ኢህአዴግ ለ17 ዓመታት ባደረገው ጦርነት የደርግ መንግስትን አሸንፎ አገሪቱን በተቆጣጠረበት ግንቦት ወር 1983 ዓም ጀምሮ በጣሊያን ኤምባሲ ተጠልለው ላለፉት 29 ዓመትት የቆዩትና ባልተከታተሉት ወይም ባልተሟገቱበት የክስ ሂደት ሞት ተፈርዶባቸው የነበሩት የደርግ ከፍተኛ ሁለት ባለስልጣናት ሞቱ ቀሪ እንደተደረገላቸው ተጠቆመ።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የነበሩት ኮሎኔል ብርሃኑ ባየህና ኤታማዦር ሹም የነበሩት ሌተናል ጀነራል አዲስ ተድላ በሌሉበት በተመሰረተባቸው የዘር ማጥፋት ክስ የተፈረደባቸውን የሞት ቅጣት በመተው ወደ ዕድሜ ልክ እስራት በመቀየር ያሻሻሉት ፕሬዝደንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ናቸው።
ፕሬዝደንቷ የቀድሞ ባለስልጣናትን የሞት ቅጣት ወደ ዕድሜልክ ያሻሻሉት ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ በአዋጁ መሠረት ስርዓቱን ተከትሎ ባቀረበው ጥያቄ መሠረት እንደሆነና ፕሬዝዳንቷም የቅጣት ማሻሻያ ደብዳቤውን ከአንድ ወር በፊት መፈረማቸው ተጠቁሟል።
ባለስልጣናቱ ዕድሜያቸው ከ80 በላይ መሆኑን፣ ከቤተሰብና ባጠቃላይ ከማንኛውም እንቅስቃሴ ተከልክለው 29 ዓመታትን ማሳለፋቸው ተጨማሪ ቅጣት ከመሆኑም በተጨማሪ ባሁኑ ጊዜ ስኳርን ጨምሮ በተለያዩ ህመሞች እየተሰቃዩ መሆኑን በመጥቀስ መንግስት ምህረት እንዲያደርግላቸው የቀድሞ ጓዶቻቸው ጥያቄ ማቅረባቸው ይታወሳል።
ባለስልጣናቱ የሞት ፍርዱ ወደ ዕድሜ ልእስራት ስለተቀየረላቸውና ዕድሜልክ የተፈረደበት ወንጀለኛ 20 ዓመታት ከታሰረ የታሰረው በቂ ሆኖ እንዲፈታ በሕግ የተደነገገ ቢሆንም ሕጉ የእስር ጊዜያቸውን በማረሚያ ቤት ላሳለፉ በመሆኑ ምናልባት በፖለቲካ ውሳኔ እንዲለቀቁ ይደረግ ይሆናል የሚሉ አስተያየት ሰጪዎች እየተናገሩ ነው።