ይዘው የተለወጡት ይመሰክራሉ፡፡ የንብ ማነብ ሥራ በምርቱም ሆነ በአሠራሩ ሒደት ለብዙዎች የሥራ ዕድል መፍጠር የሚችል መሆኑን ካሳዩት ተቋማት መካከል፣ የዓለም አቀፍ የሥነ ነፍሳት ሥነ ምኅዳር ማዕከል አንዱ ነው፡፡ ተቋሙ ለኢትዮጵያ ወጣቶች የንብ ማነብ ዕውቀትና ቴክኖሎጂን መሠረት ያደረገ የሥራ ዕድል ፈጠራ ፕሮጀክት ቀርጾ፣ በተለይም ከፍተኛ የማር ሀብት አለባቸው በሚባሉት የአማራ ክልል ሦስት ዞኖች (አዊ፣ ምሥራቅና ምዕራብ ጎጃም) ላይ ‹‹ለወጣቶች የሐርና ማር ልማት ሥራ ዕድል ፈጠራ›› ወይም (Young Entrepreneurs in Silk and Honey-YESH) በሚል ፕሮጀክት ቀርፆ ወደ ሥራ ገብቷል፡፡

የፕሮጀክቱ አስተባባሪ ወርቅነህ አያሌው (ዶ/ር) እንደሚሉት፣ ማዕከሉ የማር ዘርፉን ሌሎች ከደገፉት ትልቅ ሥራ የሚሠራበት መሆኑን በመረዳት የሙከራ ሥራዎችን በጥሩ ሁኔታ ሠርቶ በማሳየቱ፣ በወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ የሚሠራው ማስተር ካርድ ፋውንዴሽን ከላይ በተጠቀሱት የአማራ አካባቢዎች ላይ ልተተገበረው የአምስት ዓመት ፕሮጀክት አሥር ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ሰጥቷቸዋል፡፡ ፕሮጀክቱ አሥር ሺሕ ግለሰቦችን በማር ምርት ላይ በማሳተፍ ራሳቸውን የቻሉና ዘርፉን እየሠሩበትና እየተለወጡበት የሚኖሩ ዜጎችን ለመፍጠር የተጋ  መሆኑን አስተባባሪው አክለዋል፡፡ ፕሮጀክቱ ለየት የሚያደርገው ነገር ቢኖር ለወጣቶቹ ሥልጠና ከመስጠት ጀምሮ የሚሠሩባቸውን ማቴሪያሎች ማቅረብና የገበያ ዕድሎችን መፍጠር እንጂ ምንም ዓይነት የገንዘብ ድጋፍ አለማድረጉ ነው ይላሉ፡፡

በሦስቱ ዞኖች ከሚገኙ አሥራ ሦስት ወረዳዎች የተወጣጡ አሥር ሺሕ ወጣቶች በቡድን እንዲደራጁ በማድረግ፣ ስለ ዘርፉ ከተሰጣቸው ሥልጠና ባሻገር ዘመናዊ ቀፎዎች፣ የመከላከያ ግብዓቶችና ሌሎች መሣሪያዎች ከፕሮጀክቱ ድጋፍ ተደርጎላቸዋል፡፡

ከዚህ በፊት ዞኖቹ በማር ሥራ ለተሰማሩ ነዋሪዎች ምንም ዓይነት የመሬት አቅርቦት ያልነበራቸው ቢሆንም ፕሮጀክቱ ከተጀመረ ወዲህ የተመረጡት ወጣቶች የቀለም ዕፅዋቶችንና ለበርካታ አገልግሎት የሚውሉ ዛፎች፣ ፍራፍሬዎችንና አትክልቶችን ለአካባቢ ማኅበረሰብ በሚጠቅም መልኩ የሚያለሙበት የችግኝ ጣቢያ እንዲመሠርቱ ተደርጓል፡፡

ንብ ምርት ላይ መሰማራት ማለት በራሱ ከአምስት በላይ የሆኑ የሥራ ዘርፎችን መፍጠር እንደሆነ በፕሮጀክቱ አተገባበር ጊዜ ታይቷል፡፡ ንቦቹ ለሚቀስሙት ዕፅዋቶች ተብለው የሚተከሉት ዕፅዋት የመጀመርያ ገቢ ሲያስገኙ፣ ኅብረ ንብን (የንብ መንጋን) መሸጥ ቀጣዩ ገቢ ነው፡፡ ንቦችን በማዳቀልና ሠራተኛ ንቦችን በማብዛት ምርቱ ከፍ እንዲል በማድረግ የሚገኘው ገቢ ሦስተኛው ሲሆን፣ ምርቱን በማጣራት ሒደት የተገኘውን ተረፈ ምርት ማለትም እንደ ሰም ያለውን በመሸጥም ሆነ ለጧፍ ምርት በማቅረብ የሚገኘው ገቢ አራተኛው ነው፡፡ ከላይ የተጠቀሱትን ምርቶች በማምረት ሒደት ውስጥ የቀፎ ሚና ወሳኝ በመሆኑ በአካባቢው የሚገኙ በእንጨት ሥራ ላይ ለተሰማሩ ግለሰቦች ሥልጠና በመስጠት ተሸጋጋሪ የሚባለውን የቀፎ ዓይነት ሠርተው ለገበያ እንዲያቀርቡና እንዲጠቀሙ ማድረግ አምስተኛው ተግባር መሆኑም ተገልጿል፡፡ የንብ አልባሳትን አምርተው ለአናቢዎቹ በማቅረብ ገቢ የሚያገኙ የስፌት ባለሙያዎችን መጥቀም ሌላኛው ዘርፉ ያመጣው ትሩፋት መሆኑም ተጠቁሟል፡፡ አቶ ቁሜ የኔውድ በምሥራቅ ጎጃም ዞን አዋበል ወረዳ በየሽ ፕሮጀክት የተሰጠውን ሥልጠና ወስዷል፡፡ እሱን ጨምሮ ከአሥር ጓደኞቹ ጋር የኅብረት ሥራ ማኅበር በማቋቋም ማርና የማር ተረፈ ምርት ለገበያ ማቅረብ ከጀመሩ ሁለት ዓመታት አልፏቸዋል፡፡ ቁሜ የማር ፍላጎት ሰፊ ወደ ሥራው ከገቡ ጀምሮ ምንም ዓይነት የገበያ ችግር እንዳልገጠማቸውና እንዲያውም በአካባቢው ያለውን ፍላጎት እያሟሉ እንዳልሆነ ገልጿል፡፡ ከማሸጊያ ፕላስቲክ አንስቶ እስከ ፓኬጂንግ ያሉ ግብዓቶች በፕሮጀክቱ ስለተሟላላቸው፣ ከእነሱ የሚጠበቀው ማርን ቆርጦና አጣርቶ ማቅረብ ብቻ እንደሆነ ቁሜ ይገልጻል፡፡

አጠቃላይ የማር ፕሮጀክትን ሥራዬ ብለው የያዙ ወጣቶች ግን የሚያነሷቸው ችግሮችም አሉ፡፡ የገበያ ላይ ችግር የማይታይበትን ሥራ አስፍተው ይሠሩ ዘንድ ክልሉም ሆነ ዞኖቹ በራቸው ገርበብ ሊልላቸው አልቻለም፡፡ ብድር ለማግኘት ቋሚ የሆነ የመሬት መያዣ መጠየቁና ብዙዎቹም ከቤተሰቦቻቸው ጋር እንደመኖራቸው፣ የወላጆቻቸውን መሬት ማስያዝ እንደማይችሉና በዚያ ላይ አሥርና ከዚያ በላይ ሆነው መደራጀታቸው የየትኛውን መሬት ማስያዝ እንዳለባቸው ለመወሰን አስቸጋሪ በመሆኑ፣ ዕድገታቸውንም ሆነ ፍላጎታቸውን እንደገታው አበክረው ይገልጻሉ፡፡ በመሆኑም በማር ምርትና ተዛማጅ ሥራዎቹ ለመለወጥ የተነሳሳው ወኔያቸው እንዳይበርድ ክልሉም ሆነ ሌሎች አካላት እንዲደግፏቸው በመወትወት ላይ ይገኛሉ፡፡

እንደ አገር መለወጥ ካለብን በዙሪያችን ያሉትን ነገሮች ወደ ሀብት መቀየር ተነሳሽነትን እንጂ ሌላ የሚጠይቀው ነገር እንደሌለ ወጣቶቸ ላይ በተሠራው የማር ሀብት ፕሮጀክት መታየቱን የሚገልጹት ወርቅነህ (ዶ/ር)፣ ማስተር ካርድ ፋውንዴሽንም የተሠራውን ሥራ ውጤታማነት በማየት ከዚህ ዓመት ጀምሮ ለተጀመረና በአራት ክልሎች 100,000 ወጣቶችን በሐርና ማር ምርት የሥራ ባለቤት ለሚያደርገው ሁለተኛው ዙር ፕሮጀክት 55.6 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ አድርጓል ብለዋል፡፡

የአውሮፓ ኅብረት እ.ኤ.አ. በ2002 ከቻይና የሚመጣውን ማር ማገዱን ተከትሎ በዓለም ገበያ ላይ ከፍተኛ የሆነ የማር ፍላጎት አለ፡፡ ይኽን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም የኢትዮጵያ ማር በዓለም አቀፍ ገበያ ሰብሮ እንዲገባ ከገጠር እስከ ከተማ ያለው የምርትና የጥራት ሰንሰለት ጊዜ ሳይሰጠው ሊሠራበት እንደሚገባ በስፋት እየተገለጸ ነው፡፡

በኤልያስ ተገኝ

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች