እናት ባንክ ዓመታዊ ጠቅላላ ገቢውን ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ከፍ ማድረጉንና የተከፈለ ካፒታል መጠኑን ደግሞ ከ1.38 ቢሊዮን ብር በላይ ማድረስ መቻሉ ተገለጸ፡፡
ሥራ ላይ ከሚገኙ የግል ባንኮች ዘግየት ብሎ ኢንዱስትሪውን የተቀላቀለው እናት ባንክ፣ ለመጀመርያ ጊዜ ዓመታዊ ገቢውን ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ማድረሱንና የ2012 ጠቅላላ የገቢ መጠኑ 1.32 ቢሊዮን ብር መድረሱም ታኅሳስ 8 ቀን ባንኩ ባካሄደው ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ተገልጿል፡፡
በ2011 የሒሳብ ዓመት አስመዝግቦት የነበረው ጠቅላላ ገቢ 983 ሚሊዮን ብር እንደነበር ይታወሳል፡፡ የተከፈለ ካፒታል መጠኑንም 1.38 ቢሊዮን ብር እንዳደረሰ የተገለጸ ሲሆን፣ የባንኩ ጠቅላላ የሀብት መጠንም ከ9.2 ቢሊዮን ብር ወደ 11.16 ቢሊዮን ብር ከፍ እንዳለ ታውቋል፡፡ ባንኩ የ2012 የሒሳብ ዓመት ሪፖርት እንደሚያሳየው የባንኩ ተቀማጭ ገንዘብ መጠን 8.38 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡
ይህ የተቀማጭ ገንዘብ መጠን ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር 900 ሚሊዮን ብር ብልጫ አለው፡፡
የባንኩ የብር ክምችት በ2011 ከነበረው 5.09 ሚሊዮን ብር ወደ 6.4 ቢሊዮን ብር ከፍ ማለቱ ተጠቅሷል፡፡
የባንኩ የ2012 ዓመታዊ ሒሳብ ከታክስ በፊት 240 ሚሊዮን ብር የደረሰ ሲሆን፣ ከ2011 አንፃር ሲታይ የዘጠኝ ሚሊዮን ብር ብልጫ አለው፡፡ ይህም የትርፍ ዕድገት አራት በመቶ ብቻ መሆኑን ያሳያል፡፡ ያለፉት አምስት ዓመታት የትርፍ ግኝትን የሚያመላክተው መረጃ በ2008 የሒሳብ ዓመት 102 ሚሊዮን ብር፣ በ2009 ደግሞ 146 ሚሊዮን፣ በ2010 ዓ.ም. 216 ሚሊዮን ብር ማትረፉን ሲሆን፣ በ2006 ዓ.ም. 34 ሚሊዮን ብር ማትረፉ ይጠቀሳል፡፡
የባንኩን የ2012 የሥራ አፈጻጸም በተመለከተ የእናት ባንክ ዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር ወ/ሮ ሃና ጥላሁን እንደተናገሩት፣ የ2012 የሒሳብ ዓመት ለባንክ ኢንዱስትሪው ተግዳሮቶች የበዙበት እንደነበር ገልጸዋል፡፡ በተለይ በባንካቸው ላይ የፈጠረውን ተፅዕኖ 2011 የሒሳብ ዓመት በብዙ መልኩ ካለፉት ዓመታት የተለየ እንደነበር ገልጸው፣ በተለይ በመጀመርያ ሦስት ሩብ ዓመታት ላይ የተከሰተው የገንዘብ ፍሰት ችግር በዚያን ያክል ስፋትና ጥልቀት የባንክ ኢኮኖሚን ይጎዳል ተብሎ ታሳቢ አለመደረጉን አክለዋል፡፡ ይሁን እንጂ ባንኮችን ለመታደግ ብሔራዊ ባንክ በወሰደው ዕርምጃ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን የገንዘብ ፍሰቱ በመሻሻሉ፣ ችግሩን በመቅረፍ ለመቋቋም ስለመቻሉ አመልክተዋል፡፡
ይህ የገንዘብ ፍሰት ተፅዕኖ ከታሰበው በላይ የተራዘመ ስለነበር፣ ተቀማጭ ሒሳብን ማሰባሰብ ብድር ማስከፈልና ክፍያዎች የማወራረድ ሥራን አታካች አድርጎት እንደነበር የገለጹት ወ/ሮ ሃና፣ በተለይ ደግሞ ባንኮች ከዚህ ችግር ለመውጣት በሚታትሩበት ወቅት፣ የኮሮና ወረርሽኝ ተህዋሲ በአራተኛው ሩብ ዓመት መግቢያ ላይ መከሰቱ፣ ነገሩን ሁሉ ከድጡ ወደ ማጡ አድርጎት እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
የኮሮና ወረርሽኝ መከሰት በዜጎች ላይ የፈጠረው መደናገጥና ይህን ተከትሎ የታወጀው የእንቅስቃሴ ገደብ፣ ሰዎች የፍጆታ ዕቃዎችን በብዛት ገዝተው እንዲያካማቹ አስችሎአቸው እንደነበር በመጥቀስ፣ በዚህ ምክንያት ብዙ ገንዘብ ከባንክ በመውጣቱ የገንዘብ ፍሰቱ ችግር ተባብሶ አልፏል፡፡ በክፍለ ኢኮኖሚው ውስጥ ያጋጠመው የገንዘብ እጥረት ችግርና ፈተናዎች የነበሩበት ወቅት ቢሆንም፣ እንዲሁም ባንኩ ውጪያዊ ሁኔታዎች አሉታዊ ተፅዕኖዎች ቢያሳድሩበትም በሁሉም መስክ ዕድገት ማስመዝገቡ ተገልጿል፡፡ ለአብነት ከደንበኞች የተሰበሰበው ተቀማጭ ሒሳብ 8.4 ቢሊዮን ብር ሲሆን፣ ይህም አኃዝ ከአምናውን ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ17 በመቶ ከፍ ያለ መሆኑ አንዱ መሆኑ ተገልጿል፡፡ ለተለያዩ ክፍለ ኢኮኖሚዎች ብድር የመስጠት አገልግሎት ተጠናክሮ የቀጠለ መሆኑን የሚያመለክተው የባንኩ መረጃ፣ በ2012 ዓ.ም. በተሰጠው ብድር ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በ27 በመቶ ብልጫ አለው፡፡
ከዚህም በላይ የባንኩን ዕድገት በግልጽ ሊያሳዩ የሚችሉት የባንኩ ሀብት ደግሞ ከ11 ቢሊዮን በላይ ደርሷል፡፡ ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር እንደየቅደም ተከተላቸው የ17 በመቶና የ21 በመቶ ዕድገት ማሳየቱን ገልጸዋል፡፡
እናት ባንክ በአሁኑ ወቅት አገልግሎት የሚሰጥባቸውን ቅርንጫፎች ቁጥር ወደ 57 አሳድጓል፡፡