ማክሰኞ ታኅሳስ 6 ቀን 2013 ዓ.ም. ኢትዮጵያና ሱዳንን በሚያዋስነው ድንበር ላይ በሁለቱ አገሮች ሠራዊት አባላት መካከል በተፈጠረ ግጭት፣ ቁጥራቸው ይፋ ያልተደረገ የሱዳን ጦር አባላት መገደላቸውንና በርካቶችም መቁሰላቸውን የሱዳን መንግሥት ይፋ አድርጓል።
ሱዳንን ከኢትዮጵያ በሚያዋስነው አካባቢ ቅኝት በማድረግ ላይ የነበሩ የሱዳን ጦር አባላትን፣ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አባላትና የታጠቁ ሚሊሻዎች ተኩክስ ከፍተው እንደገደሏቸው፣ እንዳቆሰሏቸውና የጦሩን ንብረትም እንዳወደሙ የሱዳን መንግሥት አስታውቋል።
ድርጊቱም በሱዳን ግዛት ውስጥ የተፈጸመ በመሆኑ የአገሪቱን ሉዓላዊነት የተዳፈረ እንደሆነ በመግለጽ አውግዟል።
‹‹በወዳጅ አገር ኢትዮጵያ ያለውን የፀጥታ ሁኔታ ላለፉት ስድስት ሳምንታት በአንክሮ እየተከታተልን እንገኛለን። በኢትዮጵያ በተከሰተው ግጭት ምክንያት ከመኖሪያቸው ሸሽተው ወደ ሱዳን ድንበር የገቡ በበርካታ ሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያንን ተቀብለን እያስተናገድን ነው፡፡ ያለንበት የኢኮኖሚ ሁኔታ አዳጋች ቢሆንም፣ ሕዝባችን ባለው ወዳጅነትና መልካምነት የተነሳ ስደተኞቹን እየተቀበልን እንገኛለን፤›› ያሉት የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር አብዱላ ሃምዶክ ይህ እየሆነ ባለበት ወቅት፣ ባለፈው ሳምንት ከኢትዮጵያ ጦር በተሰነዘረ ጥቃት በርካታ የሱዳን ወታደሮች ሞተዋል ብለዋል።
በክስተቱ ላይ የሚመሩት ካቢኔ እንደተነጋገረ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ካቢኔያቸው ድርጊቱን በማውገዝ ሱዳንንና ድንበሯን ከሚጠብቀው የአገሪቱ ጦር ጎን እንደሚቆም ማረጋገጡን አስታውቀዋል፡፡
‹‹የሱዳን ጦር የአገሪቱን ድንበር የማስከበርና ማንኛውንም ወረራ የመቀልበስ አቅም እንዳለው የሱዳን መንግሥት እምነት አለው፣ ከጦሩ ጎንም ይቆማል፤›› ብለዋል።
የሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር እሑድ ታኅሳስ 4 ቀን 2013 ዓ.ም. ለሁለት ቀናት ይፋዊ የሥራ ጉብኝት አዲስ አበባ መጥተው፣ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ጋር የተወያዩ ቢሆንም የሁለት ቀናት የሥራ ጉብኝት ፕሮግራሙን በዚያው ዕለት አጠናቀው መመለሳቸው ይታወሳል።
የሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር የሁለት ቀናት የጉብኝት ፕሮግራሙን ቀርቶ በዚያው ዕለት ወደ አገራቸው መመለሳቸው የተለያዩ መላ ምቶችን የወለደ ሲሆን፣ ከዚህም ውስጥ አንዱ በሁለቱ አገሮች መሪዎች መካከል መግባባት ባለመፈጠሩ ከአውሮፕላን ማረፊያ እንደተመለሱ የሚገልጹ ወሬዎችም ተሠራጭተው ነበር።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከኢትዮጵያ ጉብኝታቸው መልስ በካርቱም በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ የኢትዮጵያ ጉብኝታቸው ለሁለት ቀናት ተይዞ በዕለቱ በመመለሳቸው ምክንያት አሉባልታዎች መነዛታቸውን፣ አሉባልታዎቹም በእውነታ ላይ የተመሠረቱ ሳይሆኑ ሐሰት ናቸው ብለዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ሃምዶክ ለሁለት ቀናት ጉብኝት አዲስ አበባ መምጣታቸውን አስታውሰው፣ ነገር ግን በራሳቸው ጥያቄ መሠረት ጉብኝቱ በአንድ ቀን እንዲያጥር መደረጉን አመልክተዋል፡፡
ከቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ እንደተባረሩ ተደርጎ መወራቱን ጠቁመው፣ ‹‹ከጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ጋር ከአውሮፕላን ማረፊያ ወደ ቤተ መንግሥት ስናመራ፣ ሁለቱም አገሮች ካለባቸው ወቅታዊ ሁኔታ አንፃር ጉብኝቱ ለአንድ ቀን እንዲሆን ሐሳብ ያቀረብኩት እኔ ነኝ፡፡ ከበፊት ጉብኝቶቼ ይልቅ ይኼኛው የተሳካ ነበር፤›› ብለዋል፡፡
‹‹በነበሩን የሁለትዮሽና የቀጣናዊ አጀንዳዎች ላይ የተሳኩ ውይይቶችን አድርገን፣ ሌሎች ለጉብኝቱ የያዝናቸውን አጀንዳዎች በስምምነት ሰርዘናል፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡
ከቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ጀምሮ በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ መልካም አቀባበል እንደተደረገላቸው፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ራሳቸው መኪና እያሽከረከሩ እንዳስተናገዷቸው ተናግረዋል፡፡
ሱዳን ችግር ባጋጠማት ወቅት ኢትዮጵያ ቀድማ የደረሰችላት ሁነኛ ወዳጅ መሆኗን ያስታወሱት የሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር፣ ኢትዮጵያ ችግር ሲገጥማትም ሱዳን እንደምትደግፋት ለማሳየት የተደረገ ጉብኝት እንደነበረ በመግለጽ፣ ከዚህ ውጪ የተባለው ሁሉ አሉባልታ ነው ሲሉ አስታውቀዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) እሑድ ታኅሳስ 11 ቀን 2013 ዓ.ም. በጂቡቲ ለኢጋድ አባል አገሮች መሪዎች ስለትግራይ ክልል ሁኔታ ሪፖርት እንደሚያቀርቡ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ሃምዶክ መናገራቸው ይታወሳል፡፡
በኢትዮጵያ በነበራቸው አጭር ቆይታም በትግራይ ክልል ወቅታዊ ሁኔታና በኢትዮጵያና ሱዳን ድንበር መካከል ያለውን አወዛጋቢ ድንበር መፍትሔ ለመስጠት የተቋቋመው የሁለቱ አገሮች የጋራ ኮሚቴ ሥራ በሚጀምርበት ሁኔታ ላይ መመካከራቸውንም ገልጸዋል።
ይህንን ውይይት በአዲስ አበባ አካሂደው ወደ ሱዳን ከተመለሱ በኋላ በሁለተኛው ቀን በኢትዮጵያና ሱዳን ድንበር ላይ በሁለቱ አገሮች መካከል ግጭት መፈጠሩ ሥጋት ቀስቅሷል።
ለድንበር ውዝግቡ መፍትሔ ለማበጀት ሁለቱ አገሮች በመከሩ በቀናት ውስጥ በድንበሩ ላይ ግጭት መፈጠሩ፣ የድንበር ውዝግቡን ከፍ ወዳለ ጠብ እንዳያሸጋግረው የፖለቲካ ተንታኞች ሥጋታቸውን እየገለጹ ይገኛሉ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ጉዳዩን አስመልክቶ በትዊተር ገጻቸው ላይ ሐሙስ ዕለት መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን፣ በመልዕክታቸውም የኢትዮጵያ የሚሊሻ አባላት በኢትዮ–ሱዳን ድንበር ፈጽመውታል የተባለውን ጥቃት መንግሥታቸው በቅርበት እየተከታተለው እንደሚገኝ አመልክተዋል።
የሱዳን መንግሥት ለጥቃቱ የኢትዮጵያን መከላከያ ሠራዊትና የአካባቢውን የሚሊሻ ኃይል ተጠያቂ ቢያደርግም፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ግን በተከሰተው ግጭት የመከላከያ ሠራዊቱ ስለመሳተፉ በትዊተር መልዕክታቸው አላካተቱም። በመልዕክታቸው የጠቀሱት በአካባቢው ያለውን የሚሊሻ ኃይል ሲሆን፣ በዚህ ኃይል በኩል ያለውን እንቅስቃሴ መንግሥታቸው በቅርበት እንደሚከታተለው እንጂ ጥቃት ስለመሰንዘሩ ያሉት ነገር የለም።
‹‹ችግሮችን ለመፍታት ሁሌም ውይይትን የምንጠቀም በመሆኑ እንደዚህ ያሉ ክስተቶች የሁለቱን አገሮች ትስስር አይበጥሱትም፤›› ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ፣ ‹‹ሁኔታውን እያራገቡ የሚገኙ ኃይሎች የሁለቱ አገሮች ታሪካዊ ትስስር ጥንካሬ አይገባቸውም፤›› ብለዋል።
ይህ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር በኢትዮ ሱዳን ድንበር ላይ የተከሰተውን ግጭት ተከትሎ፣ የግብፅ መንግሥት ባወጣው መግለጫ ላራመደው አቋም የተሰጠ አጭር ምላሽ አስመስሎታል።
ሱዳን ድንበሯን የማስከበር መብቷን የግብፅ መንግሥት እንደሚደግፍ፣ በዚህ ረገድም ለሱዳን መንግሥት ሙሉ ድጋፍ እንደሚያደርግ፣ በኢትዮ ሱዳን ድንበር ተከስቶ ያለፈውን ግጭት ተከትሎ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
በኢትዮጵያና በሱዳን ድንበር የተከሰተውን ግጭት በቅርበትና በከፍተኛ ትኩረት እንደምትከታተለው ያስታወቀችው ግብፅ፣ ይህንንም የምታደርገው በዚህ አካባቢ የሚፈጠር ማንኛውም አለመረጋጋት በቀጣናውን ደኅንነት ላይ አደጋ ስለሚፈጥር መሆኑን ጠቁማለች፡፡
በሱዳን ላይ ተመሳሳይ ጥቃት ወደፊት እንዳይከሰት ለመከላከልም ማንኛውንም ዓይነት ዕርምጃ መውሰድ አስፈላጊ እንደሆነ፣ የግብፅ መንግሥት አቋም መውሰዱን በመግለጫው አስታውቋል።
በጉዳዩ ላይ ሪፖርተር ያነጋገራቸው አንድ የፖለቲካ ተንታኝ እንደሚሉት ግብፅ ከህዳሴ ግድቡና የዓባይን ውኃ ከመጠቀም የኢትዮጵያ መብት ወደ ተግባር እንዳይለወጥ የምትከተላቸው ስትራቴጂዎች ሁለት መልክ ያላቸው እንደሆኑ፣ የሁለቱም ስትራቴጂዎች ግብ በኢትዮጵያ አለመረጋጋትን መፍጠር አንደሆነ ገልጸዋል።
በዋናነት ጥቅም ላይ ስታውለው የነበረው የመጀመርያ ስትራቴጂ በኢትዮጵያ ያሉ የፖለቲካ ኃይሎችን በመደገፍ በአገር ውስጥ ፖለቲካዊ አለመረጋጋትን፣ እንዲሁም ግጭትን በዘላቂነት መፍጠር እንደሆነ የሚገልጹት ባለሙያው፣ በዚህ ረገድ በአሁኑ ወቅት ግጭትና አለመረጋጋትን ከምንጩ ለማድረቅ የኢትዮጵያ መንግሥት እንቅስቃሴ ውስጥ ሲገባ፣ ግብፅ ሁለተኛ ስትራቴጂዋን ማንቀሳቀስ እንደ ጀመረች ያስረዳሉ።
ሁለተኛው ስትራቴጂ በኢትዮጵያና በጎረቤት አገሮች መካከል ባሉ ክፍተቶች በመግባት አለመግባባቶችን ማስፋትና ግጭትን መቀስቀስ፣ አልያም የኢትዮጵያ መንግሥት እነዚህን አለመግባባቶች ለመፍታት የሚያሳልፈውን ውሳኔ ቀዳዳዎች በመጠቀም በአገር ውስጥ ተቃውሞ እንዲነሳ ማድረግ እንደሆነ ገልጸዋል።
በኢትዮጵያና በሱዳን መካከል ያለው የድንበር ይገበኛል ጥያቄ ዛሬ የመጣ ሳይሆን ዘመናትን ያስቆጠረ መሆኑን ያስታወሱት ባለሙያው፣ በሁለቱ አገሮች ድንበር ላይም በ2012 ዓ.ም. ብቻ በርካታ ግጭቶች ተከስተው እንደነበር ነገር ግን ከግብፅ መንግሥት በኩል እንዳሁኑ ዓይነት መግለጫ ተሰጥቶና አቋም ተይዞ እንዳልነበር ገልጸዋል።
የዚህ ምክንያቱ ደግሞ በወቅቱ በአገር ውስጥ በቂ መግቢያ ቀዳዳዎች የነበሯት በመሆኑ ነው ብለዋል። የኢትዮጵያ መንግሥት በአገር ውስጥ ያሉ የደኅንነት ምንጮችን ለመፍታት ቆራጥ አቋም በመያዙ፣ ግብፅ ትኩረቷን ከኢትዮጵያ በሚጎራበቱ አገሮች ዙሪያ በማድረግ በኢትዮጵያ አለመረጋጋት ላይ ሌላ ምክንያት እየቆፈረች እንደሆነ ይገልጻሉ።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህም በሱዳንና በደቡብ ሱዳን የግብፅ መንግሥት ሴራዎችን እየጎነጎነ እንደሚገኝ በመጥቀስ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት እነዚህን እንቅስቃሴዎች በአንክሮ አስተውሎ በፍጥነት ፖለቲካዊ ምላሽ እንዲሰጥ ያሳስባሉ።
በቅርቡ የኢትዮጵያ መንግሥት ከሱዳን መንግሥት ጋር የባቡር መሠረተ ልማት ለመዘርጋት ያደረገው ስምምነት፣ ይኼንን ስምምነት ወደ ተግባር ለመቀየር የተሄደው ትርጉም ያለው ተግባር አንዱ የውጭ ጣልቃ ገብነትን ማክሰሚያ መንገድ እንደሆነም ይገልጻሉ።