Sunday, April 14, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

የታሪክ ተወቃሽ ላለመሆን ጥንቃቄ ይደረግ!

ኢትዮጵያ በረዥም ታሪኳ በርካታ ውጣ ውረዶች የታዩባት አገር ናት፡፡ እነዚህ በታሪክ የተመዘገቡ ውጣ ውረዶች ከባድ መስዋዕትነቶች አስከፍለዋል፡፡ የአገር ውስጥ ሽኩቻዎች፣ እንዲሁም የውጭ ወራሪዎችንና ተስፋፊዎችን ለመመከት የተደረጉ ተጋድሎዎች፣ በተለያዩ ዘመናት ለልማትና ለዕድገት ሊውሉ የሚችሉ የሰው ኃይልና የአገር ሀብቶችን አሳጥተዋል፡፡ ዘመናት በተቀያየሩ ቁጥር ትውልዶችም በእነዚህ ውጣ ውረዶች ውስጥ አሳልፈዋል፡፡ ታሪክም ክፉና ደግ የሚባሉ ድርጊቶችን በየፈርጃቸው ሰንዶ ይዟል፡፡ የዚህ ዘመን ትውልድም ከታሪክ ክንውኖች ክፉና ደግ የሚባሉትን በመለየት፣ በራሱ ዘመን የተሻለ አበርክቶ እንዲኖረው የራሱን አሻራ ማሳረፍ ይጠበቅበታል፡፡ ይህ አሻራ ግን በታሪክ ተወቃሽ እንዳያደርገው ልዩ ጥንቃቄ ማድረግ አለበት፡፡ ለዚህ በመጀመርያው ረድፍ ላይ የሚቀመጠው አገር የሚያስተዳድረው መንግሥት ሲሆን፣ በየደረጃው የእምነት ተቋማት፣ የትምህርት ተቋማት፣ የሲቪክና የሙያ ማኅበራት፣ የአገር ሽማግሌዎችና ታዋቂ ሰዎች፣ ምሁራን፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችና የአገር ጉዳይ ያገባናል በማለት በአደባባይ ድምፃቸውን የሚያሰሙ ይጠበቃሉ፡፡ እነዚህ ወገኖች መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ዘመናትን የተሻገረባቸውን የጋራ ማኅበራዊ እሴቶቹን በመጠበቅ፣ ምንም ነገር ከአገር ህልውናና ከሕዝብ ደኅንነት እንደማይቀድም ስምምነት ሊኖራቸው ይገባል፡፡ ለዚህ የተቀደሰ ሐሳብ ጀርባ መስጠት አይገባም፡፡

ኢትዮጵያን በተቻለ ፍጥነት የግልና የቡድን ፍላጎት ማስፈጸሚያ ሊያደርጉ ከሚፈልጉ ዘመኑን የማይዋጁ አስተሳሰቦች በመታደግ፣ መላው ሕዝቧን በእኩልነትና በነፃነት ለማኖር የምትችል አገር አድርጎ ለመገንባት የጋራ የሆነ አማካይ መፍጠር ተገቢ ነው፡፡ የአንድ ወገን ፍላጎትን በኃይል ለመጫን የሚደረጉ አጉራ ዘለል ሙከራዎችን ሳይሆን፣ የምልዓተ ሕዝቡን ፍላጎት ማዕከል ያደረገ መደላድል መፍጠር የሚቻልባቸው አማራጮችን ማወዳደር ላይ ትኩረት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ የተለያዩ ሐሳቦች በነፃነት የሚፎካከሩበት ዓውድ በመፍጠር ለሕዝብ ውሳኔ እንዲቀርቡ ዕድሎችን ማመቻቸት የግድ መሆን አለበት፡፡ የፌዴራል ሥርዓቱ ምን መምሰል አለበት ለሚለው የተለያዩ አማራጮች ቀርበው በሕዝብ መበየን ሲኖርባቸው፣ የአንድ ጎራ ፍላጎትን ለማሳካት ሲባል ተቃራኒ ሐሳቦችን መድረክ መንፈግ የለየለት ውንብድና ነው፡፡ የሥልጣን ሉዓላዊ ባለቤት የሆነውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ፍላጎት ማወቅ የሚቻለው በነፃነት የመምረጥ መብቱ ሲረጋገጥ ብቻ ነው፡፡ እኔ አውቅልሃለሁ የሚልን አምባገነን አስወግዶ በእርሱ ምትክ እዚያው ቆጥ ላይ ለመሥፈር መሞከር አያዋጣም፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከግጭት ወደ ግጭት እየተሸጋገረ ያተረፈው ነገር ቢኖር ሞት፣ መፈናቀል፣ ስደት፣ ድህነትና ኋላቀርነት ነው፡፡ ይህንን ከንቱ ድርጊት ሲፈጽሙ የነበሩ ደግሞ ታሪክ ሲወቅሳቸው ይኖራል፡፡

ኢትዮጵያዊያንም ለዘመናት የገነቡዋቸው የጋራ ማኅበራዊ እሴቶቻቸውን በመጠበቅ የብሔር፣ የሃይማኖት፣ የቋንቋ፣ የባህልና የመሳሰሉት ልዩነቶቻቸው ሳይገድቧቸው አንድነታቸውን ማስጠበቅ አለባቸው፡፡ በፖለቲካው ውስጥ የተሰገሰጉ መተዳደሪያቸውን ግጭትና ውድመት ያደረጉ ምግባረ ብልሹ ግለሰቦችንና ቡድኖችን እየተከተሉ፣ አኩሪና ዘመን ተሻጋሪ እሴቶቻቸውን መናድ የለባቸውም፡፡ ፖለቲካው ውስጥ በአብዛኛው የሚተራመሱ ግለሰቦችም ሆኑ ስብስቦች በመርህ የሚመሩ ባለመሆናቸው፣ የአገሪቱን የፖለቲካ ምኅዳር የሚጠቀሙበት የራሳቸውን ጥቅም ለማሳካት መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል፡፡ አብዛኞቹ አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያን ምሁራንና ልህሂቃን ከፖለቲካ ተገልለው ባሉባት አገር ውስጥ፣ የራሳቸውን ፍላጎት ከአገር ደኅንነትና ህልውና በላይ የሚያስቀድሙ መብዛታቸውን ማወቅ ይገባል፡፡ እነዚህ ኃይሎች የተሻለ ተጫራች ከተገኘ አገር ከመሸጥ የማይመለሱ ናቸው፡፡ ለንፁኃን ዕልቂትና ለአገር ውድመት ምንም ደንታ የማይሰጣቸው ናቸው፡፡ ኢትዮጵያዊያን ከየትኛውም ብሔር ወይም እምነት ይሁኑ አገራቸውን የማያስቀድም የፖለቲካ አጀንዳ መፀየፍ አለባቸው፡፡ በሕዝብም ሆነ በአገር ላይ ከሚያሴሩና ከሚቆምሩ ፖለቲከኞች ጋር ያላቸውን ግንኙነት ማጤን ይጠበቅባቸዋል፡፡ ኢትዮጵያ እዚህ የደረሰችው የሕይወትና የአካል መስዋዕትነት ተከፍሎባት ነው፡፡ ይህ መስዋዕትነት ከፍተኛ ደም ፈሶበታል፣ አጥንት ተከስክሶበታል፣ ላብ ተንቆርቁሮበታል፡፡ በዚህ ምክንያት አገር መቀለጃ አይደለችም፡፡

በተለያዩ ዘመናት በጉልህ ድርጊቶቻቸው የሚታወቁ በርካታ ኢትዮጵያዊያን ስማቸው በደግም በክፉም ይነሳል፡፡ ምንም እንኳ በተንሸዋረሩ ዕይታዎች ምክንያት የተዛቡ ትርክቶች እየበዙ እውነቱና ሐሰቱ ቢደበላለቁም፣ በአገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን በውጭ የታሪክ ጸሐፍት ጭምር ለእውነት የቀረቡ ሥራዎቻቸው የሚወሱ መኖራቸውን መካድ አይቻልም፡፡ በዚህም መነሻ ለአዲሱ ትውልድ አርዓያነታቸው ጎልተው የሚሰሙ ድንቃ ድንቅ ተግባሮቻቸው የሚወሱ ያሉትን ያህል፣ ለትውልዱ አንገት መድፊያ የሆኑም መኖራቸውን መዘንጋት አይገባም፡፡ በዚህ ዘመን ደግሞ ራሳቸውን በነፃ አውጭነት እያመፃደቁ ሲፎክሩ የነበሩ፣ ምን ሲሠሩ እንደነበርና መጨረሻቸው ምን እንደሆነ ነጋሪ አያስፈልግም፡፡ ሕዝቡን እርስ በርሱ ሲያባሉ፣ አገር ሲዘርፉና ሲያዘርፉ፣ በዕብሪትና በትዕቢት ተወጥረው ጦርነት ቀስቅሰው ዕልቂት በመደገስ መጨረሻቸውን ያጣደፉ አምባገነኖችን ታሪክ በክፉ ድርጊታቸው ይከትባቸዋል፡፡ ከእንዲህ ዓይነቱ እጅግ አደገኛና ኋላቀር ድርጊት አለመማር ራሱን የቻለ መርገምት ነው፡፡ ፖለቲከኞችም ሆኑ በዙሪያቸው ያሉ ተከታዮቻቸው ይህንን ልብ ሊሉት ይገባል፡፡ በገዥው ፓርቲም ሆነ በተፎካካሪዎች አመራሮች፣ አባላትና ደጋፊዎች ዘንድ የሚታዩ ዘመንን የማይዋጁ ድርጊቶች፣ በታሪክ የሚያስጠይቁ መሆናቸውን መገንዘብ የግድ ነው፡፡

በቅርቡ በትግራይ ክልል በተካሄደው ዘመቻ ከባድ የሕይወት መስዋዕትነት መከፈሉን የማይገነዘቡ፣ ወይም ለመገንዘብ የማይፈልጉ ወገኖች ይስተዋላሉ፡፡ እነዚህ እንደ ጓያ ነቃይ የፊት የፊቱን ብቻ የሚመለከቱ ኃይሎች፣ አገሪቱ ከግጭት ውስጥ እንድትወጣ የሚፈልጉ አይመስሉም፡፡ በፖለቲካ ውሳኔ ወይም በሕጋዊ መንገድ ሊፈቱ የሚችሉ ጉዳዮችን የሞት የሽረት ዓይነት እያደረጉ፣ አንፃራዊውን ሰላማዊ አየር ውጥረት ውስጥ ሊከቱ ይፈልጋሉ፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ሴረኝነት ለአገር ምንም ፋይዳ የሌለው ብቻ ሳይሆን፣ የበለጠ ደም እንዲፈስና የአገር ሀብት እንዲወድም የሚያደርግ ክፋት ነው፡፡ በሠለጠነ መንገድ በመነጋገር ሐሳብን ለምልዓተ ሕዝቡ መሸጥ የማይችል ካድሬና ተቀላቢ፣ ነገር እየቆሰቆሰ ሕዝቡን በማንነትና በእምነት ካልከፋፈለ ሥልጣን የማይገኝ ይመስለዋል፡፡ ለሰላማዊ የፖለቲካ ፉክክርና ለዴሞክራሲያዊ መርሆች ዕውቀት አልባ የሆኑ ስመ ፖለቲከኞች፣ አንድም ቀን ስለልማትና ዕድገት ሲናገሩ አይታወቁም፡፡ የእነሱ ሙያ ማስረጃ የሌለው የበደል ትርክት እየተነተኑ አገሪቱን ለቅሶ ቤት ማድረግ ነው፡፡ የተሻለ አማራጭ ፖሊሲ ቀርፀው ከመቅረብ ይልቅ፣ ወሬና አሉባልታ እየፈበረኩ የስም ማጥፋት ዘመቻ ማካሄድ ትልቁ ሥራቸው ነው፡፡ በንድፈ ሐሳብና በተግባር የተፈተኑ ምሁራንና ልሂቃን የሌሉበት የአገሪቱ የፖለቲካ ምኅዳር የተወረረው፣ በእንዲህ ዓይነቶቹ ታሪክ ይቅር የማይላቸው ስመ ፖለቲከኞች ነው፡፡

ኢትዮጵያዊያን በአገራቸው ጉዳይ ያገባቸዋል ሲባል ተሳትፎአቸው አሁን ከሚታየው በላይ በጣም ማደግ አለበት፡፡ ይህ ተሳትፎ በተለያዩ መስኮች ለአገራቸው ከሚያበረክቱት አስተዋጽኦ በመላቅ፣ በአገሪቱ የፖለቲካ ምኅዳር ውስጥ በስፋት መታየት ይጠበቅባቸዋል፡፡ በአገሪቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ እንደ ምርጫቸው በመግባት የተበላሸውን የማስተካከልና የማረም ኃላፊነት አለባቸው፡፡ ለምሳሌ አገሪቱ የምትመራበት ፌዴራሊዝም መላው ሕዝቧን በነፃነት፣ በእኩልነትና በፍትሐዊነት እንዴት በአንድነት ሊያኖር እንደሚችል አስተዋፅኦ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ማንነትን፣ ቋንቋን፣ ባህልን፣ እምነትንና መሰል ልዩነቶችን ዕውቅና በመስጠት ለዘመናት የተገነቡትን የጋራ ማኅበራዊ እሴቶችን በመንከባከብ ኅብረ ብሔራዊ አንድነት እንዴት ማጠናከር እንደሚቻል ማገዝ አለባቸው፡፡ ከበደል ትርክቶች በላይ የጋራ የሆኑ የሚያኗኑሩ ድንቅ መስተጋብሮች እንዳሉ በተጨባጭ የሚያሳዩ ታሪኮችን ፈልፍለው ማውጣት ይኖርባቸዋል፡፡ አገርን የሚያዳክሙ፣ አንድ ላይ የኖረውን ሕዝብ ጥርጣሬ ውስጥ የሚከቱና በአጠቃላይ ለታሪካዊ ጠላቶች ክፍተት የሚፈጥሩ የመሰሪዎችን ቅስቀሳዎች ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማስቆም የሚችሉ ሥራዎች ላይ ማተኮር ግዴታቸው መሆን አለበት፡፡ ኢትዮጵያዊያን በተለያዩ የዕድሜ እርከኖች፣ የዕውቀት ደረጃዎችና ማኅበረሰባዊ ጥንቅሮች ውስጥ ሆነው ለኢትዮጵያ ዘላቂ ጥቅምና ህልውና መሥራት ከቻሉ፣ በታሪክ የሚያስከብር ገድል መፈጸም አያቅታቸውም፡፡ ለዚህም ነው የታሪክ ተወቃሽ ላለመሆን ጥንቃቄ መደረግ ያለበት!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ያልተቃናው የልጆች የንባብ ክህሎት

አንብቦና አዳምጦ መረዳት፣ የተረዱትን ከሕይወት ጋር አዋህዶ የተቃና ሕይወት...

እንስተካከል!

ሰላም! ሰላም! ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እንዲሁም የሰው ዘር በሙሉ፣...

የሙዚቃ ምልክቱ ሙሉቀን መለሰ ስንብት

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ በኪነ ጥበባትም ሆነ...

‹‹ደስታ›› የተባለችው አማርኛ ተናጋሪ ሮቦት በሳይንስ ሙዚየም

‹‹እንደ ሮቦት ዋነኛው አገልግሎቴ ውስብስብ የሆኑ የቴክኖሎጂ ውጤቶችንና አሠራሮችን...

በአዲስ አበባ ከ700 ሺሕ በላይ የትራፊክ የደንብ ጥሰቶች መፈጸማቸው ተገለጸ

በአዲስ አበባ 716,624 የትራፊክ የደንብ ጥሰቶች መፈጸማቸውን፣ የአዲስ አበባ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የማፍረስ ዘመቻው በብልሹ አሠራሮች ላይም ይቀጥል!

መንግሥት በኮሪደር ልማት አማካይነት የአዲስ አበባ ከተማን ዋና ዋና ሥፍራዎች በማፍረስ፣ አዲስ አበባን ከኬፕታውን ቀጥሎ ተመራጭ የአፍሪካ ከተማ ለማድረግ መጠነ ሰፊ ሥራ ከጀመረ ሰነባብቷል፡፡...

ለድጋፍ ብቻ ሳይሆን ለተቃውሞም ማስተንፈሻ ይሰጥ!

በሕዝብ ድምፅ ተመርጦ ሥልጣን የያዘ መንግሥት ዋነኛ ሥራው በሕግ መሠረት የተሰጡትን ኃላፊነቶች በብቃት መወጣት ነው፡፡ የሕዝብን ሰላምና ደኅንነት ማስጠበቅ፣ የአገርን የግዛት አንድነትና ሉዓላዊነት ማስከበር፣...

የፖለቲካ ምኅዳሩ እንዳይዳፈን ጥንቃቄ ይደረግ!

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ምኅዳር አሁንም ጤና አልባ ሆኖ የተለመደው ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታ ውስጥ ነው የሚገኘው፡፡ ካለፉት ሃምሳ ዓመታት ወዲህ ሊሻሻል ያልቻለው የፖለቲካ ምኅዳር ሰሞኑን አዲስ...