Sunday, April 14, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየብሔረሰብ ጥናት ኢንስቲትዩት ሰነዶች በከፊል ጠፍተው ሊሆን እንደሚችል ተጠቆመ

የብሔረሰብ ጥናት ኢንስቲትዩት ሰነዶች በከፊል ጠፍተው ሊሆን እንደሚችል ተጠቆመ

ቀን:

ከ1970ዎቹ እስከ 1980ዎቹ መጀመርያ ድረስ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በመዘዋወርና የውጭ አገሮችን ልምዶች በመቀመር ከተሰናዱ የብሔረሰብ ጥናት ኢንስቲትዩት ሰነዶች ውስጥ፣ ከፊሉ ጠፍተው ሊሆን እንደሚችል ተጠቆመ፡፡ ይህ የተነገረው ኢንስቲትዩቱ ተቋምነቱ ካበቃበት ጊዜ ጀምሮ ሰነዶቹን በኃላፊነት ተረክቦ ያኖረው ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ ተከማችተው ያገኛቸውን ሰነዶች ለብሔራዊ ቤተ መጻሕፍትና ቤተ መዛግብት ኤጀንሲ (ወመዘክር) ሰኞ ታኅሳስ 12 ቀን 2013 ዓ.ም. ባስረከበበት ወቅት ነው፡፡

በኢንስቲትዩቱ በተለያዩ ደረጃዎች በአጥኚነትና በተመራማሪነት እንዲሁም በአመራርነት ያገለገሉት ያየህ ይራድ ቅጣው (ዶ/ር)፣ ላጵጌታሁን ዴሌቦ (ዶ/ር)፣ ፋሲል ናሆም (ዶ/ር)፣ ኃይሉ አርአያ (ዶ/ር)፣ እንዲሁም የኤጀንሲውና የምርጫ ቦርድ አባላትና ኃላፊዎች በተገኙበት የተደረገው ርክክብ፣ የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት ኤጀንሲ (ወመዘክር) ዋና ዳይሬክተር አቶ ይኩኖ አምላክ መዝገቡ ባደረጉት ፊርማ ተፈጽሟል፡፡

በርክክቡ ሥነ ሥርዓት ላይ ንግግር ያደረጉት ያየህ ይራድ (ዶ/ር) እነዚህ ሁሉ ጥናቶች በአጥኚዎቹም ሆነ የጥናቶቹን ኃላፊነት የሰጡ ሰዎች በውጥረት ውስጥ በነበሩበት ወቅት የተከናወኑ እንደሆኑ በማስታወስ፣ የተደከመባቸውና የተለፋባቸው ሰነዶች እንዲህ በይፋ አደባባይ ወጥተው በማየታቸው እጅግ ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ ከክምችቱ መሀል የጠፉ ሰነዶች አሉ ስለሚባል የሚመለከተው አካል እነዚህን ሰነዶች ፈልጎ ያግኛቸው ሲሉም አሳስበዋል፡፡ ይኼንንም ጥናት ያደረገ ሰው እንደጠቆማቸው፣ አሁን ምን ያህል የተሟሉ ሰነዶች ለርክክብ እንደበቁ እርግጠኛ እንዳልሆኑም ተናግረዋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

በሰነዶቹ በጥናት ላይ የተመሠረተ ማንኛውንም ዓይነት ሥራ ማከናወን ይቻላል የሚለውን ያሳዩ ናቸው ያሉት ያየህ ይራድ (ዶ/ር)፣ ሰነዶቹ በሕግና ሕገ መንግሥት፣ በታሪክ፣ በአስተዳደር፣ በኢኮኖሚና በማኅበራዊ ዘርፎች የተደረጉ ጥናቶችን የያዙ እንደሆኑ አስታውሰዋል፡፡ በጥናቶቹ እንደ ግርማ ወልደ ሥላሴ (ዶ/ር)፣ ዲበኩሉ ዘውዴ፣ እንዲሁም ፋሲል ናሆም (ዶ/ር)፣ በሕግና በሕገ መንግሥት ዘርፍ፣ እንደ አስመላሽ በየነ (ዶ/ር) በአስተዳደር ዘርፍ፣ እንደ ላጵሶ ጌታሁን (ዶ/ር) ያሉ ደግሞ በታሪክ ዘርፍ አንቱ የተባሉ ባለሙያዎች መሆናቸውን አክለዋል፡፡

‹‹ትልቁ ፈተና የነበረው እነዚህ ሰዎች በሚፈልጉትና በሚችሉት አኳኋን ሊሠሩ የሚችሉበትን ሁኔታ ማመቻት ይቻላል ወይ?›› የሚለው ነው ሲሉም፣ በወቅቱ የነበረውን ጥናቶቹን የማከናወን ችግር አስታውሰዋል፡፡ ይኼም የሆነው ውጥረት የነገሠበትና ቀይ ሽብር – ነጭ ሽብር፣ ግራ ዘመም – ቀኝ ዘመም፣ አድኃሪ – አክሳሪ እየተባለ መከራ የሚበላበት ጊዜ ስለነበር ነው ብለዋል፡፡

ፋሲል (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ የርክክቡን ቀን ‹‹ታሪካዊ ነው›› በማለት አሞካሽተው፣ አርባ ዓመታት ወደኋላ መለስ ብለው ነገሮችን መቃኘት እንዲችሉ እንዳደረጋቸው ገልጸው፣ ሰነድ መያዝ እጅግ ጠቃሚ እንደሆነና ኢትዮጵያ በርካታ ሰነዶች ያሏት የረጅም ታሪክ ባለቤት ስለሆነች አንዳንድ ሰነዶች በአገሪቱ እንደማይገኙ፣ ነገር ግን በእጅ ያሉት ምን ያህል አኩሪ እንደሆኑ ማየት ተችሏል ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡ በዚህም አግባብ አሁን ለርክክብ የበቁት ሰነዶች ጥናቶቹ በተደረጉባቸው ጊዜያት ኢትዮጵያ ምን ትመስላለች የሚለው የተያዙበት ቢሆኑም፣ ለያኔዋ ኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለወደፊትም የሚያገለግሉ እንደሆኑ ጠቁመዋል፡፡

የጨረታ ማስታወቂያ

ከእነዚህ ሰነዶች የወጣው ዋናው ሕገ መንግሥቱ እንደሆነ፣ አሁን ላለው ሕገ መንግሥት ድርሻ የተጫወተ ረቂቅ ሕገ መንግሥት ተሠርቶ እንደነበርም ገልጸዋል፡፡ ሕገ መንግሥት መንግሥትን በማቋቋም ምን ዓይነት መንግሥት ነው የሚለውን፣ በመንግሥትና በሕዝብ መካከል ምን ዓይነት ግንኙነት ይኖራል የሚሉትን (በመብትና በነፃነት የሚገለጹ) ጉዳዮች የሚይዝ እንደሆነ በማብራራት፣ ‹‹ለወደፊትም ቢሆን ስለሕገ መንግሥት በምናስብበት ጊዜ እነዚህ ሁለት ነገሮች አይቀሩም፤›› ብለዋል፡፡

አሁን ባለው ሕገ መንግሥት ሰላም፣ ልማትና ዴሞክራሲን ለማረጋገጥ ግቦች መቀመጣቸውን በማውሳት፣ የኢትዮጵያ ህልውና ከእነዚህ ጋር የተገናኘ ነው በማለት ከሚከፋፍል ፖለቲካ ይልቅ በጥናት ላይ የተመረኮዘ መፍትሔ መፈለግ ላይ ትኩረት ከተደረገ ከችግር መውጣት ይቻላል ሲሉም አሳስበዋል፡፡ ኢትዮጵያ ከችግር ተላቅቃ አታውቅም ግን መፍታትና የተደላደለ ኑሮን መኖር ይቻላል በማለት፣ ሕገ መንግሥት የአምላክ ቃል አይደለምና ቀጣይነት ያለውን የኅብረተሰብ ዕድገት ተከትሎ የሚሻሻል መሆን ይኖርበታል ብለዋል፡፡

የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወ/ሪት ብርቱካን በበኩላቸው ኃላፊነት በወሰዱ በሦስተኛው ሳምንት ገደማ የሕግ ባለሙያው አቶ አብዱ ዓሊ ሒጅራ፣ በምርጫ ቦርድ ውስጥ በርካታ ሰነዶች እንደሚገኙ በማሳወቅ እንዳይጠፉ ጥንቃቄ ይደረግባቸው ዘንድ ማሳሰቢያ እንደሰጧቸው በማስታወስ፣ ከዚያም ከባልደረቦቻቸው ጋር ተነጋግረው ወዲያውኑ የወመዘክር ሰዎችን በማግኘት ውይይት እንደጀመሩ አስታውሰዋል፡፡ ቀጣዩ ሥራ የተመሳቀለውን የሰነዶች አቀማመጥ መልክ ማስያዝ ነበር ብለው፣ እንዲህ ያሉ ዝርዝር ጥናቶች ስለነበሩ እንደነገሩ በየቦታው ወድቀው ሊቀሩ የሚገባቸው አይደሉም ሲሉ አስረድተዋል፡፡ ይሁንና፣ ምንም እንኳን ዘመናዊነትን ባይጠብቁም ሰነዶቹ እዚህ በመድረሳቸው ምሥጋናቸውን ገልጸዋል፡፡

የኤጀንሲው የሪከርድ ሥራ አመራር ዳይሬክተር አቶ ሰሎሞን ጠና ሰነዶቹን በሚመለከት በሰጡት ገለጻ፣ የርክክብ ውይይታቸው በ2012 ዓ.ም. ተጀምሮ ለዚህ ቀን የበቁት ሰነዶች የጽሑፍ፣ የፎቶግራፍ፣ የቪዲዮና የድምፅ ናቸው ብለዋል፡፡

የጨረታ ማስታወቂያ

ሰነዶቹም በጠቅላላው የሕግ ማዕቀፎች (አዋጆች፣ ደንቦች፣ መመርያዎች)፣ የሕገ መንግሥት ማርቀቅና ማፅደቅ ሒደቶች፣ የመስተዳድር ክልል ጥናቶች፣ የአስተዳደር ራስ ገዝ ስያሜዎች፣ከተሞች ደረጃና ተጠሪነት፣ የተለያዩ የመንግሥት ተቋማትን ለማዋቀር የተደረጉ ጥናቶች፣ ማቋቋሚያ አዋጆች መዋቅሮች፣ የቋንቋ፣ የታሪክ፣ የመልክዓ ምድር፣ባህል፣አሰፋፈር፣ ወዘተ ጥናቶች፣ የሴሚናር ፕሮሲዲንጎች፣ ጆርናሎችና ሌሎች ጥራዞችና ዕትሞች፣ የብሔረሰቦች ቢብሊዮግራፊ፣ የኢሠፓ መዋቅር፣ መመርያ፣ መደበኛና ልዩ ስብሰባዎች ላይ የቀረቡ ሪፖርቶች፣ኢሕዲሪ ምሥረታ፣ በተለያዩ አገሮች የተደረጉ ጉብኝቶችና የተወሰዱ ልምዶች ሪፖርቶች፣ በትጥቅ ትግል ላይ ለነበሩ ኃይሎች የቀረቡ የሰላም ጥሪዎች፣ የድርድር አስተያየቶችና ችግሩን ለመፍታት የተደረጉ ጥረቶች፣ የምርጫ ጉዳዮች (ስለምርጫ ክልል ድምፅ መስጫ ጣቢያዎች ተያያዥ ሰነዶች)፣ የማዕከላዊ ፕላን የረዥምና የመካከለኛ ዘመን መሪ ዕቅዶች፣ ሪፖርቶች፣ የብሔራዊ ቤተ መዛግብት መቋቋም አስፈላጊነትና ሌሎች የኢንስቲትዩቱን እንቅስቃሴ የዘገቡ ሪከርዶች ይገኙበታል ብለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ያልተቃናው የልጆች የንባብ ክህሎት

አንብቦና አዳምጦ መረዳት፣ የተረዱትን ከሕይወት ጋር አዋህዶ የተቃና ሕይወት...

እንስተካከል!

ሰላም! ሰላም! ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እንዲሁም የሰው ዘር በሙሉ፣...

የሙዚቃ ምልክቱ ሙሉቀን መለሰ ስንብት

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ በኪነ ጥበባትም ሆነ...

‹‹ደስታ›› የተባለችው አማርኛ ተናጋሪ ሮቦት በሳይንስ ሙዚየም

‹‹እንደ ሮቦት ዋነኛው አገልግሎቴ ውስብስብ የሆኑ የቴክኖሎጂ ውጤቶችንና አሠራሮችን...