Sunday, April 14, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበፌዴራል ተቋማት ላይ ጥቃት ለማድረስ በመዘጋጀት የተጠረጠሩ ከፍተኛ መኮንኖች ፍርድ ቤት ቀረቡ

በፌዴራል ተቋማት ላይ ጥቃት ለማድረስ በመዘጋጀት የተጠረጠሩ ከፍተኛ መኮንኖች ፍርድ ቤት ቀረቡ

ቀን:

በተለያዩ የፌዴራል ተቋማት ላይ ለጥበቃ ሥራ የተሰማሩ ግለሰቦችን በመመልመል በፌዴራል ተቋማት ላይ ጥቃት እንዲያደርሱና ከመከላከያ ሠራዊት በጡረታ የተሰናበቱ ወታደሮችን በማሰባሰብ፣ የትግራይ ልዩ ኃይልን እንዲቀላቀሉ በማድረግ የተጠረጠሩ ከፍተኛ የጦር መኮንኖች ፍርድ ቤት ቀርበው ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ተጠየቀባቸው፡፡

ተጠርጣሪዎቹ ሕገ መንግሥቱንና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በኃይል ለመናድ በማሰብ፣ እንዲሁም የሰሜን ዕዝ የመከላከያ ግንኙነት በማቋረጥ የመከላከያ ሠራዊቱ ጥቃት እንዲደርስበት በማድረግ ተጠርጥረው በእስር ላይ ከሚገኙት እነ ሜጀር ጄኔራል ገብረ መድኅን ፍቃዴ (ወዲ ነጮ) ጋር በመገናኘት ሲንቀሳቀሱ እንደነበር፣ የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቡድን ለፍርድ ቤት አስረድቷል፡፡

ቡድኑ ታኅሳስ 13 ቀን 2013 ዓ.ም. ለፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ አንደኛ ወንጀል ችሎት እንዳስረዳው ተጠርጣሪዎቹ ኮሎኔል ምሩፅ በርሄ፣ ኮሎኔል ገብረ መድኅን ገብረ መስቀል፣ ኮሎኔል ተስፋዬ ሐጎስና ኮሎኔል መብራቱ ተድላ ናቸው፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

መርማሪ ቡድኑ ቀደም ብሎ በተሰጠው 12 የምርመራ ቀናት የሠራውን ለፍርድ ቤቱ እንደገለጸው፣ የስምንት ሰዎችን ቃል ተቀብሏል፡፡ በትግራይ ክልል በፌዴራል ፖሊስ ተቋምና አባላት ላይ የደረሰውን የጉዳት መጠን ለይቶ በማስረጃ ማረጋገጡንና ከምርመራ መዝገቡ ጋር ማያያዙን ተናግሯል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ የተጠረጠሩበት የወንጀል ተሳትፎ ሰፊ ከመሆኑ አንፃር፣ ቀሪ ምስክሮችን ቃል መቀበል የሰነድ ማስረጃዎችን መሰብሰብና ግብረ አበሮችን ለመያዝ ተጨማሪ 14 ቀናት እንደሚያስፈልገው ጠቁሞ እንዲፈቀድለት ጠይቋል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ በበኩላቸው ለፍርድ ቤቱ ባቀረቡት የመቃወሚያ ክርክር እንዳስረዱት፣ መርማሪ ቡድኑ ከገለጸው የወንጀል ድርጊት ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት የላቸውም፡፡ የወንጀል ተሳትፎ አለባቸው ቢባል እንኳን ማን ምን ዓይነት ወንጀል እንደፈጸመ መርማሪ ቡድኑ ለይቶ ያቀረበው ነገር እንደሌለ በማስረዳት፣ ፍርድ ቤቱ በነፃ እንዲያሰናብታቸው ወይም የዋስትና መብታቸው እንዲከበርላቸው እንዲያደርግ ጠይቀዋል፡፡

የተጠርጣሪዎቹን መቃወሚያና የዋስትና ጥያቄ በመቃወም የተከራከረው መርማሪ ቡድኑ በድጋሚ እንዳስረዳው፣ ኮሎኔል ምሩፅ በሚሠሩበት የጥበቃ የሥራ ቦታ አባላትን በመመልመል በፌዴራል ተቋማት ላይ ጥቃት እንዲያደርሱ ሲያዘጋጁ እንደነበር፣ ኮሎኔል ገብረ መድኅን ደግሞ በተሰማሩበት ሰላም ማስከበር ተልዕኮ ላይ አባላትን አደራጅተው የትግራይ ልዩ ኃይልን እንዲቀላቀሉ ማድረጋቸውን አስረድቷል፡፡

ኮሎኔል ተስፋዬ ምንም እንኳን ወንጀሉ ሲፈጸም ሕክምና ላይ እንደነበሩ በጠበቃቸው የተገለጸ ቢሆንም፣ የተጠረጠሩበት የወንጀል ድርጊት በቅርቡ በተፈጸመ ወንጀል ብቻ ሳይሆን ከሁለት ዓመታት በፊት ጀምሮ ለፀረ ሰላም ቡድኖች መረጃ ከማቀበል ጋር በተያያዘ መሆኑን እንደነበር መርማሪ ቡድኑ አስረድቷል፡፡

ኮሎኔል መብራሃቱ ደግሞ ጡረታ የወጡ የመከላከያ ሠራዊት አባላትን በመሰብሰብ ለትግራይ ልዩ ኃይል ሲመለምሉ እንደነበር ተጠርጣሪዎች በአዲስ አበባ ከተማ ሲያደርጉት የነበረውን እንቅስቃሴ እያጣራ መሆኑን ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል፡፡

 

የጨረታ ማስታወቂያ

 

በሌላ በኩል በአገር ክህደት የተጠረጠሩት የመከላከያ ሬዲዮ መገናኛ መምርያ ኃላፊ የነበሩት እነ ሜጀር ጄኔራል ገብረ መድኅን ፍቃዴ (ሰባት ተጠርጣሪዎች) ፍርድ ቤት ቀርበዋል፡፡ ተጠርጣሪዎቹ በርካታ የሬዲዮ መገናኛዎችን ‹‹‹ይወገድ›› በማለት ከማዕከል አጓጉዘው ለትግራይ ልዩ ኃይል ማስረከባቸውን የሚያሳይ ማስረጃ ማግኘቱን ለፍርድ ቤቱ መርማሪ ቡድን አስረድቷል፡፡ ቀሪ ምርመራ እንዳለው በመግለጽም 14 ተጨማሪ ቀናት ጠይቋል፡፡ ተጠርጣሪዎቹም የፈጸሙት ወንጀል ተለይቶ አለመቅረቡንና ዋስትና ሊጠበቅላቸው እንደሚገባ በመግለጽ አቤቱታቸውን አሰምተዋል፡፡

ፍርድ ቤቱ ተጠርጣሪዎቹና መርማሪ ቡድኑ ያደረጉትን ክርክር ከሰማ በኋላ፣ ተጠርጣሪዎቹ የጠየቁትን ዋስትና ውድቅ በማድረግና መርማሪ ቡድኑም ምርመራውን በፍጥነት እንዲያጠናቅቅ በመንገር፣ አሥር የምርመራ ቀናት ፈቅዶ ለታኅሳስ 23 ቀን 2013 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቡድን ሲሸሹ አፋር ላይ እንደተያዙ ለተመሳሳይ ፍርድ ቤት በመግለጽ ታኅሳስ 12 ቀን 2013 ዓ.ም. ያቀረባቸው ብርጋዴር ጄኔራል ይልማ ከበደ፣ ኮሎኔል ሐርጎት በርሄ፣ ሌተና ኮሎኔል ሙሉ ዓለሙ፣ ኮሎኔል በረከት ወልደ አብዝጊ፣ ሌተና ኮሎኔል ግደይ ገብረየሱስ፣ ሻለቃ ሓሳቡ መሐመድ፣ የመቶ አለቃ ፀሐይ ኃይሉ፣ ኮሎኔል ይርጋለም ፈቃዱና ሌተና ኮሎኔል ተወልደ ብርሃን ይባላሉ፡፡

ተጠርጣሪዎቹ በሥራ ላይ እያሉ ወንጀል ለመፈጸም የሥራ ክፍፍል በማድረግ ይሠሩ እንደነበር በማስረጃ ማረጋገጡን ለችሎቱ ተናግሯል፡፡ በውጭ አገር ላሉ አካላት ሐሰተኛ መረጃ ሲያቀብሉ እንደነበርና በወቅቱም በመከላከያ ሠራዊት ውስጥ ችግር እንዲፈጠርና እንዲስፋፋ ሲያደርጉ እንደነበርም በምርመራ ማረጋገጡን በማስረዳት፣ ለተጨማሪ ምርመራ 14 ቀናት እንዲፈቀድለት ጠይቋል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ በበኩላቸው ለፍርድ ቤቱ እንዳስረዱት መርማሪ ቡድኑ እንደገለጸው ሳይሆን፣ በተለያዩ ቦታዎች በሥራ ላይ ነበሩ፡፡ የወንጀል ተሳትፏቸውን በጥቅል መግለጽ ተገቢ ስላልሆነ ተሳትፏቸው ተለይቶ ሊገለጽላቸው እንደሚገባ ተናግረው፣ ከተጠቀሰባቸው የወንጀል ድርጊት ጋር ምንም የሚያገናኛቸው ነገር ባለመኖሩ በነፃ እንዲሰናበቱ፣ ወይም የዋስትና መብታቸው እንዲከበርላቸው ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል፡፡

መርማሪ ቡድኑ በድጋሚ ለፍርድ ቤቱ ኮሎኔል ይርጋምና ኮሎኔል ተወልደ ሲሸሹ አፋር ላይ እንደተያዙ አስረድቶ፣ ያልተያዙ ግብረ አበሮች ስላሏቸው በዋስ ቢወጡ ሊሸሹና ጉዳት ሊያደርሱ እንደሚችሉ በመጠቆም፣ ጥያቄያቸውን ተቃውሟል፡፡ የግራ ቀኙን ክርክር የሰማው ፍርድ ቤት የተጠርጣሪዎቹን ተሳትፎ ከምርመራ መዝገቡ ዓይቶ ትዕዛዝ ለመስጠት ለሐሙስ ታኅሳስ 15 ቀን 2013 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡      

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ያልተቃናው የልጆች የንባብ ክህሎት

አንብቦና አዳምጦ መረዳት፣ የተረዱትን ከሕይወት ጋር አዋህዶ የተቃና ሕይወት...

እንስተካከል!

ሰላም! ሰላም! ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እንዲሁም የሰው ዘር በሙሉ፣...

የሙዚቃ ምልክቱ ሙሉቀን መለሰ ስንብት

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ በኪነ ጥበባትም ሆነ...

‹‹ደስታ›› የተባለችው አማርኛ ተናጋሪ ሮቦት በሳይንስ ሙዚየም

‹‹እንደ ሮቦት ዋነኛው አገልግሎቴ ውስብስብ የሆኑ የቴክኖሎጂ ውጤቶችንና አሠራሮችን...