Monday, March 4, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

አወዛጋቢ ሆኖ የቆየውን የንግድ ምክር ቤቶች የማቋቋሚያ አዋጅ ስያሜውን ጭምር የሚተካ ረቂቅ አዋጅ አዘጋጀ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የከተማ ንግድ ምክር ቤቶች ተዘለዋል

በአዋዛጋቢነቱ ሲጠቀስ የነበረውና እንዲሻሻል ተደጋጋሚ ጥያቄዎች ሲቀርቡበት የቆየው የንግድ ምክር ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅን ይተካል ተብሎ የሚጠበቀው ረቂቅ አዋጅ ተጠናቆ ሊመከርበት መሆኑ ተገለጸ፡፡

እስካሁን በሥራ ላይ የቆየው አዋጅ ቁጥር 341/1995 በርካታ ክፍተቶች ያሉበትና በአጠቃላይ ከአደረጃጀት ጀምሮ ብዥታ ያለበት መሆኑ ታምኖበት መሻሻል እንደሚገባው ጥያቄ መቅረብ ከጀመረ ከዓመታት በኋላ፣ አዋጁን ማሻሻል እንደሚገባ ታምኖበት ሲሠራ ቆይቷል፡፡

የሪፖርተር ምንጮች እንዳመለከቱት የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር እስካሁን የነበረውን አዋጅ የሚተካ ረቂቅ አዋጅ በማጠናቀቁ፣ በረቂቁ ላይ ለመምከርና ተጨማሪ ግብዓቶች ለማሰባሰብ በሚቀጥለው ሳምንት ሊመከርበት መሆኑ ታውቋል፡፡ ረቂቁም ለንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶች መላኩ የታወቀ ሲሆን፣ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በቀጣዩ ሳምንት ሐሳባቸውን እንዲሰጡ ያላቸውን ግብዓት ያቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸው የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶች እስካሁን የነበረው አዋጅ በምን መልኩ መሻሻል እንዳለበት ግብዓቶችን ከዚህ ቀደም የሰጡ መሆኑ የሚታወስ ሲሆን፣ ግብዓታቸው ምን ያህል እንደተካተተ ግን አልታወቀም፡፡

በሚቀጥለው ሳምንት ይፋ የሚሆነው ረቂቅ አዋጅ ውስጥ ምን ያህል ግብዓት እንደተካተተ ለማወቅ ቢያስቸግርም፣ አዲሱ አዋጅ ግን ከቀደመው በብዙ መልኩ የሚለይ ሊሆን እንደሚችል እምነታቸውን የገለጹ አሉ፡፡

ከስያሜው ጀምሮ ብዙ ለውጦችና ማሻሻያዎችን ይኖሩታል  የተባለው አዲሱ ረቂቅ አዋጅ፣ ከዚህ ቀደም የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት በሚል የሚታወቀው አዋጅ ‹‹የኢትዮጵያ ንግድና ኢንዱስትሪ ምክር ቤት ማቋቋሚያ አዋጅ›› በሚል የሚቀርብ እንደሆነም ታውቋል፡፡ ቀደም ብሎ ‹‹ዘርፍ ማኅበር›› በሚል የተጠቀሱትን ማኅበራት የሚያስቀርና ንግድ ምክር ቤቶች ከዚህ ቀደም ከነበረው አደረጃጀታቸው በተለየ የሚቋቋሙ መሆኑን አመልክተዋል፡፡  

በንግድና ምክር ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ ‹‹የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት›› በሚል የሚጠቀሱ ምክር ቤቶች የዘርፍ ማኅበራት ለብቻቸው እንዲደራጁ የሚያደርግና ንግድና ዘርፍ ምክር ቤቶች እንደገና በአንድ ላይ እንዲደራጁ በማድረግ ለአሠራር ምቹ ያልሆነ አደረጃጀት እንዲተገበር የሚያደርግ መሆኑ ሲጠቀስ ቆይቷል፡፡ አሁን ግን ንግድና ኢንዱስትሪን በማስተሳሰርና የውክልና ሁኔታቸውም በግልጽ በማስቀመጥ ምክር ቤቶቹ እንዲደራጁ የሚፈቅድ ይሆናል፡፡

በተጨማሪም የዘርፉ ማኅበራት ተብለው የተለዩ የቢዝነስ ተቋማትና የንግድ ዘርፍ ከሚለው የቢዝነስ ዘርፍ ጋር የሚደበላለቅ በመሆኑ፣ በንግድ ምክር ቤቶች አደረጃጀት ላይ ብዙ ችግር የፈጠረ፣ በንግድ ምክር ቤቶች አካባቢ ሲፈጠሩ የነበሩ ውዝግቦች እንደ አንድ ምክንያት ይጠቀሱ እንደነበር ይታወሳል፡፡

የአዲሱን ረቂቅ አዋጅ ዝግጅት በተመለከተ በረቂቅ አዋጁ መግቢያ ላይ አገሪቱ የምትከተለውን የነፃ ገበያ ፖሊሲ መነሻ በማድረግ፣ የንግዱና የአምራች ኢንዱስትሪው ማኅበረሰብ በራሱ ምክር ቤት ተሰባስቦ ዘመናዊ፣ ተደራሽና ቀልጣፋ ሥርዓት በመመሥረት፣ የበኩሉን ሚና እንዲጫወት ለማስቻል የተሰናዳ መሆኑን ተመልክቷል፡፡  ምክር ቤቶች በአገራችን ኢኮኖሚ ግንባታ ውስጥ ሊኖራቸው የሚገባውን ጉልህ ሚና ይበልጥ በማጠናከር፣ ለመንግሥትም ሆነ ለባለድርሻ አካላት የሚያቀርባቸው ምክረ ሐሳቦች ተቀባይነት እንዲኖራቸው የሚያስችል ጠንካራ ምክር ቤቶች እንዲፈጠሩ ማድረግ አስፈላጊ በመሆኑ፣ ማሻሻያ መደረጉንም ይጠቁማል፡፡ ምክር ቤቶች የገቢ ምንጫቸውን ለማሳደግና የአባላትን ቁጥር ለማብዛት የሚያስችል የንገዱንና የአምራች ኢንዱስትሪ ማኅበረሰቡን የሚስብ፣ ተጠያቂነት ያለው ግልጽ የሆነ የአሠራር ሥርዓት ከመፍጠር አኳያም፣ አዲሱ አዋጅ እንደ ግብ አድርጎ ያስቀምጣል፡፡ የግሉን ዘርፍ የተበታተነ አደጃጀት፣ የአባላትን ቁጥር ለማብዛት የሚያስችል የንግዱንና የአምራች ኢንዱስትሪ ማኅበረሰቡን የሚስብ፣ ተጠያቂነት ያለው ግልጽ የሆነ የአሠራር ሥርዓት ከመፍጠር፣ የግሉን ዘርፍ የተበታተነ አደረጃጀትና የአቅም ውስንነት በመፍታት የአባላትን መብትና ጥቅም ለማስጠበቅ በሚያስችል መልኩ እንደገና ማቋቋም አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱንም ያመለክታል፡፡

ረቂቅ አዋጁ 35 አንቀፆች ያሉት ሲሆን፣ በአገር አቀፍ ደረጃ የሚቋቋሙት የንግድና ኢንዱስትሪ ምክር ቤቶች እንዲሁም የክልል ንግድና ኢንዱስትሪ ምክር ቤቶች አደረጃጀትን በዝርዝር የያዘ ሲሆን፣ የኢትዮጵያም ሆነ የክልል ንግድና ኢንዱስትሪ ምክር ቤቶች ስለሚሠሩ የቦርድ አባላት ሥልጣንና ተግባራትም አዳዲስ አንቀፆች የተካተተበት ነው፡፡

በተለይ ስለቦርድ አባላት በተደነገገው አንቀጽ ሥር የኢትዮጵያ ንግድና ኢንዱስትሪ ምክር ቤት፣ በጠቅላላ ጉባዔ የተመረጡት የቦርድ አባላት ከመካከላቸው ፕሬዚዳንቱንና ምክትል ፕሬዚዳንቱን እንደሚመርጡ ይገልጻል፡፡ የምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት የጉባዔውንና የቦርዱን ስብሰባዎች ጥሪ ያስተላልፋል፣ ይመራል፣ የቦርድ አባላት ፕሬዚዳንቱንና ምክትል ፕሬዚዳንቱን ጨምሮ ከ11 መብለጥ እንደሌለባቸው የሚደነግግ በመሆኑ፣ በምክር ቤቱ የቦርድ አባል መሆን የሚችለው ኢትዮጵያዊ ዜግነት ያለው ሰው ብቻ እንደሆነም ያመለክታል፡፡

ከዚህ ቀደም በነበረው አዋጅ ያልነበረውና አዲስ ከተካተቱት ውስጥ የቦርድ አባላት ስብጥርን የሚመለከተውም ይገኝበታል፡፡ የኢትዮጵያ የንግድና ኢንዱስትሪ ምክር ቤት የቦርድ አባላት ስብጥርም፣ ከክልል የንግድና ኢንዱስትሪ ምክር ቤቶች 50 በመቶ፣ በአገር አቀፍ ደረጃ ከሚቋቋሙ የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ማኅበራት 40 በመቶ፣ በአገር አቀፍ ደረጃ ከሚቋቋሙ የንግድ ሥራ ዘርፍ ማኅበራት አሥር በመቶ ያካተተ መሆን እንዳለበት አመላክቷል፡፡

የክልል የንግድና ኢንዱስትሪ ምክር ቤቶች የቦርድ አባላት ስብጥርን በተመለከተም፣ ከግለሰብ ነጋዴዎች አሥር በመቶ፣ ከሽርክና ማኅበራት 20 በመቶ፣ ኃላፊነታቸው ከተወሰነ የንግድ ማኅበራት 40 በመቶ፣ ከንግድ ሥራ ዘርፍ ማኅበራት አሥር በመቶ ያካተተ መሆን እንዳለበት ደንግጓል፡፡

ከዚህ ቀደም አጨቃጫቂ የነበረው የቦርድ የሥራ ዘመን ጉዳይ በአዲሱ አዋጅ ገደብ እንዲኖረውና ወጥ እንዲሆን ተደርጓል፡፡ በዚህም መሠረት የቦርድ የአገልግሎት ዘመን ሦስት ዓመታት ሆኖ ማንኛውም የቦርድ አባል የሆነ ሰው ከሁለት ጊዜ በላይ መመረጥ እንደማይቻል ደንግጓል፡፡ የምክር ቤቱ የምርጫ አፈፃፀም መሥፈርትና ሥርዓት በምክር ቤቱ ውስጠ ደንብ የሚወሰን መሆኑንም አስቀምጧል፡፡

አስቸኳይ ጉባዔ እንዲጠራ ከጠቅላላ ጉባዔው አባላት ውስጥ አሥር በመቶ የሚሆኑ አባላት ተፈራርመው ጥያቄ ለቦርድ ሲያቀርቡ ወይም ቦርዱ በአብላጫ ድምፅ ሲወሰን፣ አስቸኳይ ጉባዔ እንዲጠራ ሊደረግ እንደሚችል ረቂቁ የሚያመላክት ሲሆን፣ እንዲጠራ ጥያቄው በቀረበ ወይም በተወሰነ በ30 ቀናት ውስጥ ጉባዔው መጠራት እንዳለበትም ያመለክታል፡፡

በዚህ ረቂቅ አዋጅ ንግድና ኢንዱስትሪ ምክር ቤት መከወን አለበት ተብሎ የተጠቀሰው አዲስ አንቀጽ፣ በአገር አቀፍና በክልል የሚዘጋጁ የንግድ ትርዒቶችና ባዛሮችን ደረጃ፣ መሥፈርትና ስለሚፈቀድበት ሁኔታ ሚኒስቴሩ በሚያወጣው መመርያ የሚወሰን መሆኑን ደንግጓል፡፡ በአገር አቀፍ ደረጃ ለሚዘጋጁ የንግድ ትርዒቶችና ባዛሮች ፈቃድ የሚሰጠው ሚኒስቴሩ እንደሚሆን በክልል የሚዘጋጁ የንግድ ትርዒቶችና ባዛሮች ፈቃድ የሚሰጠው፣ በክልል የንግድ ኢንዱስትሪ አስፈጻሚ ቢሮ ይሆናል፣ በአገር አቀፍና በክልል ለሚዘጋጁ የንግድ ትርዒቶችና ባዛሮች ፈቃድ ሲሰጥ፣ በትርዒቱና በባዛሩ ተሳታፊ ያልሆኑ ነጋዴዎችንና አምራቾችን የማይጎዳ መሆኑ ከግምት ውስጥ መግባት እንዳለበት፣ በሚሰጣቸው ውክልና ካልሆነ በስተቀር ከሚኒስቴሩና ከክልል የንግድና ኢንዱስትሪ አስፈጻሚ ቢሮ ውጪ ሌሎች አካላት የንግድ ትርዒቶችና ባዛሮች እንዲዘጋጁ ፈቃድ መስጠት እንደማይችሉ ተደንግጓል፡፡  

ይህ ረቂቅ አዋጅ በርካታ አዲስ ነገሮች ያሉትና ከቀድሞ የተሻለ እንደሆነ ቢገለጽም የከተማ ንግድ ምክር ቤቶችን ጉዳይ ያዘለ መሆኑ ታውቋል፡፡ ከዚህም ሌላ ከዚህ ቀደም ከንግድ ማኅበረሰቡ የተሰጡ ጥቂት የማይባሉ ምክረ ሐሳቦች እንዳልተካተቱበት አስተያየቶች እየተሰነዘሩ ነው፡፡

የአዋጁ መሻሻል አንድ ዕርምጃ ስለመሆኑ እየተገለጸ ሲሆን፣ በሚቀጥለው ሳምንት በሚደረገው ውይይት ላይ የንግዱ ማኅበረሰብ ጥያቄ አዲሱ አዋጅ መልሷል ወይ? የሚለው ሐሳብ ያነጋግራል የሚል እምነት እንዳላቸው ሪፖርተር ስለጉዳዩ ያነጋገርናቸው የንግዱ አካላት ሳይጠቁሙ አላለፉም፡፡  

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች