የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ)፣ የመላው ኢትዮጵያውያን ብሔራዊ ንቅናቄ ፓርቲ (መኢብን) እና አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት)ን ጨምሮ 26 ተፎካካሪ ፓርቲዎችን መሰረዙን አስታወቀ፡፡
ቦርዱ ተፎካካሪ ፓርቲዎችን የሰረዘው፣ በአዋጅ ቁጥር 1162/2011 ድንጋጌ መሠረት፣ ፓርቲዎቹ ማሟላት የሚገባቸውን ግዴታዎች ባለማሟላታቸው መሆኑን፣ ትናንት ምሽት ላይ በድረ ገጹ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡
ፓርቲዎቹ በአዋጅ ቁጥር 1162/2011 እና ግዴታዎችን በሚደነግገው መመርያ 03 መሠረት የተመዘገቡና በሒደት ላይ ያሉ ፓርቲዎች በመሆናቸው፣ ቦርዱ በአዋጁ መሠረት የተቀመጡ መሥፈርቶችን ማሟላታቸውን የማጣራት ሥራ ሲሠራ መቆየቱን አስታውሶ፣ ማቅረብ ያለባቸውን ተጨማሪ የመሥራቾች ፊርማ ቁጥር በመጥቀስ በጽሑፍ እንዲደርሳቸው ማድረጉንም አብራርቷል፡፡
ፓርቲዎቹ ማሟላት የሚገባቸውን መሥፈርቶች ባለማሟላታቸው ኢዴፓ፣ አንድነትና መኢብንን ጨምሮ 26 ፓርቲዎችን መሰረዛቸውን ገልጿል፡፡
የመሥራች አባላትን ካቀረቡ ፓርቲዎች መካከል ሳምፕል በመውሰድ፣ በሁሉም ክልሎችና ወረዳዎች፣ የመሥራች አባላት መሟላትን የማጣራት ሥራ አከናውኗል፡፡ ሥራው የተከናወነው በቦርዱ የክልል ቅርጫፍ ጽሕፈት ቤቶች አማካይነት ሲሆን፣ በዚህም መሠረት በሁሉም ወረዳዎች ላይ የቦርዱ ባለሙያዎች በግንባር በመገኘት የነዋሪነት ማረጋገጫ ለመስጠት ሥልጣኑ ካላቸው የአስተዳደር አካላት ጋር በመተባበር፣ የመሥራች አባላት እውነተኛነትንና መረጃዎችን ትክክለኛነት ማረጋገጡን ገልጿል፡፡
መረጃዎች በትክክል ተሞልተው አለመምጣታቸው (የማይታወቅ ወረዳ፣ ትክክለኛ ያልሆነ የወረዳ፣ የቀበሌ፣ ስም፣ ወዘተ)፣ በታችኛው ዕርከን አስተዳደር መረጃ አያያዝ ችግር የተነሳ ማጣራቱ ረዥም ጊዜ መውሰዱ (መታወቂያ ቁጥር፣ የቤት ቁጥር መረጃዎች አለመሟላት)፣ በፓርቲዎች በኩል የተጓደሉ መረጃዎች ሲኖሩ በአጭር ጊዜ አሟልቶ ያለማቅረብ ችግሮች፣ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ የተነሳ የሠራተኞች እጥረት በቦርዱ በኩል በሚገባው ፍጥነት ማጠናቀቅ አለመቻል፣ በዚህም የተነሳ የማጣራት ሒደቱ ረዥም ጊዜ ከመውሰዱም በተጨማሪ፣ በሒደቱ የተገኘው የማጣራት ውጤት ቦርዱ በፈለገው መንገድ ሊሆን አለመቻሉንም ጠቁሟል፡፡ እንደ አዲስ አበባ ባሉ የአስተዳደር አካላት የመሥራች ፊርማን ለማጣራት ባልቻለበት ሁኔታ ፓርቲዎች እንዳቀረቡት ትክክለኛ ፊርማ እንዲቆጠር ተደርጓል፡፡
ከዚህም በመነሳት ከ35 በመቶ በላይ መሥራች ፊርማቸው ትክክል የሆኑ ፓርቲዎችን ምዝገባ ለማፅደቅ የወሰነ ሲሆን፣ ከ35 በመቶ በታች የሆኑ ትክክለኛ ፊርማ ያመጡና የተለያዩ በቦርዱ የተጠየቁትን መሥፈርት ያላሟሉ ፓርቲዎች እንዲሰረዙ ወስኗል፡። በዚህም መሠረት የመሥራች ፊርማ ናሙና ማረጋገጫ ከ35 በመቶ በታች በመሆኑ የተሰረዙ ፓርቲዎች፣ የአማራ ህልውና ለኢትዮጵያ አንድነት የመሥራች አባላት ናሙናን አስመልክቶ በተደረገው ማጣሪያ 24 በመቶ ያገኘ፣ የኦሮሞ አንድነትና ዴሞክራሲ የፌዴራል የሰላም ለውጥ ፓርቲ የመሥራች አባላት ናሙናን አስመልክቶ በተደረገው ማጣሪያ 25 በመቶ ያገኘ፣ የኦሮሞ አቦ ነፃነት ግንባር የመሥራች አባላት ናሙናን አስመልክቶ በተደረገው ማጣሪያ ከአሥር በመቶ ያገኘ፣ የኦሮሞ ነፃነት አንድነት ግንባር የመሥራች አባላት ናሙናን አስመልክቶ በተደረገው ማጣሪያ ከአራት በመቶ ያገኘ፣ የተባበሩት ኦሮሞ ነፃነት ግንባር የመሥራች አባላት ናሙናን አስመልክቶ በተደረገው ማጣሪያ 33 በመቶ ያገኘ፣ የኦሮሞ ነፃነት ዴሞክራሲያዊ ግንባር የመሥራች አባላት ናሙናን አስመልክቶ በተደረገው ማጣሪያ 24 በመቶ ያገኘና በቦርዱ በተሰጠው የጊዜ ገደብ መሠረት ጠቅላላ ጉባዔ ባለማካሄድ፣ የኦሮሚያ ነፃነት ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ የመሥራች አባላት ናሙናን አስመልክቶ በተደረገው ማጣሪያ 14 በመቶ ያገኘና በቦርዱ በተሰጠው የጊዜ ገደብ መሠረት ጠቅላላ ጉባዔ ባለማካሄድ፣ የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ የመሥራች አባላት ናሙናን አስመልክቶ በተደረገው ማጣሪያ 23 በመቶ ያገኘ፣ ዱቤና ደገኒ ብሔረሰብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ የመሥራች አባላት ናሙናን አስመልክቶ በተደረገው ማጣሪያ አምስት በመቶ ያገኘ፣ የአገው ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ የመሥራች አባላት ናሙናን አስመልክቶ በተደረገው ማጣሪያ 19 በመቶ ያገኘ፣ የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ኅብረት የመሥራች አባላት ናሙናን አስመልክቶ በተደረገው ማጣሪያ 18 በመቶ ያገኘ፣ የመላው ኢትዮጵያዊያን ብሔራዊ ንቅናቄ የመሥራች አባላት ናሙናን አስመልክቶ በተደረገው ማጣሪያ 28 በመቶ ያገኘ፣ የኦሮሞ ብሔራዊ ኮንግረስ የመሥራች አባላት ናሙናን አስመልክቶ በተደረገው ማጣሪያ 18 በመቶ ያገኘ፣ የኦሮሚያ ነፃነት ብሔራዊ ፓርቲ የመሥራች አባላት ናሙናን አስመልክቶ በተደረገው ማጣሪያ 19 በመቶ ያገኘ፣ ኅብረት ለዴሞክራሲና ለነፃነት የመሥራች አባላት ናሙናን አስመልክቶ በተደረገው ማጣሪያ 17 በመቶ ያገኘ፣ የሱማሌ አርበኞች ፓርቲ የመሥራች አባላት ናሙናን አስመልክቶ በተደረገው ማጣሪያ 17 በመቶ ያገኘ፣ የአፋር አብዮታዊ ፓርቲ የመሥራች አባላት ናሙናን አስመልክቶ በተደረገው ማጣሪያ ዘጠኝ በመቶ ያገኘ፣ የሱማሌ ክልላዊ ዴሞክራሲያዊ ኅብረት የመሥራች አባላት ናሙናን አስመልክቶ በተደረገው ማጣሪያ ሦስት በመቶ ያገኘ፣ ምክክር ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ፓርቲ የመሥራች አባላት ናሙናን አስመልክቶ በተደረገው ማጣሪያ 32 በመቶ ያገኘ፣ የወይኽምረ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ የመሥራች አባላት ናሙናን አስመልክቶ በተደረገው ማጣሪያ 33 በመቶ ያገኘ፣ ከመሥራች አባላት ናሙና ትክክለኛነት ማጣራት ውጪ በሆነ መሥፈርት የተሰረዙ፣ የኢትዮጵያ ሰላማዊ የዴሞክራሲያዊ ፓርቲ የመሥራች አባላት ብዛትና ስብጥር ባለማሟላትና በቦርዱ በተሰጠው የጊዜ ገደብ መሠረት ጠቅላላ ጉባዔ ባለማካሄድ፣ አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ የመሥራች አባላት ብዛትና ስብጥር ባለማሟላትና በጠቅላላ ጉባዔ ምልዓተ ጉባዔ ባለማሟላት፣ የኢትዮጵያ ኅብረ ሕዝብ ብሔራዊ ንቅናቄ የመሥራች አባላት ብዛትና ስብጥር ባለማሟላት፣ ነፀብራቅ አማራ ድርጅት በቅፁ ላይ በግልጽ ቢቀመጥም 2,691 የፓርቲውን መሥራች አባላት የአያት ስም አሟልቶ ባለማቅረብ፣ የፊንፊኔ ሕዝቦች አንድነት ለፍትሕና ለዴሞክራሲ የመሥራች አባላት ብዛትና ከቦርዱ በተሰጠው አስተያየት መሠረት በሰነዶች ላይ ማስተካከያ ባለማድረግ፣ ሐረሪ ሪቫይቫል ንቅናቄ በቦርዱ በተሰጠው የጊዜ ገደብ መሠረት ጠቅላላ ጉባዔ ባለማካሄድ፣ በአጠቃላይ ከላይ በተጠቀሱት ምክንያቶች እንዲሰረዙ መወሰኑን አስታውቋል፡፡
በተለያዩ ምክንያቶች ማብራሪያ እንዲሰጡ ወይም አሟልተው እንዲያቀርቡ የተወሰነና የማጣራት ሒደታቸው ያልተጠናቀቀ 12 ተፎካካሪ ፓርቲዎች ማለትም፣ ኅብር ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ፣ ሐረሪ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት፣ አፋር ነፃ አውጭ ግንባር ፓርቲ፣ የቤኒሻንጉል ጉምዝ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ፣ የአፋር ሕዝብ ፓርቲ፣ የኦሮሚያ ብሔራዊ ፓርቲ፣ የመላው ኢትዮጵያዊያን አንድነት ድርጅት (መኢአድ)፣ ጋሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ፣ የወለኔ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ፣ መላው ኦሮሞ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ፣ የሲዳማ ብሔራዊ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ፣ የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃነት ግንባር (ኦብነግ) ፓርቲዎች ሲሆኑ፣ የማጣራት ሒደታቸው የተጠናቀቀ ፓርቲዎች ደግሞ የኦሮሞ ነፃነት ንቅናቄ 51 በመቶ፣ ቅማንት ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ 57 በመቶ፣ የሲዳማ አርነት ንቅናቄ 78 በመቶ፣ የጌዴዮ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት 93 በመቶ፣ የጋምቤላ ሕዝቦች ፍትሕ ሰላምና ልማት ዴሞክራቲክ ንቅናቄ 91 በመቶ፣ የኢትዮጵያ ዴሞክራቲክ ኅብረት 48 በመቶ፣ የምዕራብ ሶማሌ ዴሞክራቲክ ፓርቲ 97 በመቶ፣ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ 69 በመቶ፣ የአገው ብሔራዊ ሸንጎ 45 በመቶ፣ ካፋ አረንጓዴ ፓርቲ 61 በመቶ፣ የጋምቤላ ሕዝብ ነፃነት ንቅናቄ 94 በመቶ፣ የአፋር አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት ግንባር 49 በመቶ፣ የኢትዮጵያ ነፃነት ፓርቲ 37 በመቶ፣ የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ 48 በመቶ፣ ነፃነትና እኩልነት ፓርቲ 48 በመቶ፣ ሞቻ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ 72 በመቶ፣ የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ 79 በመቶ፣ የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ 43 በመቶ፣ የቤኒሻንጉል ጉምዝ ሕዝብ ነፃነት ንቅናቄ ለሰላምና ለዴሞክራሲ ድርጅት 48 በመቶ፣ የአፋር ሕዝቦች ፍትሐዊ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ 53 በመቶ፣ አዲስ ትውልድ ፓርቲ 64 በመቶ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ አንድነት ፓርቲ 38 በመቶ፣ የዎላይታ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ግንባር 99 በመቶ፣ የቁጫ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ 100 በመቶ፣ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ 38 በመቶ፣ የዎላይታ ብሔራዊ ንቅናቄ 96 በመቶ፣ ብልፅግና ፓርቲ 78 በመቶ፣ የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ 39 በመቶ፣ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር 47 በመቶ፣ የሲዳማ ሃድቾ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት 71 በመቶ፣ የአማራ ዴሞክራሲያዊ ኃይል ንቅናቄ 45 በመቶ፣ የጋምቤላ ሕዝብ ነፃነት ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ 93 በመቶ፣ እናት ፓርቲ 47 በመቶ፣ ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ 64 በመቶ፣ ቦሮ ዴሞክራቲክ ፓርቲ (በአዲሱ አዋጅ ቀድሞ የተመዘገበ)፣ ዓረና ትግራይ ለዴሞክራሲ ሉአላዊነት (ከማጣራቱ ቀድመው የፊርማ መሥፈርት ያጠናቀቁ)፣ የአርጎባ ብሔረሰብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (አነስተኛ ቁጥር ያለው ብሔረሰብ ፓርቲ)፣ የአርጎባ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (አነስተኛ ቁጥር ያለው ብሔረሰብ ፓርቲ)፣ የዶንጋ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (አነስተኛ ቁጥር ያለው ብሔረሰብ ፓርቲ)፣ የፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ መድረክ (ግንባር በመሆኑ ፊርማ ማቅረብ የማይገባው) መሆናቸውን ገልጿል፡፡ የማጣራት ሒደታቸው የተጠናቀቀ፣ ነገር ግን የቴክኒክ መሥፈርቶች የቀሯቸው፣ ህዳሴ ፓርቲ፣ ሳልሳይ ወያነ ትግራይ፣ የካፋ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ኅብረት፣ የራያ ራዩማ ዴሞክራሲዊ ፓርቲ፣ የሲዳማ አንድነት ፓርቲ፣ አሲምባ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ፣ ብሔራዊ ባይቶ ዓባይ ትግራይ መሆናቸውም አስታውቋል፡፡